የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረካቸው ሁሉ እንዲህ ይላል፤ “ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ፤ … ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።” (ኤርምያስ 29፥4–5, 7)
ተማርከው በባቢሎን ለነበሩት ግዞተኞች ይህ እውነት ከሆነ፣ በዚህ “ባቢሎንን በመሰለ” ዓለም ውስጥ ላሉ ክርስቲያን ግዞተኞች እንዴት አብልጦ እውነት አይሆንም? ስለዚህ ምን እናድርግ?
ቤቶችን እንደመገንባት፣ በከተማው ውስጥ እንደመኖርና አትክልቶችን እንደመትከል ያሉ፣ መደረግ ያለባቸውን የተለመዱ ነገሮችን ማድረግ አለብን። ታዲያ የምናደርገውን ሁሉ ለእውነተኛው ንጉስ እንጂ ለታይታና ሰውን ብቻ ለማስደሰት እስካላደረግነው ድረስ አይጎዳንም።
እግዚአብሔር ባስቀመጣችሁ ቦታ ሆናችሁ፣ የከተማዋን ደኅንነት አጥብቃችሁ ፈልጉ። ራሳችሁን በእግዚአብሔር – ለክብሩ እንደተላካችሁ ቁጠሩ። ምክንያቱም እውነታው ያ ነው።
ስለከተማችሁ ወደ ጌታ ጸልዩ። ታላቅ እና መልካም የሆነ ነገር ለከተማችሁ እንዲሆን ጠይቁ። ደግሞም ያ ሲፈጸም በእግዚአብሔር ኃይልና ለክብሩ እንዲሆን ጠይቁ። ከተማዋ ቁሳዊ ብልጽግናን ከምትፈልገው በላይ በሺህ እጥፍ የሚያስፈልጋት ዋነኛው መልካም ነገር ምን እንደሆነም አትዘንጉ። ክርስቲያኖች ሁሉም ዓይነት መከራ ግድ ይላቸዋል፤ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ዘላለማዊው መከራ ያሳስባቸዋል። ይህ ደግሞ እያንዳንዷ ከተማ የምትጋፈጠው ታላቁ ስጋት ነው።
ነገር ግን እግዚአብሔርም ሆነ ህዝቡ ለከተማዋ ጤንነት፣ ደህንነት፣ ብልጽግናና ነፃነት ደንታ ቢስ አይደሉም። ሁላችንም እነዚህን ነገሮች እንፈልጋለን። ኢየሱስም፦ “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” በማለት ተናግሯል (ማቴዎስ 22፥39)። እንዲያውም፣ በትንቢተ ኤርምያስ መጽሐፍ ላይ፣ “እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ” በማለት፣ ከተማን መውደድ ራስን የመውደድ መንገድ እንደሆነ ጌታ ይናገራል።
ይህ ማለት ግን በዚህ ምድር ላይ ስደተኛ መሆናችንን እንዘነጋለን ማለት አይደለም። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች “እንግዶችና መጻተኞች” ናቸው ይላል (1ኛ ጴጥሮስ 2፥11)። ጳውሎስም “አገራችን በሰማይ ነው” ብሏል (ፊልጵስዩስ 3፥20)። እንደውም፣ ለዚህች ዓለም ልናደርግላት የምንቸለው ትልቁ መልካም ነገር አባባይ ከሆኑት መስህቦቿ ነጻነታችንን አጽንተን መጠበቅ ነው። እሴቶቻችንን “ወደ ፊት ከምትመጣዋ ከተማ” በመቀበል ከተማችንን በተሻለ ሁኔታ ማገልገል እንችላለን (ዕብራውያን 13፥14)። የቻልነውን ያህል ዜጎቿን የ“ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ዜጎች እንዲሆኑ በመጥራት ለከተማችን የተሻለ መልካም ነገርን እናደርጋለን (ገላትያ 4፥26)።
ስለዚህም፣ ያለንባት ከተማ ነዋሪዎች ንጉሣችንን ማግኘት እንዲፈልጉ አቅማችን በፈቀደው መንገድ ሁሉ መልካም ነገርን አብዝተን እያደረግን እንኑር (1ኛ ጴጥሮስ 2፥12)።