በክርስቶስ ማደግ

የመጋቤያዊ አገልግሎት ከሚያስገኛቸው በሐሴት የታጀቡ ትሩፋቶች አንዱ፣ በእያንዳንዱ የጌታ ቀን ማለዳና ምሽት የእግዚአብሔርን ቃል ለእግዚአብሔር ሕዝብ የመስበክ ዕድል ማግኘት ነው። ያም ሆኖ ግን ከመጋቤያዊ አገልግሎት ተግዳሮቶች መኻል አንዱና ዋነኛው፣ ይኸው የሰበካ ተግባር ነው። ይህም ተግዳሮት፣ የስብከቱ ዝግጅት አስከትሎት በሚመጣው በደስታና በዝለት የተሞላ ሂደት፣ እንዲሁም ሰበካው በሚያስከትለው መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ሥነ-ልቦናዊ ውጥረት ብቻ የተገደበ አይደለም። ይልቁንስ ከልዩ ልዩ ዘርና ብሔረ ሰብ፣ እንዲሁም ከተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዳራዎች ለተውጣጡ፤ ለበሳልና ለአዳዲስ አማኞች፣ በእምነት ለደከሙት እንዲሁም በእምነት ለበረቱት፣ ለጎልማሶች ብሎም ለሕፃናት ጉራማይሌ ለሆኑ የጉባኤ ታዳሚዎች በሚሆን መንገድ ቃለ እግዚአብሔርን በሙላት መግለጥና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማዛመድ የሰባኪው ሌላኛው ተግዳሮት ነው። በጌታ እገዛ በመጋቤያዊ አገልግሎት ውስጥ በምቆይባቸው ጊዜያት ሁሉ ለመላው ጉባኤያችን በሚሆን መንገድ መስበክ፣ ተግዳሮት ሆኖ እንደሚቀጥል ርግጠኛ ነኝ። በዘመናችን ካሉት ግልጽ አድርጎ የመናገርና የተግባቦት ሊቃውንት መኻል ግንባር ቀደም በሆኑት፣ በዶክተር አር ሲ ስፕሮል ሥር ሆኜ የመሠልጠን ዕድል በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ። የእኚህ መጋቢ መላውን ጉባኤ ባማከለ መንገድ የመስበክ አርኣያነት፣ አብዛኛዎቹ ታማኝ መጋቢዎች እንዲኖሯቸው አጥብቀው ከሚመኟቸው ተምሳሌቶች መካከል አንዱ ነው።

በጉባኤው ውስጥ ለሚገኝ ለእያንዳንዱ ሰው በሚሆን መንገድ ለመስበክ መጣር ቀላል ተግባር አይደለም። እኛ ሰባኪዎችም ከመነሻው እስከ መደምደሚያው ድረስ የእግዚአብሔርን ቃል በሕዝቦቹ ልብ ውስጥ በሚያሰርጸውና እንዲተገብሩትም በሚያደርገው በመንፈስ ቅዱስ ላይ እንደገፋለን። መንፈስ ቅዱስ የጎልማሶችን ብቻ ሳይሆን የሕፃናትንም ልብ ዳግም በመውለድ እንደሚያድስ የማይናወጥ እምነት አለን። ስለዚህ መልእክታችንን ለታዳጊዎችና ለጎልማሶች ለማስተላለፍ መጣር አለብን። ይህም ማለት በጉባኤያችን ውስጥ ያሉት ጎልማሶች ታዳጊዎችን መታገሥ ያለባቸው ሲሆን፣ ታዳጊዎች ደግሞ ታላላቆቻቸውን ለማክበር ሁልጊዜም መጣር አለባቸው። ይህም፣ ልጆቻችን ወደ ብስለት ከሚያድጉባቸው መንገዶች አንዱ ነው። በርግጥ ሕፃናት ልጆቻችን እንደ ሕፃን እንዲሆኑልን እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ሁልጊዜም ሕፃናት ሆነው እንዲቀሩ አንፈልግም። ይልቁንም በክርስቶስ የበረቱና በሁሉም የሕይወት ገጽታዎች የበሰሉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ወደ መሆን እንዲያድጉልን እንሻለን።

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለታዳጊው ጢሞቴዎስ፣ “በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው” ሲለው እንመለከታለን [1 ጢሞቴዎስ 4፥12] ። ብስለት የዕድሜ ጉዳይ ስላልሆነ፣ ወጣት አማኞች እንኳ ስሜታዊና መንፈሳዊ ብስለት ላይ በመድረስ ለሌሎች አርኣያ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲያውም በመካከላችን የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች እጅግ የበሰሉ ሲሆኑ፣ አንዳንድ ጎልማሶች ደግሞ የብስለት ደረጃቸው ዝቅ ያለ ነው። ወጣቶችንና ጎልማሶችን ጨምሮ እግዚአብሔር ሕዝቡን የጠራው፣ “ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ” እንዲያድጉ ነው [ኤፌሶን 4፥13]። ይህም የሚሆነው፣ ሰዎች እኛን እንዲያከብሩን አይደለም፤ ነገር ግን፣ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ክርስቶስን በመመልከት፣ እንደ በሰሉ አማኞች ስንመላለስ ዐይተው ከሞት የተነሣውንና ዳግመኛ የሚመለሰውን አዳኛችንን ከፍ ከፍ እንዲያደርጉት ነው።