እግዚአብሔር መክበራችሁን አቅዷል

እግዚአብሔር እንድንገረም ስለሚፈልግ ወደ ፊት ስለሚገጥሙን አስደናቂ ነገሮች ነግሮናል።

በእርግጥም ተስፋ እንዳለን እንድናስብ ስለሚፈልግ ተስፋ የተሞሉ ነገሮችን ነግሮናል። ስለሚመጣው ነገር ባለን ተስፋ ከልብ የሆነ ደስታ ካልተሰማን ተስፋ ተስፋ አይሆንም። ለዚህም ነው ደስታ የሚፈጥሩ ነገሮችን እግዚአብሔር የነገረን። በተስፋ የደስታ ስሜት፣ ጥልቅ በሆነ እርግጠኝነት አሁን ላይ ደስ እንድንሰኝበት ይፈልጋል። “በተስፋ ደስተኞች ሁኑ” (ሮሜ 12፥12)።

ከልምዴ ልናገር የምችለው፣ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ወደፊቴ የተናገረውን አንብቤ ስሜቴን ሳይነኩ በፍጥነት ላልፋቸው እንደምችል ነው። እንዲህ ዐይነቱ ንባብ ተስፋን ማነቃቃትና ማጠንከር አይችልም። በድርቅ መኻል የማይጠወልጉ ልባቸው በደስታ የተሞላ ለምለም ዛፎች አያደርገንም።

በርግጥም ለዚህ ነው ሕጉን በቀንና በሌሊት የሚያሰላስል ክርስቲያን ለምለምነትን የተላበሰ፣ ቅጠሉ የማይጠወልግና ሌሎች ሲደርቁ እርሱ ግን ፍሬን የሚያፈራ የሆነው (መዝሙር 1፥2)። ተስፋ እስኪሰማው ድረስ የእግዚአብሔርን ተስፋ የሚሰጡ የተስፋ ቃሎችን ያሰላስላል።

የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ፍሬዎች አንሱ

እንደ ደረሰ የበለስ ፍሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተንጠለጠሉ የተስፋ ቃሎችን ስናገኝ፣ ይህ በለስ ነው ብቻ ብለን በእርሻው መካከል ጉዟችንን አንቀጥልም። ይልቁንም ቆም እንላለን። እጃችንን ዘርግተን በለሱን እንቀጥፋለን። ከበለሱ እንበላለን። እናጣጥመውማለን። የቅምሻ ሕዋሶቻችን እንደሞቱ ብንረዳ ሕይወት እንዲሰጠን እግዚአብሔርን እንለምነዋለን፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ” እንለዋለን (መዝሙር 119፥107)።

ወደ ተስፋ እርሻ አብራችሁኝ ተጓዙ። ከተወሰኑ ቀናት በፊት የሰበሰብኳቸውን በለሶች አብራችሁኝ ቅመሱ። እያነበብኩኝ ሳለ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 2፥7 ላይ እንዲህ የሚለውን ተመለከትኩ፦

“ነገር ግን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው።”

ቆም አልኩኝ። ቀጥዬም ይህንን የተስፋ በለስ አነሣሁኝ። ላለፉት ቀናት ነፍሴን ሲያድስ ነበር። ከዚህ በፊትም ሐሳቡ በዚያ እንደነበር አውቃለሁ። አሁን ግን በተስፋ ጎምርቶ ታየኝ። በስሎ ለመቀጠፍ ደርሶ ነበር። እኔም በስዬ ነበር። ጣዕሙ ምንኛ ጣፋጭ ነበር። ነፍሴን ጥሩ አድረጎ ስለ መገባት፣ እንቅልፌን ጣፋጭ አደረገው። ደግሞም በመንገዴ ሊመጣ ላለ ከባድ ነገር አጠነከረኝ። ኑና ከእኔ ጋር ቅምሻውን ተቋደሱ።

ከዘመናት በፊት

“ከዘመናት በፊት” ሲል ጊዜ ከመፈጠሩ በፊት ማለቱ ነው። ስለዚህ ከፍጥረት በፊት እግዚአብሔር ለብቻው ሳለ ማለቱ ነው። የዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ጥበቡን ሲጠቀምበት ነበር። ይህ ጥልቅ ጥበብ ነው። በዘላለማዊ ጥልቅ ጥበቡም ደግሞ ለእኛ ያዘጋጀውን ክብር አንድ ቀን በሙላት እንለማመደው ዘንድ ሲያቅድ ነበር፤ “ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው።”

ለሚወድዱት

ይህንን ክብር ያቀደው ለማን ነበር? ይህንን ክብር ያቀደው “ለሚወድዱት” ነው። ቁጥር 9 እንዲህ ይላል፤ “ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን፣ እግዚአብሔር ለሚወድዱት አዘጋጅቷል።” የምንወድደው ሁላችን የከበርን እንሆን ዘንድ ዓለም ሳይፈጠር በፊት እግዚአብሔር ወስኗል።

ከእግዚአብሔር ጥልቅ ነገር

በእግዚአብሑር ጥበብ ውስጥ ይህ ውሳኔ ሁለተኛ ደረጃን የሚይዝ አይደለም። ይልቁንም የመጣው ከእግዚአብሔር ጥልቅ ነገር እንደሆነ ጳውሎስ ይነግረናል። ቁጥር 10 እንዲህ ይላል፤ “እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል።” ተስፋን የሚሰጡት እነዚህ በለሶች፣ ከዘመናት በፊት ከነበረው ከእግዚአብሔር ጥበብ፣ ከእግዚአብሔር ውሳኔ ደግሞም “ከእግዚአብሔር ጥልቅ ነገር” የመጡ ናቸው።

ለክብራችን የወሰነው

ይህ ምንን ያጠቃልላል? ነገ ጠዋት ከመንቃታችን በፊት ልንሞት እንደምንችል ስናስብ ስለ ምን ተስፋ ሊሰማን ይችላል?

ተስፋ ማድረግ ያለብን፣ “መክበራችንን” እንደሆነ ጳውሎስ ይነግረናል። ይህ መክበር የእኛ የሚሆነው በምን መልኩ ነው? ከእግዚአብሔር በተለየ የምናገኘው አይደለም። ከክርስቶስ ተለይተን የምናገኘው አይደለም። ተስፋችን የእግዚአብሔር እና የክርስቶስ ባልሆነ ክብር መክበር አይደለም። ይልቁንም “የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን” (ሮሜ 5፥2)። እንዲሁም በክርስቶስ ክብር! “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ተካፋዮች እንድትሆኑም በወንጌላችን አማካይነት ጠርቷችኋል” (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥14)።

ዓለም የእናንተ ነች

“ተካፋዮች” የምንሆነው እንዴት ነው? በመጀመሪያ እንደ ዓለም እንደ መንግሥት እንደ ግዛት ተካፋዮች እንሆናለን። “ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር. . .” (1ኛ ተሰሎንቄ 2፥12)። “እንግዲህ ማንም በሰው አይመካ። ሁሉ ነገር የእናንተ ነውና፤ . . . ዓለምም ሆነ ሕይወት ወይም ሞት፣ አሁን ያለውም ሆነ ወደ ፊት የሚመጣው፣ ሁሉ የእናንተ ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 3፥21-22)። የዚህ ክብር ተካፋዮች የምንሆነው ልክ ለብዙ ዐሥርት ዓመታት በቀዝቃዛ እና ጨለማ እስር ቤት ውስጥ ታስሮ የነበረ አንድ እስረኛ፣ ወደ ድንቅ ብርሃን እና ነፃነት ሲወጣ በሚሰማው ዐይነት መንገድ ነው። የዐይኖቹ አድማስ እስከሚደርሱበት ድረስ፣ በሚያየው አቅጣጫ ሁሉ ውበት አለ። ይህ ውበት ያሸተዋል፣ ይሰማዋል፣ ይቀምሰዋል፤ ይህ ውበት እሱነቱን ሁሉ የሚከብና በመላ ሰውነቱ የሚሰማው ነው። ክብር የመኖሪያ ስፍራችን ይሆናል። የከበረው አዲስ ዓለም ክብራችን ይሆናል።

የእያንዳንዱ ውብ ነገር ብርሃን እና ውበት (ደግሞም እያንዳንዱም ነገር ውብ ይሆናል)። የእግዚአብሔር ብርሃን እና ውበት ይሆናል። “የእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ስለሚሰጣትና በጉም መብራቷ ስለሆነ . . .” (ራእይ 21፥23)። ከዚህ ዘመን እስር የተለቀቀ እያንዳንዱ የተዋጀ እስረኛ፣ “በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን” እያለ ይዘምራል (መዝሙር 36፥9)። ክብራችን በነገር ሁሉ ውስጥ በላይ ያለው የግዚአብሔር ክብር ይሆናል።

የእግዚአብሔር ክብር ባለጠግነት

ይህም ደግሞ ከፍጥረት እውነታ ሁሉ ይልቅ ለነፍሳችን የላቀ እና የከበረ ዋጋ ያለው ነገር ነው። ጳውሎስ ሲያብራራ፣ “አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው፣ የምሕረቱም መግለጫዎች ለሆኑት፣ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ባለጠግነት እንዲታወቅ . . .” ይላል። በምድር ላይ ብልጽግና ወደ እኛ ሲመጣ ታላቅ ደስታ እና ተስፋ ይሰማናል። ባለጠግነት ለነፃነት እና ለሕይወት ትልቅ የሆነ መንገድ ይከፍታል።

ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሁሉ ሀብት ቢኖራችሁ ከዘላለም በፊት ለእኛ ከተወሰነው “ከእግዚአብሔር ክብር ባለጠግነት” ጋር የሚወዳደር አይደለም። የተዘጋጀነው (የተፈጠርነው) ለዚህ ነው። ምድራዊ ብልጽግና ለነፃነት እና ለሕይወት ታላቅ ደስታን እና ተስፋን የሚጨምር ከሆነ ቃል የተገባልን የክብሩ ባለጠግነት ከሰዎች ሁሉ የላቅን ደስተኞች እና ነፃ ሰዎች እንዲያደርገን ምንኛ በተገባው። ይህ ነው የእኛ ክብር!

እርሱን እንመስላለን

ይሁን እንጂ ይህ ክብር የእኛ የሚሆነው እንድናየው ብቻ ሳይሆን እንድንሆነውም ጭምር ነው። “እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ እናየዋለን፤ እርሱን እንደምንመስልም እናውቃለን” (1ኛ ዮሐንስ 3፥2)። ከዘመናት በፊት እግዚአብሔር ለክብራችን አስቀድሞ ጥበብን ወስኗል። እኛ ራሳችን በምናየው ነገር የምናበራ ስለምንሆን ይህ ክብር የእኛ ይሆናል።

ዮሐንስ ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን ሲመለከት፣ “[ፊቱ] በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሓይ ነበረ።” ዮሐንስም እንደ ሞተ ሰው ወደቀ (ራእይ 1፥16-17)። ይሁን እንጂ ይህ ክብር እኛም ራሳችን የምናበራበት ክብር ነው፤ “በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ” (ማቴዎስ 13፥43)።

አዲሱ ዓለማችን እንዲሁም አዲሱ ማንነታችን ስለሆነ የክርስቶስ ክብር የእኛም ክብር ይሆናል።

ልክ እንደ እርሱ የከበረ ሥጋ

በሞት ጫፍ ያለን አንድ ቅዱስ ሰው በአሳባችሁ ለመሳል ሞክሩ። እኚህ የሞት ወራት የከበሩ አይደሉም። ብዙዎች “ምድራዊ ድንኳናቸውን” ጥለው “በሕይወት እንዲዋጥ” እየቃተቱ ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥4)። ይሁን እንጂ ከዚህ ውርደት ከሞላበት ፍጻሜ በተቃራኒ ኀያሉ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ቆሟል፤ ይህ የበሰበሰው እና ያረጀው እንዲሁም የተዳከመው ሰውነት “በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥43)። ሁሉም ቅዱሳን ምንም ያህል ቢደክሙ እና ጉዳት ቢደርስባቸው በክብር ይነሣሉ። ክብራችንን እግዚአብሔር ወስኗል።

የትንሣኤ አካላችን ክብር የሚሆነው የክርስቶስ ክብር ነው። “እርሱም ሁሉን ለራሱ ባስገዛበት ኀይል፣ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል” (ፊልጵስዩስ 3፥21)። በመከራቸው ሁሉ ውስጥ ከክርስቶስ ጋር የሚጣበቁ ከእርሱ ጋር ይከብራሉ (ሮሜ 8፥17)። ከዘመናት በፊት እግዚአብሔር ለእኛ የወሰነው ይህንን ነው። “እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው. . . አስቀድሞ የወሰናቸውን . . . አከበራቸው” (ሮሜ 8፥29-30)። ለእኛ የተወሰነው ጥበብ ይህ ነበር።

የአጽናፈ ዓለሙ ክብር

ስለዚህ ክብራችን የአዲሱ ዓለማችን ክብር እና የአዲሱ ተፈጥሮአችን ክብር ነው የሚሆነው። የማስደነቁን ብዛት ይበልጥ እንረዳው ዘንድ ጳውሎስ ሲናገር፣ ከአዲሱ ዓለም ጋራ የምንጣጣመው እኛ ሳንሆን አዲሱ ዓለም ነው ከእኛ ጋራ የሚጣጣመው ይለናል። የምንለብሰው ክብር የዓለማችንን ክብር ይወስነዋል። “ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነፃነት እንዲደርስ ነው” (ሮሜ 8፥18-21)። እኛ ሳንሆን የዓለማችንን የከበረ ነፃነት ተካፋዮች የምንሆነው፣ ይልቁንም ዓለማችን የከበረው ነፃነታችን ተካፋይ ይሆናል።

ከባድ እና ዘላለማዊ

የምታልፉበት መከራ የማያልቅ ቢመስላችሁ፣ ሐዘናችሁ እና ሥቃያችሁም እጅግ የበዛ ቢመስል፣ ደግሞም ዘመናችሁን ሁሉ ሞልቶ ሸክሙ በጣም ከባድ እንደሆነ ሕመሙም ማብቂያ የሌለው እንደሆነ ቢሰማችሁ፣ እግዚአብሔር ግን ከመጠን በላይ ከባድ አይደሉም ደግሞም ማብቂያ የሌላቸው አይደሉም ይላል። “ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል።” (2 ቆሮንቶስ 4፥17)

ይልቁንስ ከባድ የሆነው ምን እንደሆነ ማወቅ ትሻላችሁ? የክብሩ ክብደት ታላቅ ነው። ደግሞስ ምን ረጅም እንደሆነ ማወቅ ትሻላችሁ? ዘላለማዊ ክብር ረጅም ነው። ክብራችን ይህ ነው።

እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር ይመሰገናል

ይህ ብቻ አይደለም። ክብራችን የአዲሱ ተፈጥሮአችን ክብር በሙሉ ድምቀት እንደሚያበራ ፀሓይ ማብራቱ እና አዲስ የክብር ዓለም መፈጠሩ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ክብራችን ጥልቅ የሆነ አንድ ግላዊ ይዘት ይኖረዋል።

የዚያ አዲስ ዓለም ታላቅ ብርሃን፣ እንዲሁም የእያንዳንዱ ሰው ታላቅ ማንጸባረቅ ከኢየሱስ ጋር ያለን ግላዊ ንክኪን አይከለክልም። “ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ” የሚለው በጅምላ ሳይሆን በነፍስ ወከፍ ነው (ማቴዎስ 25፥21)። መልካም እና ታማኝ አገልጋዮች ሳይሆን፣ መልካም እና ታማኝ አገልጋይ ነው የሚለው።

ለእያንዳንዱ ታማኝ አገልጋይ ተራ በተራ “ከሚቀበለው ሰው በስተቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም የተጻፈበትን ነጭ ድንጋይ እሰጠዋለሁ” ይላል ኢየሱስ (ራእይ 2፥17)። ከዚህ በላይ ግላዊ ገጽታ ሊኖረው አይችልም። ክብራችን የእያንዳንዳችንን ግላዊ ክብር ይይዛል። “እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል” (1ኛ ቆሮንቶስ 4፥5፤ ለተጨማሪ ሮሜ 2፥29ን ተመልከቱ)።

በተስፋ ደስ ይበላችሁ

“ከዘመናት በፊት እግዚአብሔር ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ጥበብ” የሚያጓጓ እና የሚያረሰርስ፣ ደግሞም ኀይልን የሚሰጥ በለስ ነበር። ለብዙ ቀናት ሳጣጥመው ቆይቻለው። አብራችሁኝ ስላጣጣማችሁት አመሰግናለሁ።

እግዚአብሔር ስለ ወደፊታችሁ በወሰነው ክብር ደስተኞች ያድርጋችሁ።