ኢየሱስን ለማሰብ ሁለት መንገዶች | ሚያዚያ 7

ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ዐስብ፤ የእኔም ወንጌል ይኸው ነው። (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥8)

ጳውሎስ ኢየሱስን ለማሰብ የሚረዱን ሁለት መንገዶችን ይጠቅሳል፦ አንደኛ ከሞት እንደተነሣ አስቡ፤ ሁለተኛ ደግሞ ከዳዊት ዘር እንደሆነ አስቡ ይለናል። ታዲያ ስለ ኢየሱስ እነዚህ ሁለት ነገሮች ለመጥቀስ ለምን ፈለገ?

ምክንያቱ ከሞት ከተነሣ፣ የእኛንም ሞት ጨምሮ በሞት ላይ ድል አድራጊ ነው ደግሞም ሕያው ነው ማለት ስለሆነ ነው! “ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል” (ሮሜ 8፥11)።

ይህም ማለት መከራ የቱንም ያህል ከባድ ቢሆን፣ በዚህች ምድር ላይ ሊያደርስባችሁ የሚችለው የከፋው ነገር እናንተን መግደል ነው። ኢየሱስ ደግሞ የሞትን መውጊያ ከጠላት ቀምቶታል። እርሱ ሕያው ነው። ስለዚህ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ። “ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ” (ማቴዎስ 10፥28)።  

ከዚያ በላይ ግን፣ የኢየሱስ ትንሣኤ እንዲያው ተራ ትንሣኤ ብቻ አልነበረም። የዳዊት ልጅ ትንሣኤ ነበር። “ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ።” ጳውሎስ ለምን እንዲህ አለ?

ምክንያቱም እያንዳንዱ አይሁዳዊ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። ኢየሱስ መሲሕ ነው እያለ ነው (ዮሐንስ 7፥42)። እናም ይህ ትንሣኤ የዘላለም ንጉሥ ትንሣኤ ነበር ማለት ነው። መልአኩ ለኢየሱስ እናት ለማርያም የተናገረውን አድምጡ፦

“እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” (ሉቃስ 1፥31-33)

ስለዚህ፣ የምታገለግሉትንና ስለ እርሱም መከራን የምትቀበሉለትን ኢየሱስን አስቡ። እርሱ ከሙታን ብቻ የተነሳ አይደለም። ነገር ግን ለመንግሥቱ መጨረሻ የሌለው፣ ለዘላለምም የሚነግሥ ሕያው ንጉሥ ነው። ምንም ነገር ቢያደርጉባችሁ፣ መፍራት የለባችሁም። እንደገና ሕያው ትሆናላችሁ። ከእርሱም ጋር ትነግሣላችሁ።