ስግብግብነትና ልከኝነት

ስለ ስግብግብነት የሚደረጉ ውይይቶች ላይ ሁለት ስሕተቶች ይስተዋላሉ። የመጀመሪያው ስግብግብነት የሚመለከተው፣ የሰውነት ቅርጻቸውን ያልጠበቁ ሰዎችን ብቻ ነው የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስግብግብነት ምግብን ብቻ ያካትታል የሚለው ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ስግብግብነት መጫወቻዎችን፣ ቴሌቪዥንን፣ መዝናኛን፣ ወሲብን ወይም ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ሊያካትት ይችላል። ስግብግብነት ልክን ያለፈ የትኛውንም ነገር ይመለከታል።

የጥንት አረማውያን ሕዝቦች፣ ይህን በትክክል ተረድተውታል። በዴልፊ (በታችኛው ማዕከላዊ ግሪክ) የአፖሎ መቅደስ “ምንም ነገር ከልክ ማለፍ የለበትም” የሚል ጥበብ የተሞላበት አባባል ተጽፎበታል። የዚህ ችግር ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ከመጠን ያለፈ መሆኑን የሚዳኘው ግለ ሰቡ ስለ ሆነ ነው፤ ለክርስቶስ ተከታዮች ግን፣ ዳኛው ፈጣሪው እግዚአብሔር ነው። እኛም በዚህ ጉዳይ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የምናውቀው በዴልፊ ንግርት አድርጓል ተብሎ እንደሚታሰበው፣ በሆነ ተመስጦ ውስጥ በመግባት ቃሉን ስለምንናገር አይደለም፤ ይልቁንም ቃሉ ስላለን ነው። ለምሳሌ በምሳሌ 23፥1–3 “ከገዥ ጋር ለመብላት በምትቀመጥበት ጊዜ፣ በፊትህ ያለውን በሚገባ አስተውል፤ ስግብግብም ብትሆን እንኳ፣ በጒሮሮህ ላይ ካራ አጋድምበት፤ የእርሱ ጣፋጭ መብል አያስጐምጅህ፤ ምግቡ አታላይ ነውና።”

ይህ በመሠረቱ፣ ወደ አስተሳሰባቸው ሊስቡን ከሚሹ፣ እግዚአብሔርን ከማይፈሩ ባለ ጠጎች የቅንጦት አኗኗር ጋር ስንጋፈጥ ራስን የመግዛት ልምምድ እንዲኖረን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው። ከኢየሱስ ውልደት በፊት የነበረው የየትኛው ሰው ሕይወት ይህን በደንብ ያሳየናል ብለን ብንጠይቅ፣ ዳንኤልን እናገኛለን፡፡ ዳንኤል በተከበረው የንጉሥ ማዕድ የመቀመጥ ዕድል ነበረው፤ ነገር ግን “በንጉሡ ምግብና የወይን ጠጅ እንዳይረክስ ወሰነ” (ዳንኤል 1፥8)። ከላይ እንደ ተጠቀሰው ይህ ተመሳሳይ መርሕ፣ እግዚአብሔር በፈጠራቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ላይ ይሠራል። በርግጥ ልንደሰትባቸው ይገባል (ይህ ክርር ያለ ራስን የመካድ ጥሪ አይደለም)፤ ነገር ግን በመንፈስ የተሞላ ልባምነት(አስተዋይነት) ከሚፈቅደው በላይ እነዚህን ቀላል ተድላዎች በስግብግብነት ልንጠቀማቸው አይገባንም።

በነገራችን ላይ ጥንቁቅነት(ልባምነት) የስግብግብነት ተቃራኒ ነው። ጥንቁቅነት ማለት ጥበብ የተሞላበት ቁጥብነት ወይም ልከኝነት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በሆኑት ዮሐንስ አፈ ወርቅና በቅዱስ ጀሮም አስተምህሮ መሠረት፣ ልከኝነት ወይም ቁጥብነት አዳምና ሔዋን በዔድን ገነት ውስጥ በብዙ የጎደላቸው ሰማያዊ እሴት ነበር፤ እንዲያውም፣ በዚህ ገደብ በሌለው ምኞታቸው ምክንያት ከገነት ተባረሩ፤ ምክንያቱም (ልክ እንደ ጥንቶቹ ግሪኮችና ሮማውያን) ከልክ ያለፈው ነገር ምን እንደ ሆነ ለመወሰን፣ ራሳቸውን እንደ ፈራጆች(ዳኞች) ከፍ አድርገው ስላስቀመጡ ነው።

ስግብግብነትን ወይም ልከኝነትን አለማወቅ፣ ብዙዎቻችንን ነገሮችን ሁሉ እኛ በምንፈልገው መንገድ ብቻ እንዲሆኑ እንድንጠይቅ ያደርገናል። ይህ ይበልጥ ረቂቅ የሆነ የስግብግብነት ቅርጽ ያለው እኩይ ተግባር፣ በዛሬው ጊዜ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ዝም ተብሎ የሚታለፍ ብቻ ሳይሆን የተበረታታ ነው። የተከበረ ነገርም ሆኗል። እንደ ጥንቶቹ ሮማውያን፣ በሆዳምነታቸው እጅግ ብዙ ደስታን ከመፈለጋቸው የተነሣ፣ ምግብ ከተመገቡ በኋላ ተጨማሪ ለመብላት ሲሉ የበሉትን የሚያስወጡ ሰዎችን ለማግኘት ትቸገሩ ይሆናል። ነገር ግን አስተዋይ ዐይን በብዙ ሁኔታዎች ውስጥ ‘የረቀቀ ስግብግብነት’ ብለን ልንጠራው የምንችለውን ነገር ያስተውላል። ሲ.ኤስ. ሉዊስ በ“ስክሩቴፕ ሌተርስ” (Screwtape Letters) በተሠኘው መጽሐፋቸው ይህ ምግባር “በታካሚው እናት” ላይ ጉዳት ሲያደርስ ያሳያሉ። እርሷም “ለእንግዳ ተቀባዮችና ለአገልጋዮች አስፈሪ ናት… ሁልጊዜ የቀረበላትን ነገር ወደ ጎን በማለት፣ በየዋህነት ስሜት በትንሹ ተንፍሳና ፈገግ ብላ ‘ኦ! እባካችሁ… እኔ የምፈልገው ቀጭን ግን በጣም ቀጭን ያልሆነ ትንሽ ሻይ ብቻ ነው፤ ደግሞም በጣም ትንሽ ጥርት ያለ የተጠበሰ ዳቦ ብቻ ነው” ትላለች። ሉዊስ እንደሚጠቍመው፣ የፈለገችው ነገር ከቀረበላት ያነሰና ርካሽ ስለ ሆነ ብቻ፣ ለሌሎች ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም የፈለገችውን ለማግኘት ያላትን ቍርጠኝነት እንደ ስግብግብነት በፍጹም አትገነዘበውም፡፡

በርግጥም፣ “‘መላ ሕይወቷ ለዚህ ዐይነቱ የስሜት ባርነት ተላልፎ መሰጠቱን ስታውቅ ትደነግጣለች፡፡’ ዎርምዉድ(Wormwood) ለስክሩቴፕ እንደሚያስተምረው፣ የዚህ ዐይነቱ ስግብግብነትን የተላበሰ ስሜታዊነት ዋና ጥቅሙ፣ “በንጽሕና ላይ ለሚሰነዘር ጥቃት እንደ መድፍ ዝግጅት” ሆኖ ማገልገል ነው። በርግጥም፣ የመድፍ ጦር ለፈጣንና ቀጥተኛ ጥቃት መንገዱን ለማመቻቸት የጠላትን መከላከያ ይደበድባል። በውስጣችን ላለው ለዚህ ዝንባሌ ደንዝዘን እስከኖርን ድረስ (ይህ በየአብያተ ክርስቲያናት ብዙም አለመሰበኩ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደርጋል)፣ በግዴለሽነት በያዝነው መንገድ እንቀጥላለን፤ በመጨረሻም እንደዚያችው የታካሚው እናት መደነቃችን አይቀርም።

ከዚህ የረቀቀ ስግብግብነት ጋር ተያይዞ፣ ሌሎችን እስከማራቅ ወይም እስከ ማናደድ የሚደርስ ከእነርሱ ከልክ በላይ የመጠየቅ ዝንባሌ ብዙ ጊዜ ይታያል። ጓደኝነት (የትዳር ግንኙነትም እንደ ተጠበቀ ሆኖ) ከእግዚአብሔር የተሰጡ እውነተኛ ስጦታዎች ናቸው፤ ነገር ግን እነርሱም የስግብግብነት ማረፊያዎችና መጠቀሚያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ከሰው ትልቅ ነገር መጠበቅ አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን በስግብግብነት ለተሞላ የደስታ ፍለጋ ሲባል፣ ከሌሎች (ለምሳሌ ከልጅ) ተገቢ ከሆነው በላይ መጠየቅ፣ ወይም ከእውነታው የራቀ ግምት መያዝ፣ ፍጹም የተለየ ነገር ነው።

ግን መልካም ዜና አለ። ስግብግብነት የልብ ጉዳይ እንደ ሆነ ቢታመንም፣ ብዙውን ጊዜ በሰውነታችን የተገደበ ነው። ከልክ በላይ ከበላን፣ ሰውነታችን ይህንኑ ያሳውቀናል። እያንዳንዱ ነገር እንዲስተካከልልን ከልክ በላይ የምንጨነቅ ከሆነ፣ ራሳችን እንድናደርገው እንገደዳለን፡፡ ከሌሎች ብዙ የምንጠብቅ ከሆነ፣ በዙሪያችን መሆን አይፈልጉም። እነዚህ ሁሉ ለለውጥ ሊያገለግሉን ይችላሉ። እግዚአብሔር ይመስገን፤ ለውጥ ይቻላል። በእርሱ መንፈስ ኀይል እንዲህ ያሉ ለውጦችን ማድረግ፣ ራስን መግዛትንና ጤናማ የሆነ ራስን መካድ መለማመድን እንችላለን፡፡

እኛ ክርስቲያኖች በሕይወታችን እንደ ዋና ግብ የምንቈጥረውን ማኅበራዊና ቁሳዊ ዕድገት በምናሳድድበት ጊዜ፣ ሳናስተውል የኅብረተ ሰባችንን “ትንሽ ተጨማሪ” የማግኘት ፍላጎትን ተቀብለነዋል። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች የተቀደሰ መልክ ያላቸው የስግብግብነት ኀጢአት ናቸው፤ በርግጥም የተከበሩ ኀጢአቶች ናቸው።