ከመጽሐፍ ቅዱስ የፍትሕ መርሖች ውስጥ አንዱ፣ የሥራችንን መጥፎነት ይበልጥ ባወቅን ቁጥር ጥፋተኝነታችን የከፋ እንደሚሆንና የምንቀበለውም ቅጣት የባሰ መሆኑ ነው (ሉቃስ 12፥47-48)። የዚህ ጽሑፍ ፍሬ ሐሳብ፣ ውርጃን በተመለከተ የምናደርገውን የምናውቅ መሆኑን መግለጥ ነው፤ ይኸውም ልጆችን እየገደልን ነው። ውርጃን የሚደግፉም ሆነ የሚቃወሙ ሰዎች ይህንን በሚገባ ያውቃሉ።
ነገር ግን ያንን ከማሳየቴ በፊት፣ የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዛሬ 45 ዓመት በፊት ያደረገውን ነገር ላብራራ። በቅጽል ስሟ ሮ በተባለች ሴት እና ዌድ በተባለ ዳኛ መካከል በተደረገ የፍርድ ክርክር፣ የሴቶችን ውርጃ የመፈጸም መብት በሕገ መንግሥቱ እንዲጠበቅ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ደነገገ። ይህም የተደረገው በሁለት መንገድ ነበር።
የመጀመሪያው እርምጃ፣ “የእናትየዋን ሕይወት ወይም ጤንነት ለማዳን እስከሆነ ድረስ” በዘጠኝ ወር ውስጥ ውርጃ ማድረግ ብትፈልግ ሕግ ፈጽሞ ሊከለክላት አይችልም የሚል ነበር። ሁለተኛው እርምጃ፣ ጤና ለሚለው ማብራሪያ መስጠት ሲሆን ይህም፣ “አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ቤተ ሰባዊ እና ዕድሜን የተመለከቱ ለታካሚው ደኅንነት የሚጠቅሙ ሁሉም ነገሮችን” እንደሚያካትት ይገልጻል።
ይህም ማለት ላለፉት 40 ዓመታት ማንኛውም የመጨናነቅ ስሜት ልጁን ለማስወገድ በቂ የሕግ መሠረት ሆኖ አገልግሏል ማለት ነው። ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን ገድለናል። እንደ አገር ደግሞ በደላችንን የከፋ የሚያደርገው የምናደርገውን እያወቅን ስለምናደርገው ነው። ቀጥሎ የተዘረዘሩት ማስረጃዎች ልጆችን እየገደልን እንደሆነ እንደምናውቅ የቀረቡ ናቸው።
- ውርጃን በሚፈጽሙ ሰዎች ምስክርነት መሠረት ልጆችን እየገደሉ እንደሆነ ያምናሉ
ከሁለት ክፉ ነገሮች መካከል ክፋቱ የሚቀንሰውን ምረጡ በሚለው አባባል መሠረት፣ ብዙዎች ክፋቱ የሚቀንሰው ይሄኛው መንገድ ነው ይላሉ። በአንድ ወቅት ውርጃን የሚደግፍን አንድ ሰው፣ ፅንሶች እንዴት የሰው ልጆች እንደሆኑ ዐሥር ምክንያቶች ልሰጠው ተዘጋጅቼ ምሳ ልጋብዘው ወጣን። አስቆመኝና፣ “ልጆች እየገደልን እንደሆነ አውቃለሁ” አለኝ። እጅግ በጣም ደነገጥሁ። ቀጠለና፣ “ለሴቶች ጉዳዩ የፍትሕ ነው። ከሁለቱ ክፉ ነገሮች የከፋው የሚሆነው ሴቶችን የሥነ ተዋልዶ ነፃነት መንፈግ ነው” አለ።
ይህም ማለት ከእንግዲህ ወዲህ ሴቶች ባልተፈለገ እርግዝና የሚከሰተውን መዘዝ በመሸከም ከወንዶች በላይ ሊደክሙ አይገባም ማለት ነው። ፕሬዝዳንት ኦባማ ስለ ሴቶች መብት በተደጋጋሚ በአደባባይ እንደ ተናገሩት፣ ያልተፈለጉ ልጆችን ያለመሸከም እኩል ነፃነት የውርጃ መሠረት መሆኑን ነው። ትርጉሙ ምን እንደሆነ እናውቃለን። ልጆችን እየገደልን ነው።
- በአሜሪካ ግዛቶች ዘንድ ፅንስ መግደል እንደ ነፍስ ማጥፋት ወንጀል የሚቆጠር ነው
ሚኒሶታን ጨምሮ 38 የክልል ከተሞች ያልተወለዱ ልጆችን መግደል እንደ ነፍስ ማጥፋት ወንጀል ስለሚቆጥሩት የምናደርገውን እናውቃለን። እነዚህ ክልሎች “የፅንስ ነፍስ የማጥፋት የወንጀል ሕግ” አሏቸው።
“ፅንስን በፈለጉት ጊዜ እንደ ልጅ እና ታካሚ ይወሰዳሉ። ካልፈለጓቸው ደግሞ ልጆች አይደሉም።”
እናትዬው ልጁን የምትፈልገው ከሆነ ፅንሱን መግደል ሕገ ወጥ ይሆናል። ነገር ግን እናትዬው ልጁን የማትፈልገው ከሆነ፣ ፅንሱን መግደል የሕግ መሠረት አለው። በመጀመሪያው ሁኔታ መሠረት ሕጉ፣ ፅንሱን የሚቆጥረው መብት እንዳለው ሰው ነው ። በሁለተኛው ደግሞ ሕጉ፣ ፅንሱን እንደ ሰው አይቆጥረውም፤ መብትም እንዳለው አይቆጥርም።
ስለዚህ ሰውነት የሚወሰነው ጉልበት ባላቸው ግለሰቦች መሻት መሠረት ነው። ጉልበት መብትን ይቀርጻል። የሴሜቲክ ዘርን በሚጸየፈው የናዚ ጦር ዘመን፣ እንዲሁም ዘር ተኮር በነበረው የባርያ ንግድ ዘመን በተጨማሪም በሶቪየት ዩንየን የሠራተኞች እንግልት ወቅት ይህንን የመሰለ ለሰውነት አዲስ ፍቺ የመስጠት አሠራር ተቃውመን ነበር። የፅንስን ሰው መሆን እና አለመሆን በኀያላን መሻት ላይ ተመርኩዘን አዲስ ፍቺ ስንሰጠው የምናደርገውን እያወቅን ነው።
- የፅንስ ቀዶ ጥገና ፅንስን የሚቆጥረው እንደ ልጆች እና ታካሚዎች ነው
ዶክተር ስቲቭ ካልቪን የተባለ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ቀዶ ጥገናዎችን የሚያደርግ ሐኪም ሲሆን ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አሪዞና ዴይሊ ስታር ለሚባል ጋዜጣ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ይላል፦ “እዚህ ጋር ሙሉ ጤነኛ የሆነ የ22 ሳምንት ፅንስን እያስወረዱ፣ እዛው ሆስፒታል ውስጥ ደግሞ ዘመዱ የሆነ ፅንስ ላይ ቀዶ ጥገና ስንሠራ ልናመልጠው የማንችለው የአእምሮ ሕመም አይቀርልንም።” ፅንስን በሚፈልጓቸው ጊዜ እንደ ልጅ እና ታካሚ ይወሰዳሉ። ካልፈለጓቸው ደግሞ ልጆች አይደሉም።” የምናደርገውን እናውቃለን።
- ትንሽ መሆን፣ ሰው ከመሆን አያጎድልም
ሜትር ከሰባ ለሚረዝም አንድ ወጣት፣ በእናቷ እቅፍ ካለች 60 ሳንቲ ሜትር ከምትሆን እኅቱ ይልቅ ቁመቱ ለመኖር የበለጠ መብት አይሰጠውም። እንደምናውቀው ቁመት ለግብረ ገብ ምንም ፋይዳ የለውም። 1 ሳ.ሜ ይሁን 60 ሳ.ሜ. አሊያም ሜትር ከሰባ ምንም ልዩነት የለውም። ማንን መጠበቅ እንዳለብን ለመወሰን ቁመት ግብረ ገባዊ ፋይዳ የለውም። ትንንሾችን ስንገድል የምናደርገውን እናውቃለን።
- ያልበለጸገ የማገናዘብ አቅም፣ ሰው ከመሆን አያጎድልም
የእናቱን ጡት የሚጠባ የአንድ ወር አራስ ልጅ የማገናዘብ አቅም የለውም። ይሁን እንጂ አራስ ልጆችን መግደል ተቀባይነት ይኖረዋል ብሎ ለመሟገት የሚደፍር አንድም ሰው አይኖርም። ብዙዎች ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ይህ አራስ ልጅ ከማሕፀንም ውጪ ሆነ በማሕፀን ውስጥ ማገናዘብ ገና ባይችልም እንኳ ሰው ነው። የምናደርገውን እናውቃለን።
- ማሕፀን ውስጥ መሆን ሰው ከመሆን አያጎድልም
ቦታ ወይም አካባቢ በሕይወት የመኖርን መብት አይወስንም። ስኮት ክሉስንዶርፍ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፦ “በማሕፀን ውስጥ የተደረገ ቀላል የ18 ሳ.ሜ. ጉዞ፣ እንዴት ብሎ ነው የፅንሱን መሠረታዊ ተፈጥሮ ሰው ካለመሆን በድንገት ሰው ወደ መሆን ሊቀይር የሚችለው?” የምናደርገውን እናውቃለን።
- እናት ላይ ጥገኛ መሆን ሰው ከመሆን አያጎድልም
ሰው ሠራሽ መተንፈሻ እና ዲያሊስስ የሚጠቀሙትን ሁሉ ሰዎች እንደሆኑ ነው የምንቆጥራቸው። ፅንሶችም ምግብ እና ኦክስጅን ለማግኘት በእናታቸው ላይ ጥገኛ መሆናቸው ሰው ከመሆን አያጎድላቸውም። ይልቁንም አኗኗራችን ከዚህ ተቃራኒ ነው። አንድ ትንሽ ነገር እኛ ላይ የበለጠ ጥገኛ ሲሆን፣ እርሱን ለመንከባከብ ያነሰ ሳይሆን የበለጠ ኀላፊነት ይሰማናል። የምናደርገውን እናውቃለን።
ከቁጥር 4 እስከ 7 ያሉት ነጥቦች የሰውን ሕይወት ፍቺ ለመስጠት ምንም ዓይነት ግብረ ገባዊ ፋይዳ የላቸውም።
- የሰው ልጆች የዘረመል አወቃቀር ልዩ ነው
የሰው ልጆች የዘረመል አወቃቀር ከተፀነሱበት ጊዜ አንሥቶ ከሌሎች ፍጥረታት የተለየ ነው። የሰው ዘረመል ከጅምሩ ሙሉ እና የተለየ ነው። በአንድ ወቅት ይህ አይታወቅም ነበር። አሁን ግን እናውቃለን።
- ፅንስ ስምንት ሳምንት ሲሞላው ሁሉም የሰውነት ክፍል ይኖረዋል
ፅንስ ስምንት ሳምንት ሲሞላው ሁሉም የሰውነት ክፍል ይኖረዋል። አንጎሉ ይሠራል፤ ልቡ ይመታል፤ ጉበቱ የደም ሕዋሳትን ይፈጥራል፤ ኩላሊቱ ፈሳሾችን ያጣራል፤ ጣቶቹ አሻራ አላቸው። ይሁን እንጂ ሁሉም ውርጃዎች ማለት በሚቻል ደረጃ የሚፈጸሙት ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው። የምናደርገውን እናውቃለን።
- ፎቷቸውን ተመልክተናል
የአልትራሳውንድ ድንቅ ቴክኖሎጂ ወደ ማሕፀን ውስጥ ተመልክቶ ፅንሱ ምን እንደሚመስል ድንቅ ምስል ይሰጣል። ለምሳሌ 8ኛ ሳምንት ላይ አውራ ጣቱን ሲጠባ፣ ከሚያም ነገር ሲሸሽ፣ እንዲሁም ለድምጽ ምላሽ ሲሰጥ ያሳያል። የዚህን በዕድገት ላይ ያለ ገና ያልተወለደ ልጅ የ4 ደቂቃ አልትራሳውንድ ምስል ይህንን በመጫን ተመልከቱ። ልጆች እንደሆኑ እናውቃለን።
- ሁለት ልክ የሆኑ ነገሮች ሲጋጩ፣ የሚልቀው እሴት ሊጠበቅ ይገባል
“በሕይወት መቆየት እርጉዝ ካለመሆን ይልቅ የከበረ እና ይበልጥ መሠረታዊ ነው።”
በምናውቀው የፍትሕ መርሕ መሠረት ሁለት ትክክል የሆኑ ነገሮች ሲጋጩ፣ እሴቱ የሚልቀውን መጠበቅ ይገባል። በሰዓት 160 ኪ.ሜ. መንዳትን የምንከለክለው፣ የሕይወት ዋጋ ቀድሞ ከመድረስ ወይም በፍጥነት በመንዳት ከሚገኘው ደስታ ይልቅ የከበረ ስለሆነ ነው። ያልተወለደው ልጅ ያለመገደል መብት እና የእናትየዋ ያለመውለድ መብት በተቃርኖ ቆመው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እኩል የሆኑ መብቶች አይደሉም። በሕይወት መቆየት፣ እርጉዝ ካለመሆን ይልቅ የከበረ እና ይበልጥ መሠረታዊ ነው። ልጆችን ስንገድል የምናደርገውን እያወቅን ነው።
ከፊታችን ላለው መንገድ ሦስት ዓላማዎች
መጽሐፍ ቅዱስን ለምናምን ክርስቲያኖች በውርጃ ጊዜ ምን እንደሚፈጸም እና ለምን ደግሞ ልክ እንዳልሆነ ቢያንስ 10 ተጨማሪ ምክንያቶችን መደርደር እንችላለን። ይሁን እንጂ እዚህ ጋር የምናቀርበው ሦስት ብቻ ይሆናል።
- አላውቅም የሚል ምክንያት በመስጠት ራሳችንን ልናድን እንደማንችል ግልጽ የማድረግ ዓላማ አለን። ሁላችንም እናውቃለን። ምሳሌ 24፥11-12 ውርጃን በተመለከተ ያለው ፋይዳ የሚያስደንቅ ነው።
“ወደ ሞት የሚነዱትን ታደጋቸው፤ እየተጐተቱ ለዕርድ የሚሄዱትን አድናቸው። አንተም፣ ‘ስለዚህ ነገር ምንም አላውቅም’ ብትል፣ ልብን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ሕይወትህን የሚጠብቃት እርሱ አያውቅምን? ለእያንዳንዱስ እንደ ሥራው መጠን አይከፍለውምን?”
- ይህንን አሰቃቂ ክፋት ለመቃወም ያለንን እምነት ልናጠናክር እናልማለን።
- በምድራችን ላይ ወንጌል ተኮር የሆነና ነፍስን የሚያድስ ስብከትና ጸሎትን ልናጠናክር እናስባለን። ምክንያቱም አለማወቅ ሳይሆን ኀጢአታዊ ልብን የማደንደን ዝንባሌ የዚህ ደም መፋሰስ መሠረት ስለሆነ ነው።
በጆን ፓይፐር