እነዚህ ፍትወትን ለመዋጋት የሚረዱ ስድስት የተፈተኑና የተረጋገጡ ስልቶች ናቸው። በአእምሮዬ ውስጥ ወንዶችንም ሴቶችንም ታሳቢ አድርጌያለሁ። ለወንዶች ጕዳዩ ግልጽ ነው። ወሲባዊ ምስሎች ላይ እንድናተኲር ከሚያደርገው የእይታ ፈተና ወረራ ጋራ የሚደረገው የውጊያ አስፈላጊነት አጣዳፊ ነው። ለሴቶች ይህ በደንብ ግልጽ አይደለም፤ ነገር ግን የፈተናውን ወሰን ወደ ምግብ ወይም ቅርጽ ወይም ወደ ግንኙነታዊ ምኞቶች (relational fantasies) የምናሰፋው ከሆነ፣ በጣም አስፈላጊ ይሆናል። “ፍትወት” ስል፣ ወደ ወሲባዊ ልቅነት የሚመራውን የሐሳብ፣ የምናብና የምኞት ዓለም ማለቴ ነው። ስለዚህ፣ ክፉ ምኞቶችን ለመዋጋት የሚረዱን ስልቶች ስብስብ ዕንኾ። አ.ሸ.ን.ፈ.ና.ል. በማለት፣ በአኅጽሮተ ቃል አስቀምጬዋለኹ።
አስወግድ፤ በተቻለህና ባስተዋልኸው መጠን ተገቢ ያልሆነን ምኞት የሚቀሰቅሱ የእይታ ስፍራዎችንና ሁኔታዎችን አስወግድ።
“የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ወይም ጣፋጭነ ገሮችን ወይም ሌላ ማንኛውንም ነገር የከበረ አድርጋችሁ ክምትቈጥሩት በላይ ክርስቶስን በሙሉ ልባችሁ እጅግ የከበረና ውድ አድርጋችሁ እንድትይዙት ተፈጥራችኋል።”
“በተቻለህና ባስተዋልኸው” ያልሁት፣ ለፈተና ተጋላጭ የምንሆንባቸው ሁኔታዎች በሆነ መጠን አይቀሬ ስለ ሆኑ ነው። “ተገቢ ያልሆነ ምኞት” ያልሁት ደግሞ፣ ለግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ለምግብና ለቤተ ሰብ ያሉ ሁሉም ፍላጎቶች መጥፎ ስላልሆኑ ነው። አግባብነት የሌላቸው፣ የማይጠቅሙና ወደ ባርነት የሚመሩ ሲሆኑ እናውቃለን። ድክመቶቻችንንና መንሥኤዎቻቸውን እናውቃለን። “ማስወገድ” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስልት ነው። “ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ፤…ጽድቅን…ተከታተል” (2ጢሞቴዎስ 2፥22)። “…ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በሐሳባችሁ አትመቻቹለት” (ሮሜ 13፥14)።
ሸሽተህ እንቢ በል፤ ለእያንዳንዱ የፍትወት ሐሳብ፣ በዐምስት ሰከንዶች ውስጥ “እንቢ” በል።
በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ተናገሩ። “በኢየሱስ ስም፤ እንቢ/አይኾንም!” በሉ፤ ከዐምስት ሰከንዶች በላይ ጊዜ የላችሁም። ከዚህ በላይ ያልተገደበ ጊዜ ከተሰጠው፣ ሠርጎ በመግባት የማይነቃነቅ ኀይል ሆኖ ይቀራል። ከቻላችሁ ጮክ ብላችሁ ተናገሩ። ጠንካራና ተዋጊ ሁኑ። ጆን ኦወን እንዳለው፣ “ኀጢአትን ግደሉት፤ አሊያ ይገድላችኋል።” በፍጥነትና በኀይል አጥቁት። “ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል” (ያዕቆብ 4፥7)።
ንቃናዘወር በል፤ የላቀ ርካታን ወደሚሰጠው ወደ ክርስቶስ አእምሮህን በኀይል ዘወር አድርግ።
“እንቢ” ማለቱ ብቻ አይበቃም። ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሄድ አለባችሁ። እሾህን በእሾህ እንዲሉ፣ የኀጢአትን ተስፋዎች በክርስቶስ ተስፋዎች አጥቋቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ፍትወቶችን፣ “የሚያታልሉ ምኞቶች” በማለት ይጠራቸዋል (ኤፌሶን 4፥22)። ይዋሻሉ፤ ሊፈጽሙት ከሚችሉት በላይ ተስፋን ይሰጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት” በማለት ይጠራቸዋል (1ጴጥሮስ 1፥14፣ ቀ.ኃ.ሥ.)። የሚሸነፉለት ሞኞች ብቻ ናቸው። “ለዕርድ እንደሚነዳ በሬ…ሳያንገራግር ተከተላት” (ምሳሌ 7፥22)። ማታለል የሚረታው በእውነት ነው። አለማወቅ የሚረታው በዕውቀት ነው። የከበረ እውነትና በውበት የተሞላ ዕውቀት መሆን አለበት። “ኢየሱስ ክርስቶስን ማየትና ማጣጣም” የተሠኘውን መጽሐፌን የጻፍሁት ለዚሁ ነው። በኢየሱስ በተሰጡን የላቁ ተስፋዎችና ደስታዎች አእምሮአችንን መጠቅጠቅ አለብን። “እንቢ!” ካልን በኋላ፣ ወዲያውኑ ወደ እነዚያ መመለስ አለብን።
ፈጥነህ ቃሉን ያዝ፤ ሌሎች ምስሎችን ገፍቶ እስከሚያወጣ ድረስ፣ የክርስቶስን ተስፋና ደስታ በአእምሮህ አጥብቀህ ያዝ።
ዐይኖቻችሁን በኢየሱስ ላይ ትከሉ (ዕብራውያን 12፥2ን ተመልከቱ)። ብዙዎች የሚወድቁት እዚህ ጋር ሲደርሱ ነው። ወዲያውኑ ተስፋ ይቈርጣሉ። “ገፍቼ ላወጣው ሞክሬአለሁ፤ ግን አልተሳካም” ይላሉ። እኔም እንዲህ ስል እጠይቃለሁ፣ “ለምን ያኽል ጊዜ ሞክረኻል?” አእምሮህን ምን ያህል ተጠቅመኸዋል?” አእምሮአችን ልክ እንደ ጡንቻ ነው። ኀይልን በመጠቀም ልታጠነክሩት ትችላላችሁ። መንግሥቱን በብርታት ተናጠቁ (ማቴዎስ 11፥12)። ጨካኞች ሁኑ። የክርስቶስን ተስፋ ከማየት ዐይኖቻችሁን አትንቀሉ። አጥብቃችሁ ያዙት። ያዙት! አትልቀቁት! ይዛችሁት ቈዩ! እስከ መቼ? የሚፈጀውን ጊዜ ያህል። ተዋጉ! ለክርስቶስ ስትሉ፣ እስክታሸንፉ ድረስ ተዋጉ! አንድ በኤሌክትሪክ የሚሠራ የመኪና ማቆሚያ በር ልጃችሁን ሊጨፈልቀው ቢቃረብ፣ ይህን በር በሙሉ ኀይላችሁ በመያዝ ለርዳታ ትጮኻላችሁ፤ ርዳታውም እስኪመጣ ድረስ አጥብቃችሁ ትይዙታላችሁ፤ ትይዙታላችሁ፤ ደግሞም ትይዙታላችሁ።
ናፍቆትናርካታ፤ የላቀውን ናፍቆትና ርካታን አጣጥም።
ፍትወትን መግደል ከፈለጋችሁ፣ እሾህን በእሾህ መዋጋት አለባችሁ። የኀጢአትን ተስፋዎች በክርስቶስ ተስፋዎች አጥቋቸው።
በክርስቶስ የመደሰትን ችሎታ አዳብሩ። ፍትወት በብዙዎች ላይ ገዢነት እንዲኖረው ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ፣ ክርስቶስ ብዙም ደስ የማያሰኛቸው መሆኑ ነው። በክርስቶስ ላይ ያለን ተድላ አነስተኛ ስለ ሆነ፣ ወደ መታለል እናዘነብላለን። “ይህ እኔ አይደለሁም” አትበሉ። ለኢየሱስ ያላችሁን ፍቅር ለማነቃቃት ምን ያህል ርምጆችን ሄዳችኋል? ለደስታ ታግላችኋል? የእናንተ ድርጊት ለውጥ እንደማያመጣ(fatalist) አታስቡ። ከወሲብና ከጣፋጭ ነገሮች በላይ፣ ኢየሱስን በሙሉ ልባችሁ እንድትወድዱት ተፈጥራችኋል። ለኢየሱስ ያላችሁ ስሜት (taste) አናሳ ከሆነ፣ ሌሎች ተፎካካሪ ደስታዎች ድል ያደርጋሉ። አሁን ላይ የሌላችሁን ርካታ እንዲሰጣችሁ እግዚአብሔርን ተማጸኑት፤ “በዘመናችን ሁሉ ደስ እንዲለን፣ ሐሤትም እንድናደርግ፣ ምሕረትህን በማለዳ አጥግበን” (መዝሙር 90፥14)። እርሱ በማንነቱ (በሆነበት መንገድ) እስኪሣልባችሁ ድረስ፣ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆነውን ሰው ተመልከቱት፤ ደጋግማችሁም ተመልከቱት።
ልፋ፣ተግተህ ሥራ፤ ከሥራ ፈትነትና ሌሎች ተጋላጭ ከሚያደርጉ ነገሮች በመራቅ ወደ ጠቃሚ ተግባራት ዙር።
+ ፍትወት የሚያድግበት ስፍራ ትርፍ ጊዜ ነው። መልካም ሥራ አግኙና በሙሉ ኀይላችሁ ሥሩት። “ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ” (ሮሜ 12፥11)። “…ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ” (1ቆሮንቶስ 15፥58)። ለሥራ የምትተጉ ሁኑ። ተነሥታችሁ የሆነ ነገር ሥሩ። ክፍላችሁን ጥረጉ። ደብዳቤ ጻፉ። ቧንቧ ጠግኑ። እነዚህንም ለኢየሱስ ስትሉ አድርጉ። ክርስቶስ የሞተው፣ “መልካም የሆነውን ለማድረግ እንድትተጉ” ነው (ቲቶ 2፥14)።