መከራ ያቀጣጠለው ንቅናቄ

ዴቪድ ብሬነርድ (1718-1747)

በሕይወት የኖረው 29 ዓመት ከ5 ወር ከ19 ቀናት ብቻ ነበር። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ክርስቲያን የነበረው ለስምንት ዓመታት ሲሆን፣ በሚሲዮናዊነት ያሳለፈው ደግሞ አራት ዓመታትን ብቻ ነበር። ሕይወቱ አጭር ቢሆንም እንደ ዴቪድ ብሬነርድ ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ግን ጥቂት ናቸው።

ሕይወቱ ተጽእኖ መፍጠር የቻለው ለምንድን ነው? ጆን ዌስሊ፣ “ሁሉም ሰባኪ በጥንቃቄ ሊያነበው የሚገባው መጽሐፍ ‘Life of David Brainerd’ ነው” ያለው ለምንድን ነው? ዊልያም ኬሪ ደግሞ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለውን የብሬነርድን ሕይወት እንዴት ‘ውድ እና ቅዱስ’ ሊል ቻለ? በሕንድና በፋርስ ሚሲዮናዊ የነበረው ሄነሪ ማርቲን በ1802 የካምብሪጅ ተማሪ በነበረበት ወቅት፣ “እንደ እርሱ ለመሆን እመኛለሁ” ሲል የጻፈው ለምንድን ነው? (Life of David Brainerd 4)

ሕይወቱ እንዴት ትልቅ ተጽእኖ መፍጠር ቻለ? የቅርብ ምሳሌ በማንሣት ጥያቄውን የበለጠ ግልጽ ላድርገው፤ የብሬነርድ ሕይወት እንዴት በእኔ ሕይወት ላይ ተጽእኖ ፈጠረ? በአገልግሎት ለመቀጠል፣ በቅድስና እና በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ፍሬያማ ሕይወት ለመኖር እንድጥር የረዳኝ እንዴት ነው?

መልሱ ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ደካማ ለሆኑ፣ ለታመሙ፣ ተስፋ ለቆረጡ፣ ለተሰበሩ፣ ብቸኛ ለሆኑና በትግል ውስጥ ሆነው ወደ እርሱ ቀንና ሌሊት ለሚጮኹ ቅዱሳን፣ እርሱ ይከብር ዘንድ በሕይወታቸው አስደናቂ ነገሮችን ያደርጋል፤ ለዚህ ደግሞ የብሬነርድ ታሪክ ግልጽ ምስክር ነው። በእነዚህ መከራዎች ውስጥ የምናፈራቸው ፍሬዎች አሉ። ይህንን ለማሳየት ብሬነርድ ያለፈባቸውን የሕይወት ውጣ ውረዶች፣ ለእነርሱም የነበረውን ምላሽ፣ ደግሞም እግዚአብሔር ከነድክመቶቹ እንዴት እንደ ተጠቀመው እናያለን።

የብሬነርድ ትግሎች

ከ300 ዓመታት በፊት ብሬነርድ በሚያዚያ 20፣ 1718 አሜሪካ ወስጥ በምትገኝ ሃዳም በምትባል ከተማ ተወለደ። ክርስቲያንም የሆነው በ21 ዓመቱ ነበር። ለመጋቢነት አገልግሎት በዬል ዩኒቨርስቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ፣ ብሬነርድ ከአስተማሪዎቹ መካከል አንዱን፣ “ከወንበር በላይ ሞገስ የሌለው” ብሎ ሲናገር ይሰማዋል። በጊዜው በተማሪዎቹ እና በዩኒቨርስቲው መምህራን መካከል ውጥረት የነበረበት ወቅት ነው። ብሬነርድ ከክፍሉ ከፍተኛ ውጤት ከሚያመጡት መካከል ቢሆንም በነበረው ውጥረት ምክንያት ከዩኒቨርስቲው ተባረረ። 

በቀጣዮቹ ዓመታት በዬል ዩኒቨርስቲ የተፈጠሩትን ችግሮች ለማስተካከል ቢሞክርም አልተሳካለትም። እግዚአብሔር ለብሬነርድ ሌላ ዓላማ ነበረው። የእግዚአብሔር ዓላማ ለስድስት ዓመታት በመማርያ ክፍል ውስጥ ሆኖ ለክርስቶስ መንግሥት የጎላ ተጽዕኖ ሳያመጣ እንዲሞት ሳይሆን፣ በምድረ በዳ ለእግዚአብሔር ሲል መከራ በመቀበል በሚሲዮናዊነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ እንዲያመጣ ነበር።

የተጎሳቆለ ሰውነት

ብሬነርድ በሕመም ይሰቃይ ነበር። በ1740 ደም ማሳል ስለ ጀመረ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ለተወሰኑ ሳምንታት ለማቋርጥ ተገዶ ነበር። በግንቦት 1747 በመጽሐፉ እንዲህ ሲል ገልጿል፤ “ሰው በሌለበት ስፍራ በዝናብ በምነዳበት ወቅት ሰውነቴ እጅግ ዝሎ፣ ከአፌም ደም ብቻ ይወጣ ነበር” (Life of David Brainerd, 247)። እንዲሁም በዚሁ መጽሐፉ በሌላ ስፍራ፣ “ ከምሳ ሰዓት በኋላ ሕመሜ እጅግ እየጨመረ መጣ። ከዚህም ለማረፍ ወደ መኝታ መሄድ ግድ ሆኖብኝ ነበር… ከሕመሜ የተነሣ ለሞት የምቀርብባቸው ጊዜያት ነበሩ” (253) ብሏል።

በግንቦት 1747 ጆናታን ኤድዋርድስ ቤት በነበረበት ወቅት ዶክተሮች የማይድን የሳንባ በሽታ እንዳለበትና ለመሞት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንደ ቀረው ነግረውታል (447)። ከመሞቱ ሳምንት በፊት “ብሬነርድ፣ ‘በደረቴ ላይ የሚሰማኝ ሕመም ለመሸከም እጅግ የሚከብድ ነው። ለአንድ ደቂቃ እንኳ በዚህ ሕመም ውስጥ መቆየት እጅግ ከባድ ነው’ ይለኝ ነበር። ሕመም በተሞላበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳ እግዚአብሔርን ትዕግሥት በማጣት እንዳያሳዝን ይጨነቅ ነበር” በማለት የነበረበትን ሕመም፣ ኤድዋርድስ ገልጿል። ብሬነርድ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻው ምሽት በዙሪያው ለነበሩት፣ “ሞት ሰዎች እንደሚያስቡት አይደለም” ሲል ተናግሮ ነበር (475-476)።

ተስፋ የቆረጠ አእምሮ

ብሬነርድ የድብርት በሽታ ተጠቂ ነበር። በብዙ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ አልፏል። እጅግ የሚገርመው ግን እነዚህን ሁሉ አልፎ ቀጥሏል።

ያሳለፈውን የድብርት በሽታ በሞት መስሎ ይጠራዋል። የራሱን ሕይወት በጻፈበት የማስታወሻ ደብተሩ ላይ ከስቃዩ ለማምለጥ ሞትን የተመኘበት ቢያንስ 22 ቦታዎች አሉ። ለምሳሌ፣ እሑድ የካቲት 3፣ 1745 እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ነፍሴ የመጨረሻውን ‘ምሬትንና ሃሞትን’ (ሲኦል ማለት ይቻላል) የተሞላበት አርብን ታስታውሳለች። ‘የሚያንገዳግድን ጽዋ’ እንደገና እንድጠጣ እገደዳለሁ ብዬ እጅግ ፈርቼ ነበር። ይህ ከሞት ይልቅ እጅግ መራራ ነው። መቃብርንም ከተደበቀ ሀብት በላይ እንድመኝ አደረገኝ” (285)።

 “የኢየሱስ ክርስቶስ የርኅራኄው እቃ” እንደ ሆነ የሚገነዘበው ወደ ኋላ ዞር ብሎ ሲያይ ብቻ ነበር። ነገር ግን በጨለማ ሰዓታት ምንም የተስፋና የፍቅር ስሜት አይሰማውም ነበር። የድብርት በሽታ አስፈሪ ደረጃ የሚደርሰው፣ ራስን የማጥፋት ተፈጥሮአዊ ገደቦች መጥፋት ሲጀምሩ ነው። ነገር ግን ከዊልያም ኩፐር በተቃራኒ ብሬነርድ ራስን ለማጥፋት ፍላጎት አልነበረውም። የሞት ምኞቱ ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት አጥር ታጥረዋል፤ “እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሳ” (ኢዮብ 1፡21)። ሞቱን ብዙ ጊዜ ተመኝቷል፤ ነገር ግን ነፍሱን የሚወስዳት እግዚአብሔር ብቻ ነው ( Life of David Brainerd, 172,183,187,215,249)።

ብሬነርድ በእነዚህ የተስፋ መቁረጥ ማዕበሎች ውስጥ እያለፈ በሥራው የነበረው ትጋት እጅግ የሚያስገርም ነው። ይህን የደረሰበትን ሥቃይ በቅርበት ለሚያውቁ ሚስዮናውያን ሕይወቱ እጅግ የሚደንቅ ነበር።

ብቸኛ ነፍስ

በ1743 እ.ኤ.አ መጋቢት ወር አንድ ምሽት ሁለት ሰዎች የተናገሩትን መሸከም እንደ ነበረበት እና የተሰማውን ሐዘን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንድ ክርስቲያን ችግሬን እንዲያውቅ ጓጓሁ!” (ገጽ 204) በግል ማስታወሻውም ከአንድ ወር በኋላ፣ “ሰዎች ሲናገሩ የምሰማው ነገር እጅግ የሚያሳዝን ነው። የልቤን ሐዘን እና መንፈሳዊ ድካሜን የማዋየው እና ሰማያዊ ነገሮችን ከምክር እና ከጸሎት ጋር የምጋራው ሰው የለኝም”(207)። አንዳንድ ጊዜ  በዚህ ጭንቀት ምክንያት ብሬነርድ ወደ ሌሎች ሥራዎች ከመሄድ እንዲያፈገፍግ ሆኗል። ማክሰኞ ግንቦት 8፣ 1744 እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ልቤ በሥራ ጉዳይ ላይ ብቻ ተጠምዶ በሐሳብ ለመወሰድ ዝግጁ ነበር” (248)።
ብሬነርድ በአገልግሎቱ እስከ መጨረሻው ብቸኛ ነበር። የሕይወቱን የመጨረሻዎቹ ዐሥራ ዘጠኝ ሳምንታት ውስጥ የጆናታን ኤድዋርድስ ልጅ ከሆነችው ጄሩሻ ኤድዋርድስ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንደ ነበራቸው ብዙዎች ይጠረጥራሉ። ሆኖም ግን ብሬነርድ ባገለገለበት ዘመናት ሁሉ ብቸኛ እና የልቡን ሐሳብ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚያፈስ ሰው ነበር። እግዚአብሔርም ተሸክሞ አስቀጠለው።

የብሬነርድ ምላሽ

የብሬነርድን በርካታ ትግሎችን መጥቀስ እንችላለን፦ ከውጪ ሲያጋጥመው የነበረው መከራ፣ ለተፈጥሮ የነበረው መልካም ያልሆነ አስተሳሰብ፣ ሕንዳውያንን ለመውደድ የነበረው ፈተና፣ ይሠራበት የነበረበትን ቦታ ለመልቀቅ የነበረው ትግል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ብሬነርድ ለእነዚህ ፈተናዎች የነበረውን ምላሽ እናያለን።

እጅግ የሚያስገርመው ነገር ብሬነርድ ተስፋ አይቆርጥም ነበር። ምንም እንኳን ተጋድሎዎች ቢኖሩም በእምነቱና በአገልግሎቱ ተስፋ አለመቁረጡ የብሬነርድ ሕይወት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዲኖረው ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ነው። ብሬነርድ ሩጫውን ለመጨረስ፣ ጌታውን ለማክበር፣ መንግስቱንም ለማስፋት እና በቅድስና ለማደግ ራሱን የሰጠ ነበር። ለክርስቶስ ሥራ የነበረው የማያቋርጥ ትጋት በሕይወቱ ውስጥ የነበረውን ጨለማ ወደ ብርሃን እና ክብር ለውጦታል።

ብሬነርድ በሕይወቱ ውስጥ ቅድስናን በይበልጥ እንዲለማመድ ከሚያስችሉት ነገሮች ውስጥ የጾም ጸሎት ከሁሉ ይልቅ እጅግ አስፈላጊው ነው። በጽሑፎቹ ውስጥ ቀኑን ሙሉ በጸሎት የሚያሳልፍባቸው ቀናት እንደ ነበሩ እናነባለን። ረቡዕ ሰኔ 30፣ 1742፣ ”ቀኑን ሙሉ ያለማቋረጥ በጸሎት ሳሳልፍ ነበር” ሲል ጽፏል (172)። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በቀን ውስጥ ስድስት የተለያዩ ጊዜያትን ለጸሎት ይመድብ ነበር። ”እግዚአብሔር ይባረክ በጸሎትና በምስጋና የማሳልፍበት 5 ወይም 6 ጊዜ ነበረኝ። በልቤ ድነት ለሚያስፈልጋቸው ውድ ነፍሳት እና ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋፋት ትልቅ ሸክም አድሯል” (280)።

በጾም ጸሎት ብሬነርድ ቅድስናን እና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይበልጥ ለመጥቀም ይፈልግ ነበር። በተደጋጋሚ በግል ማስታወሻው ላይ ብዙ ቀናትን በጾም እንዳሳለፈ ይነግረናል። እጅግ የሚገርመው 25ኛውን የልደት በዓሉን ያሳለፈው በጾም ነበር።

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 20 እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይህንን ቀን በእግዚአብሔር ፊት በጾምና በጸሎት ለማሳለፍ የለየሁት ቀን ነው። በዚህ ቀን ለመለኮታዊው ጸጋ ክብር የምሰጥበት፣ በመንፈሳዊ ትግል እና ውስጣዊ ጭንቀት ውስጥ ለምትገኘው ነፍሴ ደግሞ ትቀደስ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የምቀርብበት ቀን ነው። ብቸኝነቴንና ሟች መሆኔን እንዲሁም ለዘላለማዊው እግዚአብሔር ክብር እጅግ ጥቂት እንደኖርኩ ሳስብ ልቤ በሕመም ይሞላል። ቀኑን ማንም በሌለበት ቦታ አሳለፍኩ። የልቤንም ሐዘን ለእግዚአብሔር ነገርኩ። ኦ እግዚአብሔር ሆይ! ከዚህ በኋላ በቀረኝ እድሜ ለክብርህ እንድኖር እርዳኝ” (205)።

የብሬነርድ መከራ ፍሬ

የብሬነርድ ልብ፣ ለእግዚአብሔር ፍጹም መሰጠቱ በጆናታን ኤድዋርድስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከዚህም የተነሣ ስለ ብሬነርድ ሕይወት የጻፈው መጽሐፍ ከራሱ መጽሐፍ ይልቅ በብዛት እንዲታተም ምክንያት ሆኗል። የብሬነርድ ሕይወት ለቤተ ክርስትያን የነበረው ፋይዳ ትልቅ ነው። ከብሬነርድ ሕይወት የተነሣ፣ ከበረቱት ታዋቂ ሚስዮናውያን ባሻገር ስንት የማይታወቁ የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋዮች በእርሱ ምስክርነት መጽናናትንና ብርታትን እንዲሁም በአገልግሎት ለመቀጠል አቅም አግኝተዋል?

በታሪክ ባሕር ውስጥ የወደቀች አንዲት ትንሽ ጠጠር፣ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እና በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ ባሉ ሩቅ የባሕር ዳርቻዎች ላይ የጸጋ ማዕበል ማምጣት መቻሏ እጅግ የሚያስገርም ነው። ሮበርት ግሎቨር በዚህ ሐሳብ በመገረም እንዲህ ሲል ጽፏል፦

ለሄንሪ ማርቲን የሚስዮናዊ አገልግሎት ምክንያት እና ለዊልያም ኬሪ አገልግሎት ትልቅ ተጽእኖ ያሳደረው የብሬነርድ ቅዱስ ሕይወት ነው። ኬሪ ደግሞ በአዶኒራም ጀድሰን መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ትልቅ ተጽእኖ አለው። እናም ይህ በአገልግሎት ላይ ተጽእኖ የማሳደር ሐረግ ወደ ኋላ ይመዘዛል፦ ሃስ፣ ዊክሊፍ፣ ፍራንኬ፣ ዚንዘንደርፍ፣ ዌስሊ እና ዋይትፊልድ፣ ብሬነርድ፣ ኤድዋርድስ፣ ኬሪ፣ ጁድሰን፣ ደግሞም በመንፈሳዊ ጸጋና ኀይል ወደሚቀጥለውና ዓለም አቀፋዊ ወደ ሆነው እውነተኛው ሐዋርያዊ አገልግሎት እንደርሳለን (The Progress of World-Wide Missions, 56)።

ነገር ግን የብሬነርድ አገልግሎት ዘላቂ እና ጉልህ ውጤት ከእያንዳንዱ የመጋቢ አገልግሎት ውጤት ጋር ተመሳሳይ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕንዳውያን በብሬነርድ አገልግሎት ምክንያት የዘላለም ሕይወትን አግኝተዋል።

ለቅሶና ጥርስ ማፏጨት ከበዛበት የጨለማ መንግሥት ወደ እግዚአብሔር ልጅ መንግሥት የተሸጋገረችውን የአንዲትን ነፍስ ዋጋ ማን ሊተምን ይችላል? 29 ዓመት ወይም 99 ዓመት ብንኖር አንዲትን ነፍስ ከዘላለም የገሃነም ስቃይ፣ ዘላለማዊ ደስታ ወደሚገኝበት የእግዚአብሔር ክብር ማብቃት፣ በሕይወታችን ከምናሳልፈው ትግልና መከራ ይልቅ የተሻለ ዋጋ አለው?

ወደ ፊት እና ወደ ላይ

በሕይወቴ እና በአገልግሎቴ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ላሳደረው የዴቪድ ብሬነርድ አገልግሎት እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። በጸሎት መትጋትን፣ የጾምን አስፈላጊነት፣ የእግዚአብሔር ቃል ጣፋጭነት፣ በችግር ውስጥ የማያቋርጥ ጽናትን፣ በእግዚአብሔር ክብር ላይ የማያቋርጥ ትኩረትን፣ በጸጋ ላይ ፍፁም መደገፍን፣ በክርስቶስ ጽድቅ የመጨረሻ ዕረፍትን፣ የጠፉ ኀጢአተኞችን መፈለግን፣ እየተሰቃዩ በቅድስና መኖርን፣ ዘላለማዊ በሆነው ላይ አእምሮን ማጽናት ደግሞም በ29 ዓመቱ የገደለውን በሽታ ሳይረግም ሕይወቱን መጨረሱ፣ ከእርሱ ሕይወት ብዙ እንድማር አድርጎኛል። ከዚህም የተነሣ በድክመቱና በኀጢአቱ ውስጥ ሆኖ እንኳ ዴቪድ ብሬነርድን እወደዋለሁ።

ኦ እግዚአብሔር ሆይ! በነገር ሁሉ ልክ እንደ ብሬነርድ ለሁሉም ሕዝቦች ደስታ እግዚአብሔር በነገሮች ሁሉ ላይ ያለውን ታላቅነት እንሰብክ ዘንድ የሚያበረታ ጸጋ ስጠን። በአላፊ ነገሮች ለማባከን ሕይወት በጣም ውድ ናት። ጌታ ሆይ፣ እንደ ዴቪድ ብሬነርድ የሕይወትን አላፊነት በመረዳት፣ “በሰማያዊ ጉዞዬ የተሰጠኝን ጊዜን ሳባክን እንዳልገኝ!” (186) ብለን በጸሎትና በማያቋርጥ ትጋት መኖር እንድንችል አቅሙን ስጠን።

ጆን ፓይፐር