በአፍሪካ ባሉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የብልጽግና ወንጌልን ጨምሮ፣ ወንጌሉን በማጣመም የሚደረጉ አስተምህሮዎች ዘልቀው መግባታቸውን መካድ አይቻልም። የብልጽግና ወንጌል ጉዳይን ፍቱን በሆነ መንገድ መመልከት ከመጀመራችን በፊት፣ ይህን የስሕተት ወንጌል ያለ ምንም መከልከል ብዙ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለምን ዘልቆ እንዲገባ እንደፈቀዱለት መጠየቅ አለብን። በረኞቹ እና የማንቂያ ደውል መደወል የነበረባቸው የት ነበሩ? አሁንም እንኳ ከብዙዎቹ ሀገር በቀል አፍሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት በኩል አስደንጋጭ ዝምታ ያለው ለምንድን ነው?
እንደ ማንኛውም ነገር ሁሉ ዛሬ ላይ ያለው የብልጽግና ወንጌል ችግር የሚመነጨው ትናንትና ከነበረው የአስተምህሮተ ቤተ ክርስቲያን ችግር ውስጥ ነው።
ጠቅልሎ ለመናገር ያክል ባለፉት ዓመታት አፍሪካ ውስጥ ወንጌልን ለማድረስ ይደረጉ በነበሩ ጥረቶች፣ ክርስቲያን ነን ብለው የሚሉ ሰዎች ወንጌሉን ከእነዚህ ተደጋጋሚ የማጣመም ሥጋቶች የሚጠብቁበትን እና የሚያስቀጥሉበትን ዘዴዎች አካትተው የመጡ አይመስሉም። ለምሳሌ፦ ያህል የሕይወት ለውጥ አስተምህሮን፣ ትርጉም ያለው የቤተ ክርስቲያን አባልነትን እና የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽን በጥንቃቄ ስለ መረዳት በጣም ትንሽ ትኩረት ነው የተሰጠው። በተመሳሳይም ሚሽነሪዎች እና መጋቢዎች ወንጌል ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጋር፣ ከእያንዳንዱ አባል ከስሕተት አስተማሪ ለመከላከል ካለበት ኀላፊነት ጋር፣ ወይንም ከአንድ በላይ መሪዎች ከማስፈለጉ እውነት ጋር ምን እንደሚያገናኘው አልጠየቁም። ይልቁንም ወንጌሉ ምንም አይሆንም ተብሎ ያለ ጥርጣሬ ነበር የተያዘው፤ እናም አሁን የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት እየተጎዱ ነው። ችግሩን የተረዱ ደግሞም በተሻሉና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ መፍትሔዎች የተካኑ የወንጌል ተልዕኮ አገልጋዮች እና አብያተ ክርስቲያናት አሁንም በጣም ያስፈልጋሉ።
“ክርስቲያኖች” በሙሉ የታሉ?
በወንጌል በተደረሱ የአፍሪካ አከባቢዎች እየተጉ ያሉ ሚሽነሪዎች የሚያጋጥሟቸው ከወንጌል በተቃራኒ የተከተቡ ማኅበረ ሰቦች ናቸው። አብዛኞቹ ከተሞች እምብዛም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ፍሬ የሆኑ ነገሮችን ባያሳዩም፣ ምንም እንኳ ንስሓ የገባና በክርስቶስ ያመነ ሰው ምልክት ባያሳዩም፣ በተጠመቁና በተለያዩ የሃይማኖት ወገን በሆኑ ሆኖም ግን የቤተ ክርስቲያን አባል ናችሁ ተብለው ክርስትያን መሆናቸው በተረጋገጠላቸው ሰዎች የተሞሉ ናቸው። ለምሳሌ፣ እንደ እኔ ያሉ አብዛኛዎቹ ኬንያውያን ራሳቸውን ክርስትያን እንደ ሆኑ ቢቆጥሩም፣ ቤተ ክርስቲያን ግን የሚሄዱት ከስንት አንዴ ነው። አንድ ጊዜ “ክርስቲያን” ስለ ሆኑ ወንጌሉና ቤተ ክርስቲያን እንደማያስፈልጋቸው ያስባሉ።
ከላይ ከተጠቀሱት ቡድኖች ይልቅ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የሚያዘወትሩት ሰዎች የሚካፈሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ወንጌሉ በግልጽ የማይነገርባቸው ቦታዎች ናቸው። ምንም እንኳ በሃይማኖታቸው የሚቀጣጠሉ ቢሆኑም አብዛኛዎቹ ወንጌሉን መሠረታዊ በሆነ ደረጃ እንኳ ለመግለጽ ይቸገራሉ። ከብዙ ዐሥርት ዓመታት በፊት የተቋቋሙ እውነተኛ የወንጌል አገልግሎቶች፣ በአብዛኛው ለብልጽግና ወንጌል አስተምህሮ ዐይነቶች እጃቸውን ወደ ሰጡ፣ በሥነ መለኮት ወደ ደከሙ አብያተ ክርስቲያናት ተቀይረዋል።
የሐሰት ወንጌላት በትንሽ ብቻ ወይም ያለ ምንም ተግዳሮት አፍሪካ ውስጥ ጥፋት እያደረሱ መሆናቸው ምንም አይገርምም። አብያተ ክርስቲያናት ወንጌሉን በማያውቁ ወይም በአብዛኛው ለወንጌል እንደማይገባ በሚኖሩ ሰዎች መሞላታቸው ሳይቀር፣ እውነቱን በማስመሰል ስለሚያልፉት ሐሰተኞች ማኅበረ ሰባቸውን ሊያስጠነቅቁ ይቅርና ራሳቸውን ጭምር ከወንጌል አስተምህሮ እና ከወንጌል አኗኗር ጥመቶች መጠበቅ አይችሉም።
እግዚአብሔር ታማኝ አምላክ እንደ ሆነ እና በእውነትም በእነዚህ ቦታዎች ቅሬታዎች እንዳሉት እናውቃለን። እግዚአብሔር እንዲህ ዐይነት ሰዎችን በብዛት እንዲያስነሣ እና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ገጽታ በእነርሱ እንዲሣል፣ እንዲሁም የብልጽግና ወንጌል እዚሁ እንዲሞት የዘወትር ጸሎታችን እና ተስፋችን ነው። ነገር ግን አሁን ላይ ችግሩ አለ። ስለዚህ በምን ዐይነት መንገድ የወንጌል ተልዕኮዎችን ብናደርግ ነው አሁን ላለው እና ለሚመጡት ትውልዶች ወንጌሉን መጠበቅ የምንችለው?
ነገረ መለኮታዊ ትምህርት በቂ ይሆን?
በአሁን ሰዓት አብዛኛው የወንጌል ተልዕኮ ተግባሮች ትልቁ አትኩሮታቸውን ነገረ መለኮታዊ ትምህርት ላይ እያደረጉ ነው። በአብዛኛው በከተማዎች ውስጥ ያሉት መጋቢዎች መደበኛ የሆነ ነገረ መለኮታዊ ሥልጠና የላቸውም። ጠቅለል አድርጎ ለመናገር ያክል የድሮ የወንጌል ተልዕኮ ተግባሮች ውስጥ “ሙሉ ኀላፊነት ተጥሎባቸው” የሚሄዱትን መጋቢዎች ዐቅም መገንባት ላይ ትኩረት አይጣልም ነበር። ይህ ቀጣይነት ያለው የደቀ መዝሙርነት እጦት እየጨመረ ለመጣ የነገረ መለኮት ድክመት፣ ተያይዞም ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ያሉበት ማኅበረ ሰብ በሰዓቱ ለተበከለበት ጥፋት ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ለዚህ ምላሽ እንዲሆንም በአህጉሪቷ የነገረ መለኮት ተቋማት እየተቋቋሙ ነው። ያለፉ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎቶች ብዙዎችን ወደ ጌታ ለማምጣት ቢጠቅሙም፣ ወንጌሉን ወደ ቀጣዩ ትውልድ ጠብቆ ለማስተላለፍ ግን አስተማማኝ ሆነው አልተገኙም፡፡ ስለዚህም ነገሮችን ለማስተካከል ይቻል ዘንድ ብዙ ስብሰባዎች እና ትምህርታዊ ጉባኤዎች እየተደረጉ ነው። ይህ መልካም እና አስፈላጊ ተግባር ነው። መጋቢዎችን ለማሠልጠን በአዲስ መልክ እየተካሄዱ ያሉ ተግባሮች ቢኖሩም አሁንም አህጉራችን ሥልጠናዎቹን ለመስጠት በቂ የሆኑ የበቁ ሰዎች ደግሞም ተግባሩን ለመጨረስ የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮች የሏትም።
ተጨማሪ ተግዳሮቶች
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ እነዚህን የሚበረታቱ የወንጌል ተልዕኮ ተግባር የሚፈታተኑ ተጨማሪ ተግዳሮቶች አሉ። አብዛኛው ቤተ ክርስቲያንን የመትከል እና መጋቢዎችን የማሠልጠን ተግባር በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደረግ ትኩረት ያጥራቸዋል። ስልታዊ ነገረ መለኮት እና ሌሎች የክርስትና አስተምህሮ ቅርንጫፎች እንደሚገባቸው ልክ የበለጠ ዋጋ ሲሰጣቸው፣ አስተምህሮተ ቤተ ክርስቲያን ግን በሚያሳዝን ሁኔታ በግልጽ ትኩረት ባለ መሰጠቱ ምክንያት በትክክል ሳይስተዋል ይቀራል። ይህ እውነታ በዋነኝነት የሚያሳዝንበት ምክንያት፣ እግዚአብሔር ወንጌል እንዲታይበት እና ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲቀጥልበት ያለመበት ዋነኛው መንገድ ትምህርታዊ ጉባኤዎች፣ ስብሰባዎች ወይም የሥነ መለኮት ማሠልጠኛ ተቋሞች ሳይሆኑ፣ እነዚህ ትኩረት የተነፈጋቸው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት መሆናቸው ነው።
ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው በአስተምህሮተ ቤተ ክርስቲያን በታመቀው ደብዳቤ ላይ፣ “ወደ አንተ ቶሎ ለመምጣት ተስፋ ባደርግም ይህን ትእዛዝ እጽፍልሃለሁ፤ ይህንም የምጽፍልህ ብዘገይ እንኳ ሰዎች በእግዚአብሔር ቤት እንዴት መኖር እንዳለባቸው እንድታውቅ ነው፤ ቤቱም የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ ይኸውም የእውነት ዐምድና መሠረት ነው” ብሎ ጽፏል (1 ጢሞቴዎስ 3፥14-15)። ቤተ ክርስቲያን በጋራ ያላትን ሕይወት የምታካሂድበት መንገድ ሙሉ ለሙሉ እውነትን እንዳይደፈርስ ከምትጠብቅበት መንገድ ጋር ይያያዛል።
በአፍሪካ ውስጥ ያለው የአሁኑ ትውልድ፣ ሊያጠምቋቸው ፈቃደኛ የሆኑትን ያክል ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት ሊያግዷቸው ፈቃደኛ በሚሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ቢገለገሉ ይጠቀሙ ነበር። የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ብለው ነገር ግን ለወንጌል የማይገባ ኑሮ በሚኖሩ ሰዎች መሞላታቸው፣ ለአሁኑም ለሚመጣውም ትውልድ የወንጌሉን እውነት ያጣምማል። እግዚአብሔር እውነትን ጠብቆ ማስተላለፍ የሚሻው፣ በነገረ መለኮት ርቱዕ በሆኑ መጻሕፍት በኩል አይደለም። በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በኩል ያንን እዉነትን በጋራ በመኖር የሚያንጸባርቁ ሕይወቶችን ይፈልጋል።
ታማኝ አብያተ ክርስቲያናት ያስፈልጉናል
አብያተ ክርስቲያናት ነገሮችን ዝም ብሎ ማሳለፉ በእነርሱ መብቃት እንዳለበት እና በወንጌል ተልዕኮ ውስጥ ዝም ብለው ከዳር ቆመው የሚያዩ ሰዎች ሳይሆኑ የወንጌሉ ጠባቂዎች እንደ ሆኑ ብናስተምራቸው፣ ምናልባት ኑፋቄ ሲያስተምር የሚያገኙትን ቀጣዩን መጋቢ ሊያባርሩት ይችሉ ይሆናል። አብያተ ክርስትያናትን የሕይወት ለውጥ ጸሎት ከመጸለይ እንደሚያልፍ መገንዘብ አለባቸው፤ ሰዎች ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸው ለመቀበል ጉባኤው ፊት እንዲመጡ፣ ወይም እጃቸውን እንዲያነሡ መጠየቅ ብናቆም፣ በንግግር በተካነው እና የሚያንጸባርቅ ሱፍ በለበሰው ሐሰተኛ መጋቢ ሳይሆን፣ መደነቅን በሚጭረው በእግዚአብሔር ጸጋ የተማረኩ ትናንሽ አብያተ ክርስቲያናት ሊኖሩን ይችላሉ። ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ክብር ሲሉ ወንጌሉን ተግተው የሚጠብቁ አብያተ ክርስቲያናት ሊኖሩን ይችላሉ።
የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ችግሮች መሠረት የብልጽግና ወንጌል ወረርሺኝ እና የውሸት ክርስቲያኖች አይደሉም። እነዚህ የመሠረታዊው ችግር ምልክቶች ብቻ ናቸው። ዛሬ ላይ የብልጽግና ወንጌል ሊሆን ይችላል፤ ነገ ላይ ደግሞ ኖስቲሲዝም። እግዚአብሔር አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንድትገነባ የሚፈልገው የተለያዩ የስሕተት ነፋሶችን መቋቋም በምትችልበት ሁኔታ ነው። ለእኛም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ ወንጌሉን ተከላክሎ ለመጠበቅ፣ የወንጌል ተልዕኮ ተግባርን ጤነኛ አብያተ ክርስቲያናትን በመገንባት ላይ ማተኮሩ ጠቃሚ ነው።
በኬን ምቡጓ