ፒየር ሪቸር እና ጉዪሉም ቻርቲየር የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጠው የአሜሪካን ምድር የረገጡ የመጀመሪያዎቹ የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን ሆኑ። እ.ኤ.አ በ1557 ዓ.ም ብራዚል ደረሱ። ካልቪን በፈረንሣይ ውስጥ ያለውን ቡድን በመባረክ ወደ “አዲሱ ዓለም” እንዲሄዱ ካዘዛቸው ጊዜ አንሥቶ፣ የወንጌል ተልእኮ (Missions) እና ካልቪናዊነት ተጣምረዋል።
ነገር ግን ባለፉት ምዕተ ዓመታት ሰፊ የሆነውን የካልቪናዊያን የወንጌል ሰባኪነት ታሪክ ዝም ሊያሰኘው ያልቻለውን ክስ በተወሰነ መልኩ እንደሰማችሁት እርግጠኛ ነኝ። ይህም ሐሳብ፣ “እግዚአብሔርን በግለሰብ ነፍስ መዳን ላይ ሉዓላዊ ባደረጋችሁት መጠን፣ ወንጌልን ወደ ዓለም ማዕዘናት ሁሉ የማድረስ ጥሪው ብዙም አላስፈላጊ ይሆናል” የሚል ነው። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ከሆነ፣ ወንጌልን ለእኅታችን ወይም የሥራ ባልደረባችን የማካፈል ግዴታው ብዙም አይታየንም ይላሉ። ወደ እምነት በሚመጣው ሰው ላይ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ከሆነ፣ እኛ ወኪሎች በዓለም ላይ ባለው የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ላይ እንደ ቲያትር ተመልካቾች ከትወናው ውጪ በመሆን ወደ ጎን እንገፋለን የሚል ተቃውሞ ይነሣል። የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የወንጌል ሥርጭትን አንገብጋቢነት አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ሥጋትም አለ።
እውነት ግን ሁልጊዜ ከሐሜት የበለጠ ውብ ነች። የወንጌል ተልእኮን እና የወንጌል ሥርጭት አስፈላጊነትን ዕውቅና እንደምንሰጥ ሁሉ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነትም ደስ ይለናል። በእውነቱ ከሆነ፣ የወንጌል ተልእኮን እና የወንጌል ሥርጭትን የምናከብረው በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ስለምንደሰት ነው። እርስ በእርሳቸው እየተገፋፉ ያሉ ሁለት ማግኔቶችን አንድ ላይ ለመያዝ እየሞከርን ሳይሆን ቀድሞውንም የሚሳሳቡ እና የተጣመሩ ሁለት ትላልቅ እውነቶችን በኢየሱስ ደስታ አንድ ላይ እየያዝን ነው።
እጅግ የላቀ ደስታ
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በአባቱ ሉዓላዊ ቸርነት እጅግ በላቀ ደስታ ተሞልቶ ነበር። ይህም የከበረውን ወንጌል ከትምክህተኛ ሃይማኖተኞች ሰውሮ በኀጢአተኞች ሕይወት ላይ ግን እምነትን በመዝራቱ ነው።
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ በፊትህ በጎ ፈቃድህ ሆኖ ተገኝቷልና። “ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም” (ማቴዎስ 11፥25–27)።
የኢየሱስ ተልእኮ ለኀጢአተኞች የራሱን ክብር መግለጥ ነው፤ ይህ ማለት በሌላ መንገድ አብን ማወቅ ነው። ይህ ደግሞ ሁሌም መለኮታዊ መገለጥ ነው። ኢየሱስ ሉዓላዊ የሆነውን የቤዝዎት ዕቅድ በተግባር ተገልጦ ሲመለከት፣ ልቡ አባቱን በማመስገን ተሞላ።
በማንኛውም ኀጢአተኛ ግለሰብ መዳን ላይ የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የሁላችንን ልብ እግዚአብሔር ተኮር ወደ ሆነ ደስታ የሚያነሣሣ የከበረ እውነት ነው። ታዲያ፣ በሉዓላዊ አምላካችን ላይ ባለን በዚህ ደስታ አነሣሽነት ምን እናድርግ?
እጅግ የከበረ ስጦታ
በዚያው ክፍል፣ የክርስቶስ ትኩረት ከእግዚአብሔር ደስታ በዙሪያው ላሉ ሰዎች ይህንን የከበረ ጥሪ ወደ ማቅረብ ሲዞር እንመለከታለን።
“እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና” (ማቴዎስ 11፥28–30)።
ኢየሱስ ወዲያው ከኀጢአት እስራት ነፃ ስለ መውጣት መልካሙን ዜና ወይም ወንጌልን ሰበከ።
በሌላ አነጋገር፣ በኀጢአተኞች መዳን ውስጥ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት የማየት ትክክለኛው ምላሽ ለሁሉም ኀጢአተኞች የወንጌል በር መክፈት ነው። በአምላክ ሉዓላዊነት ውስጥ ያለው የኢየሱስ ደስታ መገለጥ እና “መተንፈስ” አለበት። ፒውሪታኑ ቶማስ ቦስተን እንዲህ ይላል፦ “በመካከለኛው ኢየሱስ ልብ ውስጥ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ሙላት፣ በልቡ ውስጥ ባለው ነጻ መተንፈሻ አማካይነት ወደ ችግረኛ ኀጢአተኞች ነፍስ መፍሰስ ይፈልጋል።” (Works, 9:171)
ወይም በጆናታን ኤድዋርድስ አባባል፡- “የክርስቶስ በአባቱ ሉዓላዊነት ላይ ያለው ቅዱስ የነፍስ ደስታ እና እንደ አማላጅነቱ የተሰጠው ሥልጣን፣ ጸጋን እና ፍቅርን እንዲለማመድ አድርጎታል፤ ይህም ጸጋን በተሞላ ግብዣው ውስጥ ይታያል።” (sermon 178)
የወንጌል ተልእኮ እና የኢየሱስ ደስታ
እግዚአብሔር፣ በሉዓላዊነቱ የክርስቶስን ክብር እንዳያዩ ትምክተኛ ዐይኖችን በመሸፈን ወደር የሌለውን የልጁን ክብር እና ውበት ለማየት የትሑት ኀጢአተኞችን ዐይኖች በመክፈት ይገለጣል። ይህ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ሥራ በታሪክ ውስጥ ሲገለጥ ሲያይ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ደስታ ይደሰታል። እናም ያ መለኮታዊ ደስታ ለአብ አምልኮ በመስጠት ይገለጻል። በደስታ ከተሞላው የክርስቶስ ልብ ለሁሉም ኀጢአተኞች የሚሆን አጠቃላይ ጥሪ ይፈስሳል፤ ወደ እርሱ በመምጣት ሌላ የትም ሊያገኙት የማይችሉትን እውነተኛ የነፍስ እርካታ ያገኛሉ።
ይህ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ለወንጌል አገልግሎታችን ተገቢ እና ትክክለኛ የሆነ የልብ መነሣሣት ነው። በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ ያለኝ የግል ደስታ እና እኔን በማዳኑ ያለኝ መገረም በውስጤ ሊታፈንና ሊዳፈን የማይችል ደስታን ሊፈጥር ይገባል፣ ደግሞም ይፈጥራል። ይህ ደስታ ኀጢአተኞች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡና ከኀጢአታቸው ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱ አጠቃላይ ጥሪ በማቅረብ ከልቤ በመፍሰስ ሊገለጥ ይገባል።
በሌላ አነጋገር፣ አጠቃላይ ጥሪ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ ምንም ዐይነት ሥጋት አይፈጥርም፤ እናም በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ ያለ ደስታ፣ በካልቪናዊነት ዕይታ ጥቅም እንደሌለው ጸሎት አይደለም። ሁለቱም ከተለያየ አቅጣጫ ወደ አንድ መንገድ ይፈስሳሉ፤ ወደ አንድ የሚመጡትም የእግዚአብሔር ኀይል ማንኛውንም ነገር እንደሚያከናውን ማመን በእውነት ዳግም ለተወለዱ ሰዎች ነፍስ ምግብ እንደሆነ ስንመለከት ነው። ይህም እውነት ልባቸውን በማስፋት ወደ ሉዓላዊው አዳኛችን እቅፍ ለሚመጣ ማንኛውም ሰው በሩን በሰፊው ለመክፈት ፈቃደኛ ያደርጋቸዋል።
የክርስቶስ ፍቅር፣ የተሐድሶ ሥነ-መለኮትንና ዓለምን በወንጌል የመድረስ ፍላጎትን የሚያጣምር አስደናቂ እውነታ ነው።
በቶኒ ሪንኪ