አስተምህሮተ ምርጫን የምንቀበለው ለምንድን ነው?

ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫን ለመቀበል ዐምስት ምክንያቶች

ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫ እንደ መረጃ ልንቀበለው የሚገባ እውነት ብቻ ሳይሆን፣ ከጣፋጭነቱ የተነሣ ልንወድደው የተገባ አስተምህሮ ጭምር ነው። በርግጥ እውነት ካልሆነ ሊወደድ አይችልም። ስለዚህ የምንቀበልበትና የምንወድድበት ትልቁ ምክንያት እውነት መሆኑ ነው። ከዚያ በፊት ግን በትርጉም እንጀምር፦

ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫ ማለት፣ እግዚአብሔር ከፍጥረት በፊት ያለው ነጻ ምርጫ ማለት ነው፤ ይህም አስቀድሞ በታየ እምነት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ ለከዳተኞች እምነትንና ንስሓን የሚሰጥበት፤ ይቅርታንም በማድረግ ወደ ዘላለማዊ የደስታ ቤተ ሰቡ የሚያስገባበት ነው።

  1.  ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫን ወድደን እንቀበላለን፤ ምክንያቱም እውነት ነው።

‘ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫ’ ላይ አቀርብ የነበረው ተቃውሞ ሁሉ ውድቅ የሆነው፣ ሮሜ 9ን ማብራራት ሲያቅተኝ ነበር። ምዕራፉ የሚጀምረው ጳውሎስ ለአይሁድ ወገኖቹ ሲል የተረገመና ከክርስቶስም ተለይቶ የተጣለ ለመሆን ያለውን ዝግጁነት በማሳየት ነው (ሮሜ 9፥3)። ይህ የሚያሳየው አንዳንድ አይሁዶች እየጠፉ እንደ ሆነ ነው። ይህም እግዚአብሔር ለአይሁዶች የገባውን የተስፋ ቃል ላይ ጥያቄ ያስነሣል። አልተሳካም ማለት ነው? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይመልሳል፤ “የእግዚአብሔር ቃል ተሽሯል ማለት አይደለም” (ሮሜ 9፥6)። ለምን?

ምክንያቱም “ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤላዊ አይደለምና” (ሮሜ 9፥6)። በሌላ አነጋገር፣ የእግዚአብሔር ዐላማ በእስራኤል ውስጥ የነበረውን እያንዳንዱን ሰው ነጻ ማውጣት አልነበረም። ይልቁንም ሐሳቡ የምርጫ ነበር።

ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቅድመ ሁኔታ የሌለውን ምርጫ ለማስረዳት፣ ጳውሎስ የያዕቆብንና የዔሳውን ምሳሌ ይጠቀማል፤ “መንትዮቹ ገና ሳይወለዱ፣ ወይም በጎም ሆነ ክፉ ሳያደርጉ፣ የእግዚአብሔር ሐሳብ በምርጫ ይጸና ዘንድ፣ በሥራ ሳይሆን ከጠሪው በመሆኑ፣ “ታላቁ ታናሹን ያገለግላል” ተብሎ (ለርብቃ) ተነገራት” (ሮሜ 9፥11-12)።

በሌላ አነጋገር፣ እግዚአብሔር ከእስራኤልና ከአሕዛብ (ራእይ 5፥9) ሁሉ ለራሱ ግለ ሰቦችን የመረጠበት የመጀመሪያ ሐሳቡ፣ የተመረጡት ሰዎች በሚያሟሉት ምንም ዐይነት ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ምንም ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫ ነበር። እንዲህም ይላል፦ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ ለምራራለትም እራራለታለሁ” (ሮሜ 9፥15ሮሜ 9፥16-1811፥5-7ን ተመልከት)።

ኢየሱስም ይህን አስተምህሮ አጽንቶታል፦ “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤” (ዮሐንስ 6፥37)። ወደ ኢየሱስ መምጣት ለምርጫ ብቁ ለመሆን የምናሟላው ቅድመ ሁኔታ አይደለም። የምርጫ ውጤት ነው። አብ በጎቹን መርጧል። የእርሱ ናቸው፤ ለወልድም ሰጥቷቸዋል፤ ለዚህ ነው የሚመጡት። “ከአብ ካልተሰጠው በቀር፣ ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም” (ዮሐንስ 6፥65)። “እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤” (ዮሐንስ 15፥16ዮሐንስ 17፥269 እና ገላትያ 1፥15ን ተመልከት)።

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ፣ አንዳንዶች አምነው፣ የተቀሩት ግን ለምን አላመኑም? ለሚለው ጥያቄ የሉቃስ መልስ ምርጫ የሚል ነው፤ “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትም ሁሉ አመኑ” (የሐዋርያት ሥራ 13፥48)። ይህ “መዘጋጀት”፣ ይህ ምርጫ፣ አስቀድሞ በታየ እምነት ላይ የተመሠረተ አልነበረም፤ የእምነት መንስኤ ነበር እንጂ።

በኤፌሶን 1 ላይ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “[እግዚአብሔር] ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ [በክርስቶስ] መርጦናልና። … ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ፣ አስቀድሞ የተወሰንን እኛ ደግሞ በእርሱ ተመርጠናል፤ (ኤፌሶን 1፥411)። በዚህ ጉዳይ ላይ ለዘላለም ወሳኝ የሆነው፣ “የእግዚአብሔር ፈቃድ ምክር” ነው።

በፍርድ ቀን ላይ እግዚአብሔር፣ “ሌሎች ሳያምኑ አንተ በልጄ ለምን አመንክ” ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ምላሻችሁ ምን ይሆን? “ከሌላው ይበልጥ አስተዋይ ስለ ነበርኩ” ብላችሁ መቼም አትመልሱም። በፍጹም። ነገር ግን በርግጠኛነት፣ “ከጸጋህ የተነሣ ነው። ባትመርጠኝ ኖሮ፣ በመንፈሳዊ ሞት ሞቼ፣ ምላሽ አልባ፣ በደለኛ ሆኜ እቀር ነበር” ብላችሁ ትመልሳላችሁ።

  1. ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫን ወድደን እንቀበላለን፤ ምክንያቱም ጠላት በሆነ ዓለም ውስጥ ጸጋውን በምናውጅበት ጊዜ እንዳንፈራ እግዚአብሔር አዘጋጅቶታልና።

“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? … እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስስ ማን ነው?” (ሮሜ 8፥3133)።

  1. ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫን ወድደን እንቀበላለን፤ ምክንያቱም ትሑት እንዲያደርገን እግዚአብሔር አዘጋጅቶታልና።

“እግዚአብሔር ጥበበኞችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ … ይኸውም ማንም ሰው በእርሱ ፊት እንዳይመካ ነው። … ‘የሚመካ በጌታ ይመካ።’” (1 ቆሮንቶስ 1፥272931)።

  1.  ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫን ወድደን እንቀበላለን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለርኅራኄ፣ ለደግነትና ለይቅርታ የመነሣሻ ኀይል አድርጎታል።

“እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ … ልበሱ፤ … ይቅር ተባባሉ (ቈላስይስ 3፥12-13)። የእርሱን ምርጫ በእውነት ዐይቶና ቀምሶ፣ ደግ፣ ታጋሽና ይቅር ባይ ለመሆን ያልተነሣሣ ማንም የለም።

  1. ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫን ወድደን እንቀበላለን፤ ምክንያቱም በወንጌል ስብከት ወቅት የማያምኑ ኀጢአተኞችን ለመርዳት ትልቅ ማበረታቻ ነው።

ክርስቶስን ለማያምኑ ሁሉ በነጻ ስታቀርቡ፣ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው፣ “በጣም ከባድ ኀጢአት ሠርቻለሁ፣ እግዚአብሔር እኔን ማዳን ሊመርጥ አይችልም” አለ እንበል። ልትሉት ከምትችሉት ሁሉ ነገር በላይ እጅግ ተስፋ አስቆራጭና አጥፊ የሆነው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር በፊት የሚያድነውን እንደ መረጠ ታውቃለህን? እና እርሱ ደግሞ አንተ ውስጥ ባለ በየትኛውም ነገር ላይ አልተመሠረተም።  ከመወለድህ በፊት ወይም አንዳች መልካም ወይም መጥፎ ነገር ከማድረግህ በፊት፣ እግዚአብሔር አንተን ለማዳን ወይም ላለማዳን መርጧል።

ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት ቀርባችሁ ለመመረጥ ከሚያስፈልጓችሁ መመዘኛዎች ውስጥ የሚጎድላችሁ ምን እንደ ሆነ የመንገር ድፍረቱ አይኖራችሁም። ለመመረጥ ምንም መመዘኛዎች አልነበሩም። “ምን ላድርግ?” ብሎ ይጠይቃል። “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ ከዚያም ትድናለህ” (የሐዋርያት ሥራ 16፥31)። በዚህ መንገድ ነው “መጠራታችሁንና መመረጣችሁን የምታረጋግጡት” (2 ጴጥሮስ 1፥10)። አዳኙን ወድዳችሁ ከተቀበላችሁ፣ መመረጣችሁን ታረጋግጣላችሁ፤ እናም ትድናላችሁ።

ጆን ፓይፐር