የይቅርታ አሠራር | የካቲት 3

“በደላችንን ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና። ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉው አድነን እንጂ።” (ሉቃስ 11፥4)

ማነው ማንን መጀመሪያ ይቅር የሚለው?

  • በአንድ በኩል ኢየሱስ፣ “በደላችንን ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና” ይላል (ሉቃስ 11፥4)።
  • በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስ፣ “ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ” ይላል (ቆላስይስ 3፥13)።

“እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና” ማለት፣ የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰድነው እኛ ነን ማለት አይደለም። ይልቁንም፣ ኢየሱስ እያለን ያለው፣ በክርስቶስ ስናምን እግዚአብሔር ይቅር ስላለን (ሐዋርያት ሥራ 10፥43)፣ ይቅር ከተባልንበት ልምድ በመነሳት እኛም በተሰበረ ልብ፣ በደስታ፣ በምስጋናና በሙሉ ተስፋ ሌሎችን ይቅር እንላለን ነው።

ይህ ይቅር ባይ መንፈስ እኛ ራሳችን በይቅርታ እንደዳንን የሚያመለክት ነው። ሌሎችን ይቅር ማለታችን እምነት እንዳለን ያሳያል። ይህም ከክርስቶስ ጋር መተባበራችንን ከማሳየቱ ባለፈ፣ ትሁቱና መኀሪው መንፈስ ቅዱስ እንዳደረብን ያረጋግጣል።

ነገር ግን አሁንም ኀጢአትን እናደርጋለን (1ኛ ዮሐንስ 1፥8-10)። ስለዚህም ክርስቶስ እኛን ወክሎ በሠራው ሥራ አዲስ ይቅርታን ለመቀበል አሁንም ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንላለን። ይህንን ግን በውስጣችን ቂም እና ይቅር የማይልን መንፈስ ይዘን በድፍረት ማድረግ አንችልም። በማቴዎስ 18፥23-35 ላይ ያለውን ምሳሌ አስታውሱ። በዚህ ምሳሌ ይቅር ባይ ያልሆነው አገልጋይ የነበረበት ዐሥር ሚሊዮን ብር ዕዳ ተሰርዞለት ሳለ፣ ዐሥር ብር የተበደረውን አገልጋዩን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አልነበረም። የንጉሡ ምሕረት የእርሱን ልብ እንዳልለወጠው ይቅር ባይ ባልሆነው መንፈሱ አሳየ።

ኢየሱስ ከዚህ ሞኝነት ሊጠብቀን ይህንን ጸሎት ያስተምረናል፦ “በደላችንን ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና” (ሉቃስ 11፥4)። ኢየሱስ ይቅርታን የምንለምነው ይቅር ባይ ስለሆንን ነው ያለን ለዚህ ነው። እያልን ያለነው እንዲህ ነው፦ “አባት ሆይ፣ በክርስቶስ የተገዛውን ምህረት አብዛልኝ፣ ምክንያቱም ይቅር የተባልኩት በዚህ ምሕረት ነው። በቀልን ሁሉ ትቼ አንተ ያበዛህልኝን ምሕረትም ለሌሎች ማብዛት የምችለው በዚሁ ምህረት ነው።”

ወዳጆቼ፣ የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነት ዛሬም እንደ አዲስ ቅመሱት፣ እወቁት። ያ የይቅርታ ጸጋ ሌሎችን ይቅር እንድትሉ በልባችሁ ተትረፍርፎ ይፍሰስ። ይህን ጣፋጭ ጸጋ አጣጥሙት። በልጁ ደም የተገዛውን አዲስ ይቅርታ ለመቀበል ወደ እግዚአብሔር በምትቀርቡበት ጊዜ፣ በእርግጥም እግዚአብሔር የሚያያችሁ ሙሉ ይቅርታን እንዳገኙ እና ሙሉ ይቅርታን እንደሚሰጡ ልጆቹ እንደሆነ እርግጠኞች ሁኑ።