የቤተ ክርስቲያን አምልኮ

የመዝሙር መጽሐፍ፣ በምዕራፍ 150፥6 እንዲህ በማለት ይደመድማል፤ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ።” እግዚአብሔር ፈጥሮናል፤ ደግሞም እንድናመልከውና እንድናመሰግነው እስትንፋስን ሰጥቶናል።

የተወደዱት የባለቤቴ አያት ማረፋቸውንና ወደ ጌታ የመሄዳቸውን ዜና የሰማሁት፣ ኅዳር ወር 2002 ዓ.ም፣ ልክ አትላንታ ከተማ ከመድረሴ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ በቀብሩ ሥነ ሥርዐት ላይ በክፍቱ የአስክሬን ሣጥን አጠገብ ቆሜ፣ የመዝሙር 150፥6 ቃላትን በማስታወስ መተንፈስና ለቅዱሱ እግዚአብሔር ምስጋናን ማቅረብ፣ እንዴት ያለ ዕድለኝነት እንደ ሆነ እያሰብኩ ነበር።

የአገሬ ሰው የሆነው፣ ዮሐን ሰባስቲያን ባህ የጻፈውን የሙዚቃ ድርሰት SDG ብሎ መሰየሙ አስተዋይነት የተሞላበት ነበር። (ይህም soli Deo gloria “ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ” የሚል ትርጓሜ ያለው የላቲን ሐረግን የሚወክል አኅጽሮት ነው)፡፡ በተጨማሪም ባህ፣ “የየትኛውም ሙዚቃ የመጨረሻ ግብ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ለነፍስ መታደስ ብቻ ሊሆን ይገባዋል” በማለትም ጽፎ ነበር።

ይህ ትክክለኛው የአምልኮ ግብ ነው፤ ለእግዚአብሔር ክብርና ለነፍስ መታደስ። በመጽሐፍ ቅዱስ የምታምን ቤተ ክርስቲያን፣ በማኅበር በጋራ ለማምለክ በአንድነት ከምትመጣበት ሁኔታ በላይ፣ የምታከናውነው አስፈላጊ ነገር የለም። ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር ስለ ማንነቱና ስላደረገው ነገር፣ ከፍተኛው ምስጋናና ውዳሴ የሚገባው መሆኑን በጋራ ለማወጅ የሚሰበሰቡበት ስፍራ የማኅበር አምልኮ ነው።

ዘፀአት 20፥3 ላይ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።” ሁለት ቊጥሮችን ዐልፎም፥ “አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸውም፤ እኔ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ” ይላል። እግዚአብሔር በርግጥ፣ የፍቅራችን በኲርና በእውነት አምላካችን ከሆነ፣ እንግዲያው እርሱን ለሚያከብርና ከፍ ለሚያደርግ ቅዱስ አምልኮ ይበልጥ የምንነሣሣ እንሆናለን።

ዮሐንስ 4፥24 መሠረት ቅዱስ አምልኮ፣ “በመንፈስና በእውነት” የሆነ አምልኮ ነው። ስለዚህ የአምልኮ ስብሰባዎቻችን በግልጽ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉና በመንፈስ ቅዱስና በእግዚአብሔር ቃል የተሞሉ መሆን ይኖርባቸዋል። ጀምስ ሞንትጎመሪ ቦይስ እንዲህ ሲል በትክክል ተናግሯል፤ “መጽሐፍ ቅዱስና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች፣ የአምልኮ ማዕከላት መሆን አለባቸው።” መጽሐፍ ቅዱሳዊ አምልኮ የሚገለጠው፣ እግዚአብሔር ተኰር በሆነ ስብከት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ በምስጋና፣ በጸሎትና በቅዱሳት ሥርዐቶች አገልግሎት ነው። ትኲረቱም በእግዚአብሔር ማንነትና በሥራዎቹ ላይ ይሆናል። የአምልኮ ስብሰባዎቻችን በዚህ ላይ ትኲረት ሲያደርጉ፣ እግዚአብሔር ይከብራል፤ ለነፍሳችንም መታደስ ይሆናል፤ ደግሞም በእምነታችንም እንጠነክራለን።

ቤተ ክርስቲያኔ፣ በጀርመን ሙኒክ የምትገኝ፣ የሙኒክ የወንጌል ቤተ ክርስቲያን ስትሆን፣ የምታገለግለው እጅግ በጣም ዓለማዊ በሆነ ከባቢ ውስጥ ነው። መጀመሪያ አካባቢ ከነዋሪዎቹ የሚበዙቱ፣ በቋሚነት ወደ አምልኮ ስብሰባ መምጣት አስፈላጊ እንደ ሆነ አይሰማቸውም ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ክርስቲያኖች ያልሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችም፣ በግል ጨዋታዎች መኻል እንኳ ስለ ክርስቶስና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እንድታነሡባቸው አይፈልጉም። በዚህ እጅግ ዓለማዊ በሆነ ከባቢ ውስጥ የታዘብኩት አስደናቂ ነገር፣ እግዚአብሔር በየሰንበቱ ጥቂት የማይባል ቁጥር ያላቸው የማያምኑ ሰዎች ወደ አምልኮ ስብሰባችን እያመጣ መሆኑን ነው፡፡ ደግሞም በአምልኮ ስብሰባ ላይ ከመሆኑ የተነሣ፣ መጋቢው ለ35 ደቂቃዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ሲሰብክ፣ ያለ ምንም ችግር መስማታቸው ነው። እግዚአብሔር የሚሰበከውን ቃሉን ለራሱ ክብር፣ የጠፉትን ለማዳንና ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እየተጠቀመበት ነው። የሚያበረታታ ቁጥር ያላቸው የማያምኑ ሰዎች ወደ አምልኮ ስብሰባችን ተመልሰው ይመጣሉ፤ በአብዛኛውም ለወራት አንዳንዴም ለዓመታት ከተሳተፉ በኋላ አማኞች ይሆናሉ።

ጎን ለጎን፣ እግዚአብሔር የአምልኮ ስብሰባችንን፣ ክርስቲያኖች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑና ይበልጥ ክርስቶስን የሚመስሉ ለማድረግ እየተጠቀመበት ነው። ክርስቶስን ይበልጥ እየወደዱት ሲመጡ፣ ወደ አምልኮ ስብሰባዎች አዘውትረው መምጣት ይጀምራሉ። የተሰበከው ቃል አጠቃላይ ውጤት ደግሞ ሕይወታቸው ለእግዚአብሔር ክብር በመለወጡ ውስጥ ይታያል።

በሰንበት የማኅበር አምልኮአችን የምናደርገውና የምንሰማው ነገር፣ በቀጣይ የሳምንቱ ቀናት የሚያንቀሳቅሰን፣ የሚመራንና የሚያበረታታን እንዲሆን ይጠበቃል። ስለዚህም የማኅበር አምልኮ ሙላት፣ ያለ ችግር እግዚአብሔርን ወደምናመልክባቸው ወደ ሁሉም የሕይወት አቅጣጫዎች መፍሰስ አለበት፤ ይህም በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በቤተ ሰብ መካከልና በሌሎችም ግንኙነቶቻችን እግዚአብሔርን ማክበር እንድንችል ነው።

ወከባ በበዛት የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ ቤተ ሰቦች እንዲሁም ያላገቡ ሰዎች በጸጥታ ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ማንበባቸውና መጸለያቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም፣ ለምሳሌ እየነዱ በሚጓዙ ጊዜ ወይም መደበኛ በሆነ የቤተ ሰብ የጋራ አምልኮ ጊዜ መከናወን የሚችል ነው። እግዚአብሔር ተኰር የሆነ አምልኮ እግዚአብሔርን ያከብራል፤ ለእግዚአብሔርና ለሰዎች ያለንንም ፍቅር ያቀጣጥላል። Soli Deo gloria.