እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። (መዝሙር 1፥3)
በመዝሙር 1፥3 ውስጥ ያለው ተስፋ ወደ ክርስቶስ የሚያመለክተው እንዴት ነው?
“የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ይላል። ይህ ክፍል ጻድቃን በሚሠሩት ሁሉ ይከናወናሉ ይለናል። ታዲያ ይህ ሞኝነት ነው ወይስ ጥልቅ እውነት?
በእርግጥም በዚህ ሕይወት ውስጥ ክፉዎች የሚበለጽጉ ይመስላል። “በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር” (መዝሙር 37፥7)። “አሁን ግን ትዕቢተኞችን ቡሩካን እንላቸዋለን፤ ክፉ አድራጊዎች ይበለጽጋሉ፤ እግዚአብሔርን የሚፈታተኑትም ያመልጣሉ” (ሚልክያስ 3፥15)።
ደግሞም በዚህ ሕይወት ውስጥ ጻድቃን ብዙውን ጊዜ በመከራ ያልፋሉ፣ የመልካምነታቸውም ምላሽ ስድብ ነው። “የአምላካችንን ስም ረስተን፣… ቢሆን ኖሮ፣ እግዚአብሔር ይህን ማወቅ ይሳነዋልን? … ይሁን እንጂ ቀኑን ሙሉ ስለ አንተ ሞትን እንጋፈጣለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጥረናል” (መዝሙር 44፥20-22)። ይህንን መዝሙረኞቹም ያውቁት ነበር። እነርሱ የማያውቁትን ነገር እያቀነቀንን አይደለም።
ስለዚህ፣ ዘማሪው “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ሲል አላዋቂ ሆኖ አይደለም። በዚህ ሕይወት ባሉ አሻሚ ነገሮች ውስጥ ከሞት ወዲያ ስላለው ሕይወት እየጠቆመ ነው። በዚያም ላደረግናቸው ነገሮች ሁሉ እውነተኛ የሆነው ስኬት እና እውነተኛ የሆነው ብልጥግና ይገለጣል።
ጳውሎስም የሚያስበው እንዲሁ ነው።
በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ በሞት ላይ ያለውን ድል ያሞግሳል። “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? … ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥55-57)።
ከዚያም፣ በዚህ ድል ምክንያት፣ በአማኞች የሚደረጉ ስራዎች ሁሉ ይከናወናሉ የሚለውን ድምዳሜ ያሳየናል። “ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ … ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥58)። አንድ ነገር በከንቱ ካልሆነ ይከናወናል ወይም ይሳካል ማለት ነው።
ኢየሱስ በእኛ ምትክ ስለሞተ፣ እያንዳንዱ መልካም ሥራ — ይዋል ይደር እንጂ — እንደሚሳካ ዋስትናን ሰጥቶናል። “ምክንያቱም፣ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ” (ኤፌሶን 6፥8)። “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ … ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ” (ማቴዎስ 5፥11-12)። እዚህ የተናቀ፣ በዚያ ግን ይከብራል።
በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሞኝነት የሚመስለው፦ “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” የሚለው ተስፋ፣ በመሠረታዊነት ወደ ክርስቶስ ሥራ እና ወደ ትንሣኤው እውነታዎች ይጠቁማል። ታዋቂዋ ዘማሪ ካትሪና ቮን ሽሌግል “ነፍሴ ሆይ እረፊ” በሚለው የጥንት ዝማሬዋ እንደጻፈችው ነው፦ “ነፍሴ ሆይ እረፊ፤ የወሰደብሽን ሁሉ ከራሱ ሙላት ኢየሱስ ይከፍልሻልና።”