ምክንያቱም ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ፣ የጌታ ነጻ ሰው ነው፤ እንዲሁም ሲጠራ ነጻ የነበረ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7፥22)
ጌታ ማለት አለቃ ማለት ነው። ክርስቶስ ደግሞ መሲሕ ማለት ነው። ጳውሎስ፣ ትርጉሙ አለቃ የሆነውን “ጌታ”ን እና ትርጉሙ መሲሕ የሆነውን “ክርስቶስ”ን ቦታ ቀያይሮ ያስቀምጣቸዋል ብዬ እጠብቅ ነበር።
“የጌታ ነጻ ሰው” ብሎ ነጻነታችንን ጌታችን ከሆነው ከኢየሱስ ጋር ያያይዘዋል። ከዚያም “የክርስቶስ ባሪያ” በማለት ባርነታችንን ከመሲሐችን ከኢየሱስ ጋር ያያይዘዋል። መሲሑ የመጣው ሕዝቡን ከምርኮ ነጻ ሊያወጣ በመሆኑ እና ጌቶች ደግሞ የባሪያዎቻቸውን ሕይወት የሚቆጣጥሩ በመሆናቸው፣ ይህንን እንግዳ ያደርገዋል።
ለምንድን ነው በዚህ መንገድ የተናገረው? ለምንድን ነው ባርነትን ከነፃነት ጋር ሳይሆን ከመሲሕ ጋር፣ ነጻነትን ደግሞ ከባርነት ጋር ሳይሆን ከአለቅነት ጋር ያገናኘው?
የሚመስለኝ፦ መቀያየሩ በአዲሱ ነጻነታችን ላይ ሁለት ውጤት፣ እንዲሁም በአዲሱ ባርነታችን ላይ ሁለት ውጤት ይኖረዋል።
በአንድ መልኩ፣ “የጌታ ነጻ ሰው” ብሎ ሲጠራን፣ ለአዲሱ ነጻነታችን ገደብን ያበጅለታል፣ ማረጋገጫንም ይሰጠዋል።
- የእርሱ ጌትነት ከሁሉም ጌቶች በላይ ነው፣ ስለዚህ ነጻነታችን ክርክር የሌለውና ፈጽሞ የተረጋገጠ ነው።
- ከሌሎች ጌቶች ነጻ ብንሆንም ከእርሱ ግን ነጻ አይደለንም። ነጻነታችን በምሕረት የተገደበ ነው። ኢየሱስ ጌታችን ነው።
በሌላ በኩል፣ “የክርስቶስ ባሪያዎች” ብሎ ሲጠራን፣ ባርነታችንን ቀላልና ጣፋጭ ያደርገዋል፦
- መሲሑ የእርሱ የሆኑትን ከምርኮ እስራት አውጥቶ ወደ ሰፊ የሰላም ስፍራ ያመጣቸዋል። “ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም” (ኢሳይያስ 9፥7)።
- ጣፋጭ የሆነውን ደስታ ሊሰጣቸው የራሱ ያደርጋቸዋል። “ከዐለቱም ማር አጠግባችኋለሁ” (መዝሙር 81፥16)። ዓለቱም መሲሑ ክርስቶስ ነው።
ስለዚህ፣ ክርስቲያኖች ሆይ፣ በዚህ ደስ ይበላችሁ፦ “ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ፣ የጌታ ነጻ ሰው ነው” — የዋናው አለቃ። “እንዲሁም ሲጠራ ነጻ የነበረ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው” – የነጻ አውጪውና የአስደሳቹ መሲሕ።