ብዙ የወንጌላዊያን አማኞች፣ የእምነት አንቀጾችንና መግለጫዎችን (creeds and confessions) በደመ ነፍስ ይጠራጠራሉ፡፡ እነዚህ የእምነት አንቀጾችና መግለጫዎች፣ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የክርስትናን እምነት በዐጭርና በሚገባ መልኩ ለመግለጽ፣ ለዘመናት የተጠቀሙባቸው በአግባብ የተቀመሩ ቃላት ናቸው። ለእንደነዚህ ዐይነት ሰዎች፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ ሥልጣናዊ የእምነት መግለጫዎች የሚለው ሐሳብ በራሱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልዩ መገለጥ፣ እርሱን ለማወቅ በቂ የሆነ ብቸኛ መሠረትና በሃይማኖት ጒዳዮች ሁሉ የበላይ ባለ ሥልጣን ነው ከሚለው የእምነታቸው መሠረት ጋራ የሚጋጭ ይመስላቸዋል።
በርግጥ፣ የእምነት አንቀጾችና መግለጫዎች፣ ርቱዕ(orthodox) ፕሮቴስታንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምልከታን በሚያዳክም መንገድ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። የሮማ ካቶሊክ ሆነች የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ ለቤተ ክርስቲያናቸው ተቋማዊ መግለጫ በጣም ትልቅ ሥልጣን ስለሚሰጡ፣ የቤተ ክርስቲያን መግለጫዎች ከቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት ጋራ ከመጣጣም ይልቅ፣ ቤተ ክርስቲያን ያጸደቀችውን ሥልጣን የያዙ ሊመስሉ ይችላሉ። እንዲህ ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቅን ማንኛውም ነገር፣ ወንጌላውያን ለማስወገድ መፈለጋቸው ትክክል ነው። ሆኖም ግን፣ የእምነት አንቀጾችና መግለጫዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በግለ ሰብ የአማኞች ሕይወት ውስጥ ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ እሞግታለሁ።
በመጀመሪያ፣ የእምነት አንቀጽ የሌላቸው ክርስቲያኖች በፍጹም የሉም። “የእምነት አንቀጼ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው” ብሎ መናገሩ በራሱ፣ አንድ የእምነት አንቀጽ ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ፣ እንዲህ ዐይነቱን አገላለጽ በየትኛውም ቦታ አልተጠቀመም። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የተቀረጸ ቃል ነው። በርግጥ ሁለት ዐይነት ክርስቲያኖች ብቻ አሉ፤ እነርሱም፣ የእምነት አንቀጽ እንዳላቸው ሐቀኞች ሆነው የሚያምኑ እና የእምነት አንቀጽ ቢኖራቸውም እንደሌላቸው የሚክዱ ናቸው። ማንኛውንም ክርስቲያን ስለሚያምነው ነገር ጠይቁት፤ በትንሹም እንኳ ዐሳቢ ከሆነ፣ በቀላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አይደረድርላችሁም፤ ይልቁንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው ብሎ የሚያስበውን ማጠቃለያ፣ ይብዛም ይነስም፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ በሆነ የቃላት አቀማመጥ ይገልጽላችኋል። ሁሉም ክርስቲያኖች፣ የተቀመሩ ቃላቶች ማለትም፣ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በዐጭሩ ለመግለጽ የሚያስችሏቸው የእምነት አንቀጾች አሏቸው። እናም ማንም ሰው የእምነት አንቀጾችንና መግለጫዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥገኛ እንዳልሆኑ አድርጎ ማየት የለበትም፤ እነርሱ የተዘጋጁት በረቀቀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሐቲት ዐውድ ውስጥ ሲሆን፣ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እና አማካይነት በሰጠው ልዩ መገለጥ ላይ በዐላማ የተመሠረቱ ናቸው።
ይህን እውነታ ከተመለከትን፣ ሁለተኛው ነጥብ የሚከተለው ነው፤ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለዘመናት በቤተ ክርስቲያን ተፈትነውና ተረጋግጠው የመጡ የእምነት አንቀጽ ሲኖሯቸው፣ ሌሎች ደግሞ በሰባኪያቸው የተሠራ ወይም ራሳቸው ያዘጋጁዋቸውን ይጠቀማሉ። አሁን፣ የኋለኞቹ ከቀድሞዎቹ ያነሱ ናቸው ለማለት የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም፤ ሆኖም ግን፣ አዲስ ነገር መፍጠር አያስፈልግም በሚለው መርሕ ላይ በመመሥረት፣ የክርስትናን እምነት ገጽታዎች በመግለጽና ከቦታ ወደ ቦታ እንዲሁም ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ በመቶዎች ለሚቈጠሩ ዓመታት ጥሩ ሥራ የሠሩትን እነዚያን የነጠሩ ጤናማ ቃላቶችን ችላ ማለቱ፣ በርግጥም በጎ ምግባር አይደለም። ለምሳሌ፣ የኒቂያን የእምነት መግለጫ ላለመቀበል ከፈለጋችሁ፣ ይህን ለማድረግ ነጻነት አላችሁ፤ ነገር ግን ቢያንስ በሚቀጥሉት 1,500 ዓመታት ውስጥ ለብዙ ሰዎች በትክክል ሊያገለግል በሚችል ቀመር ለመተካት መሞከር አለባችሁ። ይህን ግን ማድረግ ካልቻላችሁ፣ ከመቃወም ይልቅ ምናልባትም ትሕትናና አመስጋኝነት ለጥንታዊው የእምነት መግለጫ ተገቢው ምላሽ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሦስተኛው፣ የቤተ ክርስቲያን የእምነት አንቀጾችና መግለጫዎች፣ ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጋራ የሚያያይዙንን ነጥቦች ይሰጡናል። ከላይ እንደ ጠቀስሁት፣ በየሰንበቱ ክርስትናን እንደ አዲስ መፍጠር አያስፈልግም፤ እናም ጸረ ታሪክ በሆነውና ወደ ፊት ላይ ብቻ ባተኰረው የእኛ ዘመን፣ እንደ ክርስቲያኖች ከዚህ ቀደም ከነበሩት ብዙ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋራ ሆን ብለን ራሳችንን አንድ ከማድረግ በበለጠ የተለየ እንቅስቃሴ ምን ሊኖር ይችላል? በተጨማሪም፣ ፕሮቴስታንቶች፣ እያንዳንዱ አማኝ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ መብት እንዳለውና በክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር በቀጥታ መቅረብ እንደሚችል በማመናቸው ምክንያት ተገቢ በሆነ መንገድ ቢኰሩም፣ ክርስትና በመጀመሪያ ደረጃ የማኅበር ሃይማኖት መሆኑን አሁንም ልንገነዘብ ይገባል። እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ለመሥራት የተጠቀማት መንገድ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የግለ ሰብ ክርስቲያኖች አበርክቶት ታላቅ ቢሆንም፣ እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በአጠቃላዩ ቤተ ክርስቲያን ውስጥና አማካይነት ከሚሠራው ታላቅ ሥራ ጋራ ሲነጻጸሩ ምንም ናቸው። ይህ ደግሞ እንደ ማንኛውም ሌላ መስክ፣ ለነገረ መለኮትም እውነት ነው። በየዘመናቱ የነበሩ የግለ ሰብ አስተማሪዎችና የሥነ መለኮት ምሁራን ግንዛቤዎች ጥልቅ ቢሆኑም፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በታላላቅ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች ላይ የተሰበሰቡትን የጻድቃንን የጋራ ጥበብ የሚስተካከለው የለም።
ይህም ወደ አራተኛው ነጥቤ ያመራኛል፤ እርሱም፣ የእምነት አንቀጾችና መግለጫዎች በአጠቃላይ፣ በጒልሕና አስፈላጊ ነገር ላይ ያተኲራሉ። እንደ ሐዋርያትና ኒቂያ ያሉ ቀደምት የእምነት መግለጫዎች በጣም ዐጭር ሲሆኑ፣ ፍጹም አስፈላጊ ስለ ሆኑ ነገሮች ይናገራሉ። ሆኖም፣ ይህ እንደ ሉተራኑ የአውግስበርግ መግለጫ ወይም እንደ ዌስትሚኒስተር የሃይማኖት መግለጫ ባሉ ይበልጥ ዝርዝር በሆኑት የእምነት አንቀጾች ላይም እውነት ነው። በርግጥ፣ እነዚህ የተለያዩ ሰነዶች የያዟቸውን የአስተምህሮ ነጥቦች ስትመለከቱ፣ ማዕከላዊና ጒልሕ ነገር ካልተካደ በቀር ምን ሊተ’ው እንደሚችል መገመት ያዳግታል። ብዙ ነገሮችን የሚዘረዝሩ የእምነት አንቀጾች ከመሆን ይልቅ፣ የጥቂት አስፈላጊ ነገሮች ማጠቃለያ ናቸው። እንዲህ በመሆናቸውም ልዩ ጥቅም አላቸው።
ወንጌላውያን ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሣ፣ ታላላቅ የእምነት አንቀጾችንና መግለጫዎችን ሊወድዱ ይገባቸዋል። ሆኖም ግን እነርሱን መከተል ያለብን፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጒም እንድንገነዘብ እስከረዱን ድረስ ብቻ ነው፤
ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን እምነቷን ከዘመን ወደ ዘመን በጥንቃቄ ያስተላለፈችበትን ዋነኛ መንገድ መካድ በርግጥም ሞኝነትና ግትርነት ነው።