ተጫዋቾቹን ሰለ ጨዋታ እያስተማረ፣ ነገር ግን በተግባር ስለማያሠለጥን አሠልጣኝ ምን ታስባላችሁ? የሒሳብ ትምህርትን የሚያስተምር፣ ነገር ግን ተማሪዎቹ ሲሳሳቱ ስለማያርም መምህርስ? ወይንም ስለ ጤንነት ብዙ እያወራ የራሱን ካንሰር ችላ የሚልስ ሐኪም?
እነዚህ ሁሉም መሥራት የሚገባቸውን ሥራ በከፊል እየሠሩ ነው ልትሉ ትችላላችሁ። ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ ማስተማርና ማሠልጠን ያስፈልጋቸዋል። ትምህርት ማስተማር፣ ማስረዳትና ስሕተትን ማረም ይጠይቃል። የሕክምና ሙያ ደግሞ ጤንነትን መጠበቅ፣ በሽታን መከላከልና ማከምን ያጠቃልላል።
ታዲያ፤ የተግሣጽ ሥርዐት የሌላት፣ ነገር ግን ደቀ መዝሙርነትን ስለምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ምን ታስባላችሁ? ይህ ትርጉም ይሰጣችኋል? ይህ ለብዙ አብያተ ክርስቲያናት ትርጉም እንደሚሰጥ ዐስባለሁ። ምክንያቱም፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ያስተምራሉ፤ ነገር ግን ጤናማ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ሥርዐት ያላቸው ጥቂቶች ነው። ልክ ዕጢን ችላ እንደሚል ሐኪም የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት በሌለበት ሰዎችን ደቀ መዝሙር ለማድረግ መሞከር ትርጉም አልባ ነው።
ቤተ ክርስቲያን ኀጢአትን የሚለማመዱ ሰዎችን በዲሲፕሊን ለመቅጣት ወደ ኋላ የምትልባቸው ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ዐስባለሁ። ሆኖም ግን፣ ይህን ለማድረግ አብዛኞቻችን የሚከብደንና የምናፈገፍግበት ምክንያት፣ ከእግዚአብሔር በላይ ብልህና መልካም ለመሆን እየጣርን ስለ ሆነ ነው ብዬ እሰጋለሁ። እግዚአብሔር “የሚወድደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል” (ዕብራውያን 12፥6)፡፡ ከእግዚአብሔር የበለጠ እናውቃለን?
እግዚአብሔር፣ ልጆቹን ለሕይወታቸው፣ ለዕድገታቸውና ለጤንነታቸው ሲል ይቀጣቸዋል፤ “እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል” (ዕብራውያን 12፥10)። አዎ ያሳዝናል! ነገር ግን መልካም ፍሬ አለው። “ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል” (ዕብራውያን 12፥11)። የጽድቅና የሰላም ፍሬ! ይህ እጅግ ውብ ነው።
የጽጌረዳ አበባን መግረዝ፣ ብዙ የጽጌሬዳ አበባዎች እንዲያድጉ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ቤተ ክርስቲያን እንድታድግ ይረዳታል። በሌላ አነጋገር፣ ይህ የተግሣጽ ሥርዐት የክርስቲያናዊ ደቀ መዝሙርነት ሌላው አካል ነው። “ደቀ መዝሙር”ና “ዲሲፕሊን” የሚሉትን ቃላት አስተውሉ። ሁለቱም ቃላት ከትምህርት አለም የተወሰዱ ሲሆን፣ እነርሱም ማስተማርና ማረምን ያካትታሉ። ይህንን ለማስረዳት የምንጠቀምባቸው ለዓመታት የቆዩ ቃላቶች አሉ። እነርሱም፦ “ፎርማቲቭ ዲሲፕሊን” (ገንቢ ዲሲፕሊን)ና “ኮሬክቲቭ ዲሲፕሊን” (የማቅናት ዲሲፕሊን) ናቸው።
የዚህ የመግቢያ ጽሑፍ ዐላማ፣ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት “ምን” እንደ ሆነ፣ “መቼ”፣ “እንዴት”ና “ለምን” እንደሚፈጸም ለአንባቢዎች ማስተዋወቅ ነው።
የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ምንድን ነው?
የማረምና የማቅናት ዐላማ ያለው የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ምንድን ነው? የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ማለት በጉባኤውና በአባላቱ ሕይወት ውስጥ፣ ኀጢአትን የማረም ሂደት ነው። ይህ ማለት፣ ኀጢአትን በግል በተግሣጽ ቃል ማረም ሊሆን ይችላል። ወይም በቀጥታ ከኅብረት አባልነት በማስወጣት ኀጢአትን ማረም ሊሆን ይችላል። የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት፣ በተለያየ መንገድ ሊፈጸም ይችላል። ነገር ግን ሁልጊዜ ዐላማው በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የእርሱን ሕግ መተላለፍ ሲኖር ኀጢአቱን ማረም ነው።
በቀል ሳይሆን የሚፈውስ፣ ትንቢታዊና ምሳሌያዊ ነው
ኀጢአትን ማረም፣ በቀል ወይም የእግዚአብሔርን ፍርድ መፈጸም ሳይሆን የሚፈውስ ትንቢታዊና ምሳሌያዊ ልምምድ ነው። የሚፈውስ ነው ስል፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲሁም ጉባኤው እግዚአብሔርን በመምሰል እንዲያድግ ይረዳል። አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል የሐሜት ንግግር ቢያወራ፣ ሌላኛው አባል ኀጢአቱን በማረም ሐሜት እንዲያቆምና የፍቅር ቃል እንዲያወጣ ሊነግረው ይገባል። እግዚአብሔር የሚናገረው ሰዎችን ለመጉዳት አይደለም። የእግዚአብሔርም ሕዝቦች እንዲሁ ሊሆኑ ይገባል።
የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ትንቢታዊ ነው ስል ደግሞ፣ የእግዚአብሔር እውነት ብርሃን በስሕተትና በኀጢአት ላይ ያበራል ማለቴ ነው። በማኅበር እንዲሁም በግለ ሰብ ሕይወት ያለብንን ነቀርሳ ነቅሶ በማውጣት እንዲቆረጥ ይረዳል። ኀጢአት የማስመሰል ጌታ ነው። ለምሳሌ፣ ሐሜት ለሰው ያለን እውነተኛ “መንፈሳዊ ጭንቀት” ይመስላል። ስለዚህ ሐሜተኛ ሰው፣ የሚናገረው ንግግር ምክንያታዊና መልካም እንደ ሆነ ያስባል። የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ግን፣ ይህን ኀጢአት ያጋልጣል። ሁሉም ይማርና ይጠቀም ዘንድ፣ ለኀጢአተኛውና በርሱ ዙሪያ ላሉ ሰዎች ኀጢአቱን ያጋልጣል።
የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ምሳሌያዊ ነው ስል ደግሞ፣ ሊመጣ ያለውን የላቀ ፍርድ የሚያስጠነቅቅ የአሁን ጊዜ ትንሸ ፍርድ ነው(1 ቆሮንቶስ 5፥5)። እንደዚህ ዐይነቱ ማስጠንቀቂያ ስጦታ ነው። አንድ የክፍል አስተማሪ የወደቁ ተማሪዎቹን ተስፋ እንዳይቆርጡ ፈርቶ አሳለፋቸው ብላችሁ ዐስቡ። ይህ ድርጊት ዓመቱ ሲያልቅ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል። ይህ መልካም ተግባር አይደለም። ልክ እንደዚሁ፣ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት በኀጢአት ወድቆ ለተገኘ ሰው፣ “ተጠንቀቅ በዚህ መንገድ ከቀጠልክ የባሰ ቅጣት ይጠብቅሃል። እባክህ ተመለስ” ብለን በፍቅር የምንናገርበት መንገድ ነው።
ሰዎች ተግሣጽን አለመውደዳቸው የሚያስገርም ነገር አይደለም። እጅግ ከባድ ነው። እግዚአብሔር ምንኛ መሓሪ ነው! በትናንሽ መንገዶች አሁን ላይ ስለሚመጣው ታላቅ ፍርድ ሕዝቡን ያስጠነቅቃል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊና ነገረ መለኮታዊ መሠረቶች
ከቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ጀርባ ትልቁ የቤዝዎት ታሪክ አለ። ይህም እግዚአብሔር መልካምና ሕይወት ወደ ተሞላው የፍጥረት አገዛዙ፣ የወደቁትን ሰዎች መመለስ ነው (ዘፍጥረት 1፥26-28፣ 3፥1-6)።
አዳምና ሔዋን እግዚአብሔርን እንዲመስሉ ተፈጥረዋል። የእስራኤል ሕዝብም እንደዚሁ! ነገር ግን አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ፣ በራሳቸው ሥልጣን ለመምራት በመፈለጋቸው ከገነት ተባርረዋል። እስራኤላውያንም፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ባለመጠበቃቸውና የእርሱን ባሕርይ ባለመግለጣቸው ወደ ምርኮ ሄደዋል።
ይህን በመስተዋት ምሳሌ መግለጽ እንችላለን። መስተዋት ከፊቱ ያለውን አካል ያሳያል። ልክ እንደዚሁ በእግዚአብሔር አምሳል ስለ ተፈጠርን፣ የምናደርጋቸው ድርጊቶች ስለ እግዚአብሔር የሚናገሩት ነገር አላቸው። ችግሩ ልክ እንደተሰበረ መስተዋት፣ የወደቀው ሰው የእግዚአብሔርን ምስል በትክክል አያንጸባርቅም። የወደቀው ሰው ስለሚዋሽ፣ ዓለም የእግዚአብሔርም ቃል አይታመንም ብላ ደምድማለች። እንዲህም ትላለች፦ ፍጡሩ ከዋሸ፣ ፈጣሪው ውሸታም መሆን አለበት።
ደስ የሚለው ዜና፣ አንዱ የአዳም ልጅ፣ አንዱ የእስራኤልም ልጅ የእግዚአብሔርን ሕግ በፍጹም ጠብቋል። ጳውሎስ እርሱን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “የማይታየው አምላክ አምሳል”(ቈላስይስ 1፥15)። አሁን፣ ከዚህ አንዱ ልጅ ጋራ የተባበሩት ይህንኑ “አምሳል” ተሸክመው እንዲኖሩ ተጠርተዋል። ይህን ደግሞ የምንማረው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ “ከክብር ወደ ክብር” (2 ቆሮንቶስ 3፥18፤ ሮሜ 8፥29፣ 1 ቆሮንቶስ 15፥49፣ ቈላስይስ 3፥9-10) ስንለወጥ ነው።
አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ እግዚአብሔርን በእውነትና በታማኝነት የሚመስሉ ሰዎችን ለማግኘት ሕዝቦች የሚሄዱባቸው ስፍራዎች ሊሆኑ ይገባል። ዓለም፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቅድስናን፣ ፍቅርንና አንድነትን ሲመለከት፣ እግዚአብሔርን በተሻለ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ያውቃሉ፤ እንዲሁም ያመሰግኑታል (ለምሳሌ ማቴዎስ 5፥14-16፤ ዮሐንስ 13፥34-35፤ 1 ጴጥሮስ 2፥12)። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ማለት፣ ከኅብረቱ አንድ ሰው፣ እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ፣ የእርሱን ቅድስና፣ ፍቅርና አንድነት መወከል ሲያቅተው ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠው ምላሽ ነው። ከመስተዋት ላይ ቆሻሻን እንደምናጸዳው፣ ትክክለኛ ያልሆኑ ምስሎችን ከክርስቶስ አካል ሕይወት ውስጥ ለማስተካከል የሚደረግ ሙከራ ነው።
የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች
ኢየሱስ በማቴዎስ 16፥16-19ና 18፥15-20 ላይ የተግሣጽን ሥልጣን ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰጥቷል። በምድር ላይ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን በመጀመሪያ በማቴዎስ 16፥18 ላይ የተጠቀሰ ሲሆን በማቴዎስ 18፥15-20 ላይ ደግሞ ኅብረቶች እንዲለማመዱት ሰጥቷል። ይህን ሐሳብ ከዚህ በኋላ በጥንቃቄ እንመለከታለን።
ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ሂደቶችን በተለያየ ቦታዎች ላይ አብራርቷል። ከእነዚህም ውስጥ 1 ቆሮንቶስ 5 ፤ 2 2 ቆሮንቶስ 2፥6፤ ገላትያ 6፥1 ፤ ኤፌሶን 5፥ 11 ፤ 1 ተሰሎንቄ 5፥14 ፤ 2 ተሰሎንቄ 3፥6-15፣ 1 ጢሞቴዎስ 5፥19-20፤ 2 ጢሞቴዎስ 3፥5ና ቲቶ 3፥9-11 ይገኙበታል።
ዮሐንስ በ2 ዮሐንስ 10 ላይ ስለ ተግሣጽ ሥርዐት ይናገራል። ይሁዳም በይሁዳ 22 እና 23 ላይ ይህን ታሳቢ አድርጎ የጻፈ ይመስላል። ተጨማሪ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ኢየሱስና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሓፊዎች በኅብረታቸው ውስጥ ኀጢአትን እንዲያርሙ ለአድማጮቻቸው ሲነግሯቸው፣ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐትን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃን መቼ ልትወስድ ይገባል?
ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃን መቼ ልትወስድ ይገባል? የዚህ ጥያቄ ዐጭሩ መልስ አንድ ሰው ኀጢአት ሲያደርግ ነው። ነገር ግን የዚህ መልስ፣ እየተነጋገርን ባለነው የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት መሠረት ይለያያል። ሥርዐቶቹ መደበኛ ወይም ኢ መደበኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ጄይ አዳምስ የግል ተግሣጽና እንደ ማኅበር የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ በማለት ይለያቸዋል።
ከባድ ሆነ ከባድ ያልሆነ ማንኛውም ኀጢአት፣ በእምነት ውስጥ ባሉ ሁለት ወንድሞች ወይም እኅቶች መካከል፣ በግል ለመተራረም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት ግን ወንድማችን የሚፈጽመውን እያንዳንዱን ኀጢአት መገሠጽ አለብን ማለት አይደለም። ነገር ግን እያንዳንዱ ኀጢአት ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን፣ በማስተዋልና በፍቅር እርስ በእርስ በግል በመተናናጽ ማደግ ይቻላል ለማለት ነው።
የትኛው ኀጢአት መደበኛ ወይም በማኅበር የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ያስፈልገዋል ወደሚለው ጥያቄ ስንሸጋገር፣ ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ መፈተሽ ያስፈልገናል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝርዝሮች
አንዳንድ የቆዩ የነገረ መለኮት ትምህርቶች፣ መደበኛ የቤተ ክርስቲያንን የተግሣጽ ሥርዐት መቼ ልንለማመደው እንደሚገባ በዝርዝር አስቀምጠዋል። ለምሳሌ የኮንግሪጌሽናሊስት (Congregationalist) አገልጋይ የሆነው ጆን አንጅል፣ የቤተክርስቲያን ተግሣጽ የሚያስፈልጋቸው ዐምስት ኀጢአቶችን አስቀምጧል። (1) ኢ-ሞራላዊና አጸያፊ ተግባራት (ለምሳሌ፣ 1 ቆሮንቶስ 5፥11-13) (2) የክርስትናን ትምህርት መካድ (ለምሳሌ፣ ገላትያ 1፥8 ፤ 2 ጢሞቴዎስ 2፥17-21፤ 1 ጢሞቴዎስ 6፥3-5፤ 2 ዮሐንስ 10) (3) መለያየትን ማስነሣት (ቲቶ 3፥ 10) (4) ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰብን አለመርዳት (ለምሳሌ 1 ጢሞቴዎስ 5፥8) (5) በእርቅ ያልተፈታ ጠላትነት (ለምሳሌ፣ ማቴዎስ 18፥7)።
እንደዚህ ዐይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝርዝሮች ጠቃሚ ናቸው። የተገለጹት እያንዳንዱ ኀጢአቶች ከባድና ውጫዊ መገለጫ ያላቸው መሆናቸውን አስተውሉ። በውስጥ ያሉ የልብ ኀጢአቶች አይደሉም። በዐይን የሚታዩ፣ በጆሮም የሚሰሙ ናቸው። በዚህ ውጫዊ መገለጫቸው፣ ዓለምንም ሆነ ሌሎች በጎችን ስለ ክርስትና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ።
ነገር ግን እነዚህ ዝርዝሮች፣ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ስላላስቀመጣቸው ብዙ ኀጢአቶች (ለምሳሌ፦ ጽንስን ማስወረድ) የሚናገሩት ነገር የለም። በተጨማሪም፣ ስለ ተግሣጽ ሥርዐት የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ስለ አንድ የተለየ ኀጢአት ብቻ ሊናገሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ 1 ቆሮንቶስ 5 ላይ ከአባት ሚስት ጋር ዝሙት የመፈጸም ኀጢአትን ያወራል። በርግጥ ጳውሎስ ይህ ኀጢአት ብቻ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ያስፈልገዋል አላለም። አብያተ ክርስቲያናት እንደዚህ ዐይነት ምሳሌዎችን መሠረት በማድረግ፣ እንዴት ለሌሎች ኀጢአቶች መጠቀም ይችላሉ?
ውጫዊ፣ ከባድና ንሰሓ አልባ ኀጢአት
በአንድ መንገድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን ለማጠቃለል፣ መደበኛ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት የሚያስፈልገው ውጫዊ፣ ከባድና ንሰሓ አልባ ለሆነ ኀጢአት ነው። ኀጢአት ውጫዊ መገለጫ አለው። በዐይናችን የምናየውና በጆሮአችን የምንሰማው ሊሆን ይገባል። አብያተ ክርስቲያናት፣ በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ትዕቢትና ስግብግብነት እንዳለ በተጠራጠሩበት ጊዜ ሁሉ፣ ያንን ሰው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማስወጣት የለባቸውም። ይህ ማለት ግን፣ የልብ ኀጢአቶች ከባድ አይደሉም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር እንጂ እኛ የሌላውን ሰው ልብ መመልከትና መመርመር አንችልም። እውነተኛ ችግሮች ደግሞ በመጨረሻም መገለጣቸው አይቀርም (1ሳሙኤል 16፥7፤ ማቴዎስ 7፥17 ፤ ማርቆስ 7፥21)።
ሁለተኛ፣ ኀጢአቱ ከባድ መሆን አለበት። ለምሳሌ፣ አንድ ወንድም የተፈጠረን ታሪክ አጋኖ ሲያወራ ብመለከት፣ በግል በጉዳዩ ላይ ላወራው እችላለሁ። ስሕተቱን ባያምን እንኳ ወደ ጉባኤው አላመጣውም። ለምን? አንደኛ፣ ነገሮችን አግንኖ መናገር እንደ ጣዖት አምልኮና ራስን በማጽደቅ ውስጥ ባሉ በማይታዩ ኀጢአቶች ላይ የተመሠረተ ነው። እነዚህን ኀጢአቶች፣ የግል ጊዜን በመስጠት ከእርሱ ጋር መወያየት የምችልባቸው ናቸው። ሁለተኛ ደግሞ እያንዳንዱን ኀጢአት ወደ ማኅበሩ ማምጣት ፍርሀት እንዲኖር ያደርጋል። በተጨማሪም ኅብረቱን ወደ ወግ አጥባቂነት (legalism) ያመራል። በሦስተኝነት ደረጃ ደግሞ፣ በኅብረት ሕይወት ውስጥ ሌሎችን በፍቅር “የኀጢአትን ብዛት የሚሸፍንበት” ስፍራ ሊሆን ይገባል(1 ጴጥሮስ 4፥8)። ሁሉንም ኀጢአት መከታተል የለብንም። እግዚአብሔርም በእኛ ላይ ይህን አላደረገም።
በመጨረሻም፣ ለኀጢአት ንሰሓ በማይገባበት ጊዜ መደበኛ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃ መውሰድ አግባብ ይሆናል። በከባድ ኀጢአት ውስጥ ያለ ሰው፣ በግሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሚገኙት የእግዚአብሔር ትእዛዛት ተወቅሶ፣ ኀጢአቱን ለመተው ፍቃደኛ ያልሆነ ሰው ነው። ይህ ሰው ከክርስቶስ ይልቅ ኀጢአቱ ውድ ሆኖበታል። ከዚህ በታች የምንመለከተው ደግሞ ከሦስቱ አንዱ ውስጥ ብቻ የማይመደብ ነው።
የመጀመሪያ መደበኛ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት በምናካሂድበት ጊዜ፣ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱም አጋጥመውኝ ነበር። የሚመረመረው ሰው የቅርብ ጓደኛና የሥራ አጋር ነበር። ሆኖም ግን፣ እኔና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ሰዎች፣ በዝሙት ኀጢአት ውስጥ እንደነበር አንድ ቀን ምሳ እየበላን እስከሚነግረኝ ድረስ አላስተዋልኩም ነበር። ወዲያውኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እርሱ ስላደረገው እንደዚህ ስላሉ ኀጢአቶች ምን እንደሚል ጠየቅኩት፤ እርሱም እንደሚያውቅ ነገረኝ። ሆኖም ግን ከእግዚአብሔር ጋራ ሰላም እንደ ሆነ ነገረኝ። ንሰሓ እንዲገባ ገፋፋሁት። ሌሎችም እንደዚሁ ሞግተውት ነበር። ነገር ግን ለሁላችንም የሚመልስልን መልስ፣ “እግዚአብሔር በዚህ ድርጊት ላይ ችግር የለበትም” የሚል ነበር። እንደዚህ ከመሰሉ፣ ወራትን ከፈጁ ውይይቶች በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ በይፋ ከኅብረት አስወጣችው። ኀጢአቱ እጅግ ከባድ፣ ንሰሓ አልባና ግልጽ የሆነ ውጫዊ መገለጫ ነበረው። ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉት እንዲሁም በውጪ ላሉት የተሳሳተ ግንዛቤን የሚሰጥ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን ሰው ለማረም፣ ለብዙ ወራት ሞክራለች። እንወደዋለን። ከኀጢአቱ ርቆ፣ ክርስቶስ ዓለም ከሚሰጠው ነገር ሁሉ በላይ ውድ እንደ ሆነ እንዲያውቅ እንፈልጋለን። ሆኖም ግን ምንም የመመለስ ልብ አልነበረውም። በሐሳቡ ጸንቶ ነበር። በኀጢአቱና በእግዚአብሔር ቃል መካከል ምርጫ ሲሰጠው፣ ኀጢአትን መረጠ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኒቱ መደበኛ የተግሣጽ ርምጃ ወሰደች።
ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃዎችን መውሰድና መለማመድ ያለባት እንዴት ነው?
ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃዎችን መውሰድና መለማመድ ያለባት እንዴት ነው? ኢየሱስ በማቴዎስ 18፥15-17 ላይ መሠረታዊውን ሐሳብ አቅርቧል። ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ ብሏል፦
“ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ። ባይሰማህ ግን ቃል ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ፊት ስለሚጸና፣ አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ አነጋግረው። እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ፣ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቍጠረው።”
እዚህ ጋር እንድታስተውሉት የምፈልገው፣ ጥፋቱ የሚጀምረው በሁለት ወንድማማቾች መኻል ነው። እርቅንም ለማምጣት ከሚያስፈልገው በላይ መኬድ የለበትም። ኢየሱስ ሂደቱን በዐራት ደረጃዎች አስቀምጦታል።
ዐራት መሠረታዊ ደረጃዎች
- በሁለቱ ሰዎች መኻል ያለው የኀጢአት ችግር በራሳቸው መፈታት ከተቻለ፣ ጉዳዩ ተዘግቷል።
- ጉዳዩ በሁለቱ ካልተፈታ ደግሞ፣ የተበደለው ወንድም ሁለት ወይም ሦስት ወንድሞችን ይዞ ይመጣል፤ “ቃል ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ፊት ስለሚጸና”(ማቴዎስ 18፥16)። ኢየሱስ ይህን ሐረግ ከዘዳግም 19 የወሰደው ሲሆን የክፍሉ ዐውድ ሰዎችን ከሐሰት ክሶች ስለ መጠበቅ የሚያወራ ነው። ዘዳግም ለየትኛውም ወንጀል የተጠረጠረን ሰው “በጥልቅ ይመረምሩት” (ዘዳግም 19፥18) ዘንድ ያዝዛል። ኢየሱስም እንዲሁ፣ ክርስቲያኖች ለእውነትና ለፍትሕ የቆሙ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ትጋትን ይጠይቃል። ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች፣ በርግጥም ከባድና ውጫዊ ጥፋት እንደ ተፈጸመ ደግሞም ንስሓ የማይገባ ሰው መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። ሌሎች ሰዎችን ማሳተፋችን ጥፋተኛው ጥፋቱን እንዲረዳ ወይም ተበዳዩ ማዘን እንደሌለበት እንዲያስተውል ያግዘዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የላይኛውና ይህ ደረጃ ለሁሉም አመቺ በሆነ ሁኔታ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ማድረግ ይቻላል።
- የሁለት ወይም የሦስት ምስክሮች ጣልቃ ገብነት መፍትሔ ካላመጣ ደግሞ፣ ተበዳይ ለቤተ ክርስቲያን እንዲያሳውቅ ታዝዟል (ማቴዎስ 18፥17)። እኔ ባለሁበት ቤተ ክርስቲያን፣ ይህ የሚደረገው ለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በማሳወቅ ነው። ምክንያቱም ጌታ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ ኀላፊነት የሰጣቸው ለሽማግሌዎች ነው (1 ጢሞቴዎስ 5፥17፤ ዕብራውያን 13፥17፤ 1 ጴጥሮስ 5፥2)። ውጫዊ መገለጫ ያለው፣ ከባድና ንሰሓ አልባ ኀጢአት የተገኘበትን ሰው ስም ይፋ ያደርጋሉ። ሌሎች በማይሰናከሉበት ሁኔታና ለቤተ ሰቡ ኀፍረትን በማያመጣ ሁኔታ ደግሞ ስለ ኀጢአቱ ዐጭር መግለጫ ይሰጣሉ። ከዚያም በተለምዶ፣ ይህን ሰው እንዲፈልጉና ወደ ንሰሓ እንዲጠሩ ለጉባኤው ሁለት ወር ይሰጣል።
- የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ የመጨረሻው ደረጃ ከኅብረቱ ወይም ከቤተ ክርስቲያን አባልነት ማስወጣት ነው። ይህ ማለት፣ የጌታን ራት መውሰድ አይችልም ማለት ነው “ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቁጠረው” (ማቴዎስ 18፥17)። ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ ውጪ እንዳለና የክርስቶስን የቃል ኪዳን ራት ዐብረነው ልንወስድ እንደማይገባ አድርገን ልንቆጥረው ይገባል(በርግጥ የቤተ ክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ይበረታታል፣ ይህ ከታች ባለው ጽሑፍ ተብራርቷል)። ጉባኤው ይህን የሚያደርገው፣ የተሰጠው ሁለት ወር ካለቀ በኋላና ኀጢአቱን ለመተው ፍቃደኛ ካልሆነ ነው። ሁለት ወርን የተጠቀምነው የቤተ ክርስቲያናችን መደበኛ ስብሰባን በዚያን ጊዜ ስለምናካሂድ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም። በማንኛውም ሁኔታ፣ ቤተ ክርስቲያን ይህን ሂደት ልታፈጥን ወይም ልታዘገይ ትችላለች።
የተግሣጽ ሂደቱን ማፍጠንና ማዘግየት ለምን ያስፈልጋል?
አንዳንድ ጊዜ የተግሣጽ ሂደትን ማዘግየት ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው፣ ለምሳሌ አንድ ኀጢአተኛ ከኀጢአቱ ጋር ለመታገል ፍላጎት ሲያሳይ ነው። ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት የኀጢአቱ ባሕርይ ብቻ ሳይሆን የኀጢአተኛውም ባሕርይ ጭምር ነው። የተለያዩ ኀጢአተኞችን ፣በተለያየ መንገድ መቅረብ ያስፈልጋል። ጳውሎስ እንዳዘዘው፦ “ሥራ ፈቶችን ገሥጿቸው፤ ፈሪዎችን አደፋፍሯቸው፤ ደካሞችን እርዷቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ” (1 ተሰሎንቄ 5፥14)። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ኀጢአታቸውን ችላ ብለውት ወይም ለኀጢአታቸው ደንታቢስ ሆነው ይሁን ወይም የእውነት ደክመው ይሁን ለመለየት ግልጽ አይደለም።
አንድ ጊዜ ሱስ ካለበት ሰው ጋራ እሠራ ነበር። ለተወሰነ ያህል ጊዜ፣ ለሥነ ምግባር ድክመቶቹ ሰበብ እንደሆነ ወይም ነፍሱ በኀጢአት ምክንያት ለዓመታት ዝላ፣ ኀጢአት ማድረጉን ማቆም አቅቶት እንደ ሆነ መለየት አልቻልኩም ነበር። እንደዚህ ዐይነት ጥያቄዎች የተግሣጽ ሂደቱን ፍጥነት ሊወስኑት ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የተግሣጽ ሂደት መፍጠን አለበት። ይህ ማለት ኢየሱስ በማቴዎስ 18 ከገለጸው ቅደም ተከተሎች አንድ ወይም ሁለት ደረጃዎችን መዝለልን ሊጠይቅ ይችላል። የተግሣጽ ሂደትን ለማፍጠን ሁለት ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች አሉ። እነዚህም (1) መከፋፈልን የሚያመጣ (2) የአደባባይ ኀጢአት(ከቤተ ክርስቲያን ባለፈ በውጪው ማኅበረ ሰብ ላይ ስለ ክርስቶስ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ኀጢአት) ስለ መጀመሪያው ምድብ፣ ጳውሎስ እንዲህ ይላል “መከፋፈል የሚያመጣን ሰው አንድ ጊዜ ምከረው፤ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀው፤ ከዚያ ካለፈ ከእርሱ ጋር አንዳች ነገር አይኑርህ” (ቲቶ 3፥10)። ጳውሎስ ምን ዐይነት ሂደትን እያመለከተ እንደ ሆነ ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ለአካሉ ስትል፣ መከፋፈልን በሚያመጡ ሰዎች ላይ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለባት ይናገራል።
ከዚህ የሚፈጥን የተግሣጽ ሂደት ደግሞ፣ በ 1 ቆሮንቶስ 5 ላይ ቀርቧል። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ፣ ክርስቲያን ያልሆነ ሰው እንኳ የሚኮንነውን ኀጢአት ያደረገን ሰው ወዲያውኑ ከቤተ ክርስቲያን እንዲያስወጡ ይነግራቸዋል። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን ያደረገውን ሰው ወደ ንሰሓ እንዲመጣ እንድታስጠነቅቅ ራሱ አላዘዘም። ያለው ይህን ነበር፦ “እንደዚህ ዐይነቱ ለሰይጣን ይሰጥ” (1 ቆሮንቶስ 5፥5)
የንሰሓ ጥሪና ሁለተኛ ዕድል ለምን አልተሰጠውም? ጳውሎስ በንሰሓና ሁለተኛ ዕድል በመስጠት ሳያምን ቀርቶ አይደለም። የተናገረውም፣ ይህንን ያደረገው ሰው “ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ” (ቁጥር 5) ነው። በርግጥ፣ ጳውሎስ ይህ ሰው ንሰሓ መግባቱን ካስመሰከረ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ መመለስ እንደሚችል ይናገራል(2 ቆሮንቶስ 2፥5 -8)። ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ፣ ይህ ኀጢአት ለሁሉም የተገለጠ ስለ ሆነ ለኅብረተ ሰቡ ስለ ክርስቶስ የሚናገረው ነገር አለ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ይህን ለሁሉም እንዲህ ብላ ግልጽ ማድረግ አለባት፦ “ይህ ተቀባይነት የለውም፤ ክርስቲያኖች እንደዚህ አያደርጉም!”
ይህን ካልን፣ 1 ቆሮንቶስ 5 ላይ በኀጢአቱ ወድቆ ስለ መሆኑ ምንም ዐይነት ጥርጣሬ እንዳልነበረው ማየቱ ተገቢ ነው። የማያከራክር እውነታ ነበር። ነገር ግን፣ ኀጢአቱን ስለ መፈጸሙ ጥያቄ ከተነሣ፣ ምንም ያህል የአደባባይ ኀጢአት ቢሆንም ኢየሱስ በማቴዎስ 18 ላይ እንዳስቀመጠው ቤተ ክርስቲያን ቆም ብላ ጥልቅ ምርመራ ልታካሂድ ይገባል። ለምሳሌ፣ በሀብት ማጭበርበር (የአደባባይ ኀጢአት) አንድ ሰው ቢጠረጠር፣ ቤተ ክርስቲያን በስማ በለው የተግሣጽ ርምጃ ልትወስድ አይገባም። ምክንያቱም ፍርድ ቤቶች በቂ ማስረጃ ባለማግኘታቸው ይህን ጉዳይ ከሦስት ወራት በኋላ ውድቅ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ታዲያ ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሂደቶችን እንድታፋጥን ሊያደርጉ የሚችሉ ሁለቱ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? (i) በቤተ ክርስቲያኑ አካል አንድነት ላይ ድንገተኛ ሥጋት ሲፈጠር ወይም (ii) በማኅበረ ሰቡ ውስጥ በክርስቶስ ስም ላይ ትልቅ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ኀጢአት ሲኖር፣ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት የተግሣጽ ርምጃዎችን ልትወስድ ትችላለች። በዚህ ሂደቶች ውስጥ ለእያንዳንዱ ውሳኔዎች የሚሆን ቀመር የለም። ስለዚህ አንድ ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ተከታትለው ሊፈቱ የሚችሉ ከአንድ በላይ ሽማግሌዎች ያስፈልጓታል።
በኅብረት መገኘትና ወደ ኅብረት መመለስ
የቤተ ክርስቲያን አባላት ብዙ ጊዜ ከአባልነትና ከጌታ ራት የታገደ ሰው በቤተ ክርስቲያኑ ሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችል እንደ ሆነ እንዲሁም በሳምንቱ ውስጥ ከእርሱ ወይም ከእርሷ ጋራ እንዴት ዐብሮ መኖር እንዳለባቸው ያስባሉ። አዲስ ኪዳን ይህን ጉዳይ በተለያዩ ቦታዎች ይገልጻል (1 ቆሮንቶስ 5፥9፣ 11 ፤ 2 ተሰሎንቄ 3፥6፣ 14-15፤ 2 ጢሞቴዎስ 3፥5 ፤ ቲቶ 3፥10፤ 2 ዮሐንስ 10) የተለያዩ ሁኔታዎች የተለያዩ ምላሽ ሊፈልጉ ይችላሉ። ነገር ግን እኔ ባለሁበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች የሚሰጡት መመሪያ በሚከተሉት በሁለት ሐሳቦች ይጠቀለላል ፡-
- ንሰሓ ያልገባውና በተግሣጽ ቅጣት ውስጥ ያለው ሰው መገኘት፣ አካላዊ ስጋትን የማያመጣ ከሆነ፣ ቤተ ክርስቲያን በሳምንታዊ ስብሰባዎቿ ላይ ይህን ግለ ሰብ መቀበል አለባት። ለዚህ ሰው፣ በእግዚአብሔር ቃል ስብከት ሥር ከመቀመጥ የተሻለ ስፍራ የለም።
- ምንም እንኳ በተግሣጽ ቅጣት ውስጥ ያለው ግለ ሰብ የቤተ ሰብ አባላት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የቤተ ሰብ ኀላፊነታቸውን መወጣት ቢገባቸውም (ለምሳሌ፣ ኤፌሶን 6፥1-3፤ 1 ጢሞቴዎስ 5፥8፤ 1 ጴጥሮስ 3፥1-2) ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት በተግሣጽ ቅጣት ውስጥ ካለው ግለ ሰብ ጋር ያላቸው ግንኙነት መለወጥ አለበት። ግንኙነታቸው የወዳጅነት ሳይሆን የታሰበበት፣ የተቆጠበና በንሰሓ የተሞላ ሊሆን ይገባል።
ይህ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ኅብረት መመለስ የሚችለው የእውነተኛ ንሰሓ ፍሬዎችን ሲያሳይ ነው። የእውነተኛ ንሰሓ ፍሬ ትርጉም የሚወሰነው በኀጢአቱ ባሕርይ ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ የንሰሓ ፍሬ ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ቀላል ነው። ሚስቱን ለተወ አንድ ሰው ንሰሓ መግባት ማለት ቀላልና ግልጽ በሆነ መልኩ ወደ እርሷ መመለስ ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ንሰሓ ማለት ኀጢአትን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፍ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ልክ ከሱስ ጋር እንደሚታገል ሰው ያንን ኀጢአት በመዋጋትና በመታገል ከፍ ያለ ጥረትና ትጋትም ማሳየት ሊሆን ይችላል።
በርግጥ፣ የእውነተኛ ንሰሓ ምንነት ጥበብ የሚፈልግ ከባድ ጥያቄ ነው። ጥንቃቄ ከርኅራኄ ጋር ሚዛኑን መጠበቁን ማረጋገጥ አለብን። ንሰሓ፣ በፍሬ እንዲገለጥ የተወሰነ ጊዜ ሊያስፈልገው ይችላል። ነገር ግን ረጅም ጊዜ መውሰድ የለበትም(2 ቆሮንቶስ 2፥5-8)። አንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ንስሓ የገባውን ግለ ሰብ፣ ወደ ኅብረቷና ወደ ጌታ ራት ለመመለስ ከወሰነች በኋላ ግን፣ የዕይታ ጊዜ መስጠት ወይም የሁለተኛ ደረጃ አባልነት ስሜት ልትፈጥር አይገባም። ይልቁንም ቤተ ክርስቲያን ይቅርታዋን በይፋ መናገር አለባት (ዮሐንስ 20፥23)፣ ንስሓ ለገባው ሰው ያላትን ፍቅር አረጋግጣ ደስታዋንም ማክበር አለባት (2ቆሮንቶስ 2፥8፣ ሉቃስ 15፥24)።
ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃን መለማመድ ያለባት ለምንድን ነው?
ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐቶችን ስትለማመድ፣ በግልጽ የተቀመጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሌላቸውና ውስብስብ የሆኑ እውነተኛ የሕይወት ሁኔታዎች ይገጥሟታል። መደበኛ የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃ፣ መቼ እንደሚያስፈልግ፣ ምን ያህል ጊዜ መውሰድ እንዳለበትና በተግሣጽ ቅጣት ውስጥ ያለው ሰው ደግሞ መቼ በእውነት ንሰሓ መግባቱን እንደምናረጋግጥ ሁልግዜ ለቤተ ክርስቲያን ግልጽ አይደለም።
ጉባኤውና መሪዎች እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመፍታት በሚሞክሩበት ጊዜ፣ ቤተ ክርስቲያን የተጠራችው ከምንም ነገር በላይ የክርስቶስን ስምና ክብር ለማስጠበቅ እንደሆነ ማስታወስ አለባቸው። የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ፣ በአፉ ክርስቲያን ነኝ የሚል፣ በተግባሩና በሕይወቱ ግን ክርስቶስ ከማያከብር ሰው ጋራ መስማማቷን ወይም አለመስማማቷን የምትገልጽበት ነው። ኀጢአትና ኀጢአቱ የተፈጸመበት ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። ነገር ግን ይህ የቤተ ክርስቲያናችን የመጀመሪያ ጥያቄ ሊሆን ይገባል፤ “የዚህ ሰው ኀጢአትና ለእርሱ ያለን ምላሽ የክርስቶስን ቅዱስ ፍቅር እንዴት ይገልጣል?”
ደግሞም ለክርስቶስ ክብር ማሰብ ማለት ክርስቲያን ላልሆኑት ሰዎች ማሰብ ማለት ነው። አብያተ ክርስቲያናት የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ መለማመድ ሲያቅታቸው ዓለምን እየመሰሉ ይመጣሉ። ከመረገጥ በቀር ምንም ጥቅም እንደሌለውና ጣዕሙን እንዳጣ ጨው ይሆናሉ(ማቴዎስ 5፥13)። በጨለማ ላለው ዓለም ምስክር መሆን አይችሉም።
እንዲሁም ለክርስቶስ ክብር ማሰብ ማለት ለሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት ማሰብ ማለት ነው። ክርስቲያኖች ኢየሱስን ለመምሰል መፈለግ አለባቸው። የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ሥርዐት ደግሞ ይህን የክርስቶስ ምስል ግልጽ ያደርገዋል። አባላት በጉባኤው የቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃ ሲወሰድ ለራሳቸው ሕይወት የበለጠ ጥንቃቄ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያሳስባቸዋል። ኮንግሪጌሽናሊስት (Congregationalist) የሆነው ጄምስ ይህን እንዲህ ያጠቃልለዋል፦ “የተግሣጽ አስፈላጊነት ግልጽ ነው። ወደ ኋላ የሸሹትን ይመልሳል፣ ግብዞችን ይለያል፣ ጤነኛ የሆነ መከባበርን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሰፍናል፣ ጥንቃቄንና ጸሎትን ያበረታታል፤ የሰውን ልጅ ድክመትና የሚያመጣውን መዘዝ በማያጠያይቅ መልኩ ያረጋግጣል፤ እንዲሁም ዐመጽን በይፋ ይቃወማል።”
በመጨረሻም፣ ለክርስቶስ ክብር ማሰብ ማለት በኀጢአት ወድቆ ላለው ሰው ማሰብ ማለት ነው። በ1 ቆሮንቶስ 5 ላይ ጳውሎስ ይህን ሰው ከጉባኤው ማስወጣት የፍቅር መገለጫ እንደ ሆነ አውቋል “ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ” (1 ቆሮንቶስ 5፥5)።
ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ ርምጃን መለማመድ ያለባት ለምንድን ነው? ለግለ ሰቡ ጥቅም፣ ክርስቲያን ላልሆኑት ጥቅም፣ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና ለክርስቶስ ክብር። እነዚህን መሠረታዊ ግቦችን በአእምሮአችን መያዝ አብያተ ክርስቲያናትና ሽማግሌዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዲፈቱ ያግዛቸዋል። በዚህም በውድቀታችንም እንኳ የእግዚአብሔር ጥበብና ፍቅር እንደሚልቅ እንገነዘባለን።
በ ጆናታን ሊማን
ማጣቀሻ
1. John Angell James, Church Fellowship or The Church Member’s Guide፣ 10ኛ ዕትም፣ 11ኛ ምዕራፍ ከሆነው, ከWorks of John Angell James ከገጽ 53 የተወሰደ
2. James, Christian Fellowship, ገጽ 53.
3. Mark Dever, Nine Marks of a Healthy Church (Crossway, 2004)፣ ገጽ 174-78.
.