የመሞቻው ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ፣ ይጠብቃቸው ከነበረው ቀውስ የተነሣ ኢየሱስ ትኩረቱን በይበልጥ የደቀ መዛሙርቱን ደስታ ማረጋጋት ላይ አድርጎት ነበር። በዮሐንስ 16፥4-24 ላይ የደስታቸው ጠንቆች የሆኑን ሁለት ነገሮች በማንሣት ይናገራል። አንደኛው፣ ትቶአቸው ወደ አብ ሊሄድ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቅርቡ በሞት ሊለያቸው መሆኑ ነው። ሁለቱም ዘላቂ ደስታን የሚቀንሱ ይመስላሉ።
ኢየሱስ ለተፈጠረባቸው ግርታ መልስ ሲሰጥ ምዕተ ዓመታትን ተሻግሮ የእኛንም የሚፍገመገም ደስታ በሚያረጋጋ መንገድ ነበር። ይህ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም። ለማድረግ የፈለገውም ይህንኑ ነው፤ “ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ” (ዮሐንስ 15፥11)።
ሐዘናችሁ ለጥቂት ጊዜ ነው
የመጀመሪያው ነገር፣ ትቶአቸው ሊሄድ ነው። ይህ ደግሞ ለመስማት ደስ የሚል ዜና አይደለም። “እንግዲህ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ . . . . ይህን በመናገሬም ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል” (ዮሐንስ 16፥5-6)። ይህ ሐዘን ከፍቅር እና ከአላዋቂነት የመነጨ ነው። በእርሱ ደስ ይላቸው ስለ ነበር ከፍቅር የመነጨ ነው። እንዲሁም በአካል ከእነርሱ መለየቱ ለእነርሱ የሚበጅ እንደሚሆን ስለማያውቁ ከአላዋቂነት የመነጨ ነው።
ስለዚህ ኢየሱስ ከእነርሱ ቢለይም ደስታቸውን ግን ለማጠናከር የፈለገው ፍቅራቸውን በመቀነስ ሳይሆን አላዋቂነታቸውን በማስወገድ ነበር። እንዲህ ይላቸዋል፤ “ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ” (ዮሐንስ 16፥7)። መሄዱ ለደቀ መዛሙርቱ የሚበጅ ከሚሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው፣ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ክብር ይበልጥ ጉልህ ስለሚያደርገው ነው። አዎን፤ በሥጋ ቢገኝ ከሚሆነው በላይ ጉልህ ያደርገዋል፤ “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። . . . . የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው” (ዮሐንስ 16፥13-15)።
ይህ አስደናቂ ነው። ለደቀ መዛሙርቱም ሆነ ለእኛ ያለውን ትርጒም ተመልክተን ይሆን? “ምነው እዚያ ተገኝቼ ፊት ለፊት ባየው ኖሮ!” ወይም፣ “ምነው ኢየሱስን ልክ ያኔ ይመስል እንደ ነበረው በራእይ ባየው፤ ተጨባጭ ነገር ባገኝ!” የሚሉ የዘመናችን ክርስቲያኖች ቁጥር ቀላል አይደለም።
እንዲህ ያሉት መሻቶች ኢየሱስ ከመሞቱ፣ ከሞት ከመነሣቱ እና በሥጋ እዚህ ባይኖርም በመንፈሱ አማካይነት ከመገኘቱ የተነሣ ያለንን ጥቅም ካለማወቅ የሚመጡ ናቸው። አብ የላከው አጽናኙ የእውነት መንፈስ፣ ከሙታን የተነሣው የክርስቶስ መንፈስ ነው። “ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ” (ዮሐንስ 14፥18)። መንፈስ ቅዱስ መጣ ማለት ኢየሱስ መጣ ማለት ነው። በምድር ላይ በሥጋ ከመገኘቱ ይልቅ ይህ መገኘቱ የተሻለ መሆኑንም ኢየሱስ ይናገራል።
የክርስቶስ መንፈስ፣ ከሙታን የተነሣውን ክርስቶስን በማክበር ብቻ ሳይሆን፣ አብ በክርስቶስና ሞትን ድል በመንሣቱ አማካይነት ለእኛ የሆነውን ሁሉ እውን በማድረግ በውስጣችን ይሠራል፤ ይህ ደቀ መዛሙርቱ በሕይወት እያሉ ካወቁት እጅግ የላቀና ድንቅ ነው። ከሞት ከተነሣው ክርስቶስ ፊት ካለው ከእግዚአብሔር ክብር የሚበልጥ ክብር የለም (2 ቆሮንቶስ 4፥6)። በመንፈስ ቅዱስ በተሞላን መጠን፣ ይህንን ክብር በይበልጥ እናያለን፣ ደግሞም እንደሰትበታለን።
ከሞቱ አስቀድመው በነበሩት በእነዚህ የመጨረሻና ጨለማ ጊዜያት ኢየሱስ ደስታቸውን ለማረጋጋት የወደደበት የመጀመሪያው መንገድ ይህ ነበር። ለረጅም ጊዜ የሚለያዩበት ጊዜ እየቀረበ ቢሆንም፣ የምድር ላይ ቆይታው ላልተወሰነ ጊዜ ቢራዘም እንኳ ከእነርሱ ጋር ከሚሆነው በተሻለ መንገድ አብሯቸው ይሆናል።
እውነተኛ ሐዘን ለጥቂት ጊዜ
ኢየሱስ ደስታቸውን ለማረጋጋት የሄደው ሁለተኛው መንገድም ልክ እንደ መጀመሪያው አስደናቂ ነው። “ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ስለማታዩኝ …” (ዮሐንስ 16፥10) ብሎ ሲናገር፣ ደቀ መዛሙርቱ በትክክል የሰሙት መስሏቸው ነበር። እነርሱ የተረዱት የሚለያቸው ለረጅም ጊዜ ምናልባትም እስከ ሕይወታቸው ማብቂያ ድረስ እንደሆነ ነበር።
ነገር ግን በድንገት ኢየሱስ እነዚህን ያልተጠበቁ ቃላት ይናገራል፤ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ (ዮሐንስ 16፥16)።” በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ግራ ይጋባሉ፤ “ወደ አብ እሄዳለሁ” ብሎ ነበር። በእርሱ ምትክ የእውነት መንፈስን እንደሚልከው እንጂ በፍጥነት ስለ መመለሱ አልተናገረም ነበር። ስለዚህ “‘ጥቂት ጊዜ’ ማለቱስ ምን ይሆን? የሚለውም ነገር አልገባንም እያሉ ይጠያየቁ ነበር (ዮሐንስ 16፥18)።”
ኢየሱስ ወደ አብ የሚሄድበት መንገድ አሰቃቂ በሆነ ስቅላት እንደ ሆነ ለደቀ መዛሙርቱ ለማስረዳት በሞከረባቸው ጊዜያት ሁሉ ይቃወሙት ነበር፤ አልያም ግራ ይጋቡ ነበር። “እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ” (ማርቆስ 9፥32)። አሁን ግን ሊነግራቸው የፈለገው ይህንን ነው። በተከታዮቹ ሦስት ቀናት ውስጥ በደስታቸው ላይ የተጋረጠው ስጋት ምን ያህል ታላቅ እንደሚሆን ገና አልተረዱም። ደስታቸው የተረጋጋና ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ለዚህ ሊያዘጋጃቸው ይገባ ነበር።
ይህን የሚያደርገው ሐዘን እንደሚጠብቃቸው በማስጠንቀቅ ነበር። ሕይወታቸው ሐዘን የማይኖርበት እንደሆነ በመንገር ደስታቸውን ሊያረጋጋ አይሞክርም። በተቃራኒው፣ ሐዘኑ ከባድ ነው የሚሆነው። ደግሞም እጅግ ተቃርቧል “ጥቂት ጊዜ …።” “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤” ብሏልና። የሐዘናቸውም መንሥኤ ይኸው ነው። በቀጥተኛ አነጋገር “ስለምሞት አታዩኝም” አላለም። ይሁን እንጂ ለማለት የፈለገው ይህንኑ ነው። ቀጥተኛ ያልሆኑ አነጋገሮቹን “ምሳሌ” (ዮሐንስ 16፥25) ይላቸዋል።
የሐዘናቸውን አይቀሬነት ለደስታቸው መረጋጋት እንዲያገለግል የሚያደርግበት መንገድ፣ በመጀመሪያ ሐዘኑ አጭር እንደሚሆን በመንገር ሲሆን (“ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ”)፤ ከዚያ ደግሞ ሐዘናቸውን ከሦስት ነገሮች ጋር በማነጻጸር ነው፤ (1) የዓለም ደስታ፣ (2) የወደፊት ደስታቸው፣ እና (3) ከወሊድ በኋላ ያለው የእናት ደስታ።
1. እውነተኛ ሐዘን ከማይከስም ደስታ ጋር ሲወዳደር
“እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል” (ዮሐንስ 16፥20)።
ኢየሱስ በሐዘናቸው መቃረቢያ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ይህን የተናገረው ለምን ይሆን? ምክንያቱም ከባባድ ነገሮች አስቀድሞ መምጣታቸው ከታወቀ፣ ሕይወትን የማናጋት ዐቅማቸው አነስተኛ ስለሚሆን ነው። ኢየሱስ በእኔ ሞት ዓለም በቁስላችሁ ላይ እንጨት ይሰድዳል እያላቸው ነው። በለቅሷችሁ ሳግ መኻል እንዲህ የሚሉ የፌዝ ድምፆችን ትሰማላችሁ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስቲ ራሱን ያድን (ሉቃስ 23፥35)።”
ደቀ መዛሙርቱ ይህን ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። እግዚአብሔር ለድነታቸው ያዘጋጀው እቅድ አካል ነው። ሄሮድስ ኢየሱስን ልብስ በማልበስ የተጫወተው የፌዝ ጨዋታም የዘላለማዊው እቅዱ አካል ነበር (የሐዋርያት ሥራ 4፥27-28)። ዓለም በሞት የመደሰቱ ኹነት ለኢየሱስ አስደንጋጭ አልነበረም። የሞቱ ሥቃይ፣ ጭካኔ በተሞላ ፌዝ የተከበበ እንደሚሆን ያውቅ ነበር። “ዓለም ግን ሐሴት ያደርጋል።”
ይህን ማወቅ ለደቀ መዛሙርቱ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ማወቃቸው ግን ሐዘንን እንዳያዩ አያደርጋቸውም። ነገር ግን በሐዘኑ የሚደርስባቸውን ተጐጂነት ይቀንሰዋል። አሁን የገዳዮቹ የፌዝ ደስታ እንኳ የእግዚአብሔር እቅድ አካል እንደ ሆነ አውቀዋል። ኢየሱስም እንዲህ እያላቸው ነው፤ አይቀሬ ቢሆንም፣ ለአጭር ጊዜ ነው።
2. የወደ ፊት ደስታቸው
ታዝናላችሁም፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። (ዮሐንስ 16፥20)
ይህ፣ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ” (ዮሐንስ 16፥16) ለሚለው ግራ አጋቢ ለሆነባቸው ንግግር ኢየሱስ የሰጠው ትርጓሜ ነው። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይሞትና ይቀበራል። ከዚያ ወዲያ አያዩትም፤ ስለዚህም ያዝናሉ። እጅግ ያዝናሉ። ከዚያም ከሦስት ቀናት በኋላ ያዩታል። “ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ፤” እናም “ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል” (ዮሐንስ 16፥20)።
ከሞቴ በስቲያ ትንሣኤ አለ እያለ ነው። በሐዘናችሁም ማግስት ደስታ አለ። የነገ ጥዋቱን አስፈሪነት ስትመለከቱ፣ እኔ ይህን እንደ ነገርኳችሁ አስታውሱ። ለእኔ ካላችሁ ፍቅር የተነሣ ልባችሁ በሐዘን ይሰበር፤ ነገር ግን አላዋቂነት ተስፋችሁን አያጨልመው።
የዓለም ደስታ በድንገት ይለወጣል። ለዓለም ደስታ፣ ለእናንተ ግን ሐዘን ምክንያት የሆነው ነገር ከዚያ ወዲያ አይኖርም። ሕያው እሆናለሁ። እነርሱ ይወድቃሉ። ያኔ እነርሱ ሳይሆኑ የምትደሰቱት እናንተ ትሆናላችሁ። የኔ ሞት አይቀሬ እንደ ሆነው ሁሉ ሐዘናችሁም የማይቀር ነው። ነገር ግን እኔ በመቃብር እንደማልቀር ሁሉ እናንተም በሐዘን ውስጥ አትቀሩም።
3. እናት ልጇን ከተገላገለች በኋላ
ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ስለ መጣ ጭንቋን ትረሳለች። (ዮሐንስ 16፥21)በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ፣ የውልደቱ ደስታ የምጡን ጭንቅ ይከተላል ከሚለው ግልጽ ፍቺ ያለፈ ነገር እየተላለፈ ነው። ያ ትክክልና ጠቃሚ ነው። በቅድሚያ ጭንቅ ቀጥሎ ደስታ። በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት ውስጥ በኢየሱስና በደቀ መዛሙርቱ ላይ እውን የሚሆነው ይህ ነው።
ይሁን እንጂ የምጥ ሕመም ከልጁ በፊት የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ልጁን የሚያስገኝ ነው። ልክ ከምጥ ጭንቅ በኋላ አንዲት ሽመላ ሰዓቱን ጠብቃ ልጁን ይዛ እየበረረች በመስኮት እንደምትገባ ዓይነት አይደለም። ልጁ የምጡን ጭንቅ ተከትሎ አይደለም የሚመጣው። ልጁ የሚመጣው በምጡ ጭንቅ አማካይነት ነው።
ከኢየሱስ ሞት በስቲያ ያለው አዲሱ ደስታም ልክ እንዲሁ ነው። በምሳሌው ውስጥ የእናቲቱ የምጥ ጭንቅ የሚወክለው ኢየሱስ የመለየቱን ኹነት ብቻ ሳይሆን (“ከእንግዲህ ስለማታዩኝ …”)፣ የኢየሱስንም ጭንቀት (ሥቃይ) ጭምር ነው፤ መሄዱን ብቻ ሳይሆን መታመሙንም ነው። ስለዚህ በሌላኛው በኩል የሚገኘው ደስታ ጭንቁን ተከትሎ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን፣ የሚመጣበትም መንገድ ነው። የኢየሱስ የመስቀል ሥቃይ አዲሱን ደስታ ቀድሞ የሚመጣ ብቻ ሳይሆን የሚያፈልቀውም ጭምር ነው።
ኢየሱስ በቁጥር 20 ላይ በሚጠቀማቸው ቃላት ለዚህ አጽንኦት ይሰጣል፤ “ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል” ይላል። ሐዘናችሁ “በደስታ ይተካል” አላለም፤ ነገር ግን ቃል በቃል “ወደ ደስታ ይለወጣል” ነው ያለው። ሄንሪ አልፎርድ ይህንን በዚህ መንገድ ገልጾታል፤ “ወደ ደስታ ይቀየራል ብቻ ሳይሆን የለቅሶው ምክንያት ራሱ የደስታ ምክንያት እንዲሆን ራሱ ወደ ደስታነት ይቀየራል፤ ልክ የክርስቶስ የውርደት መስቀል ለክርስቲያን ክብሩ እንደ ሆነው ማለት ነው” (ገላትያ 6፥14)። (Greek New Testament, vol. 1, 870).
ከመስቀሉ እና ከትንሣኤው አንጻር አሁን ከምንገኝበት ቦታ የተነሣ፣ የመስቀሉ ሥቃይ እንዴት በርግጥ ደስታችን እንደሚሆን ይበልጥ ግልጽ ሆኗል። የክርስቶስ ሥቃይ ኀጢአታችንንና የእግዚአብሔርን ቁጣ አስወግዶ ወደ እግዚአብሔርና ወደ ደስታ አድርሶናል። “ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ …” (1ኛ ጴጥሮስ 3፥18)፤ ደግሞም “በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት … አለ” (መዝሙር 16፥11)። “በእርሱም በኩል [ከሥቃዩ የተነሣ] አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን” (ሮሜ 5፥2)።
ስለዚህ ኢየሱስ ከልጅ መወለድ በኋላ እናቲቱ፣ “ሰው ወደ ዓለም ስለ መጣ ጭንቋን ትረሳለች” ሲል፣ የምጡ ጭንቅ ከሚታወስ ሕመም ወደ ደስታ ምንጭነት ተለውጧል እያለ ነው። የኢየሱስ ጭንቅና በደቀ መዛሙርቱ ላይ ያለው ተጽዕኖም ልክ እንዲሁ ነው። ኢየሱስ ደስታቸውን ለማረጋጋት ይህን አስቀድመው እንዲያውቁ ፈልጓል። ይህ ሁሉ ጭንቅ “ወደ ደስታ ይለወጣል” (ዮሐንስ 16፥20)።
ሌላ ኢየሱስ ስለ ደስታቸው የተናገረውና በስቅለት ቀን ሊመጣ ካለው ማዕበል ሊያረጋጋቸው የሚችል አንድ ይበልጥ የሚያስደንቅ ተጨማሪ ነገር አለ። ለእናቲቱ የሚወለደው ሕፃን “በምሳሌው” ውስጥ ከትንሣኤው በኋላ ኢየሱስን የሚወክል ነው። ከትንሣኤው በኋላ ደግሞ ኢየሱስ ሊሞት አይችልም። “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷልና፤ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለን” (ሮሜ 6፥9)። የሞትና የጭንቅ ምጥ ሕይወትን ሲያስገኝ፣ ይህ አዲስ ሕይወት መቼም የማይሞት ይሆናል።
ይህ ማለት ኢየሱስ ቃል የገባው ደስታ የማይጠፋ ደስታ ነው ማለት ነው። “ሆኖም እንደ ገና ስለማያችሁ ደስ ይላችኋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም” (ዮሐንስ 16፥22)። ደስታው የማይጠፋበት ምክንያት ይህ ነው፤ “እንደ ገና ስለማያችሁ።” ከሙታን እነሣለሁ። ሕያው እሆናለሁ፤ በመንፈሴም ለዘላለም ከእናንተ ጋር እሆናለሁ። ደስታችሁ ከእናንተ ሊወሰድ አይችልም ምክንያቱም እኔ ከእናንተ አልለይም። ደስታችሁ እኔ ነኝ (ዮሐንስ 15፥11፤ 17፥13)። “ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ” (ዮሐንስ 14፥18)።
ይህን ደስታ ማንም ሊወስደው አይችልም
ኢየሱስ ከእኛ ተለይቶ ወደ አብ መሄዱ ለእኛ የሚበጅ ስለ መሆኑ አዘውትሮ ሲነገር አንሰማም። “ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ” (ዮሐንስ 16፥7)።
በእርግጥ፣ ኢየሱስ ወደ አብ ከመሄዱ አስቀድሞ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ በዓለም ውስጥ በሥራ ላይ ነበር። ነገር ግን ከኢየሱስ ትንሣኤ በፊት አድርጎ የማያውቀው አንድ ነገር ቢኖር፤ ከሙታን የተነሣውን የመላ ዓለሙን ጌታ ማክበር ነበር! አሁን ግን በዓለም ውስጥ የሚሠራው ዋነኛ ተግባሩ ነው። “[እርሱ] ያከብረኛል!” (ዮሐንስ 16፥14)። በየዕለቱና በሉዓላዊነት በእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ውስጥ ይህን ያደርጋል። የክርስቶስን ክብር ከተመለከትን ምን ጊዜም ምክንያቱ ይህ ነው፦ “ይህም የሚሆነው መንፈስ ከሆነ ጌታ ነው” (2ኛ ቆሮንቶስ 3፥18)። ያለዚህ፣ የሁላችንም እምነት አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር።
መንፈስ ቅዱስ በዚህ ክርስቶስን የማላቅ ሥራው አማካይነት ደስታችን ከእኛ እንደማይወሰድ ኢየሱስ የሰጠውን ተስፋ ይፈጽማል (ዮሐንስ 16፥22)። አስቡት! ተጠራጣሪዎችና ተሣላቂዎች ደስታችሁን ሊወስዱት አይችሉም። የላቦራቶሪ ውጤታችሁን የያዘው ሐኪም ደስታችሁን መውሰድ አይችልም። ታማኝ ያልሆነው የትዳር አጋራችሁ ደስታችሁን ሊወስድ አይችልም። ከመስመር የወጡ ልጆቻችሁም ደስታችሁን መውሰድ አይችሉም። የፖለቲካው ሁኔታ፣ ዓለም አቀፋዊው ስጋት፣ በትምህርት ቤቶች የሚፈጸሙት ግድያዎች፣ ዘረኝነት፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ሥራ አጥነት፣ ሥነ መለኮታዊ ክርክሮች፣ ያልተሳኩ ሕልሞች እንዲሁም ያለፉ ውድቀቶቻችሁ ትዝታ፣ ደስታችሁን ሊወስዱባችሁ አይችሉም፤ ማንም ይህን ሊያደርግ አይችልም።
“ሆኖም እንደ ገና ስለማያችሁ ደስ ይላችኋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም” (ዮሐንስ 16፥22)። ትርጓሜው፤ ከሙታን እነሣለሁ። ይህንንም ፊታችሁ በመቅረብ አረጋግጥላችኋለሁ። ከዚያም ወደ አብ ከሄድኩ በኋላ መንፈሴን በእናንተ ላይ እናፈሳለን። ዳግመኛ እስክመጣ ድረስም መንፈሴ ለእናንተ ክብሬን ይገልጥላችኋል፤ ከዚህም የተነሣ ደስታችሁን ከእናንተ ሊወስድ የሚችል አይኖርም።
ደስታ ብቻ አይደለም
ኢየሱስ ተስፋ የሰጠው ደስታን ብቻ አይደለም፤ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐንስ 16፥33)። በርግጥም አይዞን! አለመበርታት አንችልም! ዓለምን፣ ሲኦልን፣ ዲያብሎስንና ሞትን ጨምሮ ማሸነፉ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ጠላቶቻችን ላይ እንደ ኀያል ተዋጊ ሆኖ ከእኛ ጋርና በውስጣችን ይኖራል። “ልጆች ሆይ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ እነርሱንም አሸንፋችኋቸዋል፤ ምክንያቱም በእናንተ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል (1ኛ ዮሐንስ 4፥4)።”
ስለዚህ፣ አዎ፣ መከራ ይኖራል። በዚህ በወደቀው ዓለም ውስጥ ያሉትን ብዙ የሐዘን ዐይነቶች ልንቆጥራቸው አንችልም። ይሁን እንጂ እንዲህ እንድናዝን የሚያደርገን ዓለም የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፍ አይደለም። ስለዚህ በዚህ ዓለም ውስጥ የክርስቲያን ቃል ይህ ነው፤ “ሐዘንተኞች ስንሆን ሁልጊዜ ደስተኞች ነን (2ኛ ቆሮንቶስ 6፥10)።” በእያንዳንዱ ሐዘን ውስጥ፣ በአጽናኙ እየተጠበቅን ነው። ስለዚህ፣ “አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል (1ኛ ጴጥሮስ 1፥6)።”
“ምነው ወደ ኋላ ሄጄ እርሱ በሥጋ እንዳለ ባየው ኖሮ!” ብሎ ለመጮህ ይዳዳችሁ ይሆናል። ነገር ግን ይህን አስታውሱ፣ በምድር ላይ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ካዩት ይልቅ አሁን እናንተ በመንፈሱ በቃሉ ውስጥ ይበልጥ ታዩታላችሁ። ደግሞም እንደ ገና ታዩታላችሁ፤ ነገር ግን በፊት በነበረበት ሁኔታ አይደለም። ፊቱም፣ “በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሓይ” ይሆናል (ራእይ 1፥16)። በጴጥሮስ ቃላት ተጽናኑ፤ “አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሏችኋል” (1ኛ ጴጥሮስ 1፥8-9)። ከእናንተ ሊወሰድ የማይችለው ደስታ ይህ ነው።