ወላጆች ከልጆቻቸው በላይ በቀላሉ የቅጣት ጥቅም ይታያቸዋል። ልጅ እያለሁ፣ ወላጆቼ የሚቀጡኝ ስለሚወዱኝ ነው የሚለውን ሐሳብ አልስማማበትም ነበር። በፍጹም በዚያ መልኩ አላየሁትም ነበር። የራሴ ተከላካይ ጠበቃ ሆኜ፣ የቅጣቴን ክብደት፣ የተደረገብኝን የጥድፊያ ብይን፣ የወንጀሌንና የቅጣቴን አለመመጣጠን አብሰለስላለሁ። ለራሴ ከመጠን በላይ በማዘን ትራሴን በእንባ አርሳለሁ። ፍትሓዊ አይደለም! ገና በዕድሜ ጠና ካልኩ በኋላ ነው ቅጣትን በትክክለኛው መነጽር ለመመልከት የበቃሁት። አሁንማ፣ ከፍቅራቸው ስለሚመነጭ የወላጆቼ ተግሣጽ ደስተኛ ነኝ።
ታዲያ የእግዚአብሔር ቅጣትስ? ስለ እርሱ አመስጋኞች ነን? በዚያ ውስጥ ፍቅሩ ይታየናል?
አማኞች ስንሆን፣ ይህን የልጅነት ትምህርት ወደ እምነት ጉዟችን አምጥተን ለመተርጐም እንቸገራለን። ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቅጣት የምናየው ባልበሰለ የልጅ ዕይታ ይሆናል። በመከራ ስናልፍ፣ “ለምን?” የሚል ጥያቄ እንድናነሣ ያደርገናል። የእግዚአብሔር ሕዝብ መጥፎ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው፣ በመደነቅ ወይም በብስጭት አልያም በጥርጥር ጥያቄ ውስጥ እንገባለን። የእግዚአብሔርን ጥበብ ጥያቄ ውስጥ እንከትታለን። የልቡ ተነሣሥቶት ላይ ጥያቄ እናነሣበታለን። በልጅነታችን እንዳጋጠመን የወላጆቻችን ቅጣት፣ የቅጣታችንን ከባድነትና ተገቢነት፣ የዳኝነቱን ፍትሓዊነት ሁሉ ጥያቄ እናነሣበታለን። በዚህ ህመም ውስጥ ማለፍ ያለብኝ፣ ለምንድን ነው?
ይህ በርግጥ በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ ትኵረት ከተሰጠው ጉዳይ ጋር የሚገጥም ነው። ጸሓፊው የአሁኑን ፈተናና መከራ በመንፈሳዊ ብስለት እንዲያጤኑት፣ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን ያነሣሣቸዋል። እግዚአብሔር ልጆቹን እንዴት እንደሚይዝ እንዲያስታውሱ ያበረታታቸዋል። አስታዋሽ አስፈልጓቸው ነበር።
ሁላችንስ እንደዚያው አይደለን? እነርሱን በተመለከተ፣ “ልጆች እንደ መሆናችሁ እንዲህ በማለት የተናገራችሁን ማበረታቻ ቃልም ረስታችኋል”[1] (ዕብራውያን 12፥5) የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል ልናስታውስ ይገባናል። እነዚህ ቃላት ቀደም ሲል “በመስቀል ታግሦ… ከኀጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ” (12፥2-3) በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ እንዲያስቡ የተሰጠው ምክር አካል ናቸው።
የእግዚአብሔርን ቃል ወደ መርሳት ውስጥ ሸርተት እንላለን። ስለዚህ፣ የዕብራውያን ጸሓፊ የእግዚአብሔርን አባታዊ ቅጣት፣ “ምክር” ወይም “ማበረታቻ” በማለት ያን ቃል ያስታውሰናል። እዚህ ጋር ጥቅም ላይ የዋለው ቃል በዮሐንስ ወንጌል ለመንፈስ ቅዱስ ጥቅም ላይ ከዋለው “አጽናኝ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና አለው። በዮሐንስ ወንጌል ፐራክሌቶስ (paraclētos) ሲሆን እዚህ ደግሞ ፐራክሌሲስ (paraclēsis) ነው። የዕብራውያን ጸሓፊ እንዳንረሳው የሚነግረን ይህ አጽናኝ የእግዚአብሔር ቃል ከምሳሌ 3፥11-12 ላይ የተወሰደ ጥቅስ ነው። ጸሓፊው ሁለት ነገሮችን ይነግረንና ማብራሪያውን ያስከትላል። የመጀመሪያው፣ የጌታን ቅጣት ማቅለል የለብንም፤ ሁለተኛው፣ በምንገሠጽበት ጊዜ መድከም የለብንም፤ ሦስተኛው ደግሞ ማብራርያው ነው፤ “ምክንያቱም ጌታ የሚወድደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል” (ቍ. 5ለ-6)።
ቅጣት፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው አባታዊ ግድ መሰኘት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ነጥብ ግልጽና ልንስተው የማይገባ ነው። መከራና ትግል ሲገጥመን፣ ተስፋ ማጣትና ስደት ሲከሰትብን፣ እግዚአብሔር አይጥለንም። አልረሳንም፤ ደግሞም በእርሱ ዘንድ የተጠላንና የማንፈለግ አይደለንም። ይልቅ፣ እንደ ልጆቹ ይመለከተናል።
ጸሓፊው ይህን ጭብጥ ያስፋፋዋል። እነዚህን በመከራ ውስጥ ያሉ አማኞችን ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ወደሚያሳዩት ፍቅር ይጠቁማቸዋል። ምድራዊ ወላጆቻችን፣ “መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፡፡” ጸሓፊው “መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው” ሲል፣ ወላጆቻችን ከስሕተት የጸዱ አለመሆናቸውን ያሳየናል። በተቻላቸው መጠን ምርጥ አስተዳደግ እንዲኖረን ለፍተዋል፤ ለዚህም “እናከብራቸውም ነበር፡፡” በመደበኛው አኳኋን ዐድገን ወደ ዐዋቂነት ስንደርስ፣ በተለይ የራሳችን ልጆች ሲኖሩን፣ ወላጆቻችን እኛን ለማሳደግ ያሳዩትን ጥረት እናደንቃለን። የተሻልን እንድንሆንና መልካም ሥነ ምግባር እንዲኖረን ስለ ጣሩ እናከብራቸዋለን። በእውነቱ፣ ማንም ልባቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ፣ አምሮታቸውን እንዴት እንደሚገቱ ወይም ምላሳቸውን እንዴት እንደሚገሩ ያላስተማራቸውን ሰዎች ልናዝንላቸው ይገባል።
እግዚአብሔር ግን መልካም ሆኖ እንደ ታየው ሳይሆን፣ “ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል፡፡” እዚህ ጋር፣ እግዚአብሔር የሚያደርገውን ማወቁን በተመለከተ የጥርጥር ጥያቄ አይነሣም። ልጅ በማሳደግ ጥረቱ ውስጥ አንዳችም የግንዛቤ ዕጥረት፣ የተሳሳተ አመለካከት፣ ወይም ኢፍሓዊነት ኖሮ አያውቅም። ታዲያ ቅጣት ደስ የሚያሰኝ ነው? አይደለም ይለናል የዕብራውያን ጸሓፊ። “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም” (12፥11ሀ)። ልናስተባብለው የማንችለው ሐቅ ነው፤ ቅጣት ይጎመዝዛል። ማቅኛ ነው። ወደ አዲስ አቅጣጫ ይዘውረናል። ከኀጢአተኛ የአመለካከት፣ የድርጊት፣ የአስተሳሰብና የንግግር ዐጕል ልማዶች እንድንወጣ ያስገድደናል። ልማዶቻችንን በተሻለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕይታ እንድንመለከታቸው ያደርገናል። መንገዱ ህመም ቢኖረውም፣ ወሮታው ግን ቡሩክ ነው። “ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል” (12፥11ለ)።
“ለለመዱት” የሚለውን በጣም አስፈላጊ ነጥብ መዘንጋት የለብንም። እነዚህ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በመከራቸው አማካይነት እንዲሠለጥኑ ያበረታታቸዋል። በሌላ አነጋገር፣ ቅጣቱ ተጽእኖና ውጤት እንዲኖረው ካስፈለገ፣ እንዲሁ መከራቸውን መቋቋም ብቻ ሳይሆን በመከራቸው ሊሠለጥኑ ይገባል። ሊማሩበት ይገባል፤ ወደ ትምህርት ቤት መመላለስ ለመማራችን ዋስትና እንደማይሆነው ሁሉ፣ መሠልጠንም በራሱ ዝም ብሎ የሚከሰት አይደለም። አንዳንድ በብዙ መከራ ያለፉ ክርስቲያኖች፣ የተማሩት በጣም ጥቂት ብቻ ነው። በአንጻሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ በእግዚአብሔር ቅጣት ከመሠልጠናቸው የተነሣ፣ ለእግዚአብሔርም ለእኛም የሚታይ ፍሬ ይገኝባቸዋል።
በዚህ ረገድ የኢዮብን ታሪክ ማየት ያግዘናል። ኢዮብ እጅግ ከባድ በሆነ መከራ እምነቱ ተፈትኗል። ሕይወቱን ያጠቁት አሳዛኝ ክሥተቶች የመጡበት ኀጢአተኛ ስለ ሆነ ወይም በኀጢአቶቹ ምክንያት አልነበረም። የተፈተነው፣ ታማኝ ስለ ነበረ ነው (ኢዮብ 1፥1፣ 8፤ 2፥3)። በኢዮብ መፈተን ውስጥ የሰይጣንና የእግዚአብሔር ዐላማ ለየቅል ነበር። ኢዮብ አብዛኛውን ቤተ ሰቡን እንዲሁም ብልጽግናውንና ጤናውን ሁሉ በአንድ ጊዜ ማጣቱን አስታውሱ። ሚስቱ እንኳ ትታዋለች። ምክሯ፣ “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” የሚል ነበር(2፥9)። ኢዮብ በዚህ ሁሉ ሽብር ከተሠቃየ በኋላ፣ ሦስት ጓደኛ ተብዬዎቹ፣ መልካም ሰዎች መጥፎ ነገር እንደማያጋጥማቸውና ኢዮብም ይህ የደረሰበት በኀጢአቱ ምክንያት እንደ ሆነ በመክሰስ ሌላ መከራ ጨመሩበት። ምክራቸውም፣ “ንስሐ ግባ!” የሚል ነበር (8፥5-6፤ 15፥4-5፤)። ኢዮብ ግን ከእግዚአብሔር ቃል የተማረ ስለ ነበር፣ ጉዳዩን አጽናኝ ነን ከሚሉት ጋራ ተሟገተ። ሙግቱ ከእግዚአብሔርም ጋራ ነበር። በግራ መጋባት ስሜት ውስጥ ሆኖ፣ እግዚአብሔርን ተጠየቅ አለው። እግዚአብሔር ማብራርያ እንዲሰጠው ፈለገ። በስተመጨረሻም እግዚአብሔር ተናገረ፤ ነገር ግን ጌታ ሳይሆን ኢዮብ ነበር በጥያቄ ለምርመራ የቀረበው (ምዕራፍ 38)።
ኢዮብ በዐፈርና በዐመድ ላይ ተቀምጦ ተጸጸተ (42፥6)። በመከራው ውስጥ እግዚአብሔርን ባለማመኑ ንስሓ ገባ። የእግዚአብሔርን ፍትሕና በመከራው በኩል ለእርሱ ያለውን መልካም ዐላማ በመጠራጠሩና ልቡ በመዛሉ ንስሓ ገባ። የእግዚአብሔርን ጥበብ፣ ሞገስና ፍቅር ጥያቄ ውስጥ በመክተቱ ተጸጸተ። ያገጠሙትን ፈተናዎች ሁሉ እግዚአብሔር ለበጎ እንደሚጠቀማቸው ሳያስተውል በመቅረቱ ንስሓ ገባ። የዕብራውያን ጸሓፊም የሚለው ይህንኑ ነው። እግዚአብሔር ፈተናዎቻችንን እንደ ቅጣት በመጠቀም ለበጎ ያደርግልናል።
ይህን እንድናምን፣ የሚሰማ ጆሮ ያስፈልገናል።
የእግዚአብሔር ማስተማርያ ቃሉ ነው። ሆኖም ሁኔታዎች ትኵረታችንን ይይዙታል፤ ስለ ሆነም እግዚአብሔር ሥራ ማጣትን፣ አስቸጋሪ ሕፃናትን፣ የተቸገሩ ታዳጊዎችን፣ ጕዳትን፣ ፍቺን፣ አደጋንና ሌሎችንም ብዙ ዐይነት ትኵረት ያዥ ሁኔታዎችን ይጠቀምባቸዋል። ሸክሞቹ ትልልቅ ወይም ትንንሽ ሊሆኑ ይችላሉ። የኢዮብ ትልልቅ ነበሩ።
ምናልባት ከርሱ ጋራ ሲነጻጸር፣ የእናንተ ትንንሽ ይሆናሉ። ይሁን ግድ የለም። እግዚአብሔር የሚወድዳቸውን ይቀጣል። በፈተናና በከባድ ሁኔታዎች ትኵረታችሁን ከያዘ በኋላ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ያለው የእግዚአብሔር ቃል በጆሮአችን ውስጥ ለማቅናት፣ ለማጽናናት፣ ለመገሠጽ፣ ለማሠልጠንና ለመሳሰሉት ድምፅ ሆኖ የማቅኛ መሣሪያ በመሆን ያገለግላል። ይህ አባታዊ “ቅጣት” ነው። በእንግሊዝኛው ቅጣት (discipline) ደቀ መዝሙር (disciple) ከሚለው ቃል ጋር ቅርበት አለው። የእግዚአብሔር ቅጣት እኛን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ያገለግላል። የሚያጋጥሙን ፈተናዎች፣ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንና በመንግሥቱ ውስጥ ይበልጥ ማገልገል እንድንችል፣ እኛን ወደ ብስለት ለመምራት በመለኮት የታቀዱ ናቸው።
የምታልፉባቸው ከባድ ሁኔታዎች እያቀኗችሁና እያሠለጠኗችሁ ይሆን? ከእግዚአብሔር አባታዊ ቅጣት የተነሣ ለክርስቶስ የሚገባ ደቀ መዝሙር ወደ መሆን እየመጣችሁ ይሆን? የእግዚአብሔር አባታዊ ቅጣት ለአማኞች ብቻ ነው፤ ለደቀ መዛሙርት ብቻ ነው። በርግጥ አማኝ ያልሆኑም ሰዎች ቢሆኑ በሕይወት ውጣ ውረድ ብዙ ሊማሩበትና ከዚህም የተነሣ መፈተናቸው የተሻለ ሰው ወደ መሆን ሊያመጣቸው ይችላል። የሕይወት ውጣ ውረድ ግን አይቀድሳቸውም። በመከራውም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን እየተሠሩበት አይደለም። የእግዚአብሔር ቅጣት ግን ልጆቹን የሚቀድስ ነው። ቅጣቱ ፍቅርን በተግባር የሚገልጥ ነው፤ ምክንያቱም የሚወደን፣ በማቅበጥና ሁሉንም በመስጠት ሳይሆን በማቅናት ነው። ደቀ መዛሙርት እያደረገን ነው።
ምናልባትም ከባባድ ሁኔታዎች ሊሆኑ ይችላሉ ቆም እንድትሉና ድምፁን እንድትሰሙ ያደረጓችሁ፤ የእግዚአብሔር የቅጣት ድምፅ ጆሮአችሁ ውስጥ ካለ፣ ጠቢብና ታዛዥ የምትሆኑት አለማመንን ስትሰናበቱት፣ ከኀጢአት ጋር ያላችሁን ትስስር ስትበጥሱና ያልተገቡ ልማዶችን፣ አመለካከቶችን፣ ቅራኔዎችን፣ ጥያቄዎችን ብሎም ከመጠን ያለፈ ራስ ተኰር ሐዘናችሁን ወደ ኋላ ላታዩ ቈርጣችሁ ስትተዉአቸው ብቻ ነው። ይህን በማድረግ፣ “ጌታ ሆይ፣ የአንተ ፈቃድ እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን” ብላችሁ መጸለይን እየተማራችሁ በእግዚአብሔር እመኑ።
ጄ. ማርክ ቢች