የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊን ምንድን ነው?

ተጫዋቾቹን ሰለ ጨዋታ እያስተማረ፣ ነገር ግን በተግባር ስለማያሰለጥን አሰልጣኝ ምን ታስባላችሁ? የሒሳብ ትምህርትን የሚያስተምር፣ ነገር ግን ተማሪዎቹ ሲሳሳቱ ስለማያርም መምህርስ? ወይንም ስለ ጤንነት ብዙ እያወራ የራሱን ካንሰር ችላ የሚልስ ሐኪም?

እነዚህ ሁሉም መሥራት የሚገባቸውን በገሚስ እየሠሩ ነው ልትሉ ትችላላችሁ። ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ ማስተማር እና ማሰልጠን ያስፈልጋቸዋል። ትምህርት ማስተማር ደግሞ ማስረዳት እና ስሕተትን ማረም ይጠይቃል። የህክምና ሙያ ደግሞ ጤንነትን መጠበቅ፣ በሽታን መከላከል እና ማከምን ያጠቃልላል።

ታዲያ፤ አንዲት የዲሲፕሊን ሥርዓት የሌላት፣ ነገር ግን ስለ ደቀ መዝሙርነት የምታስተምር ቤተክርስቲያን ምን ታስባላችሁ? ይህ ትርጉም ይሰጣችኋል? ይህ ለብዙ አብያተ ክርስቲያናት ትርጉም እንደሚሰጥ አስባለሁ። ምክንያቱም፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ያስተምራሉ፤ ነገር ግን ጤናማ የቤተክርስቲያን ዲሲፕሊን ያላቸው ጥቂቶች ነው። ዕጢን ችላ እንደሚል ሃኪም፣ የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት በሌለበት ሰዎችን ደቀመዝሙር ለማድረግ መሞከር ትርጉም አልባ ነው።

ቤተ ክርስቲያን ኀጢአትን የሚለማመዱ ሰዎችን በዲሲፕሊን ለመቅጣት ወደኋላ የምትልባቸው ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ አስባለሁ። ሆኖም ግን፤ ይህን ለማድረግ አብዛኞቻችን የሚከብደን እና የምናፈገፍግበት ምክንያት፣ ከእግዚአብሔር በላይ ብልህ እና መልካም ለመሆን እየጣርን ስለሆነ ነው ብዬ እሰጋለሁ። እግዚአብሔር “የሚወድደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል።” (ዕብራውያን 12፥6) ከእግዚአብሔር የበለጠ እናውቃለን?

 እግዚአብሔር፣ ልጆቹን ለህይወታቸው፣ ለእድገታቸው እና ለጤንነታቸው ሲል ይቀጣቸዋል። “እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል” (ዕብራውያን 12፥10)። አዎ ያሳዝናል! ነገር ግን መልካም ፍሬ አለው። “ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል” (ዕብራውያን 12፥11)። የጽድቅና የሰላም ፍሬ! ይህ እጅግ ውብ ነው።

የጽጌረዳ አበባን መግረዝ፣ ብዙ የጽጌሬዳ አበባዎች እንዲያድጉ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት እንድታድግ ይረዳታል። በሌላ አነጋገር፣ ይህ የዲሲፕሊን ስርአት የክርስቲያናዊ ደቀ መዝሙርነት አካል ነው። “ደቀመዝሙር” እና “ዲሲፕሊን” የሚሉትን ቃል አስተውሉ። ሁለቱም ቃላት ከትምህርት አለም የተወሰዱ ሲሆን፣ እነርሱም ማስተማር እና ማረምን ያካትታሉ።  ይህንን ለማስረዳት የምንጠቀምባቸው ለአመታት የቆዩ ቃላቶች አሉ። እነርሱም፦ “ፎርማቲቭ ዲሲፕሊን” እና “ኮሬክቲቭ ዲሲፕሊን” ናቸው።

የዚህ የመግቢያ ጽሑፍ ዓላማ፣ የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት “ምን” እንደሆነ፣ “መቼ”፣ “እንዴት” እና “ለምን” እንደሚፈጸም ለአንባቢዎች ማስተዋወቅ ነው።

የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ሥርዓት ምንድን ነው?

የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ሥርዓት ምንድን ነው? የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት ማለት በጉባኤውና በአባላቱ ሕይወት ውስጥ፣ ኅጢአትን የማረም ሂደት ነው። ይህ ማለት፣ ኃጢአትን በግል በተግሳጽ ቃል ማረም ሊሆን ይችላል። ወይም ከሕብረት አባልነት በማስወጣት ኃጢአትን ማረም ሊሆን ይችላል። የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርዓት፣ በተለያየ መንገድ ሊፈጸም ይችላል። ነገር ግን ሁልጊዜ ዓላማው በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የእርሱን ሕግ መተላለፍ ሲኖር ኅጢአቱን ማረም ነው።

በቀል ሳይሆን መድሐኒት፣ ትንቢታዊ እና ምሳሌያዊ ነው

ኅጢአትን ማረም፣ በቀል ወይም የእግዚአብሔርን ፍርድ መፈጸም ሳይሆን መድሐኒት የሆነ፣ ትንቢታዊ እና ምሳሌያዊ ልምምድ ነው። መድሐኒት ነው ስል፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲሁም ጉባኤው እግዚአብሔርን በመምሰል እንዲያድግ ይረዳል። አንድ የቤተክርስቲያን አባል የሐሜት ንግግር ቢያወራ፣ ሌላኛው አባል ኅጢአቱን በማረም ሃሜት እንዲያቆምና የፍቅር ቃል እንዲያወጣ ሊነግረው ይገባል። እግዚአብሔር የሚናገረው ሰዎችን ለመጉዳት አይደለም። የእግዚአብሔርም ህዝቦች እንዲሁ ሊሆኑ ይገባል።

የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ሥርዓት ትንቢታዊ ነው ስል ደግሞ፣ የእግዚአብሔር እውነት ብርሃንን በስህተትና በኃጢአት ላይ ያበራል ማለቴ ነው። በማህበር እንዲሁም በግለሰብ ሕይወት የሚገኙብንን ካንሰሮች ነቅሶ በማውጣት እንዲቆረጥ ይረዳል። ኅጢአት የማስመሰል ጌታ ነው። ለምሳሌ፣ ሃሜት ለሰው ያለን  እውነተኛ “መንፈሳዊ ጭንቀት” ይመስላል። ስለዚህ ሃሜተኛ ሰው፣ የሚናገረው ንግግር ምክንያታዊ እና መልካም እንደሆነ ያስባል። የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ሥርዓት ግን፣ ይህንን ኅጢአት ያጋልጣል። ሁሉም ይማርና ይጠቀም ዘንድ፣ ለኃጢአተኛው እና በሱ ዙሪያ ላሉ ሰዎች ኅጢአቱን ያጋልጣል።

የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት ምሳሌያዊ ነው ስል ደግሞ፣ ሊመጣ ላለው የላቀ ፍርድ የሚያስጠነቅቅ ምሳሌ ስለሆነ ነው(1 ቆሮንቶስ 5፡5)። እንደዚህ ዐይነቱ ማስጠንቀቂያ ስጦታ ነው። አንድ የክፍል አስተማሪ የወደቁ ተማሪዎቹን ተስፋ እንዳይቆርጡ ፈርቶ አሳለፋቸው ብላችሁ አስቡ። ይህ ድርጊት አመቱ ሲያልቅ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል። ይህ መልካም ተግባር አይደለም። ልክ እንደዚሁ፣ የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት በኃጢአት ወድቆ ለተገኘ ሰው “ተጠንቀቅ በዚህ መንገድ ከቀጠልክ የባሰ ቅጣት ይጠብቅሃል። እባክህ ተመለስ” ብለን በፍቅር የምንናገርበት መንገድ ነው።

ሰዎች ተግሳጽን አለመውደዳቸው የሚያስገርም ነገር አይደለም። እጅግ ከባድ ነው። እግዚአብሔር ምንኛ መሃሪ ነው! በትናንሽ መንገዶች ስለሚመጣው ታላቅ ፍርድ ህዝቡን ያስጠነቅቃል።

የመጽሃፍ ቅዱስ ሥነ መለኮት መሠረቶች

ከቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት ጀርባ ትልቁ የቤዝሆት ታሪክ አለ። ይህም እግዚአብሔር መልካም እና ሕይወት ወደተሞላው የፍጥረት አገዛዙ፣ የወደቁትን ሰዎች መመለስ ነው (ዘፍጥረት 1፥26-28፣ 3፥1-6)።

አዳምና ሔዋን እግዚአብሔርን እንዲመስሉ ተፈጥረዋል። የእስራኤል ሕዝብም እንደዚሁ! ነገር ግን አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ህግ በመተላለፍ፣ በራሳቸው ለመምራት በመፈለጋቸው ከገነት ተባረዋል። እስራኤላውያንም፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ባለመጠበቃቸውና የእርሱን ባህሪ ባለመግለጣቸው እንዲሰደዱ ሆነዋል።

ይህንን በመስታወት ምሳሌ መግለጽ እንችላለን። መስታወት ከፊቱ ያለውን አካል ያሳያል። ልክ እንደዚሁ በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠርን፣ የምናደርጋቸው ድርጊቶች ስለእግዚአብሔር የሚናገሩት ነገር አላቸው። ችግሩ ልክ እንደተሰበረ መስታወት፣ የወደቀው ሰው የእግዚአብሔርን ምስል በትክክል አያንጸባርቅም። የወደቀው ሰው ስለሚዋሽ፣ አለም የእግዚአብሔርም ቃል አይታመንም ብላ ደምድማለች። እንዲህም ትላለች፦የፈጠረው ከዋሸ፣ እርሱም ውሸታም መሆን አለበት። ፍጡር በሚገኝበት ስፍራ፣ ፈጣሪ ይገኛል።

ደስ የሚለው ዜና፣ አንድ የአዳም ልጅ፣ የእስራኤልም ልጅ የእግዚአብሔርን ሕግ በፍጹም ጠብቋል። ጳውሎስ ይህንን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “የማይታየው አምላክ አምሳል”(ቆላስይስ 1፥15) አሁን፣ በልጁ አንድ የሆኑት ይህንኑ “አምሳል” ተሸክመው እንዲኖሩ ተጠርተዋል። ይህንን ደግሞ የምንማረው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ “ከክብር ወደ ክብር” (2ኛ ቆሮንቶስ 3፥18፤ ሮሜ 8፥29፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥49፣ ቆላስይስ 3፥9-10) ስንለወጥ ነው።

አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ እግዚአብሔርን በእውነት እና በታማኝነት የሚመስሉ ሰዎችን ለማግኘት አሕዛብ የሚሄዱባቸው ስፍራዎች ሊሆኑ ይገባል። አለም፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቅድስናን፣ ፍቅርን እና አንድነትን ሲመለከት፣ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል ያውቃሉ እንዲሁም ያመሰግኑታል (ለምሳሌ ማቴዎስ 5፥14-16፤ ዮሐንስ 13፥34-35፤ 1 ጴጥሮስ 2፥12)። ስለዚህ የቤተክርስርቲያን የዲሲፕሊን ስርአት ማለት፣ ከኅብረቱ አንድ ሰው፣ እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ፣ የእርሱን ቅድስና፣ፍቅር እና አንድነት መወከል ሲያቅተው ቤተክርስቲያን የምሰጠው ምላሽ ነው። ከመስታወት ላይ ቆሻሻን ለማጽዳት እንደምንጠቀመው፣ ትክክለኛ ያልሆኑ ምስሎችን ከክርስቶስ አካል ሕይወት ውስጥ ለማስተካከል የሚደረግ ሙከራ ነው።

የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች

ኢየሱስ በማቴዎስ 16፥16-19 እና 18፥15-20 ላይ የዲሲፕሊንን ስልጣን ለአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሰጥቷል። በምድር ላይ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን በመጀመሪያ በማቴዎስ  16፥18 ላይ የተጠቀሰ ሲሆን በ ማቴዎስ 18፥15-20 ላይ ደግሞ ህብረቶች እንዲለማመዱት ሰጥቷል።ይህንን ሐሳብ ከዚህ በኋላ በጥንቃቄ እንመለከታለን።

ጳውሎስ ስለቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት ሂደቶች በተለያየ ቦታዎች አብራርቷል። ከእነዚህም ውስጥ 1 ቆሮንቶስ 5 ፤ 2 ቆሮንቶስ 2፥6፤  ገላትያ 6፥1 ፤ ኤፌሶን 5፥ 11 ፤ 1 ተሰሎንቄ 5፥14 ፤ 2 ተሰሎንቄ 3፥6-15፥ 1 ጢሞቴዎስ  5፥19-20፤  2 ጢሞቴዎስ 3፥5 እና ቲቶ 3፥9-11 ይገኙበታል። 

ዮሐንስ በ2ኛ ዮሐንስ 10 ላይ ስለ ዲሲፕሊን ስርአትን ይናገራል። ይሁዳም በይሁዳ 22 እና 23 ላይ ይህንን ታሳቢ አድርጎ የጻፈ ይመስላል። ተጨማሪ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል።ኢየሱስ እና የመጽሃፍ ቅዱስ ጸሃፊዎች በኅብረት ውስጥ ኃጢአትን እንዲያርሙ ሲነግሯቸው፣ የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአትን ታሳቢ በማድረግ ነው።

ቤተ ክርስቲያን መቼ የዲሲፕሊን እርምጃ ልትወስድ ይገባል?

ቤተክርስቲያን መቼ የዲሲፕሊን እርምጃ ልትወስድ ይገባል? የዚህ ጥያቄ አጭሩ መልስ አንድ ሰው ኃጢአት ሲያደርግ ነው።ነገር ግን የዚህ መልስ ፣ እየተነጋገርን ባለነው የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት መሰረት ይለያያል። ስርአቶቹ መደበኛ ወይንም ኢ መደበኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ጄይ አዳምስ የግል ተግሳጽ እና እንደማህበር የቤተክርስቲያን ተግሳጽ በማለት ይለያቸዋል።  

ከባድ ሆነ ከባድ ያልሆነ ማንኛውም ኅጢአት፣ በእምነት ውስጥ ባሉ ሁለት ወንድሞች ወይም እህቶች መካከል፣ በግል ለመተራረም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት ግን ወንድማችን የሚፈጽመውን እያንዳንዱን ኃጢአት መገሰጽ አለብን ማለት አይደለም። ነገር ግን እያንዳንዱ ኃጢአት ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን፣ በማስተዋል እና በፍቅር እርስ በእርስ በግል በመተናናጽ ማደግ ይቻላል ለማለት ነው።

የትኛው ኃጢአት መደበኛ ወይም በማህበር የቤተክርስቲያን ዲሲፕሊን ያስፈልገዋል ወደሚለው ጥያቄ ስንሸጋገር፣ ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ መፈተሽ ያስፈልገናል።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝርዝሮች

አንዳንድ የቆዩ የስነመለኮት ትምህርቶች፣ መደበኛ የቤተክርስቲያንን የዲሲፕሊን ስርአት መቼ ልንለማመደው እንደሚገባ በዝርዝር አስቀምጠዋል። ለምሳሌ የኮንግሪጌሽናሊስት (Congregationalist) አገልጋይ የሆነው ጆን አንጅል፣ የቤተክርስቲያን ዲሲፕሊን የሚያስፈልጋቸው አምስት ኃጢአቶችን አስቀምጧል። (1) ኢ-ሞራላዊና አጸያፊ ተግባራት (ለምሳሌ 1ኛ ቆሮንቶስ 5፥11-13)  (2) የክርስትናን ትምህርት መካድ (ለምሳሌ ገላቲያ 1፥8 ፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥17-21፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥35፤ 2 ዮሐንስ 10) (3) መለያየትን ማስነሳት (ቲቶ 3፥ 10) (4) ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተሰብን አለመርዳት (ለምሳሌ 1 ጢሞቴዎስ 5፥8) (5) ለሰው መሰናከል ምክንያት መሆን (ለምሳሌ፦ ማቴዎስ 18፥7)።

እንደዚህ ዐይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝርዝሮች ጠቃሚ ናቸው። የተገለጹት እያንዳንዱ ኅጢአቶች ከባድና ውጫዊ መገለጫ ያላቸው መሆናቸውን አስተውሉ። በውስጥ ያሉ የልብ ኅጢአቶች አይደሉም። በዐይን የሚታዩ፣ በጆሮም የሚሰሙ ናቸው። በውጫዊ መገለጫቸው፣ ዓለምንም ሆነ ሌሎች በጎችን ስለክርስትና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ።

ነገር ግን እነዚህ ዝርዝሮች፣ መጽሃፍ ቅዱስ በግልጽ ስላላስቀመጣቸው ብዙ ኃጢአቶች (ለምሳሌ፦ ጽንስ ማስወረድ) የሚናገሩት ነገር የለም። በተጨማሪም፣ ስለዲሲፕሊን ስርአት የተጻፉ የመጽሃፍ ቅዱስ ጽሁፎች ስለአንድ የተለየ ኃጢአት ብቻ ሊናገሩ ይችላሉ። ለምሳሌ 1ኛ ቆሮንቶስ 5 ላይ ከአባት ሚስት ጋር ዝሙት የመፈጸም ኃጢአትን ያወራል። በእርግጥ ጳውሎስ ይህ ኃጢአት ብቻ የቤተክርስቲያን ዲሲፕሊን ያስፈልገዋል አላለም። አብያተ ክርስቲያናት እንደዚህ አይነት ምሳሌዎችን መሰረት በማድረግ፣ እንዴት ለሌሎች ኃጢአቶች መጠቀም ይችላሉ? 

ውጫዊ፣ ከባድ እና ንሰሓ አልባ ኃጢአት

በአንድ መንገድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን ለማጠቃለል፣ መደበኛ የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት የሚያስፈልገው ውጫዊ፣ ከባድ እና ንሰሓ አልባ ለሆነ ኅጢአት ነው። ኅጢአት ውጫዊ መገለጫ አለው። በዐይናችን የምናየውና በጆሮአችን የምንሰማው ሊሆን ይገባል። አብያተ ክርስቲያናት፣ በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ትዕቢት እና ስግብግብነት እንዳለ በተጠራጠሩበት ጊዜ ሁሉ፣ ያንን ሰው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማስወጣት የለባቸውም። ይህ ማለት ግን፣ የልብ ኃጢአቶች ከባድ አይደሉም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር እንጂ እኛ የሌላውን ሰው ልብ መመልከት እና መመርመር አንችልም። እውነተኛ ችግሮች ደግሞ በመጨረሻም መገለጣቸው አይቀርም (1ሳሙኤል 16፥7፤ ማቴዎስ 7፥17 ፤ ማርቆስ 7፥21)።

ሁለተኛ፣ ኅጢአቱ ከባድ መሆን አለበት። ለምሳሌ፣ አንድ ወንድም የተፈጠረን ታሪክ አጋኖ ሲያወራ ብመለከት፣ በግል በጉዳዩ ላይ ላወራው እችላለሁ። ስሕተቱን ባያምን ራሱ ወደ ጉባኤው አላመጣውም። ለምን? አንደኛ፣ ነገሮችን አግንኖ መናገር እንደ ጣዖት አምልኮ እና ራስን በማጽደቅ ውስጥ ባሉ በማይታዩ ኅጢአቶች የተመሰረተ ነው። እነዚህን ኅጢአቶች፣ የግል ጊዜን በመስጠት ከእርሱ ጋር መወያየት የምችልባቸው ናቸው። ሁለተኛ ደግሞ እያንዳንዱን ኅጢአት ወደ ማህበሩ ማምጣት ፍርሃት እንዲኖር ያደርጋል። በተጨማሪም ኅብረቱን ወደ ሕግ አክራሪነት (legalism) ያመራል። በሦስተኝነት ደረጃ ደግሞ፣ በሕብረት ህይወት ውስጥ ሌሎችን በፍቅር “የኀጢአትን ብዛት የሚሸፍንበት” ስፍራ ሊሆን ይገባል(1ኛ ጴጥሮስ 4፡8)። ሁሉንም ኅጢአት መከታተል የለብንም። እግዚአብሔርም በእኛ ላይ ይህንን አላደረገም።

በመጨረሻም፣ለኅጢአት ንሰሃ በማይገባበት ጊዜ መደበኛ የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰድ አግባብ ይሆናል። በከባድ ኅጢአት ውስጥ ያለ ሰው፣ በግሉ በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ በሚገኙትን የእግዚአብሔር ትዕዛዞች ተወቅሶ፣ ኅጢአቱን ለመተው ፍቃደኛ ያልሆነ ሰው ነው። ይህ ሰው ከክርስቶስ ይልቅ ኅጢአቱ ውድ ሆኖበታል። ከዚህ በታች የምንመለከተው ደግሞ ከሶስቱ አንዱ ውስጥ ብቻ የማይመደብ ነው።

የመጀመሪያ መደበኛ የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአት በምናካሂድበት ጊዜ, ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱም አጋጥመውኝ ነበር። የሚመረመረው ሰው የቅርብ ጓደኛ እና የስራ አጋር ነበር። ሆኖም ግን፣ እኔ እና ሌሎች የቤተክርስቲያን ሰዎች፣ በዝሙት ኅጢአት ውስጥ እንደነበር አንድ ቀን ምሳ እየበላን እስከሚነግረኝ ድረስ አላስተዋልኩም ነበር።ወድያውኑ፣ መጽሃፍ ቅዱስ እንደዚህ ስላሉ ኅጢአቶች ምን እንደሚል እንደሚያውቅ ነበር የጠየኩት እርሱም እንደሚያውቅ ነገረኝ። ሆኖም ግን ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም እንደሆነ ነገረኝ። ንሰሃ እንዲገባ ገፋፋሁት። ሌሎችም እንደዚሁ። ነገር ግን ለሁላችንም የሚመልስልን መልስ “እግዚአብሔር በዚህ ድርጊት ላይ ችግር የለበትም” የሚል ነበር። እንደዚህ ከመሰሉ፣ ወራትን ከፈጁ ውይይቶች በኋላ ቤተክርስቲያኒቱ በይፋ ከኅብረት አስወጣችው። ኅጢአቱ እጅግ ከባድ፣ ንሰሃ አልባ እና ግልጽ የሆነ ውጫዊ መገለጫ ነበረው። ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ቤተክርስቲያን ውስጥ ላሉት እንዲሁም በውጪ ላሉት የተሳሳተ ግንዛቤን የሚሰጥ ነበር። ቤተክርስቲያኒቱ ይህንን ሰው ለማረም፣ ለብዙ ወራት ሞክራለች። እንወደዋለን። ከኅጢአቱ ርቆ፣ ክርስቶስ አለም ከሚሰጠው በላይ ውድ እንደሆነ እንዲያውቅ እንፈልጋለን። ሆኖም ግን ምንም የመመለስ ልብ አልነበረውም። በሃሳቡ ጸንቶ ነበር። በኅጢአቱ እና በእግዚአብሔር ቃል መካከል ምርጫ ሲሰጠው፣ ኅጢአትን መረጠ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኒቱ መደበኛ የዲሲፕሊን እርምጃ ወሰደች።

እንዴት ቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን እርጃዎችን መውሰድ መለማመድ አለባት?

 እንዴት ቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን እርጃዎችን መውሰድ መለማመድ አለባት? ኢየሱስ በማቴዎስ 18፥15-17 ላይ መሠረታዊውን ሐሳብ አቅርቧል። ለደቀመዛሙርቱም እንዲህ ብሏል፦

“ወንድምህ ቢበድልህ  ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ። ባይሰማህ ግን ቃል ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ፊት ስለሚጸና፣ አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ አነጋግረው። እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ፣ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቍጠረው።”

እዚህ ጋር እንድታስተውሉት የምፈልገው፣ ጥፋቱ የሚጀምረው በሁለት ወንድማማቾች መሃል ነው። እርቅንም ለማምጣት ከሚያስፈልገው በላይ መኬድ የለበትም። ኢየሱስ ሂደቱን በአራት ደረጃዎች አስቀምጦታል።

አራት መሠረታዊ ደረጃዎች

  1. በሁለቱ ሰዎች መሃከል መፍታት ከተቻለ፣ ጉዳዩ ተዘግቷል።
  2. መፍታት ካልተቻለ ደግሞ፣ የተበደለው ወንድም ሁለት ወይንም ሶስት ወንድሞችን ይዞ ይመጣል “ቃል ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ፊት ስለሚጸና”(ማቴዎስ 18፥16) ኢየሱስ ይህንን ሃረግ ከዘዳግም 19 የወሰደው ነው። የክፍሉ አውድ ሰዎችን ከሃሰት ክሶች መጠበቅ ነው። ዘዳግም ለየትኛውም ወንጀል የተጠረጠረን ሰው “በጥልቅ ይመርምሩት” (ዘዳግም 19፥18) ዘንድ ያዛል። ኢየሱስም እንዲሁ፣ ክርስቲያኖች ለእውነት እና ለፍትህ የቆሙ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ትጋትን ይጠይቃል። ሁለት ወይንም ሶስት ምስክሮች፣ በርግጥም ከባድ እና ውጫዊ ጥፋት እንደተፈጸመ እናም ​​ንስሃ የማይገባ ሰው መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። ሌሎች ሰዎችን ማሳተፋችን ጥፋተኛው ጥፋቱን እንዲረዳ ወይንም ተበዳዩ ማዘን እንደሌለበት እንዲያስተውል ያግዘዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የላይኛው እና ይህ ደረጃ ለሁሉም አመቺ በሆነ ሁኔታ በተለያዩ ስብሰባዎች ማድረግ ይቻላል።
  3. የሁለት ወይንም የሦስት ምስክሮች ጣልቃገብነት መፍትሔ ካላመጣ ደግሞ፣ ተበዳይ ለቤተ ክርስቲያን እንዲያሳውቅ ታዟል (ማቴዎስ 18፥17)። እኔ ባለሁበት ቤተክርስቲያን፣ ይህ የሚደረገው ለቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች በማሳወቅ ነው። ምክንያቱም ጌታ ቤተክርስቲያንን እንዲመሩ ኃላፊነት የሰጣቸው ለሽማግሌዎች ነው(1 ጢሞቴዎስ 5፥17፤ ዕብራውያን 13፥17፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፥2)። ውጫዊ መገለጫ ያለው፣ ከባድ እና ንሰሃ አልባ ኅጢአት የተገኘበትን ሰው ስም ይፋ ያደርጋሉ። ሌሎች በማይሰናከሉበት ሁኔታ እና ለቤተሰቡ ኀፍረትን በማያመጣ ሁኔታ ደግሞ ስለኅጢአቱ አጭር መግለጫ ይሰጣሉ። ከዚያም በተለምዶ፣ ይህንን ሰው እንዲፈልጉ እና ወደ ንሰሃ እንዲጠሩ ለጉባኤው ሁለት ወር ይሰጣል።
  4. የቤተክርስቲያን ዲሲፕሊን የመጨረሻው ደረጃ ከህብረቱ ወይንም ከቤተክርስቲያን አባልነት ማስወጣት ነው። ይህ ማለት፣ የጌታን እራት መውሰድ አይችልም ማለት ነው “ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቁጠረው” (ማቴዎስ 18፥17)። ከእግዚአብሔር የቃልኪዳን ህዝብ ውጪ እንዳለ እና የክርስቶስን የቃልኪዳን እራት አብረነው ልንወስድ እንደማይገባ አድርገን ልንቆጥረው ይገባል(በእርግጥ የቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ይበረታታል፣ ይህ ከታች ባለ ጽሁፍ ተብራርቷል)። ጉባኤው ይህንን የሚያደርገው፣ የተሰጠው ሁለት ወር ካለቀ በኋላ እና ኅጢአቱን ለመተው ፍቃደኛ ካልሆነ ነው። ሁለት ወርን የተጠቀምነው የቤተክርስቲያናችን መደበኛ ስብሰባን በዚያን ጊዜ ስለምናካሂድ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም። በማንኛውም ሁኔታ፣ ቤተክርስቲያን ይህንን ሂደት ልታፈጥን ወይንም ልታዘገይ ትችላለች። 

ለምን የዲሲፕሊን ሂደቱን ማፍጠን እና ማዘግየት ያስፈልጋል?

አንዳንድ ጊዜ የዲሲፕሊን ሂደትን ማዘግየት ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው፣ ለምሳሌ አንድ ኅጢአተኛ ከኅጢአቱ ጋር ለመታገል ፍላጎት ሲያሳይ ነው። የኅጢአቱ ባህሪ ብቻ ሳይሆን የኅጢአተኛውም ባህሪ ሊታይ ይገባል። የተለያዩ ኅጢአተኞችን ፣በተለያየ መንገድ መቅረብ ያስፈልጋል። ጳውሎስ እንዳዘዘው፦ “ሥራ ፈቶችን ገሥጿቸው፤ ፈሪዎችን አደፋፍሯቸው፤ ደካሞችን እርዷቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ” (1ኛ ተሰሎንቄ 5፡14)። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ኅጢአታቸውን ችላ ብለውት ወይንም ለኅጢአታቸው ድንታቢስ ሆነው ይሁን ወይም የእውነት ደክመው ይሁን ለመለየት ግልጽ አይደለም።

አንድ ጊዜ ሱስ ካለበት ሰው ጋር እሰራ ነበር። ለተወሰነ ያህል ጊዜ፣ ለስነ ምግባር ድክመቶቹ ሰበብ እንደሆነ ወይም ነፍሱ በኅጢአት ምክንያት ለዓመታት ዝላ፣ ኅጢአት ማድረጉን ማቆም አቅቶት እንደሆነ መለየት አልቻልኩም ነበር። የእንደዚህ አይነት ጥያቄዎች መልስ የዲሲፕሊን ሂደቱን ሊያዘገዩት ይገባል።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የዲሲፕሊን ሂደት መፍጠን አለበት። ይህ ማለት ኢየሱስ በማቴዎስ 18 ከገለጸው ቅደም ተከተሎች አንድ ወይም ሁለት ደረጃዎችን መዝለልን ሊጠይቅ ይችላል። የዲሲፕሊን ሂደትን ለማፍጠን ሁለት ግልጽ መጽሃፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች አሉ። እነዚህም (1) መከፋፈልን የሚያመጣ (2) የአደባባይ ኅጢአት(ከቤተክርስቲያን ባለፈ በውጪው ማህበረሰብ ላይ ስለክርስቶስ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ኅጢአት) ስለ መጀመሪያው ምድብ፣ ጳውሎስ እንዲህ ይላል “መከፋፈል የሚያመጣን ሰው አንድ ጊዜ ምከረው፤ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀው፤ ከዚያ ካለፈ ከእርሱ ጋር አንዳች ነገር አይኑርህ” (ቲቶ 3፥10)። ጳውሎስ ምን አይነት ሂደትን እያመለከተ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ቤተክርስቲያን ለአካሉ ስትል፣ መከፋፈልን በሚያመጡ ሰዎች ላይ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለባት ይናገራል ።

ከዚህ የሚፈጥን የዲሲፕሊን ሄደት ደግሞ፣ በ 1ኛ ቆሮንቶስ 5 ላይ ቀርቧል። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ፣ ክርስቲያን ያልሆነ ሰው እንኳን የሚኮንነውን ኅጢአት ያደረገን ሰው ወዲያውኑ ከቤተክርስቲያን እንዲያስወጡ ይነግራቸዋል። ጳውሎስ ቤተክርስቲያኒቱ ይህንን ያደረገውን ሰው ወደ ንሰሓ እንዲመጣ እንድታስጠነቅቅ ራሱ አላዘዘም። ያለው ይህንን ነበር፦ “እንደዚህ ዐይነቱ ለሰይጣን ይሰጥ” (1ኛ ቆሮንቶስ 5፡5)

ለምን የንሰሓ ጥሪ እና ሁለተኛ ዕድል አልተሰጠውም? ጳውሎስ በንሰሃ እና ሁለተኛ ዕድል በመስጠት ሳያምን ቀርቶ አይደለም። የተናገረውም፣ ይህንን ያደረገው ሰው “ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ” (ቁጥር 5) ነው።  በእርግጥ፣ ጳውሎስ ይህ ሰው ንሰሓ መግባቱን ካስመሰከረ ወደ ቤተክርቲያኒቱ መመለስ እንደሚችል ይናገራል(2ኛ ቆሮንቶስ 2፡5 -8)። ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ፣ ይህ ኅጢአት ለሁሉም የተገለጠ ስለሆነ ለህብረተሰቡ ስለክርስቶስ የሚናገረው ነገር አለ። ስለዚህ ቤተክርስቲያን ይህንን ለሁሉም እንዲ ብላ ግልጽ ማድረግ አለባት፡ “ይህ ተቀባይነት የለውም፤ ክርስቲያኖች እንደዚህ አያደርጉም!”

ይህንን ካልን፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 5 ላይ በኅጢአቱ ወድቆ ስለመሆኑ ምንም አይነት ጥርጣሬ እንዳልነበረው ማየቱ ተገቢ ነው። የማያከራክር እውነታ ነበር። ነገር ግን፣ ኅጢአቱን ስለመፈጸሙ ጥያቄ ከተነሳ፣ ምንም ያህል የአደባባይ ኅጢአት ቢሆንም ኢየሱስ በማቴዎስ 18 ላይ እንዳስቀመጠው ቤተክርስቲያን ቆም ብላ ጥልቅ ምርመራ ልታካሂድ ይገባል። ለምሳሌ ፣ በሃብት ማጭበርበር(የአደባባይ ኅጢአት) አንድ ሰው ቢጠረጠር፣ ቤተክርስቲያን በስማ በለው የዲሲፕሊን እርምጃ ልትወስድ አይገባም። ምክንያቱም ፍርድ ቤቶች በቂ ማስረጃ ባለማግኘታቸው ይህንን ጉዳይ ከሶስት ወራት በኋላ ውድቅ ሊያደርጉት ይችላሉ።

ታዲያ ቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ሂደቶችን እንድታፋጥን ሊያደርጉ የሚችሉ ሁለቱ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? (i) በቤተክርስቲያኑ አካል አንድነት ላይ ድንገተኛ ሥጋት ሲፈጠር ወይም (ii) በማኅበረሰቡ ውስጥ በክርስቶስ ስም ላይ ትልቅ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ኃጢአት ሲኖር፣ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት የዲሲፕሊን እርምጃዎችን ልትወስድ ትችላለች። በዚህ ሂደቶች ውስጥ ለእያንዳንዱ ውሳኔዎች የሚሆን ቀመር የለም። ስለዚህ አንድ ቤተክርስቲያን እንደዚህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ተከታትለው ሊፈቱ የሚችሉ ከአንድ በላይ ሽማግሌዎች ያስፈልጓታል።

በህብረት መገኘት እና ወደህብረት መመለስ

የቤተክርስቲያን አባላት ብዙ ጊዜ ከአባልነት እና ከጌታ እራት የታገደ ሰው በቤተክርስቲያኑ ሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችል እንደሆነ እንዲሁም በሳምንቱ ውስጥ ከእሱ ወይም ከእሷ ጋር እንዴት አብሮ መኖር እንዳለባቸው ያስባሉ። አዲስ ኪዳን ይህንን ጉዳይ በተለያዩ ቦታዎች ይገልፃል (1ኛ ቆሮንቶስ 5፥9፣ 11 ፤ 2ኛ ተሰሎንቄ 3፥6፣ 14-15፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥5 ፤ ቲቶ 3፥10፤ 2ኛ ዮሐንስ 10) የተለያዩ ሁኔታዎች የተለያዩ ምላሽ ሊፈልጉ ይችላሉ። ነገር ግን እኔ ባለሁበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች የሚሰጡት መመሪያ በሚከተሉት በሁለት ሐሳቦች ይጠቀለላል ፡-

  • ንሰሓ ያልገባው እና በዲሲፕሊን ቅጣት ውስጥ ያለው ሰው መገኘት፣ አካላዊ ስጋትን የማያመጣ ከሆነ፣ ቤተክርስቲያን በሳምንታዊ ስብሰባዎቿ ላይ ይህንን ግለሰብ መቀበል አለባት። ለዚህ ሰው፣ በእግዚአብሔር ቃል ስብከት ስር ከመቀመጥ የተሻለ ስፍራ የለም።
  • ምንም እንኳን በዲሲፕሊን ቅጣት ውስጥ ያለው ግለሰብ የቤተሰብ አባላት፣ መጽሃፍ ቅዱሳዊ የቤተሰብ ኃላፊነታቸውን መወጣት ቢገባቸውም (ለምሳሌ፦ ኤፌሶን 6፥1-3፤ 1 ጢሞቴዎስ 5፥8፤ 1 ጴጥሮስ 3፥1-2) ሌሎች የቤተክርስቲያን አባላት በዲሲፕሊን ቅጣት ውስጥ ካለው ግለሰብ ጋር ያላቸው ግንኙነት መለወጥ አለበት። ግንኙነታቸው የወዳጅነት ሳይሆን የታሰበበት፣ የተቆጠበ እና በንሰሃ የተሞላ ሊሆን ይገባል።    

ይህ ሰው ወደ ቤተክርስቲያኒቱ ሕብረት መመለስ የሚችለው የእውነተኛ የንሰሃ ፍሬዎችን ሲያሳይ ነው። የእውነተኛ ንሰሃ ፍሬ ትርጉም የሚወሰነው በኅጢአቱ ባህሪይ ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ የንሰሃ ፍሬ ምን እንደሆነ ለማወቅ ቀላል ነው ። ሚስቱን ለተወ አንድ ሰው ንሰሃ መግባት ማለት ቀላል እና ግልጽ በሆነ መልኩ ወደ እርሷ መመለስ ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ንሰሃ ማለት ኅጢአትን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፍ ማለት አይደለም።

በእርግጥ፣ የእውነተኛ ንሰሃ ምንነት ጥበብ የሚፈልግ ከባድ ጥያቄ ነው። ጥንቃቄ ከርኅራኄ ጋር ሚዛኑን መጠበቁን ማረጋገጥ አለብን። ንሰሃ፣ በፍሬ እንዲገለጥ የተወሰነ ጊዜ ሊያስፈልገው ይችላል። ነገር ግን ረጅም ጊዜ መውሰድ የለበትም(2 ቆሮንቶስ 2፥5-8)። አንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ንስሃ የገባውን ግለሰብ፣ ወደ ኅብረቷ እና ወደ ጌታ እራት ለመመለስ ከወሰነች በኋላ ግን፣ የእይታ ጊዜ መስጠት ወይንም የሁለተኛ ደረጃ አባልነት ስሜት ልትፈጥር አይገባም። ይልቁንም ቤተ ክርስቲያን ይቅርታዋን በይፋ መናገር አለባት (ዮሐንስ 20፥23)፣ ንስሐ ለገባው ሰው ያላትን ፍቅር አረጋግጣ (2ቆሮንቶስ 2፥8) እና ደስታዋንም ማክበር አለባት (ሉቃስ 15፥24)።

ቤተክርስቲያን ለምን የዲሲፕሊን እርምጃን መለማመድ አለባት?

ቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን ስርአቶችን ስትለማመድ፣ በግልጽ የተቀመጠ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል የሌላቸው እና ውስብስብ የሆኑ እውነተኛ የህይወት ሁኔታዎች ይገጥሟታል። መደበኛ የቢተክርስቲያን የዲሲፕሊን እርምጃ፣ መች እንደሚያስፈልግ፣ ምን ያህል ጊዜ መውሰድ እንዳለበት እና በዲሲፕሊን ቅጣት ውስጥ ያለው ሰው ደግሞ መች በእውነት ንሰሃ መግባቱን እንደምናረጋግጥ ሁልግዜ ለቤተክርስቲያን ግልጽ አይደለም።

ጉባኤው እና መሪዎች እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመፍታት በሚሞክሩበት ጊዜ፣ ቤተክርስቲያን የተጠራቸው ከምንም ነገር በላይ የክርስቶስን ስም እና ክብር ለማስጠበቅ እንደሆነ ማስታወስ አለባቸው። የቤተክርስቲያን ዲሲፕሊን፣ በአፉ ክርስቲያን ነኝ የሚል፣ በተግባሩና በህይወቱ ግን ክርስቶስ ከማያከብር ሰው ጋር መስማማቷን ወይም አለመስማማቷን የምትገልጽበት ነው። ኅጢአት እና ኅጢአቱ የተፈጸመበት ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። ነገር ግን ይህ የቤተክርስቲያናችን የመጀመሪያ ጥያቄ ሊሆን ይገባል “እንዴት የዚህ ሰው ኅጢአት እና ለእርሱ ያለን ምላሽ የክርስቶስን ቅዱስ ፍቅር ይገልጣል?”

ደግሞም ለክርስቶስ ክብር ማሰብ ማለት ክርስቲያን ላልሆኑት ሰዎች ማሰብ ማለት ነው። አብያተ ክርስቲያናት የቤተክርስቲያን ዲሲፕሊንን መለማመድ ሲያቅታቸው አለምን እየመሰሉ ይመጣሉ። ከመረገጥ በቀር ምንም ጥቅም እንደሌለውና ጣዕሙን እንዳጣ ጨው ይሆናሉ(ማቴዎስ 5፥13)። በጨለማ ላለው ለዓለም ምስክር መሆን አይችሉም።

እንዲሁም ለክርስቶስ ክብር ማሰብ ማለት ለሌሎች የቤተክርስቲያን አባላት ማሰብ ማለት ነው። ክርስቲያኖች ኢየሱስን ለመምሰል መፈለግ አለባቸው። የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ሥርዓት ደግሞ ይህንን የክርስቶስ ምስል ግልጽ ያደርገዋል። አባላት በጉባኤው የቤተክርስቲያን የዲሲፕሊን እርምጃ ሲወሰድ ለራሳቸው ሕይወት የበለጠ ጥንቃቄ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያሳስባቸዋል።

ኮንግሪጌሽናሊስት (Congregationalist) የሆነው ጄምስ ይህንን እንዲህ ያጠቃልለዋል፦ “የዲሲፕሊን አስፈላጊነት ግልጽ ነው። ወደ ኋላ የሸሹትን ይመልሳል፣ ግብዞችን ይለያል፣ ጤነኛ የሆነ መከባበርን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሰፍናል፣ ጥንቃቄ እና ጸሎትን ያበረታታል፤ የሰውን ልጅ ድክመትና የሚያመጣውን መዘዝ በማያጠያይቅ መልኩ ያረጋግጣል እንዲሁም ዐመጽን በይፋ ይቃወማል።”

በመጨረሻም፣ ለክርስቶስ ክብር ማሰብ ማለት በኅጢአት ወድቆ ላለው ሰው ማሰብ ማለት ነው።በ 1ኛ ቆሮንቶስ 5 ላይ ጳውሎስ ይህንን ሰው ከጉባኤው ማስወጣት የፍቅር መገለጫ እንደሆነ አውቋል “ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ” (1ኛ ቆሮንቶስ 5፥5)።

ቤተ ክርስቲያን ለምን የዲሲፕሊን እርምጃን መለማመድ አለባት? ለግለሰቡ ጥቅም፣ ክርስቲያን ላልሆኑት ጥቅም፣ ለቤተክርስቲያን ጥቅም እና ለክርስቶስ ክብር። እነዚህን መሠረታዊ ግቦችን በአእምሮአችን መያዝ አብያተ ክርስቲያናት እና ሽማግሌዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዲፈቱ ያግዛቸዋል። በዚህም በውድቀታችንም እንኳን የእግዚአብሔር ጥበብ እና ፍቅር እንደሚልቅ እንገነዘባለን።

ጆናታን ሊማን


ማጣቀሻ

1. John Angell James, Church Fellowship or The Church Member’s Guide፣ 10ኛ ዕትም፣ 11ኛ ምዕራፍ ከሆነው, ከWorks of John Angell James ከገጽ 53 የተወሰደ

2. James, Christian Fellowship, ገጽ 53.

3. Mark Dever, Nine Marks of a Healthy Church (Crossway, 2004)፣ ገጽ 174-78.

.