መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በእውነተኝነት የሚገልጥ መሆኑን እናምናለን?
ለምን ዝም ብላችሁ አብዮቱን አትቀላቀሉም? የሚለው መጠይቅ፣ ወግ አጥባቂ ክርስቲያኖችን በመመልከት በግብረ ሰዶማዊነት፣ በተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ፣ እንዲሁም በመላው የLGBT ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያለንን አቋም ለምን እንደማንቀይር በግርምት ለሚታዘቡ ሁሉ ትርጉም የሚሰጥ ይመስላል። የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጽ ትምህርት ችላ እንድንል በተደጋጋሚ ይነገረናል።
ነገር ግን ችግሩ የሚቀርበውን ሐሳብ አለመረዳታችን ሳይሆን ልንቀበለው አለመቻላችን ነው።
እውነት ነው፤ በርካታ ለዘብተኛ ቤተ እምነቶችና አብያተ ክርስቲያናት ለዚህ ወሲባዊ አብዮት እጅ ሰጥተዋል። ግብረ ሰዶማዊነትን ‘የማጽደቁ’ ሂደት መፋፋሙን ተከትሎ፣ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትና ቤተ እምነቶች እንቅስቃሴውን ተቀላቅለዋል፤ እንዲያውም አቀንቃኞች የሆኑም አሉ። በጽናት በመቃወም የጸኑ፣ ለጊዜው በመኻል ሰፋሪነት የቆሙና በግብረ ሰዶማዊነት ላይ ያላቸውን አቋም በግልጽ ለመናገር ያልደፈሩ ወይም ያልፈለጉ ቤተ እምነቶችና አብያተ ክርስቲያናትም አሉ። ግብረ ሰዶማውያንን ለአገልግሎት የመሾምና የማጋባት ጉዳዮችም፣ በበርካታ ቤተ እምነቶችና ማኅበሮች በተደጋጋሚ ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛሉ።
እኛ ግን ይህን አናደርግም፤ ምክንያቱም አንችልም! ከእነዚያ ለዘብተኛ አስተምህሮ ከሚከተሉት አብያተ ክርስቲያናት በተቃራኒ፣ ክርስትናን እንዳሻን ልናሻሽለው የምንችለው የአስተሳሰብ መንገድ እንደ ሆነ አንመለከተውም። መጽሐፍ ቅዱስን ከሚናገረው የተለየ መልእክት እንዲሰጥ ተደርጎ የሚተረጎም አልያም ወደ ጎን ሊባል የሚችል ጥንታዊ የእምነት ጽሑፎች የተጠረዙበት ስብስብ ብቻ አድርገንም አናየውም።
ይልቁንም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ እንደሚናገረው፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትና ሕጸጽ አልባ የሆነ መጽሐፍ አድርገን እንረዳዋለን። የክርስትና እምነትም በክርስቶስና በነቢያት፣ በሐዋርያትም በተገለጡና በቅዱሳት መጻሕፍት አማካይነት ለእኛ በደረሱን በግልጽ እውነቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንገነዘባለን። ክርስትና በመጽሐፍ ቅዱስ፣ “ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ [የ]ተሰጠው እምነት” ተብሎ መገለጹን እናምናለን።
በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ለ2ሺሕ ዓመታት ያስተማረቻቸውን እውነቶች በመያዛችን በተቃውሞ፣ በመገለልና መሳለቂያ በመሆን ውስጥ ራሳችንን እናገኘዋለን።
እውነታው ይህ ነው፤ ክርስትናን ከታሪካዊው የክርስትና አስተምህሮና የሥነ ምግባር ትምህርቶች ጋር አያይዘው የሚረዱ ክርስቲያኖች፣ እነዚህ ትምህርቶች እውነት መሆናቸውን ከማመን ባለፈ፣ እውነተኛና ዘላቂ የሰዎች ደስታ የሚፈልቅበትን ብቸኛ መንገድ የሚጠቁሙ መሆናቸውንም ያረጋግጣሉ። የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን የምንቃወመው ከቅዱሳት መጻሕፍት ተቃራኒ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚጻረር ማንኛውም ልምምድ ሰብአዊ ዕድገትን (ልምላሜን) የሚያከስም መሆኑን ስለምናምንም ጭምር ነው።
ወንጌሉ፣ ኀጢአቱን ለሚናዘዝ እንዲሁም ክርስቶስ የተሰቀለውና ከሞት የተነሣው ጌታ መሆኑን ለሚያምን ሁሉ፣ የድነትን ዋስትና ሰጥቷል። ነገር ግን የኀጢአትን ምንነት በትክክል ካልተረዳን ወይም አላግባብ ከተረጎምን፣ የክርስቶስን ሥራና መድኅን ፈላጊዎች የመሆናችንን ዕውቀት ዋጋ እናሳጣዋለን። በተጨማሪም፣ በወሲባዊ ግብረ ገብነት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ከተውን፣ ንስሓን በተመለከተ ራሳችንንም ሆነ ዓለምን ግራ እናጋባለን።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው አስተምህሯዊ እውነቶች ስብስብ ብቻ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርን የመፍጠር ታሪክ፣ የሰው ልጆችን ኀጢአት እውነታ፣ በክርስቶስ የተገለጠውን እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን የሚያድን ፍቅሩን፣ እንዲሁም ታሪክ ወደ የት እያመራ እንደሚገኝ የሚናገር መጽሐፍ ነው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህን ታሪክ ለመቀየርም ሆነ በተሳሳተ መንገድ ለመተረክ የሚደረግን ማንኛውንም ጥረት በተመለከተ ማስጠቀቂያ ሰጥቶናል። እውነት ነው፤ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመስበክ ፈንታ መጽሐፍ ቅዱስ “ልዩ ወንጌል” በማለት የሚጠራውን ትምህርት የማስተማርን ኀጢአት በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
በአሜሪካ ውስጥ የሚታየው ወቅታዊው ገጽታ፣ ወሲባዊ አብዮቱን ለመቀላቀል የተቻላቸውን እያደረጉ የሚገኙትን ብዛት ያላቸውን ለዘብተኛ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትና ከዚህ ጋር የማይስማሙ ብዛት ያላቸውን ወግ አጥባቂ አብያተ ክርስቲያናትን ያካተተ ነው። ክርስትና ለሁለት ሺሕ ዓመታት ሲያስተምረው የቆየውን ትምህርት እያስተማሩ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ወግ አጥባቂዎቹ መሆናቸውን ለመመስከር፣ የሚያስፈልገው ጥቂት ታማኝነት ብቻ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስን ባለ ሥልጣንነትና ታሪካዊውን የክርስትና እምነት በመያዝ መጽናት ለመገለል የሚዳርገን መሆኑ ተነግሮናል። ምናልባትም እውነት ነው፤ ነገር ግን ባለፉት ዐራት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ አባላትን በገፍ ለማጣት የተገደዱት ለዘብተኞቹ አብያተ ክርስቲያን ሲሆኑ ከእምነት ጋር እየተፋታ በሚገኘውም ዘመን ዓለማዊነትን የተቀበሉ ቤተ እምነቶች ከፍተኛ የአባላት ዕጦትን አስተናግደዋል።
ሰዎች ታሪክን በተመለከተ ሊሰጡ የሚችሉትን ብያኔ መገመት አያስቸግርም፤ ይሁን እንጂ ከዚያ ይልቅ ትኩረታችን መለኮት የሚሰጠው ዘላለማዊ ብያኔ ነው። እውነትን በፍቅር መናገርና ለሰዎች ሁሉ መልካም ባልንጀሮች ለመሆን መጣር ይኖርብናል፤ ነገር ግን በታሪክ ውስጥ መጥፎ ዘገባ እንደሚሰፍርልን ስለ ተነገረን ብቻ እምነትን አንተውም።
በግብረ ሰዶማዊነት ልምምድ ውስጥ ላሉት የሚኖረን ምላሽ በእውነተኛ ርኅራኄ የተሞላ መሆን አለበት። ቢሆንም ግን፣ የእውነተኛ ርኅራኄ ማዕከላዊ ኀላፊነት እውነትን መናገር ሲሆን ይህ ልንናገረው የሚገባን እውነተኛ መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጧል። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚያጣምሙና የሚቀይሩ ሰዎች ለግብረ ሰዶማውያን በርኅራኄ ምላሽ እየሰጡ አይደሉም። ሐሰት በፍጹም ርኅሩኄ ሊሆን አይችልም፤ በመጨረሻውም ወደ ሞት ይመራል።
በመጨረሻ፣ ቤተ ክርስቲያን ወይ እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል ታውጃለች፤ አልያም ደግሞ፣ ከዚያ ለመሸሽ መንገዶችን መፈለግ ትጀምራለች። ሁሉም የሚያጠነጥነው በእምነት ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ወሲባዊነትን አስመልክቶ እግዚአብሔር ስለሚፈልገውና ስለሚያዝዘን ነገር እውነተኛውን ነገር እንደሚነግረን እናምናለን? እንዲህ ከሆነ የት መቆም እንዳለብንና ምን መናገር እንዳለብን እናውቃለን ማለት ነው፤ አለበለዚያ ግን ግራ መጋባታችንን አምነን ምንም ዕውቀቱ እንደሌለን ለዓለም የምንናዘዝበት ሰዓት ነው ማለት ነው።