የብልጽግና ወንጌል ቤተ ክርስቲያንን እንዴት መለየት እንችላለን?

የብልጽግና ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ዘጠኝ መገለጫዎች

ከክርስቶስ ጋር የነበሩኝ የመጀመሪያዎቹን ዘጠኝ ዓመታት ያሳለፍኩት፣ በእንደዚህ ዐይነት አከባቢ ውስጥ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ያሉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በቀጣዩ ስድስት ዓመታት ለእረኝነት አገልግሎት ባዘጋጀኝ በሥነ መለኮታዊ ማገገሚያ ውስጥ አሳለፍኩ። የጤነኛ ቤተ ክርስቲያን ምልክት የሆኑት ዘጠኙ መገለጫዎች የብልጽግና ወንጌል የሚያስተምሩትን ጨምሮ ማንኛውንም ቤተ ክርስቲያን ለመመዘን የሚያስችል መስፈርት ማቅረብ እንደሚችሉ ግልጽ ሆኖልኛል።

እናም በግልጽ የምናገኘውም የብልጽግና ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ፀረ “ዘጠኙ መገለጫዎች” ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ነው።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አንዳንድ ምሳሌዎች ሁሉንም የሚገልጹ ላይሆኑ ይችላል። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ዓለም ዐቀፋዊና በበይነ መረብ፣ ራዲዮና ቴሌቭዥን ላይ በሚገኙ ሰባኪዎች የሚተላለፉ ናቸው። የብልጽግና ወንጌል በተለያዩ የሃይማኖት ወገኖች ውስጥ ሊገኝ የሚችል እንቅስቃሴ ስለ ሆነ፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተገለጹትን ትምህርቶች ከየትኛውም ወንጌላዊ ክርስትና ውስጥ ካለ የሃይማኖት ወገን ጋር መያያዝ የለበትም።

  1. ገላጭ[1] ስብከት

በብልጽግና ወንጌል አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚደረግ ስብከት ዐውዱን በጠበቀ መልኩ ከሚደረግ ስብከት እጅግ የራቀ ነው። ከዚያ በተቃራኒ የሚደረገው ስብከት ዐላማው አድማጮችን ገንዘብና ገንዘብ ነክ ነገሮችን እንዲሰጡ ለመገፋፋት ሲሆን ገንዘብ የሚሰጠውም ለማግኘት ነው። ሰባኪዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ዐሥራትና መባ የተጻፉ ክፍሎችን ሳምንቱን ሙሉ ያለአግባብ ይጠቀማሉ። ሰሚዎቻቸውን፣ ለእግዚአብሔር ስትሰጡት መልሶ ለእናንተ የሚሰጥበትን ሕግ ተጠቃሚ እንድትሆኑ በማለት “የእምነት ዘር” በመዝራት እምነታቸውን እንዲቀሰቅሱ እያስተማሩ የራሳቸውን ገንዘብ ያካብታሉ።

እግዚአብሔር በእምነት ለሚደረግ ስጦታ ስለሚሰጠው ምላሽ፣ ተነጥለው ከተወሰዱ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ እየወሰዱ እንደ ምሳሌ ይጠቀሙታል። ሚልክያስ 3፥10 ሰሚዎቻቸውን እንዲሰጡ ለማምታታት ደጋግመው ከሚጠቀሙባቸው ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነው። የብልጽግና ሰባኪዎች ከዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት ነገሮችን አጉልተው ያሳያሉ። በመጀመሪያ አድማጮቻቸውን ዐሥራት ባለመስጠታቸው እግዚአብሔርን እየዘረፉት እንደ ሆነ ይነግሯቸዋል። በሁለተኝነት ደግሞ፣ አድማጮቻቸውን እግዚአብሔር የበለጠ እንዲሰጣቸው የበለጠ በመስጠት እንዲፈትኑት አጽንኦት ሰጥተው ይነግሯቸዋል።

ነገር ግን ሚልክያስ 3፥10ን በትክክለኛ ዐውደ ንባቡ ውስጥ አስገብተን ማየት አለብን። እስራኤላውያን፣ የእስራኤል ካህናትን ለመመገብ ወደሚውለው ብሔራዊ ግምጃ ቤት በቂ ምግብ ባለመስጠት እግዚአብሔርን እየዘረፉት ነበር። ከዚህም የተነሣ ካህናቶቹ የክህነት ሥራቸውን ትተው፣ ለመኖር ሲሉ ወደ ግብርና መሄድ ነበረባቸው (ነህምያ 13፥10-13) ። ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በመታዘዝ እንዲሰጡትና እንዲፈትኑት አጥብቆ ተናገራቸው። እንዳላቸው ቢያደርጉ በፊት ያደርገው እንደ ነበረ ዋጋቸውን ይከፍላቸዋል (2 ዜና መዋዕል 31፥7-10)። የሙሉ ክፍለምንባቡ ሐሳብ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ አንድ የተወሰነ ምዕራፍን የሚመለከት ነው። እንደ ክርስቲያናዊ ትምህርት ይህን ክፍል ማስተማር፣ በውስጡ ያሉትን ትእዛዞችና ተስፋዎች አንድ በአንድ በግለ ሰብ ደረጃ ወደ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከማስተላለፍ ያለፈ ነገር ያስፈልገዋል። ምንም እንኳ ስለ መስጠት ለክርስቲያኑ የሚሆን ከፍ ያለ ትርጉም ቢኖረውም፣ በመጀመሪያ ግን በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል ላለው ልዩነት፣ በተለይም እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጣቸው ተስፋዎች ባሕርይና እንዴት አድርገው በክርስቶስ በኩል ለክርስትያኖች እንደ ተፈጸሙ ቦታ መስጠት ያስፈልጋል።

ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን ስብከትን የምትጠቀምበት የእግዚአብሔርን ቃል ለሰዎች ለማስተማር ነው። ሰሚዎቹን በእግዚአብሔር ቃል በመሞገት እንዲቀበሉት፣ እንዲበረቱ፣ እንዲረዱትና እንዲተገብሩት ይመራቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል በመታዘዝ ለሚኖር አማኝ ምን ያህል ዋነኛና አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት እያንዳንዱ ንባብን በወንጌል ዙሪያ ያደርጋል። ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን አማኞችን የተቀደሰ አኗኗር የግድ የሚያስከትለው ገንዘብና ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ጥቅሞችን ሳይሆን ጌታን የሚያከብር እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንደ ሆነ ያሳውቃቸዋል።

  1. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮት

የብልጽግና ወንጌል ነገረ መለኮት፣ ቃላቶቻችን የእግዚአብሔር ቃላቶች ያላቸውን ዐይነት የመፍጠር ኀይል እስከሚኖራቸው ድረስ ሰው የሆነ ዐይነት መለኮትነት ከእግዚአብሔር ይካፈላል በሚለው መሠረታዊ ስሕተት ላይ የተገነባ ነው። ለዚህም ውሸት በመደገፊያነት የሚቀርቡት ታዋቂ ክፍሎች መዝሙር 82፥6ምሳሌ 18፥20-21ሮሜ 4፥17 ናቸው። በተደጋጋሚ ሰው “ትንሹ አምላክ” እንደ ሆነ ደግሞም ያልነበሩ ነገሮችን ወደ መኖር በመጥራት፣ በመፍጠር፣ ፍጻሜያችንን በቃላት በመቆጣጠርና ተስፋ ያጣና ውሱን የሆነን አምላክ ለኛ ጥቅም በእኛ ቦታ እንዲንቀሳቀስ በማስተዳደር፣ አምላክነትን ማሳየት የምንችልበት ኀይል እንዳለን ይነገራል።

ነገር ግን የትኛዎቹም በማስረጃነት የቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህን የብልጽግና ወንጌል አስተምህሮ አይደግፉም። በመዝሙር 82፥6 ላይ መዝሙረኛው በእስራኤል አገር ላይ እየገዙ ስለ ነበሩት ግብረ ገብነት ስለ ጎደላቸው ገዢዎች ወደ እግዚአብሔር እያለቀሰ ነው። እግዚአብሔርም በእርሱ ቦታ ሆነው አገሪቱን እየገዙ መሆኑን አጉልቶ ለማሳየት ጥፋት እያጠፉ ያሉትን ገዢዎች “አማልክት” ብሎ በቀጥታ ያናግራቸዋል። የእርሱን ቃል ለአገዛዛቸው እንደ መስፈርት ሊጠቀሙበት ይገባ ነበር። ቀጥሎ ባለው ክፍል ውስጥ ዘላለማዊ ፍጥረታት እንዳልሆኑ ያስታውሳቸዋል። ይልቁንም በጽድቅ ከመኖርና ከማስተዳደር የጎደሉ ተራ ሰዎች ብቻ ናቸው። ይህ ክፍል የሚናገረው፣ ሰውን ወደ ግማሽ አምላክነት ከፍ ስለ ማድረግ አይደለም። ሰውን ሉዓላዊ በሆነ ሥልጣን ማንቀሳቀስ የሚያስችል ዐቅም ስለ መስጠትም አይደለም። ይልቁንም ብቻውን እውነተኛና ሕያው የሆነው አምላክ የእነዚህ ገዢዎችን ግብረ ገብነት የጎደለውን ሥራቸውን እየፈረደበት ነው።

ምሳሌ 18፥20-21 መርሕ ነው እንጂ ተስፋ አይደለም፤ እናም ሁለት እውነቶችን አውጥቶ ይገልጻል። የመጀመሪያው ቃላቶቻችን ልባችን ያለበትን ሁኔታ ያሳያሉ እንጂ ፍጻሜያችንን አይቆጣጠሩም። በሁለተኛነት ደግሞ ቃላቶቻችን የሚያስከትሉትን ነገር እንድንቀበል የሚያደርጉበት ጊዜ ይመጣል። ይህ ክፍል የሕይወታችንን ርዝማኔ በማወጅ ቃል ኀይል መኖሩን ተስፋ አይሰጠንም። አንዳንድ የብልጽግና ሰባኪዎች እንደሚያስተምሩትም፣ ራሳችንን እስከ ሞት ድረስ ብንረግምም እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ኀይል እንደሌለውም አይናገርም።

ሮሜ 4፥17 ጳውሎስ፣ እግዚአብሔር አብርሃምን ገና ልጅ ባልነበረው ጊዜ እንዳጸደቀውና የሕዝቦች አባት እንደሚሆን እንደ ተናገረው ያስተምረናል። ይህ ክፍል ቅዱሳን ተጨማሪ ገንዘብ፣ የሥራ ዕድገት፣ ወይም ጠፍተው ያሉ የሚወዷቸውን ሰዎች ደኅንነት ከማምጣት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ይልቁንም ይህ ክፍል እግዚአብሔር ብቻ ያልነበረን ነገር ወደ መኖር መጥራት የሚችል የመሆኑን እውነት የሁሉ የበላይ አድርጎ የሚያስቀምጥ ነው።

ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተተከለና ዐውደ ንባቡን የጠበቀ ጤናማ አስተምህሮ አባላቶቿን ታስተምራለች። ጤናማ አስተምህሮ ለሰሚዎቹ በክርስቶስ ለማደግ የሚያስፈልጉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንጥረ ነገሮችን ማቅረብ የሚችል ጤነኛ ትምህርት ነው (2 ጢሞቴዎስ 3፥16-17)። ቤተ ክርስቲያን ጤነኛ መሆን እንድትችል መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስተምሩ የተወሰኑ ክፍሎችን ከዐውደ ንባባቸው ነጥሎ በማውጣት ሳይሆን በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ዐውደ ንባብ ውስጥ አድርገውና ሁሉንም አስተምህሮአዊ እምነቶቻቸውን በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተክለው መሆን አለበት (1 ጢሞቴዎስ 1፥5ቲቶ 2፥1-102 ዮሐንስ 1-6 )።

  1.  ወንጌሉ

በብዙ የብልጽግና ወንጌል አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የወንጌሉ መልእክት በአብርሃም ቃል ኪዳን ውስጥ ካሉት ቁሳዊ በረከቶች ጋር አንድ ተደርጎ ይታያል። ምንም እንኳ የክርስቶስ ፍጹም ሕይወት፣ ሞት፣ መቀበርና ትንሣኤ ቢታወጅም ደግሞም በክርስቶስ በኩል ያለ ደኅንነት የሁሉ የበላይ ተደርጎ ቢነገርም፣ ብዙ የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች፣ የአንድ ሰው በወንጌል የማመኑ ማስረጃ እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃል የገባውን በረከት መቀበሉ ነው ይላሉ (ዘፍጥረት 12-15)።

ይህ ትምህርት ሰዎችን ከሁለት መደምደሚያዎች ወደ አንዱ ሲመራ ተመልክቻለሁ። አንድ ሰው ሀብትና ጤና ካለው፣ የአብርሃምን ተስፋ ቃል ስለ ተቀበለ ድኛለሁ ብሎ ርግጠኛ ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ በረከቶች በአማኙ ሕይወት የማይታዩ ከሆነ፣ በቂ እምነት የላቸውም ማለት ነው። በኀጢአት ውስጥ ናቸው። ተጨማሪ ዐሥራት መስጠት አለባቸው። ወይም ደግሞ ምናልባት በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ለሙሉ አላመኑም፤ ደግሞም የአብርሃምን በረከቶች ለመቀበል ዳግም መወለድ አለባቸው።

ከዚህ በተቃራኒ ጤነኛ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወንጌል ባለማፈር ያውጃሉ። ይህም በእግዚአብሔር አምሳል የመፈጠራችንን እውነት (ዘፍጥረት 1፥26-27)፣ በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደ ነበረን (ዘፍጥረት 2፥7-25)፣ ሆኖም ግን የፊተኛው አባታችን አዳም ኀጢአት በመሥራቱ ምክንያት ሙሉ የሰው ዘር በአካል (ዘፍጥረት 3፥1-19)ና በመንፈስ (ሮሜ 5፥12) ከፈጠረን ቅዱስ ና ጻድቅ ከሆነው እግዚአብሔር መለየቱን ያካትታል። በኀጢአት ምክንያት የሰው ዘር ከእግዚአብሔር ስለ ተለየ፣ ለኀጢአት ቤዛ ክፍያው የደም መፍሰስና ሞት ነው (ዘሌዋዊያን 1፥3-17)። የወንጌል ውበቱ ከዘላለም እስከ ዘላለም እግዚአብሔር ሆኖ የሚኖረው (ዮሐንስ 1፥1) ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የመምጣቱ (ዮሐንስ 1፥14)፣ በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት ፍጹም ሕይወት የመኖሩ (ዕብራውያን 7፥26)፣ ደግሞም በኀጢአተኞች ምትክ ሲሞት ደሙን የማፍሰሱ (ማርቆስ 10፥451 ጴጥሮስ 2፥24) እውነት ነው። ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ ለሦስት ቀን ተቀብሮ ነበር (ማቴዎስ 27፥57-66)፤ በሦስተኛውም ቀን ከመቃብር ተነሣ (ማቴዎስ 28፥1-8)። ደግሞም አሁን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁና የዘላለም ሕይወትን እንዲቀበሉ፣ ሁሉንም ሰዎች ከኀጢአታቸው እንዲናዘዙ፣ በእርሱም እንዲያምኑ ይጠራቸዋል (ዮሐንስ 3፥16)።

መጽሐፍ ቅዱሳዊው ወንጌል፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም ከሰጠው ቃል ኪዳን መፈጸም የተነሣ በዚህ የሕይወት ዘመን ክርስቲያኖች ሀብታምና ባለ ጠጋ ይሆናሉ ብሎ ቃል አይገባም። ይልቁንም ክርስቲያኖች በአብርሃም በኩል “የምንባረከው” መንፈስ ቅዱስን በመቀበል (ገላቲያ 3፥14)ና በሚመጣው ዘመን መሬት ብቻ ሳይሆን አዲሱን ፍጥረትን በሙሉ በመቀበል ነው (ሮሜ 4፥13ራእይ 21-22)።

  1. የሕይወት መለወጥ

የሕይወት መለወጥ በብልጽግና ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች ግራ የሚያጋባ ድብልቅ ነው፤ ይህም በቀላሉ የማመንና በሥራ የመዳን ነው። የብልጽግና ሰባኪዎች ኀጢአተኛ “የሚድነው” “የኀጢአተኞች ፀሎት”ን ብሎ ሲጨርስ ነው እያሉ በማስተማር ይታወቃሉ። ይህ ቀላል ደኅንነት ከተከናወነ በኋላ አዲሱ አማኝ ራሱን ለቤተ ክርስቲያኗ አመራርና ትምህርት ማስገዛት፣ ሁልጊዜ ዐሥራት መክፈል፣ በአብዛኛው መባ መስጠትና በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በቀጣይነት ለማገልገል መጣር አለበት። ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ማድረግ እስከ ቀጠለ ድረስ ደኅንነቱን ያስጠብቃል። ነገር ግን እነዚህን ነገሮች ረዘም ላለ ጊዜ ካቆማቸው ደኅንነቱን ሊያጣው ይችላል። ይህን ትምህርት ለማስፋፋት መሪዎች የተለያየ ዐይነት ሥነ ልቦናዊ ዘዴዎችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጠቀም ለጌታ በሚል ስም የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያደርጉ የቤተ ክርስቲያን አባላቶቻቸውን በማምታታትና በመበዝበዝ ይታወቃሉ። አገልግሎታቸው “ከፀጋ እንዳይወድቁ “ ና ደኅንነታቸውን እንዳያጡ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ቃል ይገባላቸዋል።

አንዳንድ የብልጽግና ወንጌል ተከታዮች ይደክማቸውና በመሪዎቻቸው ላይ ይናደዳሉ። እያገለገሏቸው ያለበትን መንገድ መጠየቅና የሚጠይቋቸውን ነገር ሁሉ ለማድረግ እምቢ ማለት ይጀምራሉ። በእንደዚህ ዐይነት ሰው ላይ ያላቸውን ቁጥጥር እያጡ እንደ ሆነ የተሰማቸው መሪዎች ያ አባል በዐመፅ ውስጥ እንዳለ፣ መከፋፈልን እየፈጠረ እንዳለ ደግሞም ካልተናዘዘና እንደ ገና ማገልገል ካልጀመረ ደኅንነቱን በማጣት መንገድ ላይ እንዳለ በመናገር መልስ ሲሰጡ ዐይቻለሁ። በእንደዚህ ዐይነት አጋጣሚዎችም እንድ ሰው የወሰደውን ርምጃ ፍሬዎች ለመጠቆምና ሌሎች እንዳይከተሉት ለማነሣሣት 1 ሳሙኤል 15፥23 ለድጋፍ የሚቀርብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆኖ ይውላል። ነገር ግን ይህ ክፍል የሚያወራው ስለ ንጉሥ ሳኦል በቀጥታ እግዚአብሔርን አለመታዘዝ እንጂ ስለ አንድ እውነተኛ አማኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ አስተምህሮዎችና የቤተ ክርስቲያን ልምምዶች ላይ ጥያቄ ማንሣት አይደለም።

ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስለ ሆነው የሕይወት ለውጥ በፍቅር ታስተምራለች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናነበው የሕይወት ለውጥ የሚካሄደው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው ወንጌል ሲሰበክ (ሮሜ 1፥16-1710፥9-17)ና ኀጢአተኛው ኀጢአቱን ሲናዘዝ ደግሞም እምነቱን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሲያደርግ (ሐዋርያት ሥራ 3፥19ሮሜ 3፥21-26) ነው። የሕይወት ለውጥ የሚካሄደው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በኀጢአት ምክንያት ሙት የሆነውን ኀጢአተኛ በክርስቶስ ሕያው ሲያደርገው ነው (ዮሐንስ 3፥3-8ኤፌሶን 2፥1-10) ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሕይወት ለውጥ አትኩሮቱን የሚያደርገው በመናዘዝና በክርስቶስ ሥራ በማመን ላይ እንጂ እንዲሁ የሆነ ፀሎትን በማድረግና ደኅንነትን በማጣት ፍርሀት ድካም ላይ እስኪወድቅ ድረስ በማገልገል ላይ አይደለም።

  1. ወንጌልን ማካፈል

የብልጽግና ወንጌል አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ጊዜ ወንጌልን ማካፈል ተዓምራትና ድንቅን ዐብሮ ከማሳየት ጋር መሆን አለበት ብለው ያስተምራሉ። እነዚህ ሁለት ነገሮች ሲጣመሩ ኀጢአተኞች ይናዘዛሉ ደግሞም በኢየሱስ ያምናሉ ይባላል። ወንጌልን ከማካፈል በፊት ባለው የፀሎት ጊዜ ልክ በማርቆስ 16፥15-16 እንደ ተዘረዘረው ኀጢአተኞች የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ተዓምራታዊ ሥራ ካላዩ ከኀጢአታቸው እንደማይናዘዙ ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ።

የዚህ ክፍል የመጀመሪያዎቹናና የጥንቶቹ ይበልጥ የታመኑት ቅጂዎች ውስጥ መኖር አለመኖሩ አከራካሪ ስለሆነ ያለንን አስተምህሮአዊ አቋም በዚህ ክፍል ላይ ብቻ መገንባት ብልህነት አይደለም። ከዚያ በተጨማሪም ሰዎች በወንጌል ማካፈል ስኬታማ እንዲሆኑ በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱትን ምልክቶች ማሳየት አለባችሁ ማለት አደገኛና አምታች ነው።

መጽሐፍ ቅዱሳዊው ወንጌልን ማካፈል ወንጌሉን ማወጅና ኀጢአተኞችን ወደ ንሰሓ መጥራት ነው። ወንጌሉ ውጤታማ ለመሆን መሻሻሎች፣ ቃጭሎች ወይንም ፊሽካዎች አያስፈልጉትም (1 ቆሮንቶስ 15፥1-4)። የተሰበከው ወንጌል ኀጢአተኞችን ለማዳን ኀይል እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ነው (ሮሜ 1፥1610፥17)።

  1. የቤተ ክርስቲያን አባልነት

የብልጽግና ወንጌል አብያተ ክርስቲያናት መደበኛ አባልነት ኖረዉም አልኖረውም የቤተ ክርስቲያን አባልነትን ከዘወትር መገኘት፣ ዐሥራት ከማውጣትና ከማገልገል ጋር እኩል ያደርጉታል። እነዚህን ነገሮች ለረጅም ጊዜ ካደረጓቸው ወደ ቤተ ክርስቲያኗ አባልነት “የልጅ ልጅነት” ይካተታሉ። በአንድ አጋጣሚ ለሃያ ዓመታት ያህል አንዲት ቤተ ክርስቲያን ይሄድ የነበረ፣ የአባልነት ጥቅሞችን ያገኝ የነበረ ነገር ግን ደንቡን በጠበቀ መልኩ ቤተ ክርስቲያኗን ያልተቀላቀለ ሰው ትዝ ይለኛል። ገንዘባቸውን ስለሚሰጡና በየሳምንቱ ስለሚያገለግሉ ጥቅሙ አይታያቸውም። እንዲህ ዐይነት ሰዎች ለሁሉ በተገለጠ ኀጢአት ሲኖሩና የቤተ ክርስቲያንን ተግሣጽ ሲሸሹ አይቼአለሁ።

ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን አባልነትን ለአማኞች እንደ በረከትና ኀላፊነት ታቀርባለች። በረከቱ ቤተ ክርስቲያን የአማኙን እምነት ማጽናቷና አማኙን በፍቅር መገንባቷ ነው (ኤፌሶን 4፥11-16)። ኀላፊነቱ ደግሞ ኢየሱስ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥልጣን በመገዛት ለእርሱ ሥልጣን እንዲገዙ ክርስቲያኖችን ማዘዙ ነው። በቀላሉ እንደፈለግህ መለየት የምትችል ከሆነ፣ የእውነት የዚያ አካል አባል አይደለህም ማለት ነው።

  1. የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ

በብልጽግና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ በሁለት የተራራቁ ሐሳቦች ላይ ሲያርፍ አስተውያለሁ። የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አካሄድን ያልጠበቀ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽና ደንቡን ያልጠበቀ ውግዘት ነው (ማቴዎስ 18፥15-171 ቆሮንቶስ 5፥1-132 ቆሮንቶስ 2፥62 ተሰሎንቄ 3፥6-15)። በኀጢአት በመመላለስ በመቀጠላቸው ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን፣ በግል “ከኅብረቱ የተገለሉት” ግለ ሰቦች፣ በአደባባይ ግን በዐመፃቸው ምክንያት ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ሊኖረን የማይገባ ሰዎች ተብሎ ይነገርላቸዋል።

ሁለተኛው ከልክ የሚያልፍ የራቀ ሐሳብ ደግሞ የቤተ ክርስትያን መሪዎች የአንድ መሪን ወይም ታዋቂ አባልን ወይም የሁለቱንም ኀጢአት ሙሉ ለሙሉ ችላ ማለት ነው። ይህን አካሄድ ሲከተሉ የዛን ግለ ሰብ ንሰሓ ባለመግባት በኀጢአት ውስጥ መመላለስ መቀጠል የሚያውቁ መሪዎች ዕውቅና ከመስጠትና ርምጃ ከመውሰድ በፈቃዳቸው እምቢ እያሉ ነው። ስለ ሌሎች አባላት ኀጢአት አንሥተው ሲያወሩ፣ “እግዚአብሔር ይቅር ይላል ደግሞም ፍቅሩ ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናል” እንዲሁም “ፈራጅ እግዚአብሔር ብቻ ነው ” በማለት የሚናገሩ መሪዎችና አባላት አይቼ ዐውቃለሁ። በኀጢአት እየተመላለሱ በአገልግሎት ስለሚቀጥሉ አገልጋዮች ደግሞ ሮሜ 11፥29 ን በማጣመም “የእግዚአብሔር ስጦታ ጸጸት የለበትም” ይባላል። የብልጽግና ሰባኪዎች ከጉባኤያቸው አባላት የሚነሡ ጥያቄዎችን ለማሸሽ ( ”የቀባኋቸውን አትንኩ፤ በነቢያቴ ላይ ክፉ አታድርጉ”) 1 ዜና 16፥22ን ብዙ ጊዜ ይጠቀማሉ። አንዳንድ ጊዜ በ 1 ጢሞቴዎስ 5፥17-20 ላይ የተጻፈውን በማድረግ ፈንታ የብልጽግና ወንጌል አብያተ ክርስቲያናት የመሪውን ኀጢአት በመሸፈንና ዕረፍት በማስወጣት ይታወቃሉ።

ጤነኛ አብያተ ክርስቲያናት ለንጹሕና ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ያለውን ፍላጎት ይቀበላሉ። ሕዝቦቻቸውን ክርስቶስን ወደ መምሰል እንዲያድጉ ሲረዱ በዓለም ውስጥ እንደ ከዋክብት ያበራሉ (ኤፌሶን 4፥11-32ፊልጵስዩስ 2፥1-18)። መሪዎች ከፈተና፣ የተሳሳተ ወሳኔ ከመወሰንና ከኀጢአት ውጪ እንዳልሆኑ ጤነኛ አብያተ ክርስቲያናት ይረዳሉ። ስለዚህም ጤነኛ አብያተ ክርስቲያናት፤ መሪዎችን መገሠጽን ጨምሮ ለቤተ ክርስቲያናዊ ተግሣጽ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዘውን ነገር ያስተምራሉ ደግሞም ይከተላሉ (1 ጢሞቴዎስ 5፥17-20)።

  1. ደቀ መዝሙርነት

በብልጽግና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደቀ መዝሙርነት ብዙ ጊዜ ከመጋቢው ወይም ከሌላ ዋነኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ጋር ወዳለ ጤነኛ ወዳልሆነ የእርስ በርስ ጥገኝነት ያመዝናል። የደቀ መዝሙርነት የመጀመሪያው ደረጃ “ጋሻ ጃግሬነት” ደረጃ ተብሎ ይታወቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጋሻ ጃግሬ የመሪዉን መሣርያ የሚሸከምና መሪውን የሚጠብቅ ነበር (1 ሳሙኤል 14፥6-72 ሳሙኤል 18፥15)። በብልጽግና ወንጌል አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ግን ጋሻ ጃግሬነት ይፋዊ ያልሆነ አገልግሎት ሆኗል። ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ጉዞ ማደግ የሚፈልጉ አዲስ የተለወጡ ሰዎች በቡድን ይደረጋሉ። ይህ ቡድንም የመጋቢዉን ወይም የቤተ ክርስቲያን መሪውን የስሜት፣ የአካልና የመንፈስ ፍላጎቶች ለማገልገል ይሠለጥናሉ። መጋቢው፣ ጋሻ ጃግሬዎቹን መጽሐፍ ቅዱሱን ከመሸከም ጀምሮ የተለያዩ ክፍያዎቹን እስከ መክፈል ድረስ በ “አገልግሎት” ስም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፉ ኀላፊነት ይሰጣቸዋል። አንዳንድ ወጣ ባሉ ሁኔታዎች ድሮ ጋሻ ጃግሬ የነበሩና መጋቢው ከሰበከ በኋላ እንዲያሹት አንዳንዴ ደግሞ ጭራሽ ፆታዊ ጥቅም እንዲሰጡት ይጠየቁ የነበሩ ሰዎችን የምክር አገልግሎት ሰጥቼ ዐውቃለሁ።

ጋሻ ጃግሬዎች በተጣለባቸው ኀላፊነት ውስጥ መቆየት ከቻሉ ከማዕረግ፣ የመስበክ ፈቃድና ሹመት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ዕድገቶችን ማግኘት ይችላሉ። በአብዛኛው ጊዜ መጋቢው ይህን የሚያደርገው፤ እነዚህ የሚሾሙ ወንዶች ( እና አንዳንዴ ሴቶችም) መጋቢው ሲሰብክ ከፊት ቁጭ ብለው ድጋፋቸውን ስለሚገልጡለት፤ የአገልግሎቱን የቁጥር ዕድገት ለመደገፍ ነው። አንዳንድ መጋቢዎች በሥራቸው ለዐሥርት ዓመታት ያህል የተሾሙ ወንዶች ቁጭ ብለው እንደ ተማሩ ተኩራርተው ሲያወሩ ሰምቼ ዐውቃለሁ። ከስንት አንዴ ነው እነዚህ የተሾሙ አገልጋዮች ቤተ ክርስቲያን እንዲተክሉ፣ እየሞቱ ያሉ አብያተ ክርስትያናትን እንዲያነቃቁ ወይም በሩቅ አገር በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት እንዲሳተፉ የሚላኩት። በሚያሳዝን ሁኔታ በአንድ አጋጣሚ ለዐሥራ ዐምስት ዓመታት ከአንድ መጋቢ ሥር እንደ ተሾመ አገልጋይ የቆየ ነገር ግን አንድ ጊዜም እንኳ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሊያሟላው ስለሚገባው ነገሮች ተምሮ የማያውቅ ሰው የምክር አገልግሎት ሰጥቼ ዐውቃለሁ።

ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን ምዕመኖቿን በመጋቢው ወይም በመሪው ላይ ሳይሆን በኢየሱስ ላይ ይበልጥ እንዲደገፉ ታስተምራለች። አማኞች የሚያድጉት ስለ ኢየሱስ ያላቸውን ዕውቀት ሥር በመስደድ (2 ጴጥሮስ 3፥18) እና በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ኢየሱስን በመምሰል (1 ቆሮንቶስ 4፥1611 ፥1ኤፌሶን 5፥1) ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ደቀ መዝሙሮች ጥገኞችን ሳይሆን የሚያፈሩት ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ደቀ መዝሙሮችን ነው (2 ጢሞቴዎስ 2፥2ቲቶ 2፥1-8)።

  1. የቤተ ክርስቲያን አመራር

የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች አባላቶቻቸው በመጋቢያቸው ውክልና በኩል ስለሚኖሩ ከምዕመኖቻቸው የማያቋርጥ ድጋፍ ያገኛሉ። የመጋቢያቸው የአገልግሎት አድማስ ሲሰፋና ሀብቱ እየጨመረ ሲመጣ ምዕመኖቹ ደስ የሚሰኙት ብልጽግናው የራሳቸው የሆነ ያህል ነው። አንዳንድ ጉባኤዎች የእግዚአብሔር በረከት ወደ እነርሱም እየወረደ እንዲመጣ መጋቢያቸው አለ የተባለ አዲስ ስሪት መኪና እንዲኖረው፣ ውድና ስመጥር የሆነ ልብስ እንዲለብስ ደግሞም በትልቅ ቤት ውስጥ እንዲኖር ይፈልጋሉ። አንድ ጊዜ፣ “መጋቢዬ በከፍታ የሚኖር ከሆነ፣ ለእኔና ለቤተ ሰቤ በከፍታ እንድንኖር መንገድ እየጠረገልን ነው።“ ተብሎ ተነግሮኛል።

አብዛኛውን ጊዜ መጋቢው ለጉባኤው የእግዚአብሔር ድምፅ እንደ ሆነና ስለዚህም ሥልጣኑ እንደማይጠየቅ ይነገራል። የአመራር መዋቅሩ በዋና ሥራ አስኪያጅና በንጉሣዊ አገዛዝ መኻል ነው። ሌሎች መጋቢዎችና ሽማግሌዎች የሚመረጡት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሊያሟሏቸው በሚገባቸው መስፈርቶች ላይ ተመሥርተው ሳይሆን፣ ከመጋቢው ጋር ባላቸው ቅርበትና በሥራቸው ዐይነት እንደ ሆነ ብዙ ጊዜ ተመልክቻለሁ።

ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የበቁ መሪዎችን ከፍተኛ ቦታ ትሰጣለች። 1 ጢሞቴዎስ 3፥1-7 እና ቲቶ 1፥5-9 የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ሊመሩ የሚገባቸው ወንዶች ሊያሟሏቸው የሚገቧቸውን መስፈርቶች በግልጽ ይዘረዝራሉ። መስፈርቶቹ ትኩረት የሚሰጡት፣ የሰውየውን የሥራ ዐይነት ወይም ከመጋቢው ጋር ስላለው ጓደኝነት ሳይሆን፣ ስለ ሰውየው ባሕርይ ነው። መሪዎች ያለባቸው ኀላፊነት መንጋውን መጠበቅ፣ ጤነኛ አስተምህሮ መመገብ፣ በትሕትና መምራትና ከስሕተት አስተማሪዎች መከላከል ነው።

እረኛ የሌላቸው በጎች

ከላይ በተዘረዘሩት በሁሉም ወይም በአንዳንዶቹ አስተምህሮዎች ሥር ላሉ ሰዎች በልቤ ጥልቅ ሐዘን አለ። ኢየሱስ እንዳዘነላቸው እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው እንደ ነበሩት ናቸው (ማቴዎስ 9፥36)። በኢየሱስ ጊዜ የነበሩት እነዚህ ውድ ነፍሳት ያለአግባብ መጠቀሚያ ሆነው፣ ተጨንቀውና በመሪዎቻቸው እየተቸገሩ ነበር። የራሳቸው የሃይማኖት መሪዎች እንደዚህ እያደረጓቸው ስለ ነበር ሌላ የሚያውቁት የሕይወት ዘይቤ አልነበረም። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የመከሩ ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ እንዲጸልዩ በመንገር መልሶላቸዋል።

በአሁን ዘመን ተበትነውና ተጨንቀው ላሉት በጎች ያለኝ ጥልቅ ሐዘን ሁለት ነገሮችን እንዳደርግ ይገፋፋኛል። እነዚህን ተበትነው ያሉ በጎችን የሚፈልጉና የሚያገለግሉ ሠራተኞችን እንዲልክ ወደ ጌታ እንድጸልይና በእኔ ከተማ ውስጥ ያሉ በጎችን መድረስ እችል ዘንድ፣ ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን ለመምራት መትጋት ነው። ይህ ጽሑፍ በዓለም ዙሪያ ባሉ ከተሞች ውስጥ ጤነኛ አብያተ ክርስቲያናት ሲበዙ ማየትን እንድትፈልጉ በልባችሁ ውስጥ እሳትን ለመጫር እንዲያገለግል ጸሎቴ ነው።

ዲ. ኤ. ሆርተን


[1] የስብከት ንባቡን ዐውድ በመጠበቅ የሚደረግ ማብራሪያ