ሁለቱ ጥልቅ ፍላጎቶቻችን | ሚያዚያ 2

በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታም በኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት፣ ለተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን። (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥1)

እንደ ቤተ ክርስቲያን እኛ ሁላችን በእግዚአብሔር በአባታችን እና በጌታም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ነን። ይህ ምን ማለት ነው?

“አባት” የሚለው ቃል በዋነኝነት የሚያመለክተው እንክብካቤን፣ መሸከምን፣ ጥበቃን፣ መግቦትን እና ተግሣጽን ነው። ስለዚህም፣ በአብ ውስጥ መሆን ማለት በዋናነት በሰማያዊ አባታችን በእግዚአብሔር ጥበቃና እንክብካቤ ሥር መሆን ማለት ነው።

ሌላኛው መጠሪያ ደግሞ “ጌታ” የሚለው ነው፦ እኛ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ነን። “ጌታ” የሚለው ቃል በዋናነት ስልጣንን፣ አመራርንና ባለቤትነትን ያመለክታል። ስለዚህ፣ በጌታ ውስጥ መሆን ማለት ከታላቁ ጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃላፊነት፣ ሥልጣን፣ አገዛዝ እና ባለቤትነት ሥር መሆን ማለት ነው።

ስለዚህም ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ መሆናቸውን (ማለትም በአባት እንክብካቤ ሥር መሆናቸውን)፣ ደግሞም አገልጋዮች መሆናቸውን (ማለትም በጌታ ኃላፊነት ሥር መሆናቸውን) እንዲያስታውሱ በማድረግ ሰላምታን ያቀርብላቸዋል። እነዚህ ሁለቱ የእግዚአብሔር መገለጫዎች — አባትነቱ እና ጌትነቱ — ደግሞም የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብነት እና አገልጋይነት፣ ከሁለቱ ጥልቅ ፍላጎቶቻችን ጋር አብረው ይሄዳሉ። 

እያንዳንዳችን በአንድ በኩል አዳኝና እርዳታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሕይወትን ዓላማና ትርጉም እንፈልጋለን።

  1. የሚራራልን ደግሞም ከኃጢአትና ከመከራ የሚያድነን የሰማይ አባት ያስፈልገናል። በጣም ደካማ እና ለጥቃት የተጋለጥን ስለሆንን በእያንዳንዱ እርምጃችን የእርሱን እርዳታ እንሻለን።
  2. በሕይወታችን የሚመራን፣ ጥበብ የሆነውን የሚነግረን፣ ትልቅ እና ትርጉም ያለውን የሕይወትን ዓላማ እና የመኖርን ትርጉምን የሚሰጠን፣ እንዲሁም እግዚአብሔር ለፈጠረን ዓላማ እንድንኖር የሚያደርገን ሰማያዊ ጌታ ያስፈልገናል። ምንም እንኳን ውድ እና አስፈላጊ ቢሆንም፣ በአባታችን እንክብካቤ ውስጥ ደህንነታችን ተጠብቆ ብቻ መኖርን አንፈልግም። የምንኖርለት የከበረ ምክንያት እንፈልጋለን።

መሐሪ አባት ጠባቂያችን እንዲሆን እንፈልጋለን። ደግሞም ሁሉን ቻይ የሆነው ጌታ፣ አዛዣችንና መሪያችን እንዲሆን እንሻለን። ስለዚህ፣ ጳውሎስ በቁጥር 1 ላይ፦ እናንተ “በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታም በኢየሱስ ክርስቶስ የሆናችሁ” ቤተ ክርስቲያን ናችሁ ሲል፣ ሁለት ነገሮችን እያለን ነው፦ (1) እግዚአብሔር አባታችን ነው፣ ስለዚህ ዕረፍት እና እርዳታን ከእርሱ ዘንድ ልናገኝ እንችላለን እያለን ሲሆን፣ (2) ኢየሱስ ጌታችን ነው፣ ስለዚህ የመኖርን ድፍረት እና ትርጉም ከእርሱ ዘንድ እንቀበላለን እያለን ነው።