የሕማማቱ ቅዳሜ ማታ
“ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ ሥጋውንም አውርዶ በበፍታው ከከፈነው በኋላ፣ ከዐለት በተወቀረ መቃብር አኖረው፤ የመቃብሩንም ደጃፍ በድንጋይ ገጠመው።” (ማርቆስ 15፥46)
ሁላችንም ኢየሱስ እንደ ሞተ እናውቃለን። “ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ፤ ይህንም ብሎ ሞተ” (ሉቃስ 23፥46)። ነገር ግን ከሞተ በኋላ ምን ሆነ? ሥጋው በዮሴፍ መቃብር ውስጥ እንዳረፈ እናውቃለን፤ ነገር ግን ስለ ሰብአዊ ነፍሱስ ምን ማለት ይቻላል?
በዚህ ጥያቄ ላይ ማሰላሰል መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞትና ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ለሚያስተምረው ትምህርት ብርሃን የሚሰጥ ነው። ከዚህም በላይ፣ ሞትንም ያለ ፍርሀት እንድንጋፈጠው ያበረታታናል።
ሞት ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሞት በትክክል ምንድን ነው? ሞት መለያየት ነው፤ አንድ መሆን የነበረባቸው ነገሮች መነጣጠል ነው። በመሠረቱ ከእግዚአብሔር መለየት ነው። ጳውሎስ በኤፌሶን 2፥1 ላይ ይህንኑ ይጠቊማል፤ “እናንተም በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ።” በኀጢአት መመላለስ ማለት ሙት መሆን፣ ለጨለማ ኀይላት ባሪያ መሆን፣ ከእግዚአብሔር መለየት፣ የቊጣው ልጆች መሆን ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ መለያየት፣ መራራቅ፣ ጠላትነት፣ ከሕያው እግዚአብሔር ሕይወትና ተስፋ መገለል ነው። በዚህ እንድምታው፣ ሁላችንም በተፈጥሯችን ሙታን ሆነን እንወለዳለን፤ ኢየሱስም በመስቀል ላይ መከራ ሲቀበል የታገሠው ይህንኑ ሞት ነው።
ነገር ግን ሞት ከእግዚአብሔር መለየት ብቻ አይደለም። ሞት የነፍስን ከሥጋ መለየትንም ያመለክታል። እግዚአብሔር የሰውን ልጆች ሥጋ ያላቸው ነፍሳትና ነፍስ ያላቸው ሥጋዎች አድርጎ ፈጥሯቸዋል። ሞት ደግሞ ይህን ኅብረት ይለያየዋል። ነገር ግን እነዚህ ሁለት ነገሮች ከተለያዩ በኋላ ምን ይሆናሉ? መዝሙር 16፥10 መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት እንድንመለከት መስኮት ይከፍትልናል።
“በሲኦል አትተወኝምና፤ በአንተ የታመነውም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም።”
ይህ ክፍል ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በፊት አንድ የሰው ልጅ ሲሞት ይፈጸም ወደ ነበረው መደበኛ ሁኔታ ይመራናል። ነፍስ በ “ሲኦል” ትተዋለች፣ ሥጋ ደግሞ መበስበስን ያያል ወይም ይፈራርሳል።
በሐዋርያት ሥራ 2፥29-31፣ ጴጥሮስ ይህን መዝሙር ዳዊት ሲጽፍ የክርስቶስን ትንሣኤ አስቀድሞ እንዳየ ይነግረናል፤ “ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ።” ጴጥሮስ ሁለተኛውን መስመር የኢየሱስን ሥጋ ወይም አካል እንደሚያመለክት አድርጎ እንዳነበበው አስተውሉ። ስለዚህ ከኢየሱስ በፊት፣ በሞት ጊዜ ነፍሳት በተለምዶ ወደ ሲኦል ይወርዱ ነበር፤ ሥጋ ደግሞ ይበሰብሳል። ሁላችንም የኋለኛውን በሚገባ እናውቃለን፣ የመጀመሪያው ግን በጣም ግልጽ አይደለም። ፈጣን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ጴጥሮስ በመዝሙር 16 ላይ ያለው የዳዊት ትንቢት መልካም ዜና ነው ብሎ ያሰበበትን ምክንያት ያሳየናል።
ሲኦል ምንድን ነው?
በብሉይ ኪዳን ሲኦል የሙታን ነፍስ ስፍራ ነው፤ ይህም የጻድቃን ( እንደ ያዕቆብ ዘፍጥረት 37፥35፣ 1 ሳሙኤል 28፥13-14)ና የክፉዎችም (መዝሙር 31፥17) ጭምር ስፍራ ነው። በአዲስ ኪዳን ሲኦል የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ሄዲስ ተብሎ ተተርጕሟል። በብሉይና በአዲስ ኪዳን ያለው የሲኦል ገለጻ ከግሪኩ አፈ ታሪክ ሄዲስ ጋራ የተወሰነ መመሳሰል አለው። ከምድር በታች ነው (ዘኍልቍ 16፥30-33)። ደግሞም በሮች (ኢሳይያስ 38፥10)ና መወርወሪያዎች ያሉት ከተማን ይመስላል (ኢዮብ 17፥16)። የሰዎች ነፍሳት የሚኖሩበት የጨለማ ምድር ነው (ኢሳይያስ 14፥9፤ 26፥14)። አንዳች ሥራ የማይሠራበትና ጥበብ የሌለበት የመረሳት ምድር ነው (መዝሙር 88፥12፤ መክብብ 9፥10)። ከሁሉም በላይ ጕልህ የሆነው፣ ሲኦል ማንም እግዚአብሔርን የማያመሰግንበት ስፍራ መሆኑ ነው (መዝሙር 6፥5፤ 88፥10-11፤ 115፥17፤ ኢሳይያስ 38፥18)።
በአዲስ ኪዳን ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ከሁሉ የሰፋው ገለጻ የሚገኘው በሉቃስ 16፥19-31 ላይ ነው። እዚያ ላይ እንደምንማረው፣ ልክ እንደ ግሪኩ አፈ ታሪክ ሄዲስ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ሲኦል ሁለት ክፍሎች አሉት፤ ትክክለኛው ሄዲስ ባለ ጠጋው ሰው የተላከበት (ሉቃስ 16፥23) እና “የአብርሃም ዕቅፍ” ማለትም መላእክት አልዓዛርን የወሰዱበት ስፍራ (ሉቃስ 16፥22) ነው። እንዲሁም ሄዲስ፣ በውስጡ የታሰሩት ነፍሳት በእሳት የሚሠቃዩበት የሥቃይ ስፍራ ነው። በሌላ በኩል የአብርሃም ዕቅፍ ከሄዲስ ጋራ በቅርብ ርቀት ላይ ቢሆንም፣ በታላቅ ገደል የተለየ ነው (ሉቃስ 16፥26)። ደግሞም ልክ እንደ ግሪኩ ኤሊሲየም የምቾትና የዕረፍት ስፍራ ነው።
ብዙ ምሥጢር ቢኖርም፣ ምስሉ ግልጽ መሆን ይጀምራል። የሙታን ነፍሳት ሁሉም ወደ ሲኦል ወይም ሄዲስ ይወርዳሉ። ሲኦል ሁለት የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ነው፤ አንዱ ለጻድቃን ሌላው ደግሞ ለክፉዎች። ከክርስቶስ በፊት የሞቱት ጻድቃን ከአብርሃም ጋራ በሲኦል ይኖሩ ነበር። እናም ከሕያዋን ምድር ቢቈረጡም እንዲሁም በምድር ላይ ካለው የእግዚአብሔር አምልኮ ቢለዩም እንደ ክፉዎቹ ግን አይሠቃዩም ነበር።
ኢየሱስ ሲሞት ወዴት ሄደ?
ታዲያ ይህ፣ ኢየሱስ በሕማማት ቅዳሜ የት እንደ ነበረ ምን ይጠቊመናል? በሉቃስ ወንጌል 23፥43 ላይ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ለነበረው ወንበዴ ከተናገረው ቃል በመነሣት፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ነፍሱ በአብ ፊት ለመሆን ወደ ሰማይ መሄዷን ያምናሉ። ነገር ግን ሉቃስ 23፥43 ኢየሱስ በእግዚአብሔር ፊት እንደሚሆን አይናገርም። የሚናገረው፣ ከወንበዴው ጋራ እንደሚሆን ነው፤ “ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።” ደግሞም፣ በብሉይ ኪዳንና በሉቃስ 16 መሠረት፣ አሁን ንስሓ የገባው ወንበዴ ኢየሱስ “ገነት” ብሎ በጠራው፣ የጻድቃን ሙታን የምቾትና የዕረፍት ስፍራ በሆነው በአብርሃም ዕቅፍ የመገኘቱ ዕድል ሰፊ ነው።
ስለዚህ ለኀጢአታችን ከሞተ በኋላ፣ ኢየሱስ ወደ ሄዲስ፣ ወደ ሞት ከተማ ይጓዛል። በሮቿንም ከመንጠልጠያቸው ይሰብራል። አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን፣ መጥምቁ ዮሐንስንና ሌሎችንም የብሉይ ኪዳን ታማኞችን ነጻ ያወጣቸዋል። ከሲኦልም ኀይል ይቤዣቸዋል (መዝሙር 49፥15፤ 86፥13፤ 89፥48)። መንፈሳቸው፣ ከአዲሱ ኪዳን ቅዱሳን ጋራ ፍጹም እንዲሆን የተሰጠውን ተስፋ ሳያገኙ በዚያ ለረጅም ጊዜ ጠብቀው ነበር (ዕብራውያን 11፥39-40፤ 12፥23)።
ከትንሣኤው በኋላ፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የተቤዣቸውን ሙታንንም ከርሱ ጋራ ወሰዳቸው። ስለዚህ አሁን ገነት ከሥቃይ ስፍራ አጠገብ በታች አትሆንም። እግዚአብሔር በሚኖርበት በሦስተኛው ሰማይ፣ ከሁሉ በላይ በሆነው ሰማይ ውስጥ ትገኛለች (2 ቆሮንቶስ 12፥2-4)።
አሁን በቤተ ክርስቲያን ዘመን፣ ጻድቃን ሲሞቱ መላእክት ተሸክመው ወደ አብርሃም ዕቅፍ ብቻ አይወስዷቸውም። ከሁሉ ይልቅ እጅግ ከሚበልጠው ከክርስቶስ ጋራ ለመሆን ይሄዳሉ (ፊልጵስዩስ 1፥23)። ክፉዎች ግን፣ የመጨረሻው ፍርድ እስኪደርስ ድረስ በሄዲስ ውስጥ በሥቃይ ይቈያሉ፤ በዚያን ጊዜ ሄዲስ በርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን አሳልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም እንደ ሥራቸው ይፈረድባቸዋል፤ ከዚያም ሞትና ሄዲስ ወደ ገሃነም፣ ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ (ራእይ 20፥13-15)።
ለእኛ የሆነ መልካም ዜና
ይህ ለሕማማት ሳምንት ምን ትርጕም አለው? የክርስቶስ ወደ ሄዲስ መጓዝ እርሱ በርግጥ በሁሉ ነገር እንደ እኛ መሆኑን ያሳያል። ስለ እኛ የእግዚአብሔርን ቊጣ መሸከም ብቻ ሳይሆን፣ ሞትን፣ የነፍሱን ከሥጋው መለየትን ታግሦአል። ሥጋው በዮሴፍ መቃብር ውስጥ ነበር (ሉቃስ 23፥50-53)፤ ነፍሱ ደግሞ፣ በምድር ልብ ውስጥ በሲኦል ሦስት ቀን ቈይታለች (ማቴዎስ 12፥40)።
ነገር ግን መዝሙር 16 በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ኢየሱስ እንደ እኛ ብቻ ሳይሆን ከእኛም የተለየ ነው። የኢየሱስ ሥጋ እንደ እኛ ተቀበረ፣ ነገር ግን አልበሰበሰም። የኢየሱስ ነፍስ እንደ ብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ወደ ሄዲስ ወረደች፤ ነገር ግን በዚያ አልተተወችም። እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው። የትንሣኤው መከር በኩራት እንዲሆን ነፍሱን አሁን ከከበረው ሥጋው ጋራ አንድ አደረጋት።
ይህም ለእኛ መልካም ዜና ነው። ምክንያቱም በክርስቶስ ያሉ አሁን ማንም እግዚአብሔርን የማያመሰግንበትን የመረሳትን ምድር ዐልፈው ይሄዳሉ። ከዚህ ይልቅ ስንሞት፣ ስለ እኛና ስለ ድነታችን ለታረደው በግ ምስጋናን ከሚዘምሩት መላእክትና ከቀድሞ ቅዱሳን ጋራ እንቀላቀላለን።
ጌታ ተነሥቶአል። ጌታ በርግጥ ተነሥቶአል።