በሕይወቴ በጣም አስደሳች ከሆኑት ጊዜያት መኻል አንዱ፣ ወደ ክርስቶስ የመጣሁበት ጊዜ ነበር። ለወንጌል ስብከት በቅናት ተሞልቼ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ለጓደኞቼ መለወጤን ስነግራቸው፣ ዕብድ እንደ ሆንኩ ዐሰቡ፤ ይህ አስደንግጦኝም አናድዶኝም ነበር። ወንጌሉን ባካፍላቸውም ሳያሳምናቸው ቀረ፤ በሚያሳዝን ሁኔታ አስቂኝ ሆኖ አገኙት። በመጨረሻም፣ እንዲህ በማለት ጠየቁኝ፣ “ስለ ኢየሱስ የተማርከውን ነገር አንድ ትምህርት ጀምረህ ለምን አታስተምረንም?” የተናገሩት በቁም ነገር ነበር። ፈነደቅሁኝ። ለመገናኘት ቀጠሮ ያዝን፤ ሆኖም ፈጽሞ አልመጡም።
ለወንጌል ስብከት ጥልቅ ፍላጎት ቢኖረኝም፣ አልተሳካልኝም ነበር። ይህን መገንዘብ የቻልሁት በአገልግሎቴ ጅማሮ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ክርስቶስ የጠራቸውና በመንፈሱ አማካይነት በተለይ በስብከተ ወንጌል ውጤታማ እንዲሆኑ ስጦታ የሰጣቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉም ተረድቻለሁ። እስከ ዛሬ ድረስ፣ ማንም ሰው መለወጡ በከፊል በእኔ ተጽእኖ ምክንያት እንደ ሆነ ከተናገረ እደነቃለሁ። በአንድ በኩል፣ ታላቁ ተልእኮ በዋነኛነት፣ ለስብከተ ወንጌል የተሰጠ ተልእኮ ባለመሆኑ ደስ ይለኛል።
ኢየሱስ ተልእኮውን ከመስጠቱ በፊት የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው፣ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” (ማቴዎስ 28፥18)። እንዲህም በማለት ቀጠለ፣ “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 28፥19)። ኢየሱስ ይህን ተልእኮ ለቤተ ክርስቲያን ሲሰጥ፣ በሥልጣን እየተናገረ ነበር። በሁሉም ዘመናት ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን እንድትሰብክ ብቻ ሳይሆን፣ ደቀ መዛሙርት እንድታደርግም ትእዛዝን ሰጥቷል። ይህም፣ ደቀ መዝሙር ምንድን ነው? የሚል ትልቅ ጥያቄን ያስነሣል፡፡
የደቀ መዝሙር ቀላሉ ፍቺ የሚሆነው፣ አእምሮውን ወደ አንድ የተወሰነ ዕውቀትና ምግባር የሚመራ ሰው የሚለው ነው። ስለዚህ፣ ደቀ መዝሙር ማለት ተማሪ ወይም ተመሪ ነው። የግሪክ ፈላስፎች ሶቅራጥስ፣ ፕሌቶና አርስቶትል ደቀ መዛሙርት ነበሯቸው። ሶቅራጥስ፣ በግሪክ ታሪክ ውስጥ ታላቁ ዐሳቢ (thinker) አድርጎ የሚቈጥረው፣ የሆሜር ደቀ መዝሙር አድርጎ ራሱን ይገልጻል፡፡
ሆሜርን እንደ ፈላስፋ ሳይሆን እንደ ገጣሚ ወደ ማሰብ እናዘነብላለን። ነገር ግን ሶቅራጥስ የጥንቷ ግሪክ ታላቅ መምህር አድርጎ ይመለከተው ነበር። ሶቅራጥስ ፕሌቶ የሚባል የራሱ ተማሪ፣ ፊተኛ ደቀ መዝሙር፣ ነበረው። ፕሌቶም የራሱ ደቀ መዛሙርት ነበሩት፤ አርስቶትል ፊተኛው ተማሪው ነበር። አርስቶትልም ደግሞ ደቀ መዛሙርት ነበሩት፤ በጣም ታዋቂው ተማሪው፣ ታላቁ እስክንድር ነበር። የጥንቷ ዓለም በአራቱ ሰዎች ማለትም በሶቅራጥስ፣ በፕሌቶ፣ በአርስቶትልና በታላቁ እስክንድር እንዴት እንደ ተቀረጸች ማሰቡ የሚያስደንቅ ነው። እንዲያውም፣ እያንዳንዳቸው በራሳቸው መንገድ የሌላው ደቀ መዛሙርት የነበሩትን፣ የእነዚህን አራት ግለ ሰቦች ተጽእኖ ሳይረዱ፣ የምዕራባውያንን ሥልጣኔ ታሪክ መረዳት ክባድ ነው ማለት ይቻላል።
አርስቶትል “ዘዋሪ” ፈላስፋ በመባል ይታወቅ ነበር። ይህ ማለት፣ በአንድ የተወሰነ ቦታ ሳይሆን፣ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የሚያስተምር ዘላን መምህር ነበር። በአቴንስ ጐዳኖች ሲራመድ ተማሪዎቹ ይከተሉት ነበር። በአንድ በኩል፣ የአርስቶትል ደቀ መዛሙርት ከዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ጋር በተያያዘ ከእርሱ ትምህርት በመቅሰም ዐብረውት ኖረዋል።
ኢየሱስ ወደ ሕዝቦች ሁሉ እንድንሄድ ሲነግረን፣ የራሳችንን ሳይሆን፣ የእርሱን አጀንዳ ይዘን ወደ ዓለም ሁሉ መሄድ አለብን።
እነዚህ ፅንሰ ሐሳቦች የደቀ መዝሙርነት ተፈጥሮን ለማብራራት ይረዳሉ። ይሁን እንጂ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የደቀ መዝሙርነት መሠረታዊ ጠባይ ሙሉ በሙሉ ከመያዝ ይጐድላሉ። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ደቀ መዝሙርነት ከመምህሩ ጋራ መራመድንና ከእርሱ ቃላት መማርን በውስጡ ይይዛል፤ ነገር ግን ከዚያም የበለጠ ነው።
ኢየሱስ “ረቢ” የነበረ ከመሆኑም በላይ፣ በርግጥም በታሪክ ውስጥ ከሁሉ የላቀ “ዘዋሪ” አስተማሪና ደቀ መዝሙር አድራጊ ነው። በሚሄድበት ሁሉ፣ ተማሪዎቹ ይከተሉታል። ኢየሱስ በአደባባይ አገልግሎቱ ጅማሬ፣ የተወሰኑ ሰዎችን ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑ መርጧል። ኢየሱስ በተመላለሰበት ወቅት፣ የተናገራቸውን ትምህርቶች በቃል እንዲይዙ ይጠበቅባቸው ነበር። ከዚህም በላይ፣ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ትምህርት ቤት ለመግባት ማመልከቻ አላስገቡም። እርሱ ደቀ መዛሙርቱን መርጧል። ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ያሉት ሰዎች ወደሚኖሩበት ሄዶ፣ “ተከተሉኝ” የሚል ቀላል ትእዛዝ ሰጣቸው። ትእዛዙ ቃል በቃል ነበር፤ አሁን ያላቸውን ኀላፊነት እንዲተው ጠራቸው። ኢየሱስን ለመከተል ሥራቸውን፣ ቤተ ሰቦቻቸውንና ጓደኞቻቸውን መተው ነበረባቸው።
ይሁን እንጂ፣ ኢየሱስ ከዘዋሪ አስተማሪም በላይ ነበረ። ደቀ መዛሙርቱ፣ “ጌታ” ብለው ይጠሩት ነበር። ኢየሱስን እንደ ታላቅ አስተማሪ ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ጌታ አድርገው ስለ ተከተሉት የአኗኗር ዘይቤአቸው ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ጌትነቱ ከትምህርት ክፍል ዐልፎ ለሚሄደው ለክርስቶስ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ መገዛት፣ የደቀ መዝሙርነት መሠረታዊ ጠባይ ነው። የኢየሱስ ጌትነት መላ ሕይወትን ያጠቃልላል። የግሪክ ፈላስፎች ከመምህራናቸው የተማሩ ቢሆንም፣ በዚያ ትምህርት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ሞክረዋል። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲህ ዐይነቱ ሥልጣን የላቸውም። እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የገለጠውን ነገር ብቻ እንድንረዳና እንድናስተምር ተጠርተናል፤ ይህም የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍትን ያካትታል፤ ምክንያቱም የሚያመለክቱት ወደ ክርስቶስ ነው፤ እንዲሁም የአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍትን ያካትታል፤ እነዚህ ደግሞ ክርስቶስ በስሙ እንዲናገሩ የሾማቸው ሰዎች የተናገሯቸው ቃላት ናቸው።
ታላቁ ተልእኮ፣ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሥልጣኑን በመላው ዓለም እንዲያሰፉ ያቀረበው ጥሪ ነው። ብዙ ሰዎች እርሱን “ጌታ” ብለው እንዲጠሩት፣ ወንጌሉን ለሁሉም ማካፈል አለብን። ይህ ጥሪ የስብከተ ወንጌል ጥሪ ብቻ አይደለም። ለቤተ ክርስቲያናችን አባላትን ለማስገኘት የሚደረግ ብቻ ጥሪም አይደለም። ይልቁንስ፣ ክርስቶስ የሚጠራን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ ነው። ደቀ መዛሙርት የጌታቸውን አስተሳሰብና ምግባር ለመከተል በሙሉ ልባቸው ቊርጠኞች የሆኑ ሰዎች ናቸው። እንዲህ ዐይነቱ ደቀ መዝሙርነት የክርስቶስን ልብ የመማርና ፈቃዱን የመከተል፣ ራሳችንን ለጌትነቱ በፍጹም መታዘዝ የማስገዛት የሕይወት ዘመን ተመክሮ ነው።