የትንሣኤ እሑድ ጠዋት
ለፋሲካ በዓል የሚሆን ዶሮ ፍለጋ ገበያ ለገበያ እንደሚበተኑ ሸማቾች፣ እኔና እናንተም ፍለጋ ላይ ነን።
ሁላችንም እንፈልጋለን። የተጠማች ነፍሳችን የሚያብረቀርቁ ደስታዎችንና ጣፋጭ ርካታዎችን በመፈለግ በዚህች ዓለም ጥግና ሥርቻ ሁሉ ትፈትሻለች።
ጥልቅና ዘላቂ ደስታን የሚፈልግ ማንም ሰው፣ ለትንሣኤ ከፍተኛ ትኲረት መስጠት አለበት። ይኸውም በተከፋፈለ ልብ ሳይሆን፣ በክርስቶስ ላይ ባረፈ እውነተኛ፣ ልባዊና የጋለ ትኲረት ሊሆን ይገባዋል። የትንሣኤውን ትርጕም ካጣን፣ በዓለም ላይ ከሁሉ የላቀውን ደስታ እናጣዋለን።
የኢየሱስ ደስታ
ሊሰቀል የተዘጋጀው ክርስቶስ የሞት ጥላ ሲያስጨንቀው፣ ትኲረቱን ወደ ደስታ አዞረ። ስቅለቱ በተፈጸመበት በዚህ የሕማማት ሳምንት ሁሉ፣ ኢየሱስ እንደሚሞት ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ ይነግራቸው ነበር። እነርሱ ግን ይህን ሁሉ ለመረዳት ይቸገሩ ነበር። ዮሐንስ 16፥19-24 ላይ ጭንቀታቸውን በቀጥታ በሚነካ መልኩ መለሰላቸው።
“ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ባወቀ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ፣ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኋችሁ፣ ምን ማለቴ እንደ ሆነ እርስ በርሳችሁ ትጠያየቃላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።”
“ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ተወልዷልና ስለ ደስታዋ ጭንቋን ትረሳለች፤ ለእናንተም እንደዚሁ አሁን የሐዘን ጊዜ ነው፤ ሆኖም እንደ ገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።”
“በዚያ ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ለምኑ ትቀበላላችሁ፤ ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል።”
በትንሣኤው የሚመጣውን ለውጥ ኢየሱስ ሲተነብይ ለመስማት ወደ ሕማማት ሳምንት ወደ ኋላ እንመለሳለን። ደቀ መዛሙርቱ የትንሣኤ እሑድን እንደ እውነተኛ ደስታ ፈንጠዝያ እንዲጠባበቁት ፈልጎ ነበር። ይህ ደስታ ለሚፈልጉ ሁሉ ያለው ትርጕም የሚከተለው ነው።
በደም የተገዛ ደስታ
የዐርብ ስቅለትን ሥቃይ ፊት ለፊት እየተጋፈጠ፣ ኢየሱስ ስለዚህ ደስታ ተናገረ። ክሕደትን ተቀበለ፤ ታልፎ ተሰጠ፤ ድብደባ ደረሰበት፤ የዕንጨት ስብርባሪዎችን፣ ምስማሮችንና ጦሮችን ተጋፈጠ። ነገር ግን ስለ ደስታ ከመናገር ሊያቆም አልቻለም! ወደ ፊት እንዲቀጥል ያደረገው ደስታ ብቻ ነበር። ደስታ በአእምሮው ነበር፤ ደስታ በአንደበቱ ላይ ነበር፤ ደስታም ከመከራው እንዲሸሽ ሳይሆን ወደ መከራው እንዲገባ ይስበው ነበር (ዕብራውያን 12፥2)።
ኢየሱስ ወደ መስቀል የሄደው ለደስታ ነው፤ ደስታን ለመግዛት፣ ደስታን ለመፍጠርና ደስታን ለመስጠት።
ዓለም የእግዚአብሔርን አሠቃቂ ግድያ እያከበረ ሳለ፣ ከዚህ ከሚገነፍለው የዐመፀኞች ጥላቻ ባሕር ውስጥ በደም የተገዛና ሊጠፋ የማይችል ደስታ ወጣ።
የማይከስም ደስታ
የሕይወት ራስ መገደል፣ ይህን ኢየሱስ የተናገረለትን ደስታ ሊያጠፋው ካልቻለ፣ ማንም ሊያጠፋው አይችልም። መቼም ቢሆን አይጠፋም። ከዓለም የሚመጣ ተቃውሞ፣ በወንጌሉ ላይ የሚደረግ ተቃውሞና ክርስቶስን የሚንቅ የባህል ጥላቻ የኢየሱስን የትንሣኤ ደስታ ሊያሸንፉት አይችሉም።
በዚህ ሳምንት እንዳየነው፣ ሊጠፋ የማይችለው የትንሣኤ ደስታ የመጣው፣ ዓለም እስካሁን ካመጣው ከሁሉ ከባሰው ቊስል፣ አሳዛኝ ክሥተትና ክፋት ውስጥ ነው። ይኸውም፣ ከእግዚአብሔር ልጅ ግድያ ውስጥ ነው። ሞት፣ ዲያብሎስ፣ አጋንንትና የተቀናጀው የሰው ልጆች ዐመፅ በአንድነት ተባብረው ይህን ደስታ ሊያደናቅፉት አይችሉም። አሳዳጆች ይህን ደስታ ሊሰርቁት አይችሉም። የትኛውም ኀይል፣ የትኛውም ክሥተት፣ የትኛውም ጠላት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ከመቃብር ፈልቆ የወጣውን የትንሣኤ ደስታ ሊነጥቀው አይችልም።
ዓለማዊ ደስታዎች ከዚህ አንጻር ሲታዩ ጠፊዎች ናቸው። ሕመምና ድኽነት ደስታን ያፈራርሳሉ። እንዲሁም እርጅናና ቀስ በቀስ የሚመጣው ሞት የሕይወትን ዓለማዊ ደስታዎች ሁሉ ያተንናሉ (መክብብ 12፥1-8)። ሞት ከአንዱ በቀር ደስታዎቻችንን ሁሉ ያስወግዳል። አንድ ደስታ ብቻ በሞት ሊከሽፍ አይችልም። ምክንያቱም ይህ ደስታ የተገዛው በደም ስለ ሆነ ነው።
አዲስ የተወለደ ደስታ
የኢየሱስ የትንሣኤ ደስታ ከሞት ጥፍሮች ያመልጣል። ምክንያቱም እርሱ የአዲሱ ፍጥረት ደስታ ነው፤ ከዚህ ከወደቀው ዓለም ክፋት ነጻ የወጣ ደስታ።
ይህም፣ የትንሣኤን በዓል አስደናቂ ያደርገዋል። ጆናታን ኤድዋርድስ በድፍረት እንዳወጀው፣ “የክርስቶስ ትንሣኤ እስካሁን ከተከሠቱት ክሥተቶች ሁሉ እጅግ አስደሳቹ ክሥተት ነው።” ቻርለስ ስፐርጀንም በትክክል እንዲህ ብሏል፤ “ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ያገኘሁትን ደስታ ማንም ሰው ከእኔ ሊወስድ አይችልም።” ትንሣኤ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ዘላለማዊ አድናቆት፣ ክብርና መገረም የሚገባው እጅግ ደስታ የሞላበት መለኮታዊ ክሥተት ነው። ነገር ግን ከአስደናቂ ታሪካዊ ትዕይንትም በላይ ነው።
ኢየሱስ ሥር ነቀል የሆነን ዓለም ዐቀፋዊ ውልደትን ለማስተዋወቅ የተለመደውን የምጥ ምሳሌ ተጠቅሟል። የርሱ ሞት የአዲሱ ፍጥረት ምጥ ነበር፤ ትንሣኤው ደግሞ አዲሱ ፍጥረት ወደ ታሪክ መምጣቱን የሚያበስር ነበር። ኢየሱስ በትንሣኤው አማካይነት አንድ ቀን በሙታን ትንሣኤና በፍጥረት ሁሉ መታደስ የሚደመደመውን፣ ሊቆም የማይችል ተከታታይ ክሥተትን ጀመረ።
ዋናው ነጥብ ይህ ነው። በዚህ የወደቀ ዓለም የረጅም ጊዜ የደስታ ፍለጋ ታሪክ ውስጥ፣ የሰው ልጆች ሁሉ ለዘመናት በርካታና ደስታ ማጣት ውስጥ ዐልፈዋል፤ የክርስቶስ ትንሣኤ ግን የላቀው ደስታ መገኘት ምልክት ነው። በምድር ላይ ደስታ ከዚህ የላቀ መግለጫን አግኝቶ አያውቅም። ዮሐንስ 15፥11 ላይ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ፍጹም ደስታን አቀረበላቸው። ይህ ግብዣ ሊቀርብ የሚችለው በዓለም ታሪክ የመጨረሻ ፍጻሜ ላይ ብቻ ነበር። ይህ ወቅት በትንሣኤ ማለዳ ተበስሯል።
ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከትንሣኤ በኋላ የሚመጣውን ደስታ እንዲጠሙት ይፈልጋል፤ ይህ ደስታ አዲስ ሆኖ የመጣ ደስታ፣ ለረጅም ጊዜ የተጠበቀ ደስታ፣ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከዚህ በፊት ሙሉ በሙሉ ታይቶም ሆነ ተሞክሮ የማያውቅ ደስታ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ እጅግ አስደናቂ የሆነውን የደስታ ክሥተት ያመጣል። ምክንያቱም፣ ዘላለማዊ የሆነና ለዘላለም የማይሸነፍ ደስታን ያቀጣጥላል።
ብሉይ ኪዳን ስለዚህ ደስታ ትንቢት ተናገረ፤ የክርስቶስ ልደት ይህን ደስታ አበሰረ። የሕማማት ሳምንት ይህን ደስታ ያጠፋው መስሎ ነበር። የክርስቶስ ትንሣኤ ግን፣ ከኀይለኛው የዐመፀኞች የጥላቻ ባሕር ውስጥ ለዘላለም የማይጠፋውን የእግዚአብሔር የደስታ ብርሃን እንደ ኦሎምፒክ ችቦ ያበራበት የታሪክ ነጥብ ነው።
በነጻ የሚሰጥ ደስታ
ነገር ግን ይህ ደስታ በዚህ ወሳኝ በሆነ የዓለም ታሪክ ወቅት በገባበት ታላቅነት ልክ፣ ወደ እኛም ይቀርባል። ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከዚህ ደስታ አብዝተው እንዲጠይቁና እንዲፈልጉ አስተማራቸው። ይህ የመሲሓዊው ዘመን ክፍት ግብዣ ነው።
ይህ ደስታ የዮሐንስ ወንጌልን አመክንዮ ትርጕም ይሰጠዋል። ኢየሱስ መሞትና ወደ አብ መሄድ እንዳለበት ተናገረ፣ እናም ደስታውን ለደቀ መዛሙርቱ ይተወዋል። ኢየሱስ ከአብ ጋራ ከሆነ በኋላ፣ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ውስጥ እንዲኖር ላከው (ይህም የአዲሱ ፍጥረት ሌላው የማይሳሳት ምልክት ነው)። ከክርስቶስ ጋራ አንድ የሆኑት ደቀ መዛሙርት፣ አሁን በመንፈስ ቅዱስ በወልድ በኩል ወደ አብ ይጸልያሉ።
የትንሣኤ በዓል ጸሎትን፣ መንፈሳዊነትንና ደስታን በአዲስ መልክ ይቀርጻል። በዚህ አዲስ ፍጥረት መጀመር፣ ደቀ መዛሙርቱ በሁሉም አቅጣጫ መንፈሳዊ ብልጽግናን በእነርሱ ላይ ሊያፈስስ ለሚጓጓው አብ መጸለይ የሚችሉ የማደጎ ልጆች ሆኑ። ይህም ማንም ሊወስደው ወደማይችለው ሙሉና አጥጋቢ ደስታ ይመራቸዋል።
ይህም ለደቀ መዛሙርቱ ታላቅ ዜና ነው።
ለእናንተ የሆነ በቃላት የማይገለጽና ክቡር ደስታ
በዮሐንስ 16፥19-24 ለደቀ መዛሙርቱ ተስፋ የተሰጠው የኢየሱስ ትንሣኤ ደስታ አሁን ለእኔና ለእናንተም ቀርቧል። እኛም “መግለጽ የማይቻልና ክብር የሞላበት” ተመሳሳይ ደስታ ተስፋ ተሰጥቶናል (1 ጴጥሮስ 1፥8)።
እግዚአብሔር በክርስቶስ ይህን የትንሣኤ ደስታ በሕይወታችሁ ውስጥ ማፍሰስ ያስደስተዋል። ይህም ደስታ የሚሞላና ከእናንተ ሊወሰድ የማይችል ደስታ ነው። ታዲያ ምን እናደርጋለን? ቸር የሆነውን አባታችንን አብዝቶ እንዲሰጠን እንጠይቀዋለን!
ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረው የትንሣኤው ደስታ ደርሷል፤ እርሱም እጅግ ግላዊ ነው። ትንሣኤው ዓለም ዐቀፋዊ ክሥተት ነው። ደግሞም ወደ እኛ በመቅረብም በሕይወታችን ያለውን የእግዚአብሔርን ሥራ ያስታውሰናል። “የትንሣኤ ዋና ነጥብ እግዚአብሔር የዚህን ዓለም የልብ ስብራት በማጽዳት ሂደት ውስጥ መሆኑ ነው” (ጆን ፓይፐር)። ስለዚህ፣ “የክርስቶስ ትንሣኤ ለወደፊቱ ብቻ ሳይሆን፤ አሁን ቊስላችሁን ለመቋቋም የሚያስችል ተስፋም ይሰጣችኋል” (ቲም ኬለር)።
እንዲህ ዐይነቱ የሚያድስና የሚያነቃቃ ደስታ ለእኔና ለእናንተ በክርስቶስ ትንሣኤ ተገዝቷል።
በታላቅ ደስታ ደስ ይበላችሁ
የትንሣኤ በዓል ግልጽ ተቃርኖዎችን ያሳያል።
ክርስቶስ አሁንም ሙት ከሆነ፣ ሞት ይነግሣል፤ ደስታዎቻችንም ሁሉ ከንቱ ናቸው። ልናገኝ የምንችለውን ጊዜያዊ ደስታን ማሳደድ ይኖርብናል። ወይም ጳውሎስ እንዳለው፣ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ነገ እንሞታለንና እንብላ፣ እንጠጣም (1 ቆሮንቶስ 15፥32)።
ነገር ግን ሞት ከሞተና ሙታንም ከተነሡ፣ ክርስቶስም ከሙታን ተነሥቶ ከሆነ! ወንድሞችና እኅቶች፣ አሁን በጨለማው ውስጥ ላበራው የማይጠፋና የማያልቅ ዘላለማዊ ደስታ ብርሃን ፈንጠዝያ እናድርግ፤ እናክብር፤ ይህ ብርሃንም ሊጠወልግ፣ ሊዝግ ወይም ሊሰረቅ የማይችልን በክርስቶስ ያለ የደስታ ሕይወት ያቀርብልናል!
ዛሬ፣ በክርስቶስ የትንሣኤ ደስታ ሐሤት አድርጉ፣ በሕይወታችሁ ውስጥ ይበልጥ እንዲያድግ ጸልዩ፤ ለዘላለምም እንደ ውድ ሀብት ያዙት።