በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ ይህም በመጀመሪያ ለአይሁድ፣ ቀጥሎም ለአሕዛብ ነው። በወንጌል የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጦአልና፤ ጽድቁም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በእምነት የሆነ ነው፣ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው። (ሮሜ 1፥16–17)
በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን ጽድቅ ያስፈልገናል። እኛ ግን ያ የለንም። እኛ ያለን ኃጢአት ነው።
እግዚአብሔር ደግሞ እኛ የሚያስፈልገን፣ ነገር ግን የማይገባን ነገር አለው፤ እርሱም ጽድቅ ነው። እኛ ደግሞ እግዚአብሔር የሚጠላውና የሚጸየፈው ነገር አለን፤ ያም ኃጢአት ነው። ታዲያ ለዚህ ሁኔታችን የእግዚአብሔር ምላሽ ምንድን ነው?
የእርሱ ምላሽ፣ በእኛ ፈንታ ሞቶ ፍርዳችንን የተሸከመው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሰው አምሳል፣ የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆን በመላክ ፈጸመው፤ በዚህም ኀጢአትን በሥጋ ኰነነ” (ሮሜ 8፥3)። ፍርዱን የተሸከመው የማን ሥጋ ነበር? የእርሱ። የማን ኃጢአት ነበር የተፈረደበት? የኛ። ታላቁ ልውውጥ ይህ ነው። ይህን ሃሳብ በድጋሚ በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፥21 ላይ እናገኘዋለን፦ “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው።”
እግዚአብሔር ኃጢአቶቻችንን በሙሉ በክርስቶስ ላይ በማድረግ ቀጥቷቸዋል። በክርስቶስ የመታዛዝ ሞትም፣ እግዚአብሔር ጽድቁን ፈፅሞና አረጋግጦ ለእኛ እንዲቆጠርልን አደረገ። የእኛ ኃጢአት በክርስቶስ ላይ፣ የእርሱም ጽድቅ በእኛ ላይ ሆነ።
ለትልቁ ችግራችን ክርስቶስ የእግዚአብሔር መልስ እንደሆነ ከልክ በላይ አጽንዖት ልንሰጥው አንችልም። ሁሉም የክርስቶስ ውለታ አለበት።
ክርስቶስን ከልክ በላይ ልትወዱት አትችሉም። ስለ እርሱ ከልክ በላይ ልታስቡ፣ ወይም ከልክ በላይ ልታመሰግኑት፣ ወይም ከልክ በላይ በእርሱ ላይ ልትታመኑ አትችሉም። ይቅርታችን፣ ቅድስናችን፣ ጽድቃችን ሁሉ ክርስቶስ ነው።
ወንጌል፣ የእኛ ኃጢአት በክርስቶስ ላይ፣ የእርሱ ጽድቅ ደግሞ በእኛ ላይ እንደ ተጫነ የሚያበስር የምሥራች ነው። እናም ይህ ታላቅ ልውውጥ የእኛ የሚሆነው በሥራ ሳይሆን በእምነት ብቻ ነው። “በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም” (ኤፌሶን 2፥8-9)።
ሸክማችንን የሚያራግፍልን፣ ደስታንና ብርታትን የሚሰጠን ታላቁ የምሥራች ይህ ነው።