ያልተወለዱ ሕፃናትን መግደል ስሕተት የሚሆንባቸው 10 ምክንያቶች

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልተወለደ ፅንስ ሰብዓዊ መብት መሟገት አይደለም። ይልቁንም፣ እውነት እነዚህ ያልተወለዱ ፅንሶች ሰው ከሆኑ፣ ውርጃ ሊደርስባቸው አይገባም ብሎ መሞገት ነው። ፅንስን ማቋረጥ ላይ የሚሠሩ አንዳንድ ሐኪሞች፣ ያልተወለዱ ፅንሶች ሰው መሆናቸውን ያምናሉ፤ ይሁን እንጂ በመደበኛነት ውርጃን ይፈጽማሉ። ምክንያቱም ደግሞ፣ እነዚህ ሐኪሞች ምንም እንኳ ፅንስን ማቋረጥና ንጹሕ ነፍስን ማጥፋት አሰቃቂ ነገር እንደሆነ ቢያምኑም፣ በእናት እና በልጇ ላይ ሊፈጠሩ በሚችሉ ከባድ ሁኔታዎች ምክንያት ግን ይህንን ማድረግ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለው ያስባሉ። ከእነዚህ ሐኪሞች አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚመሩ ክርስቲያኖች መሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ግን ስሕተታቸው አይታያቸውም። ይህንንም ጽሑፍ የጻፍኩት እነዚህ ሐኪሞች አቋማቸውን በድጋሚ እንዲያጤኑት ለማሳሰብና ለማበረታታት ነው።

  1.  እግዚአብሔር በዘፀአት 20፥13 ላይ አትግደል ብሎ አዝዟል።

አንዳንድ ግድያዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተቀባይነት እንዳላቸው ይገባኛል። በዘፀአት 20፥13 ላይ ያለው ‘አትግደል’ የሚለው ቃል፣ በዕብራይስጥ ‘ራሀዝ’ ማለት ነው። ይህ ቃል በዕብራይስጥ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ 43 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ቀጥተኛ ትርጉሙም፣ በጭካኔ የሚፈጸም የግለሰብ ግድያ ማለት ነው። ዘኁልቁ 35፥27 ላይ ካለው ከአንድ ዐውድ በስተቀር፣ ጦርነት ላይ የሚፈጸምን ወይም በፍርድ የተወሰነን ግድያ ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሎ አያውቅም። ይልቁንም፣ ሕጋዊ እና ሕገ ወጥ በሆነው ግድያ መካከል ግልጽ የሆነ መስመርን ያሰምራል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘኁልቁ 35፥19፣ “ደም መላሹም ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው” ይላል። ‘ነፍሰ ገዳዩ’ የሚለው ይህ ቃል፣ በአስርቱ ትእዛዛት ላይ ከተከለከለው ‘ራሀዝ’ ከሚለው ቃል የመጣ ነው። ‘ይግደለው’ የሚለው ቃል ደግሞ ሕጋዊ የሆነን የሞት ፍርድን የሚያመለክት ነው።

አብዛኛውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ሕጋዊ ስለሆነ ግድያ ሲናገር፣ በውስጥ ታዋቂነት የእግዚአብሔርን ሥልጣን ለገዢ ባለ ሥልጣናት ስለ ማካፈል እያወራ ነው። መንግሥት ሰላምንና ፍትሕን ለማስፈን በእግዚአብሔር እንደተሾመ አካል ድርሻውን ሲወጣ፣ በሮሜ 13፥1-7 ላይ፣ “ሰይፉን በከንቱ አልታጠቀም” የተባለለትን መብቱን እየተወጣ ነው ማለት እንችላለን። ይህንንም መብቱን ጥፋተኛን ለመቅጣት እንጂ፣ ንጹሐንን ለማጥቃት በፍጹም መጠቀም የለበትም (ሮሜ 13፥4)።

ስለዚህ፣ “አትግደል” የሚለው ትዕዛዝ፣ ግልጽ በሆነ መልኩ፣ ንጹሐን የሆኑን ያልተወለዱ ሕፃናትን መግደልን ያካትታል ማለት ነው።

  1. በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለን ፅንስ ማጨናገፍልዩ የሆነውን የእግዚአብሔር ሰውን-የማበጀት ሥራ ማጨናገፍ ነው

ፅንስ ከማሕፀን ሲወርድ ምን እንደሚፈጠር ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት እንችል ይሆን? እስቲ ሁለት ክፍሎችን እንመልከት፦ መዝሙር 139፥13፣ “አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ” ይላል።

ከዚህ ጥቅስ የምንረዳው ነገር ቢኖር፣ በማሕፀን ውስጥ የሚካሄደው ሰውን የመፍጠር ሂደት የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ነው። ዳዊት እዚህ ጋር “አንተ” የሚለው እግዚአብሔርን ነው። ሂደቱም እንደ ጅምላ የፋብሪካ ምርት ሳይሆን፣ ጥንቃቄ እንደሞላው የሽመና ሥራ ነው። “በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ” ሲል፣ በማሕፀን ውስጥ ያለ ጽንስ በእግዚአብሔር እየተበጀ መሆኑን ያሳያል። እያበጀም ያለው በአጽናፈ ዓለሙ ላይ ካለ ከየትኛውም ፍጥረት በተለየ መልኩ የራሱ አምሳል የሆነውን ሰውን ነው።

ብዙም የማይታወቀው ሌላኛው ጥቅስ ደግሞ በኢዮብ መጽሐፍ ላይ ይገኛል። ኢዮብ፣ ምንም እንኳ በዚያ ባሕል ውስጥ ባሪያዎች ሙሉ ሰው እንዳልሆኑና እንደ ንብረት ተደርገው ቢታሰቡም፣ እርሱ ግን የአገልጋዮቼን አቤቱታ ሳልቀበል ቀርቼ አላውቅም በማለት ተቃውሞውን ሲያሰማ እንመለከታለን። እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ኢዮብ እንዴት እየተከራከረ እንዳለ ነው።

ኢዮብ 31፥13-15 እንዲህ ይላል፦ “ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቼ አቤቱታ ባቀረቡ ጊዜ፣ ፍርድ አዛብቼ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ሲነሣ ምን አደርጋለሁ? ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ? እኔን በማሕፀን ውስጥ የፈጠረኝ እነርሱን የፈጠረ አይደለምን? በሆድ ውስጥ የሠራንስ እርሱ ራሱ አይደለምን?”

ቁጥር 15፣ ኢዮብ አገልጋዩን ከሰው አሳንሶ ቢመለከት ኖሮ፣ ጥፋተኛ የሚሆንበትን ምክንያት ይገልጻል። ጉዳዩ ያለው አንዱ ሰው ነፃ ሆኖ ሌላው ደግሞ ባርያ ሆኖ መወለዱ ላይ አይደለም። ጉዳዩ ከመወለድ የሚቀድም ነው። ኢዮብንም ሆነ አገልጋዮቹን በማሕፀን ውስጥ ያበጃቸው እግዚአብሔር ነው። የኢዮብ ሙግት መነሻ ይህ ነበር።

ስለዚህ መዝሙር 139 እና ኢዮብ 31 በፅንስ ሂደት ውስጥ ዋነኛው ሸማኔ፣ ፈጣሪ እና ሠሪ እግዚአብሔር መሆኑን ይነግሩናል። ታዲያ ይህንን ማንሳት ለምን አስፈላጊ ሆነ ካልን፣ ምክንያቱ፣ ሰውን መፍጠር የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ስለሚያስረዳ ነው የሚል ነው። እናት እና አባት ዘርን ቢያበረክቱም፣ የፅንሱን ማንነት የሚፈጥረው ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በማሕፀን ውስጥ ፈጣሪ እና አበጂ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶ ሲናገር፣ ሂደቱ ልዩ የሆነ የእርሱ ሥራ መሆኑን እያሳሰበ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ እይታ አንፃር፣ ፅንስን ማበጀት ልዩ የሆነ የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ ነው።

‘ሙሉ ሰውነት’ ምን እንደሆነ ያለ ማቋረጥ ልንከራከር እንችላለን። ነገር ግን በሙሉ መተማመን ማለት የምችለው፦ ማሕፀን ውስጥ የሚካሄደው ነገር የእግዚአብሔር ልዩ የሆነ ሰውን የማበጀት ሥራ ነው። ታዲያማ እግዚአብሔር እና እግዚአብሔር ብቻ ነው የዚህን ሂደት ጥልቀትና ምስጢራዊነት የሚያውቀው። ስለዚህ በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለ ፅንስን ማቋረጥ እግዚአብሔርን መስደብ እንዳይደለ ማሰብ ሞኝነት ነው።

አዎንታዊ በሆነ አነጋገር ስናስቀምጠው፦ በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለን ፅንስን ማቋረጥ ወይም ማበላሸት በእግዚአብሔርን ሥራ ላይ ማመጽ ነው። ውርጃ በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔርም ላይ የሚደረግ ዐመፃ ነው። እርግዝና ከተፈጠረበት ቅጽበት አንስቶ ልዩ በሆነ መልኩ እግዚአብሔር በሥራ ላይ ነው። መዝሙር 139፥13 እና ኢዮብ 31፥15 ለዚህ ግልጽ የሆነን ምስክርነት ይሰጣሉ።

  1. ፅንስን ማቋረጥ፣ “የንጹሐንን ደም አታፍስሱ” ከሚለው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ከተጠቀሰው ትዕዛዝ ስር የሚካተት ነው።

‘የንጹሐን ደም’ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 20 ጊዜ የሚሆን ተጠቅሷል። የተጠቀሰበትም አውድ፣ ሰዎች ይህንን ደም እንዳያፈሱ በሚያስጠነቅቅ ወይም ያፈሰሱትን በሚኮንን መልኩ ነው። የንጹሐን ደም የሚለው ደግሞ የሕፃናትንም ደም ይጨምራል (መዝሙር 106፥38)። ኤርምያስ ሲናገር፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ’ ይላል (ኤርምያስ 22፥3)። ታዲያ ያልተወለዱት ደም በምድር ከሚፈሱት እኩል ንጹሕ አይደለምን?

  1. እግዚአብሔር ለደካሞች፣ ደግሞም ረዳት ለሌላቸውና ለተጠቁ ጥበቃና ከለላ እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ይናገራል

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጻተኞች፣ ስለ መበለቶች እና ወላጅ አልባ ስለሆኑ ሕፃናት በተደጋጋሚ ይናገራል። እነርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ የተለየ እንክብካቤን ስለሚያገኙ፤ የእግዚአብሔርም ሕዝቦች የተለየ እንክብካቤን ሊያሳዩአቸው ይገባል።

“መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብፅ መጻተኛ ነበራችሁና [እናንተም በአንድ ወቅት ፅንስ ነበራችሁ!]። ባል በሞተባት ወይም አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አታውሉ። ግፍ ብታውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ [ልክ በዘፍጥረት 4፥10 ላይ የአቤል ደም ከምድር ወደ እግዚአብሔር እንደጮኸው] ጩኸታቸውን በርግጥ እሰማለሁ። ቍጣዬ ይነሣል፤ በሰይፍም እገድላችኋለሁ።” (ዘፀአት 22፥21-24)።

“እግዚአብሔር በተቀደሰ ማደሪያው፣ ለድኻ አደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች ነው” (መዝሙር 68፥5)።

“ለዐቅመ ቢሶችና ለድኻ አደጎች ፍረዱላቸው፤ የችግረኛውንና የምስኪኑን መብት አስከብሩ። ወገን የሌለውንና ችግረኛውን ታደጉ፤ ከግፈኛውም እጅ አስጥሏቸው” (መዝሙር 82፥3-4)።

“መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤ የድኻ አደጉንም ነፍስ አጠፉ። እነርሱም “እግዚአብሔር አያይም፤ የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም” አሉ። … በደላቸውን ወደ ራሳቸው ይመልሳል፤ በክፋታቸውም ያጠፋቸዋል፤ እግዚአብሔር አምላካችን ይደመስሳቸዋል” (መዝሙር 94፥6-723)።

  1. የውርጃ ተሟጋቾች የሰውን ነፍስ ማጥፋትንበሕይወት ውስጥ ከሚገጥሙ አስቸጋሪ ወይም አሰቃቂ ሁኔታዎች በታች አሳንሶ በመፈረጅ፣ እግዚአብሔር መከራን በመከልከል ብቻ ሳይሆን በመከራ ውስጥም ኀይሉን መግለጽ እንደሚወድ ይክዳሉ። በዚህም መጽሐፍ ቅዱሳዊውን አስተምህሮ ይቃወማሉ።

ታዲያ ይህ ማለት መከራን ለራሳችን ወይም ለሌሎች መመኘበት አለብን ማለት አይደለም። ነገር ግን፣ መከራ አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ በዚህ በወደቀው ዓለም (ሮሜ 8፥20-25ሕዝቅኤል 18፥32)፣ በተለይም ደግሞ ወደ መንግሥቱ ለሚገቡትና (የሐዋርያት ሥራ 14፥221ኛ ተሰሎንቄ 3፥3-4) የቅድስናን ኑሮ ለመኖር ለተጠሩት በእግዚአብሔር የተወሰነላቸው አስፈላጊ ድርሻ እንደሆነ እንመለከታለን (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥12)። ይህ ማለት ግን መከራ እግዚአብሔርን ያስደስተዋል ማለት አይደለም። ቢሆንም ግን መከራን እንደ አሰቃቂ ጉዳት ብቻ ልንቆጥረው አይገባም። ይልቁንም ወደ እግዚአብሔር መቅረቢያ፣ ለዚህኛውም ሕይወት መጠንከሪያ (ሮሜ 5፥3-5ያዕቆብ 1፥3-4ዕብራውያን 12፥3-112ኛ ቆሮንቶስ 1፥94፥7-1212፥7-10)፣ እንዲሁም በሚመጣው ሕይወት የክብር መገለጫ እንደሆነ ልናስተውል ይገባል።(2ኛ ቆሮንቶስ 4፥17ሮሜ 8፥18)።

የውርጃ ተሟጋቾች፣ ‘በዚህ ሕይወት ከሚገጥም ችግር ይልቅ ፅንስን ማቋረጥ ይሻላል’ በማለት ሲናገሩ፣ ጸጋው በመከራ ውስጥ ድንቅ ነገሮችን ማድረግ እንደሚችል ካስተማረው ከእግዚአብሔር በላይ እኛ እናውቃለን እያሉ ነው።

  1. የሚገደሉት ፅንሶች ወደ መንግሥተ ሰማይ ይሄዳሉ ወይም በሚመጣው ዓለም ሙሉ ሰው ይሆናሉ ብሎ በዚህ ለመጽናናት መሞከርና ድርጊቱን ማጽደቅ አስከፊ የሆነ ኀጢአት ነው።

እንዲህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በኀጢአቱ ልቡ ለተሰበረና በንስሓ የእግዚአብሔርን ፊት ለሚፈልግ ሰው አስደናቂ የሆነ ተስፋ ነው። ሆኖም ግን በሚመጣው ዘመን የሚሆነውን በማሰብ ግድያን ለማጽደቅ መሞከር እጅግ የለየለት ክፋት ነው። ይህ ልክ ነው ካልን፣ የአንድ ዓመት ሕፃንን ወይም እውነተኛ አማኝን መግደል ልክ ነው ልንል ነው ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ ኀጢአት እየሠራን እንኑር?“ (ሮሜ 6፥1) ወይስ “በጎ እንዲመጣ ክፉ እንሥራ?” በማለት ይጠይቃል (ሮሜ 3፥8)። የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ በፍጹም የሚል ነው። በእግዚአብሔር ቦታ ጣልቃ በመግባት ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚሄደውንና የማይሄደውን ለመወሰን መሞከር ኀጢአት ነው። እግዚአብሔርን መታዘዝ እንጂ፣ እንደ እግዚአብሔር መሆን አልተፈቀደልንምና።

  1. መጽሐፍ ቅዱስ በፍትሕ መጓደል ምክንያት ወደ ሞት የሚነዱትን እንድንታደግ ያዘናል

“ወደ ሞት የሚነዱትን ታደጋቸው፤ እየተጐተቱ ለዕርድ የሚሄዱትን አድናቸው። አንተም፣ “ስለዚህ ነገር ምንም አላውቅም” ብትል፣ ልብን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ሕይወትህን የሚጠብቃት እርሱ አያውቅምን? ለእያንዳንዱስ እንደ ሥራው መጠን አይከፍለውምን?” (ምሳሌ 24፥11-12)

ፅንሶች በዚህ ውስጥ የማይካተቱበት ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ፣ ምግባራዊ ወይም ሃይማኖታዊ ምክንያት የለም። ያልተወለዱ ፅንሶችን ማስወረድ ይህንን ቃል አለመታዘዝ ነው።

  1. ኢየሱስ ሕፃናት ወደ እርሱ እንዳይመጡ ለሚከለክሉና የአዳኙ ትኩረት አይገባቸው ብለው ለሚያስቡ የሰጠው ግሣጼ፣ ያልተወለዱ ሕፃናትን ለሚያስወርዱም የሚሠራ ነው

“ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ ያመጡ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ባዩ ጊዜ ገሠጿቸው። ኢየሱስ ግን ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና” (ሉቃስ 18፥15-16)። የግሪኩን ትርጉም ስንመለከት፣ ሉቃስ ‘ሕፃናት’ በማለት በሉቃስ 18፥15 ላይ የተጠቀመው ቃል፣ በኤልሳቤጥ ማሕፀን ውስጥ ያለውን ፅንስ ለመግለፅ በሉቃስ 1፥41፣ 44 ላይ ከተጠቀመው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው።

“ትንሽ ልጅ አምጥቶም በመካከላቸው አቆመ፤ ዐቅፎትም፣ ‘ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ሁሉ የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው’ አላቸው” (ማርቆስ 9፥36-37)።

  1. ሕይወትን ለሰው መስጠት እና መውሰድ የፈጣሪው የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ መብት አይደለም

ኢዮብ ቤት ወድቆባቸው ልጆቹ በሙሉ መሞታቸውን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ እንዲህም አለ፦ “ዕራቍቴን ከእናቴ ማሕፀን ወጣሁ፤ ዕራቍቴንም እሄዳለሁ። እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን” (ኢዮብ 1፥21)።

ኢዮብ ከእናቱ ማሕፀን ስለመውጣቱ ሲናገር፣ “እግዚአብሔር ሰጠ” ይላል። ስለ ሞቱ ደግሞ ሲናገር፣ “እግዚአብሔር ነሣ” ይላል። ውልደት እና ሞት የእግዚአብሔር ሥራዎች ናቸው። አስደናቂ በሆነው በዚህ ሕይወት ውስጥ ሰጪውና ወሳጁ እግዚአብሔር ነው። እኛ የምንመርጥበትና የምንወስንበት ምንም መብት የለንም። በዚህ ውስጥ የእኛ ድርሻ የተሰጠንን መንከባከብና ለእርሱ ክብር መጠቀም ብቻ ነው።

  1. በመጨረሻም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን የኀጢአትን ይቅርታ፣ የኅሊናን ዕረፍት እና የዘላለምን ተስፋ ያስገኛል። እንደዚህ ባለው ታላቅ ፍቅር የተያዘ የትኛውም የክርስቶስ ተከታይ ለጥቅም ወይንም ነቀፌታን ለመሸሽ ሲል ይህንን እውነት እንዲተው ከሚፈትኑት ፍርሀትና ስግብግብነት ነፃ ነው።

በፅንስ ማስወረድ ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉ የጉዳዩን ከባድነት እንዲገነዘቡ፣ ደግሞም ስለ ፅንሱ ሕይወት ጥብቅና መቆም የሚችሉበትን እምነት እና ፍቅር በክርስቶስ ኢየሱስ እንዲያገኙ ጸሎቴ ነው።

ጆን ፓይፐር