በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ፣ “ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” የሚለው ጥቅስ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል (ዮሐንስ 12፥24)። በእያንዳንዱም ክርስቲያን ላይ ሞታችኋልና የሚለው ቃል ታትሟል (ቈላስይስ 3፥3)። ከልብ የሆነ የአማኝ ኑዛዜም፣ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ” የሚል ነው (ገላትያ 2፥20)። ግን ይህ ምን ማለት ነው? እኔ ክርስቲያን ስሆን የሞተው ማነው? መልሱ ሥጋዬ ነው፤ “የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር ሰቅለውታል” (ገላትያ 5፥24)። ሥጋ ማለት ምንድን ነው? ቆዳዬ ወይም ሰውነቴ አይደለም፤ ያ የጽድቅ መሣሪያ መሆን ይችላል (ሮሜ 6፥13)። መልሱን የሥጋ ሥራዎች በተባሉት ውስጥ ማግኘት እንችላለን። የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው፦ ይኸውም “ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፣ ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ እንዲሁም እነዚህን የመሰለው ነው” (ገላትያ 5፥19-21)። እነዚህ የአካል ተግባር ብቻ ሳይሆኑ አመለካከትንም ይጨምራሉ።
ሥጋ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉሙን የምናገኘው ሮሜ 8፥7-8 ባለው ክፍል ላይ ነው፦ “ለኀጢአት የተገዛ አእምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ጠበኛ ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛም፤ መገዛትም አይችልም። በሥጋ የሚመሩትም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይችሉም።” ሥጋ በእግዚአብሔር ላይ የሚያምፀው የቀድሞ እኔነቴ ነው። በሥጋ ሳለሁ የማልታዘዝ ነበርኩ፤ በኀጢአት የታመምኩ መሆኔን ማመን የማልፈልግ ነበርኩ፤ ሕክምና እንደሚያስፈልገኝ መቀበል አልፈልግም ነበር። በሥጋ ሳለሁ የእግዚአብሔርን ሳይሆን የራሴን ጥበብ እተማመን ነበር። ስለዚህ በሥጋ የማደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ማስደሰት አይችልም ነበር። ምክንያቱም “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም” (ዕብራውያን 11፥6)። ሥጋ ምንም ነገር በእምነት አያደርግም።
ስለዚህ ሥጋ የቀድሞው እምነት የለሹ ማንነቴ ነው። እግዚአብሔር ሲያድነኝ የሞተው ይህ ማንነት ነው። “አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ” እንዳለው ማለት ነው (ሕዝቅኤል 36፥26)። በአዲሱ እና በድሮው ልብ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ … አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” (ገላትያ 2፥20)። የቀድሞው ልብ በራሱ የሚታመን ሲሆን አዲሱ ግን ተስፋውን በክርስቶስ ላይ ያደርጋል።
በኢየሱስ በመታመን ኀጢአትን ተዋጉት
በሥጋ የሞቱ ሰዎች እንዴት ከኀጢአት ጋር ይፋለማሉ? ክርስቲያኖች ለሰይጣን ውሸቶች የሞቱ ስለሆኑ በእግዚአብሔር ልጅ በመታመን ይታገሉታል። ለምሳሌ፣ እንደዚህ ዐይነት ውሸቶች፦ የክርስቶስን ምክር እና የተስፋ ቃል ከመታመን ይልቅ፣ እንዴት ደስተኛ መሆን እንዳለብህ በራስህ አመለካከት ስትተማመን የበለጠ ደስተኛ ትሆናለህ። ክርስቲያኖች ለዚህ ዐይነት ተንኮል ሞተዋል። ሰይጣንን የሚዋጉበት መንገድ፣ የክርስቶስ መንገዶች እና ተስፋዎች ከሰይጣን የተሻሉ መሆናቸውን በማመን ነው። ይህ ኀጢአትን የምንታገልበት መንገድ የእምነት ተጋድሎ ይባላል (1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥12 ፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥7)። የዚህ ተጋድሎ ድሎች ደግሞ ከእምነት የሆኑ ሥራዎች ይባላሉ (1ኛ ተሰሎንቄ 1፥3 ፤ 2ኛ ተሰሎንቄ 1፥11)። በዚህ ውጊያ ውስጥ ክርስቲያኖች በእምነት የተቀደሱ ይሆናሉ (የሐዋርያት ሥራ 26፥18)።
ስለ እምነት ተጋድሎ ትንሽ እናስብ። ይህ የቀልድ ጨዋታ አይደለም፤ ለዘላለም ሕይወት የሚደረግ ጦርነት ነው። “እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና፤ ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ” (ሮሜ 8፥13)። ቁልፍ ጥቅስ ነው። ይህ የተጻፈው ለአማኞች ነው። በኀጢአት ላይ የሚደረገው ተጋድሎ ከድነት ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ማለት ኀጢአትን በመግደል የዘላለም ሕይወት እናገኛለን ማለት አይደለም። ተጋድሎአችን “በመንፈስ ቅዱስ በኩል” የሚደረግ ነው። ክብሩን እርሱ እንጂ እኛ አንወስድም። ትግሉን ማሸነፋችን ጥርጣሬ ውስጥ ነው ማለትም አይደለም፤ “ይልቁንም በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ” የሚለው መተማመን አለን (ፊልጵስዩስ 1፥6)። በተጋድሎአችን ፍጹም መሆን አለብን ማለትም አይደለም፤ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፤ “ይህን ሁሉ አግኝቻለሁ ወይም ፍጹም ሆኛለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ” (ፊልጵስዩስ 3፥12)።
እግዚአብሔር የሚፈልገው ተጋድሎ
በሮሜ 8፥13 የተጠቀሰው ከኀጢአት ፈጽሞ ነፃ መሆን ሳይሆን፣ ከኀጢአት ጋር እስከ ሞት ድረስ የሚደረግ ተጋድሎ ነው። ይህ ለክርስቲያናዊ ሕይወት ፍጹም አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ ሥጋችን ስለ መሰቀሉ ምንም ማስረጃ ማቅረብ አንችልም። ሥጋችን ካልተሰቀለ ደግሞ የክርስቶስ አይደለንም (ገላትያ 5፥24)። የዚህ ጦርነት ውጤት በጣም ከፍተኛ ዋጋ አለው። ጦርነቱ ጨዋታ አይደለም። ውጤቱ ገነት ወይም ሲኦል ነው። ታዲያ በእምነት መጋደል ምን ማለት ነው? እንዴት ነው ኀጢአትን በእምነት የምናሸንፈው?
ለምሳሌ፣ በዝሙት ተፈተንኩ ብለን እናስብ። ይህ ፈተና ኀይል የሚያገኘው፣ ሳደርገው የማገኘውን ደስታ በማሳየት ነው። የፈተናዎች ሁሉ ኀይል የሚመጣው ኀጢአትን በማድረግ የሚገኘውን ደስታ ከማሰላሰል ነው። ማንም ሰው ኀጢአትን ማድረግ አለብኝ ብሎ በግዴታ ስሜት አያደርገውም።
ስለዚህ ምን ላድርግ? አንዳንዶች “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏል፤ ስለዚህ ይህንን አታድርግ ይላሉ። ነገር ግን ከዚህ ምክር በተጨማሪ አንድ እጅግ አስፈላጊ ነገር አለ፤ እምነት። ብዙዎች፣ “አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” ለማለት ስለማይደፍሩ በግብረ ገብ ብቻ ለመሻሻል ይሞክራሉ (ገላትያ 2፥20)። በፍቅር የሚገለጽ እምነት ሳይገባቸው ለመውደድ ይሞክራሉ (ገላትያ 5፥6)። ከዝሙት፣ ስግብግብነት፣ ፍርሃት ወዘተ… ጋር የሚደረገው ተጋድሎ የእምነት ተጋድሎ ነው። አለበለዚያ ውጤቱ አጉል ወግ አጥባቂነት ነው።
ከኀጢአት ጋር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት መታገል
የምኞት ፈተና ሲመጣ “ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ” ተብለናል (ሮሜ 8፥13)። በመንፈስ ማለት ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር ሰይጣንን ለመፋለም ካቀረበልን መሣሪያዎች ሁሉ ለመግደል የምንጠቀመው አንዱን ብቻ ነው፤ ይኸውም የመንፈስን ሰይፍ ነው (ኤፌሶን 6፥17)። ስለዚህ ጳውሎስ ኀጢአትን በመንፈሱ ግደሉ ሲል፣ እኔ እንደተረዳሁት በመንፈስ ቅዱስ በተለይም በሰይፉ ላይ እምነታችሁን ጣሉ ማለቱ ነው።
የመንፈስ ሰይፍ ምንድን ነው? የእግዚአብሔር ቃል ነው (ኤፌሶን 6፥17)። እምነት እዚህ ጋር ያለው ድርሻ ይህን ይመስላል፤ “እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው” (ሮሜ 10፥17)። የእግዚአብሔር ቃል የሰይጣንን የውሸት መረብ በጣጥሶ እውነተኛ እና ዘላቂ ደስታ የት እንደሚገኝ ያሳየኛል። ስለዚህ ቃሉ የኀጢአትን ተስፋ ማመን አቁሜ፣ እግዚአብሔርን የሚያስደስት የተስፋ ቃል እንድታመን ይረዳኛል (መዝሙር 16፥11)።
ምን ያህል አማኞች፣ እምነት ማለት ክርስቶስ ለኀጢአታችን እንደ ሞተ ማመን ብቻ እንዳልሆነ መገንዘባቸውን እጠራጠራለሁ። እምነት ማለት የእግዚአብሔር መንገድ ከኀጢአት የተሻለ እንደሆነ ማመንም ጭምር ነው። የእርሱ ፈቃድ ጥበብን የተሞላ ነው። የእርሱ እርዳታ የበለጠ ርግጥ ነው። የእርሱ የተስፋ ቃላት ይበልጥ ዋጋ አላቸው። ሽልማቶቹም የበለጠ ያረካሉ። እምነት የሚጀምረው ወደ መስቀሉ ወደ ኋላ በመመልከት ቢሆንም የሚቀጥለው ግን ወደ እግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ወደ ፊት በመመልከት ነው። “አብርሀም ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም። እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ እርግጠኛ ነበር” (ሮሜ 4፥20-21)። “እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም ርግጠኛ የምንሆንበት፣ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው” (ዕብራውያን 11፥1)።
እምነት በልቤ ውስጥ ዋነኛውን ቦታ ሲይዝ በክርስቶስ እና በተስፋ ቃሎቹ እረካለሁ። ኢየሱስ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም” ሲል ይህንን ማስረዳቱ ነው (ዮሐንስ 6፥35)። ለደስታ ያለኝ ጥማት በክርስቶስ መገኘት እና በተስፋ ቃላቱ የሚረካ ከሆነ የኅጢአት ኅይል ተሰበረ ማለት ነው።
እርካታ ኀጢአትን ድል ያደርጋል
የእምነት ተጋድሎ በእግዚአብሔር እንደ ረካን ለመቆየት የሚደረግ ትግል ጭምር ነው። “ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ አለ። ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ” (ዕብራውያን 11፥24-26)። እምነት የደስታ ሙላትን ይፈልጋል፤ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “የሕይወትን መንገድ ታሳየኛለህ፤ በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣ በቀኝህም የዘላለም ፍስሓ አለ” (መዝሙር 16፥11)።
ስለዚህ እምነት ወደ ኀጢአት አያንደረድርም ማለት ነው። ደስታን መፈለጉንም በቀላሉ አያቆምም። የእግዚአብሔር ቃል ሚና፣ ለራሱ ለእግዚአብሔር ያለንን ጥማት ማርካት ነው። ይህንን ሲያደርግ ልባችንን ከኀጢአት ማታለያዎች ይጠብቅልናል። ኀጢአት በቅድሚያ የሚያደርገው ምኞቴን ብፈጽም የማገኘውን ደስታ ማሳየት ነው። እኔ ግን የመንፈሱን ሰይፍ አንሥቼ እጋደላለሁ።
ከመመኘት ይልቅ ዐይኔን ባጣው የተሻለ እንደሆነ አንብቤያለሁ (ማቴዎስ 5፥29)። ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምሥጋና ባሰላስል የእግዚአብሔር ሰላም ከእኔ ጋር እንደሚሆን አንብቤያለሁ (ፊልጵስዩስ 4፥7-8)። የሥጋን ነገር ማሰብ ሞትን እንደሚያመጣ፣ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሰላም እና ሕይወትን እንደሚያመጣ አንብቤያለሁ (ሮሜ 8፥6)። እምነቴ በእግዚአብሔር ሰላም እንዲረካ ስጸልይ በመንፈሱ ሰይፍ የምኞትን መርዝ አሸንፈዋለሁ። በእግዚአብሔር ጸጋም የሚያጓጓ ኀይሉ ይሰበራል።
ወደ ፊት የሚመለከት እምነት
በሥጋ የሞቱ ሰዎች ከኀጢአት ጋር የሚጋደሉት በዚህ መንገድ ነው። ክርስቲያን መሆን ማለት ይህ ነው። የቀድሞ ማንነታችን ሞቷል፤ በቦታው አዲስ ፍጥረት ተተክቷል። አዲስ የሚያደርገውም እምነት ነው። የኢየሱስን ሞት ወደ ኋላ በመመልከት ማመን ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት ያለውን የእርሱ የተስፋ ቃል ጭምር በመመልከት ማመን ነው። ስላደረገው ነገር እርግጠኛ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ፊት ስለሚያደርገውም ነገር ደስ መሰኘት ማለት ነው።
ዘላለማዊነት ላይ አተኩረን የእምነትን ገድል እንጋደላለን። ዋነኛ ጠላታችን፣ ኀጢአት ወደፊት ሕይወታችንን በደስታ ይሞላዋል የሚለው የውሸት አመለካከት ነው። ዋነኛ መሣሪያችን ደግሞ እግዚአብሔር የወደፊት ሕይወታችንን በደስታ የተሞላ ያደርገዋል የሚለው እውነት ላይ ነው። እምነታችን ውሸትን ድል የምናደርግበት መሣሪያ ነው፤ ምክንያቱም እምነት በእግዚአብሔር ደስ ይሰኛልና።
ስለዚህ ከፊታችን ያለው ፈተና እግዚአብሔር የሚለውን እርሱ ስላዘዘን ብቻ ማድረግ ሳይሆን፣ ከልባችን እርሱ መልካም ስለሆነ እርሱን መፈለግ ጭምር ነው። ምክንያቱም እርሱ መልካም ነው። ፈተናው ጽድቅን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ጽድቅን መፈለግ ጭምር ነው። ተግዳሮቱ በጠዋት ተነሥተን በጸሎት ቅዱሳት መጻሕፍትን ማሰላሰል፣ ደግሞም የእግዚአብሔርን “የከበረና እጅግ ታላቅ የተስፋ ቃል” በማመን ደስታና ሰላም እስክናገኝ ድረስ መጽናት ነው (ሮሜ 15፥13፤ 2ኛ ጴጥሮስ 1፥4)። በፊታችን ደስታ ስለተቀመጠ፣ የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ከባዶች አይሆኑብንም (1ኛ ዮሐንስ 5፥3)። በፊታችን ሐሴት ስላለ፣ የኀጢአት ማታለያም እኛን ለመሳብ ተራና ርካሽ ይሆንብናል።
በ ጆን ፓይፐር