የጌታ ራት እንዴት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ይመሠርታል?

እጮኛሞች ተጋብተዋል የምንለው መቼ ነው? “አዎን ቃል እገባለሁ” ሲሉ ነው? ወይስ የሚያጋባቸው አገልጋይ፣ ባልና ሚስት ብሎ ሲጠራቸው ነው? ወይስ የጋብቻ ሥነ ሥርዐቱ ሲጠናቀቅ ነው?

እነዚህ እያንዳንዳቸው ነገሮች፣ ለጋብቻ ምሥረታ አስፈላጊ ሚና ቢኖራቸውም፣ እርስ በርስ ግን የተያያዙ ናቸው። የጋብቻ ሥነ ሥርዐት ካልተጠናቀቀ፣ ሙሉ ለሙሉ ተጋብተዋል ለማለት የምንቸገረው ለዚህ ነው። ይህ ደግሞ ሕጋዊ መሠረት አለው። የዚህ ግንኙነት መቋረጥ ፍቺ ብቻ ሳይሆን የሕጋዊ ውል መቋረጥ ነው።

እነዚህ ነገሮች ሁሉ፣ እንዴት ከጌታ ራት ጋር ይገናኛሉ? ብዙ ክርስቲያኖች፣ የጌታን ራት እንደ ግል የጥሞና ጊዜ አድርገው እንደሚቆጥሩ አስባለሁ። ወደ ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ፤ የእግዚአብሔርን ቃል እሰማለሁ፤ እንጀራውን እቆርሳለሁ፣ ጽዋውንም እጠጣለሁ፤ የክርስቶስ ሞትና የኀጢአቴን ስርየት አስታውሳለሁ፤ ከዚያም ወደ ቤቴ እሄዳለሁ። በርግጥ “ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ” የምንፈጽመው ሥርዐት ስለ ሆነ፣ ከቤተ ክርስቲያን ጋር እናያይዘዋለን። ለአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ግን የጌታ ራትና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያላቸው ግንኙነት ከዚህ የዘለለ አይደለም።

ነገር ግን የጌታ ራት፣ ቤተ ክርስቲያንን አንድ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት መሟገት እፈልጋለሁ። የጌታን ራት በጋራ መውሰድ፣ ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ከሚያደርጓት አስፈላጊ ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ነው። ክርስቲያኖች የጌታን ራት በጋራ በሚወስዱበት ጊዜ አንድ አካል ይሆናሉ። የጌታ ራት ብዙዎችን አንድ ያደርጋል።

በሁለት ምክንያቶች በዚህ ሐሳብ ላይ አተኩራለሁ። በመጀመሪያ፣ ይህ ሐሳብ በወንጌላውያን ክርስቲያኖች ዘንድ፣ በስፋት ችላ የተባለ ጉዳይ ነው። በመቀጠል እንደምናየው፣ ጳውሎስ የጌታ ራት ብዙዎችን አንድ እንደሚያደርግ በግልጽ አስተምሯል። ነገር ግን ይህ የጳውሎስ ንግግር፣ ስለ ጌታ ራትና ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን አስተሳሰብ እንዲቀርጽ የፈቀዱ በቁጥር እጅግ ያነሱ መጋቢዎችና አብያተ ክርስቲያናት ናቸው ያሉት። ሁለተኛው ደግሞ፣ መጋቢዎችና ቤተ ክርስቲያን የሚገጥሟቸውን በርካታ ተግባራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ የጌታ ራት እንዴት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚመሠርት ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ በጌታ ራት ላይ ማን ሊሳተፍ ይችላል? ማንስ ሊመራው ይገባል? ይህን የጌታ ራት ለመውሰድ የትኞቹ የቤተ ክርስቲያን ስብሰባዎች ተፈቅዶላቸዋል?

የጌታን ራት እንዴት መውሰድ እንዳለብን ጥበብ በተሞላበት መንገድ ለማወቅ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መነጽር አተኩረን ልናይ ይገባል።

እንዴት የጌታ ራት ብዙዎችን አንድ ያደርጋል?

ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 10፥16-17 የተናገረውን አስታውሱ፦ “የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።” ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች፣ የሚቆርሱት እንጀራና የሚጠጡት ጽዋ፣ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ለማድረግና በሞቱ ያገኙትን በረከት ለማሰላሰል እንደ ሆነ ያሳስባቸዋል። ጳውሎስ በቁጥር 17 ላይ በክርስቶስና በአማኞች መካከል ባለው “ቀጥተኛ” ግንኙነት ላይ በመመርኮዝ  የ“ጎንዮሽ” ግንኙነትን ይመሠርታል። “እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።” ጳውሎስ በዚህ ክፍል ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ፣ ብዙዎች ሆነን ሳለን አንድ አካል መሆናችንን ነው። በጌታ ራት ላይ የምናደርገው የጋራ ተሳትፎን በመጥቀስ፣ ጳውሎስ ይህን ሐሳብ ደግፎ ሁለት ጊዜ ጽፎታል። “እንጀራው አንድ እንደ ሆነ… ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።” ጳውሎስ ይህንን ሐሳብ ሁለት ጊዜ አጽንኦት ሰጥቶ መድገሙ፣ እንጀራው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት በላይ ትርጉም እንዳለው ያመለክታል። በምትኩ፣ የጌታን ራት በጋራ በማክበር ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደ ተመሠረተ ጳውሎስ ይነግረናል። አንድ እንጀራ ስላለ፣ አንድ አካል አለ።

ጳውሎስ፣ የጌታ ራት ብዙዎችን አንድ እንደሚያደርጋቸው ይናገራል። የጌታ ራት “እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ” አንድ አካል ያደርገናል። በሌላ አነጋገር፣ የጌታ ራት ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው። እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ፣ ስለ እንጀራና እንዴት እርሱን መብላት እንዳለብን አይደለም። ከአንድ በላይ የሚቆረስ እንጀራ የሚያስፈልጋት፣ ብዙ የአባላት ቁጥር ያለባት ቤተ ክርስቲያን አንድ አይደለችም ማለትም አይደለም። በምትኩ፣ ጳውሎስ፣ “አንዱን እንጀራ” ሲል ቤተ ክርስቲያን እንደ ማኅበር በጋራ የምታከብረውን የጌታን ራት ለመወከል ነው። የጳውሎስ ሐሳብ፣ የጌታን ራት በምንወስድበት ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እናደርጋለን። በክርስቶስ ያለን አንድነት ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አንድነትን ይፈጥራል።

በሌላ አነጋገር፣ የጌታ ራት የአዲስ ኪዳን መሐላ ምልክት ነው። የጌታን ራት በምንወስድበት ጊዜ፣ ከክርስቶስ ጋራና እርስ በርስ ያለንን ግንኙነት እናድሳለን። ይህ በሁለት መልክ የተቀመጠው ግንኙነት ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ያደርጋታል።

የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ደረጃዎች

እግዚአብሔር፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን በሁለት ደረጃዎች ፈጥሯል። የመጀመሪያው ደረጃ፣ ክርስቲያኖችን ፈጥሯል። እንዴት? እግዚአብሔር ስለ ወንጌል የሚሰብኩ ሰባክያንን ይልካል (ሮሜ 10፥14-17)። ለሚሰሙትም ወንጌሉን ተቀብለው እንዲመሰክሩ መንፈሱን ይልክላቸዋል (1 ቆሮንቶስ 12፥3)። የእርሱ ቃል በሕይወታቸው እንዲሠራ፣ በክርስቶስ አዲስ ሕይወትን ይሰጣቸዋል (ያዕቆብ 1፥18)። እግዚአብሔር፣ ቃሉና መንፈሱን በመላክ ቤተ ክርስቲያንን ፈጥሯል። እግዚአብሔር የወንጌል ሕዝቦችን ፈጥሯል። እነዚህም ሕዝቦች ክርስቶስን በማመን የዳኑ ናቸው። ይህ የመጀመሪያው ደረጃ ነው።

ሰዎች ወደ ክርስቶስ ሲመጡ፣ ዓለም አቀፋዊ ለሆነው የክርስቶስ አካል ብልቶች ይሆናሉ። በመንፈስ አንድ ናቸው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ለመፍጠር፣ ሰዎች ወደ ክርስቶስ መምጣት ብቻ ሳይሆን ወደ ሰዎችም መምጣት አለባቸው። በአንድነት መምጣት አለባቸው፤ ይህ ደግሞ ትጋትን ይፈልጋል። ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ በአንድ ከተማ ወይም በአንድ ክፍል ስለ ተገኙ ብቻ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አትፈጠርም። አለበለዚያ፣ ሌላ ክርስቲያንን ሱቅ ውስጥ ስታገኙት ቤተ ክርስቲያን በተፈጠረ ነበር። ስትለያዩ በፈረሰም ነበር። ቤተ ክርስቲያን የ”ክርስቲያን” ስብስብ ብቻ አይደለችም። የእያንዳንዱ ሰው ድምር ውጤት ብቻ አይደለችም። ሰዎችን አንድ የሚያደርግ የላቀ ነገር አለ።

የወንጌል ሕዝብና ወንጌላዊ ሥርዐት

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን ለመፍጠር የወንጌል ሰዎች ወንጌላዊ ሥርዐትን ሊፈጥሩ ይገባል። ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሰጡና ያስገዙ ሲሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያን ትወለዳለች። ይህ ሁለተኛው ደረጃ ነው። ወደ ኋላ ተመልሳችሁ የትዳሩን ምሳሌ አስቡ። ትዳር ሊፈጠር የሚችለው፣ ወንድና ሴት ባልና ሚስት ለመሆን ራሳቸውን ሲሰጡ ነው። ቃል ኪዳኑ ትዳርን ይመሠርታል። በተመሳሳይ፣ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላኛቸው ራሳቸውን ሲሰጡና ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንድታደርግ ያዘዛትን፣ ይኸውም ለአምልኮ፣ እርስ በእርስ በፍቅር ለመተናነጽ፣ ሸክምን ለመጋራት፣ ለመጠመቅ እንዲሁም የጌታን ራት በጋራ ለመውሰድ ሲሰበሰቡ ቤተ ክርስቲያን ትወለዳለች።  

ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ለወንጌል ትክክለኛ ምላሽ እንድንሰጥ ያስቻለን የማዳኑ ሥራ፣ አንዳችን ለአንዳችን የተሰጠን እንድንሆን ያስችለናል። የእግዚአብሔር ሥራና የእኛ ሥራ በውድድር ውስጥ አይደሉም። እንደ ክርስቲያን መሰብሰብ የቻልነው፣ እግዚአብሔር መጀመሪያ ክርስቲያን ስላደረገን ብቻ ነው። እግዚአብሔር፣ ክርስቲያኖችን በመፍጠርና አንዳቸው ለሌላቸው የተሰጡ እንዲሆኑ በማስቻል ቤተ ክርስቲያንን ፈጥሯል።

ጥምቀት እና የጌታ ራት

ክርስቲያኖች እነዚህን ሥርዐቶች የሚፈጽሙት እንዴት ነው? የጥምቀትና የጌታ ራት ሥርዐቶች እጅግ ወሳኝ ሚና አላቸው። በጥምቀት፣ ለክርስቶስና ለሕዝቡ በይፋ ቃል ትገባለህ/ሽ። ጥምቀት፣ እምነታችን ይፋ የሚሆንበት ነው። አዲስ አማኝ እምነቱን ለዓለም የሚያሳይበትና ቤተ ክርስቲያንም እንደ አማኝ የምትቀበልበት ሥርዐት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ጥምቀት አማኝን ከዓለም የሚለየው ነው። በጥምቀት፣ ቤተ ክርስቲያን “ይህ የኢየሱስ ነው” ብላ ለዓለም ትናገራለች።

በጌታ ራት፣ ለክርስቶስና ለሕዝቡ ያለንን መሰጠት እናድሳለን። ከጥምቀት በተለየ ሁኔታ፣ የጌታ ራት ሁላችንም በጋራ የምንፈጽመው ሥርዐት ነው። የጌታ ራት፣ ክርስቲያኖችን ከከበባቸው ዓለም ለይቶ አንድ አካል መሆናቸውን የሚያሳይ ሥርዐት ነው። በውስጡ የሚደረጉት ሥርዐቶችን ዐይተን “ክርስቲያኖች” እንድንል ሳይሆን “ቤተ ክርስቲያን” እንድንል ያደርገናል።

እስቲ አስቡት፣ አንድ ክርስቲያን ወደ አዲስ ከተማ በመሄድ ወንጌልን ሰብኮ፣ በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ ክርስቶስ መጡ። የመጡትን ሁሉንም አጠመቃቸው። እነዚህ የተጠመቁ ክርስቲያኖች እንዴትና መቼ ቤተ ክርስቲያን ይሆናሉ? ለዚህ ጥያቄ እጅግ መሠረታዊና አስፈላጊ መልስ አቀርባለሁ። ይህም፣ ቤተ ክርስቲያን የሚሆኑት የጌታን ራት አንድ ላይ ሲወስዱ ነው። የጌታን ራት መውሰድ፣ ለክርስቶስና ለወንድሞቻችንን ያለንን መሰጠት እንደሚገልጽ አስታውሱ። በጌታ ራት ውስጥ የሚገኘውን የክርስቶስን ትሩፋቶች ማግኘት ማለት፣ የክርስቶስን ሕዝቦች እንደ ወንድምና እኅት መቀበል ማለት ነው። የጌታ ራት ራሱ ከ“ክርስቲያኖች ስብስብ” ወደ “አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን” እንድንሸጋገርና አንዳችን ለሌላኛችን የተሰጠን እንድንሆን ያደርገናል። በጌታ ራት ምክንያት እንደ አንድ አካል ተሰብስበናል። ጳውሎስ እንደሚለው፣ “እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና” (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥17)።

አብያተ ክርስቲያናት መጀመሪያ እንደ ቤተ ክርስቲያን ሲመሠረቱ፣ አባላት እርስ በርሳቸው የገቡት ቃል ኪዳን ምን እንደ ሆነና ምን እያደረጉ እንዳሉ ማብራራት ብልኅነት ይመስለኛል። በኮንግሪጌሽናሊስት (Congregationalist)ና ባፕቲስ (Baptist) ወግ ይህ “የቤተ ክርስቲያን ቃል ኪዳን” ተብሎ ይጠራል። ይህም የጌታን ራት በሚወስዱበት ጊዜ ይነበባል። ይህ ጥሩ ልምምድ ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ የቃል ንግግር ግን፣ የጌታን ራት ከመውሰዳችን ተነጥሎ ብቻውን ቤተ ክርስቲያንን ሊፈጥር አይችልም። ነገር ግን ይህ ቃል ኪዳን፣ የጌታ ራት ከጀርባው ያነገበውን ትርጉም ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ የቃል ኪዳን ንባቦች መረዳታችንን ያሳድጉታል። እንዲሁም እንጀራውንና ጽዋውን ስንወስድ ምን እያደረግን እንደ ሆነ ያስታውሱናል።

የቤተ ክርስቲያን አጀማመር፣ እንደ ትዳር አጀማመር ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ ምሳሌ እንደ ሌሎች ምሳሌዎች ፍጹም አይደለም። ነገር ግን የተሻለ መረዳት እንዲኖረን ያግዘናል። ትዳር የሚፈጠረው፣ ወንድና ሴት ቃል ኪዳን ሲፈጽሙ፣ ደግሞም አገልጋይ ወይም ሕጋዊ ሰው ትዳራቸውን ሲያረጋግጥ ነው። “አዎ ቃል እገባለሁ” የሚለው መሐላ አዲስ ግንኙነትን ያስጀምራል። ነገር ግን ይህ ግንኙነት የሚጸናው ባልና ሚስት በአካል ግንኙነት ሲያደርጉ ነው።

እንዲሁም በተመሳሳይ፣ የአማኞች ስብስብ  ያላቸውን አንድነት የጌታን ራት በጋራ በመውሰድ ካላጸኑ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሊሆኑ አይችሉም። ቤተ ክርስቲያን ለመሆን የሚፈልጉ አማኞች፣ የጌታን ራት አንድ ላይ ካልወሰዱ፣ የክርስቶስን ትእዛዝ መተላለፍ ብቻ ሳይሆን መጀመሪያውኑ ቤተ ክርስቲያን አይደሉም። የጌታ ራት፣ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ሥርዐት ነው።

የጌታ ራት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ይሠራል? የጌታ ራትና ጥምቀት፣ የወንጌል ሕዝብ ወንጌላዊ ሥርዐትን የሚፈጥሩባቸው መንገዶች ናቸው። የጌታ ራት ክርስቲያኖች በጋራ መጥተው፣ አንዳቸው ለሌላኛቸው ራሳቸውን የሚሰጡበትና ከ”ብዙ” ወደ “አንድ” የሚሻገሩበት ሥርዐት ነው። በጌታ ራት፣ ከክርስቶስ ጋራ ያለን ኅብረት፣ የእርስ በርስ ግንኙነትን ይፈጥራል። የጌታ ራት፣ ብዙዎችን አንድ ያደርጋል።

በውበት የተሞላ ግልጽነት

እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ያለው ዕቅድ ግልጽና ውበትን የተሞላ ነው። ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት ምን ያስፈልጋል? በወንጌሉ ሥርዐት የሚመራ፣ በስብከተ ወንጌል የተገኘ የወንጌል ሕዝብ። ቤተ ክርስቲያን፣ ወንጌልና ሥርዐቶቹ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚመሠርቱበት ቦታ ነው። ጥምቀት፣ አንዱን ከብዙ ጋራ ያገናኛል፤ የጌታ ራት ደግሞ ብዙዎችን አንድ ያደርጋል።

ጥምቀትና የጌታ ራት፣ ወንጌሉን በቤተ ክርስቲያን ቅርጽና መዋቅር ውስጥ ያስገባሉ። ብዙዎችን አንድ ማድረግ፣ የወንጌል ምልክት ነው። ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረት በአንድነት ሲመጡ ከወንጌል የሚርቁ ሳይሆን ወንጌሉን በጥልቀት የሚረዱ ይሆናሉ።

ቦቢ ጀሚሰን

***

የአርታዒ ማስታወሻ፥ ይህ መጣጥፍ ከ ተሻሻለው “Understanding the Lord’s Supper, in the Church Basics series (B&H, 2016).” የተወሰደ ነው። በB&H ፈቃድ እንደገና ታትሟል።