የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች አንዳንድ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊንን ሲተገብሩ የሚከተሉትን ስሕተቶች ይሠራሉ፦
- የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊን ምን እንደሆነ እና ለምን ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ለጉባኤያቸው አያስተምሩም።
- ትርጉም ያለው የቤተ ክርስቲያን አባልነትን ተግባራዊ አያደርጉም። ትርጉም ያለው የቤተ ክርስቲያን አባልነትን ተግባራዊ ማድረግ የሚከተሉትን ያካትታል፦ (1) ሰዎችን ከመቀላቀላቸው በፊት አባልነት ምን እንደሆነ ማስተማር (2) እሁድ እሁድ ለመካፈል ብቻ የሚመጡ ሰዎችን አባል እንዲሆኑ ማበረታታት (3) አባል መሆን ለሚፈልጉ ሁሉ በጥንቃቄ ቃለ መጠይቅ ማድረግ (4) መንጋውን አዘውትሮ መንከባከብ እና (5) በሳምንታዊው ስብሰባ ላይ ማን እንዳለ በትክክል የሚያንፀባርቅ ወቅታዊ የአባልነት ዝርዝር መያዝ
- ጌታን መቀበል ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መለወጥ ምን ማለት እንደሆነ እና በተለይም የንስሓን አስፈላጊነት ለጉባኤያቸው አያስተምሩም።
- አዳዲስ አባላት ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ሲገቡ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊን አያስተምሯቸውም። በተጨማሪም ደግሞ ከእገዳ በፊት መልቀቂያ ማስገባት እንደማይሠራ አያስረዷቸውም።
- አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ ሰነዶች (መተዳደሪያ ደንብ፣ የአባልነት ቅጽ፣ ውስጠ ደንብ ወዘተ) የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊንን ያካተተ መሆኑን ማረጋገጥ ተስኗቸው፣ በዚህም ቤተ ክርስቲያንን ለፍርድ ቤት ክስ እና አደጋ አጋልጠዋል።
- ማቴዎስ 18 ወይም 1ኛ ቆሮንቶስ 5 ያስቀመጧቸውን መመሪያዎችና ደረጃዎችን እንደ ችግሩ ዐይነት አይከተሉም። ለምሳሌ፣ በማቴዎስ 18 መሠረት ኀጢአትን በግል በመገሠጽ ሂደቱን አይጀምሩም።
- ወደ መደበኛ ዲሲፕሊን የሚገቡበትን ትክክለኛ ጊዜ አያውቁም፤ አጉል በመፍጠን ወይም በመዘግየት ብዙ ነገር ያበላሻሉ።
- የተወሰነው ዲሲፕሊን የሚያስፈልግበትን ምክንያት በበቂ ሁኔታ ጉባኤውን አያስተምሩም፤ ደግሞም አያስረዱም። በዝግ ወስነው፣ በግድ ያስፈጽማሉ።
- ዲሲፕሊን ስለሚሰጥበት ኀጢአት ለጉባኤው ብዙ ያልተገቡ ዝርዝሮችን በማብራራት፣ የተቀሩትን የቤተሰብ አባላት ያሸማቅቃሉ፤ ደካማ በጎችንም ያሰናክላሉ።
- የቤተ ክርስቲያንን የተግሣጽ ሂደቶች ሙሉ በሙሉ እንደ የፍርድ ቤት ሂደት በመመልከት በንስሓ ላልተመለሰው ሰው ሊደረግ የሚገባውን የእረኝነት ኀላፊነት ይዘነጋሉ።
- በኀጢአተኞች መካከል ያለውን ልዩነትና ይህም ቤተ ክርስቲያን ወደ ተከታዩ የዲሲፕሊን ደረጃዎች ከመሄዷ በፊት ኀጢአተኞችን ለምን ያህል ጊዜ መሸከም አለባት የሚለውን ጉዳይ እንደሚነካው ብዙ ትኩረት አይሰጡም (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥14)።
- እነርሱ ራሳቸው በጌታ ምሕረት ተደግፈው እንዳሉ በመዘንጋት ዲሲፕሊኑን ፍጹም ጻድቃን እንደሆኑ በማሰብ ያደርጋሉ። ይህን የተሳሳተ አቋም ተከትሎ ደግሞ ሌሎች ስሕተቶች ይከተላሉ፤ ለምሳሌ ከመጠን በላይ ከባድ ቅጣትን ያለ ርኅራኄ ያደርጋሉ።
- ኀጢአተኛውን በእውነት አይወዱም። ይህም ጌታ በንሰሓ እንዲመልሰው ባለ መጸለይ ይገለጣል።
- ከሚጤስ ጧፍ ወይም ከተቀጠቀጠ ሸምበቆ በጣም ብዙ ይጠብቃሉ። በሌላ አገላለጽ፣ በኀጢአት እስራትና በጥልቅ ባርነት ውስጥ ለነበረው ሰው ያልተገቡ ከፍተኛ የንስሓ ፍሬዎችን ይጠይቃሉ።
- ንሰሓ ለመግባት ፈቃደኛ ካልሆኑ ኀጢአተኞች ጋራ ጉባኤው ምን አይነት ግንኙነት ሊኖረው እንደሚገባ በትክክል አያስተምሩም። ለምሳሌ በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በዲሲፕሊን ከተቀጣው ሰው ጋር እንዴት ግንኙነት እንደሚያደርጉ፣ በተጨማሪም ለንሰሓ እንዲያበረታቱት አያስተምሩም።
- ዲሲፕሊን የተደረገበት ግለሰብ የእግዚአብሔርን ቃል መስማቱን እንዲቀጥል የቤተ ክርስቲያን ፕሮግራሞችን እንዲካፈል አይጋብዙም (የወንጀል ስጋት ከሌለ ማለት ነው)። እንዲሁም፣ ሁሉም አባል ዲሲፕሊን የተደረገበት ግለሰብ ቤተ ክርስቲያን መምጣት እንዲቀጥል ተስፋ ማድረግ እንዳለባቸው አያስተምሩም።
- የዲሲፕሊን ሂደቱን የመምራት ኀላፊነት ሙሉ በሙሉ በአንድ ሰው (ምናልባትም ዋናው መጋቢ) ጫንቃ ላይ ይጭናሉ። በዚህም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ዋና መጋቢው የግል ጠብ እንዳለው እንዲጠረጥሩ ያደርጋሉ።
- በአባላት ሕይወት ውስጥ በቂ የሆነ የሽማግሌዎች ተሳትፎ አያደርጉም። በዚህም ሽማግሌዎች የበጎቹን ሁኔታ አያውቁም። የክትትል ማነስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን የዲሲፕሊን ሥራ በሚገባ የመሥራት አቅሟን ማዳከሙ አይቀሬ ነው።
- በየሳምንቱ የእግዚአብሔርን ቃል አያስተምሩም።
- የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊን ስለሚመጣው የመጨረሻ ቅጣት በፍቅር ማስጠንቀቂያ መሆኑን ከማስተማር ይልቅ፣ አባላት በበቀል መንፈስ ይህን ውሳኔ እንዲያስፈጽሙ ያደርጋሉ።
- መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ምክንያቶች የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊን እርምጃ ይወስዳሉ (ካርታ መጫወት፣ ጭፈራ፣ ወዘተ)።
- ለግለሰቡ ጥቅም፣ ለቤተ ክርስቲያን ስም ጥቅም፣ በውጭ ላለው ማኅበረሰብ እና ለክርስቶስ ክብር ጥቅም ላልሆኑ ምክንያቶች ዲሲፕሊንን ያደርጋሉ።
የአርታዒ ማስታወሻ፡ እነዚህ ከጆናታን ሊማን Church Membership: How the World Knows Who Represents Jesus (Jonathan Leeman) መጽሐፍ ለንባብ እንዲመቹ ተደርገው የተወሰዱ ናቸው።