ይህን ጽሑፍ የምጽፈው ክርስቲያን ወላጆች ከልጆቻቸው መታዘዝን እንዲጠብቁ ለመማጸን ነው። እንድጽፈውም የተነሣሣሁት፣ ትንንሽ ልጆች ወላጆቻቸው ለሚያዟቸው ትእዛዞች ትኩረት ሳይሰጡ ሲቀሩና ምንም የሚጠብቃቸው መዘዝ ሳይኖር ሲቀር ሳይ ነው። ወላጆች ሁለት እና ሦስት ጊዜ ልጆቻቸው እንዲነሡ ወይም እያደረጉ ያሉትን እንዲያቆሙ፣ አልያም እንዲመጡ ወይም እንዲሄዱ ይነግሯቸውና ከሦስተኛው አለመታዘዝ በኋላ እየሳቁ ለልጆቻቸው መደለያ ይሰጧቸዋል። ይህ ነገር የሚሹትን ባሕርይ ሊያስገኝም ላያስገኝም ይችላል።
ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሣሡኝ ሁለት ነገሮችን ባለፈው ሳምንት ተመለከትሁ። አንደኛው ምክንያት በካሊፎርኒያ ሳንታ ሮዛ ከተማ በፖሊስ የተገደለውን የ13 ዓመት ልጅ የሆነውን የኤንዲ ሎፔዝ ግድያን ተመልክቼ ነው። ፖሊሶቹ ልጁ ላይ ተኩሰው የገደሉት፣ በሽጉጥ ሊተኩስባቸው ስለ መሰላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይዞት የነበረው የመጫወቻ ሽጉጥ ነበር። ይህንን ነገር ወሳኝ እንዲሆን ያደረገው ፖሊሶቹ ሽጉጡን እንዲጥል ከአንድም ሁለት ጊዜ ነግረነዋል ማለታቸው ነው። እርሱ ግን በተቃራኒው እነርሱ ላይ ደገነው። እነርሱም ተኮሱበት።
የጉዳዩን ዝርዝር ሁኔታ አላውቅም። ኤንዲ ትእዛዛቸውን ይስማ አይስማ አላውቅም። ስለዚህ ርግጠኛ ሆኜ አልታዘዘም ነበር ማለት አልችልም። በዚህም ምክንያት እዚህ ጋር የማነሣው ነጥብ ስለ ኤንዲ ሎፔዝ አይሆንም ማለት ነው። ይልቁንም መላምት ላይ መሠረት ያደረገ ይሆናል። ስለዚህ የፖሊሶቹን ትእዛዝ ሰምቶ ነገር ግን ትእዛዛቸውን ተላልፎ ቢሆንሰ? እንደዚያ ሆኖ ከሆነ ሕይወቱን አስከፍሎታል። የበላይ አካላት ሥልጣንን መተላለፍ ውጤቱ እንዲህ ያለ ነው።
የሐዘን ችግኝ ሲለማ
እንዲህ ያለው ክስተት እንዴት እንደሚገነባ በአውሮፕላን ውስጥ ሆኜ ተመለከትኩ። አንዲት እናት ልጇ በሽጉጥ ተመትቶ እንዲሞት ስታዘጋጀው ተመለከትኩ።
የተቀመጥኩት ከእናትየው እና ሰባት ዓመት አካባቢ ከሚሆነው ልጇ ጀርባ ነበር። እጁ ላይ በያዘው ታብሌት እየተጫወተ ነበር። የአውሮፕላኑ አስተናጋጅ ሆስተስ አውሮፕላኑ ሲነሣ ሁሉም ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች መዘጋት እንደሚኖሩባቸው ተናገረች። ልጁ አላጠፋውም። እናትየውም አላዘዘችውም። አስተናጋጇም ስታልፍ አይታው እንዲያጠፋው ነግራው ሄደች። አሁንም አላጠፋውም ነበር። እናትየውም ከእርሱ መታዘዝን አልጠበቀችም ነበር።
በስተ መጨረሻ አንድ ጊዜ አስተናጋጇ ከጎናቸው ቆማ ታብሌቱን ለእናቱ ሊሰጣት እንደሚገባ ተናገረች። የዚያን ጊዜ አጠፋው። ነገር ግን አስተናጋጇ ሄዳ ስፍራዋን ስትይዝ መልሶ አበራው። አውሮፕላኑ በሚነሣበት ጊዜ እየተጠቀመበት ቀጠለ። እናት ምንም ርምጃ አልወሰደችም ነበር። “በፖሊስ ተመትቶ እንዲሞት እያዘጋጀችው ነው” ስል ለራሴ ተናገርኩ።
ልጆቻቸውን በሞኝነት መንገድ ለሚያሳድጉ የሚሆን የመፍትሔ መንገድ
የማያምኑ ወላጆችን አለመታዘዝ እና ስንፍናን የምረዳው ነገር ነው። መንፈሳቸው የታወሩ ሰዎችን ባሕርይ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምድቦች አሉኝ። ነገር ግን የክርስቲያኖች ችላ ባይነት ፈጽሞ ግራ ያጋባኛል።
መታዘዝን ከመጠየቅ እና ከመቀበል የመጉደሉ ምክንያት ምንድን ነው? ርግጠኛ አይደለሁም። ነገር ግን የሚከተሉት ዘጠኝ ምልከታዎች ምናልባትም አንዳንድ ወላጆችን ከለዘብተኛ አስተዳደግ ከንቱነት ለመታደግ ይረዱ ይሆናል።
- ከልጆች መታዘዝን መጠበቅ፣ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ በሚደነግገው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ውስጥ የሚታይ ነው።
“ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና” (ኤፌሶን 6፡1)። ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ እግዚአብሔር ይጠብቃል እያልን፣ ነገር ግን ወላጆች ከልጆቻቸው መታዘዝን እንደሚጠብቁ ግን (እግዚአብሔር) አይጠብቅም ማለት ትርጉም የማይሰጥ ነገር ነው። እግዚአብሔር በቦታቸው ላይ ላስቀመጣቸው ባለ ሥልጣናት በደስታ እና በታዛዥ መንፈስ መታዘዝ፣ ስለሚያስገኘው በረከት ማስተማር የእኛ ድርሻ ነው። ወላጆች ለትንንሽ ልጆች እንደ እግዚአብሔር ወኪሎች ናቸው። ልጆች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ችላ እንዲሉ ማለማመድ ከባድ አደጋ ነው።
- መታዘዝ በወንጌል ምድብ ውስጥ የሚገባ አዲሱ ኪዳን ነው
መታዘዝ “ሕጋዊ” ምድብ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በወንጌል ምድብ ውስጥም የሚገባ ነው። ጳውሎስ የወንጌል ዐላማ፣ “በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት” ነው በማለት ይናገራል (ሮሜ 1፥5)። እንዲሁም፣ “በተናገርሁትና ባደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም” ይላል (ሮሜ 15፥18)።
የጳውሎስ ዐላማ፣ “አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ ማድረግ” እንደ ሆነ ይናገራል (2 ቆሮንቶስ 10፥5)። ይህን ከአብያተ ክርስቲያናትም ይጠብቀው ነበር። “በዚህ መልእክት ላይ ላለው ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፣ እንደዚህ ያለውን ሰው በጥንቃቄ ተከታተሉት፤ በሥራውም እንዲያፍር ከእርሱ ጋር አትተባበሩ” (2 ተሰሎንቄ 3፥14)።
እግዚአብሔር የሾማቸውን ባለ ሥልጣናት እንዲታዘዙ ልጆቻቸውን የማያስተምሩ ወላጆች፣ ከእግዚአብሔር ቃል የሳተ ሕይወት እንዲኖሩ እያዘጋጇቸው ነው። ይህ ሕይወት አጽንኦት ሊሰጡት ከሚወዱት የወንጌል ጉዞ የሳተ ይሆናል።
(ይህ አስተምህሮ ምንኛ ወሳኝ እንደሆነ የሚጠራጠር ካለ “እግዚአብሔርን በመታዘዝ ማስደሰት፤ የተረሳው የአዲስ ኪዳን አስተምህሮ” የሚለውን ምዕራፍ ከ ዌይን ግሩደም ስለ እግዚአብሔር ስም ዝና ከሚለው መጽሐፍ ላይ እባካችሁ አንብቡ።)
- ከልጆች መታዘዝን መጠበቅ እውን የሚሆን ነገር ነው።
በማይታዘዙ ልጆች ዘንድ ወላጆች አቅመ ቢስ ሆነው ማየት የሚያሳፍር ነገር ነው። ልጆች እንዲታዘዙ እግዚአብሔር የሚያዘው፣ ከልጆች መታዘዝን መጠበቅ የሚቻል ነገር ስለ ሆነ ነው። ዓመት ያልሆናቸው ልጆች መንካት፣ መብላት፣ መጎተት፣ መውጋት፣ መትፋት ስለሌለባቸው ነገሮች ውጤታማ በሆነ መንገድ ማሳየት ይቻላል። እናንተ ከእነርሱ በላይ ትገዝፋላችሁ። ለራስ ወዳድነት አሳልፎ ከመተው ታላቃቸው መሆናችሁን ተጠቅማችሁ ለደስታ የተጠበቁ እንዲሆኑ አድርጉ።
- ከልጆች መታዘዝን መጠበቅ፣ መዘዝ በማያመጡ ነገሮች ላይ ልንለማመደው ይገባል። ይህም ከቤት ውጪ መዘዝ በሚያመጡ ነገሮች ላይ መታዘዝን መጠበቅ እንዲቻል ነው።
ልጆች ከቤት ውጪ ከቁጥጥር ውጪ የሚሆኑበት አንደኛው ምክንያት፣ በቤት ውስጥ እንዴት መታዘዝ እንዳለባቸው ስለማይማሩ ነው። ለዚህም ነገር አንደኛው ምክንያት፣ ቤት ውስጥ የሚገጥሙን ብዙ ነገሮች ልንፋለምላቸው የሚገባን ነገሮች ስለማይመስሉን ነው። ጊዜ ወስደን የልጆችን መታዘዝ አለመፈለግ ከመጋፈጥ ይልቅ ራሳችን ነገሮቹን ማድረግ ይቀለናል። ይህ ደግሞ ለልጆች መታዘዝ አማራጭ ያለው ነገር እንደ ሆነ እንዲያስቡ ያለማምዳቸዋል። በቤት ውስጥ ከልጆቻችሁ መታዘዝን በቋሚነት የምትጠብቁ ከሆነ ከቤት ውጪ አስደሳች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
- መታዘዝን መጠበቅ፣ ጥረት የሚጠይቅ ፍሬው ግን ያማረ ነው
አንድ ሕፃን ልጅ አልጋ ውስጥ እንዲቆይ ብትነግሩት ነገር ግን ችላ ብሎ ቢነሣ፣ እናንተም ተነሥታችሁ አለመታዘዙን ከማረም ይልቅ ተመልሰህ ተኛ ማለት ይቀላል። ወላጆች ይደክማቸዋል። ያሳዝኑኛል። ከ40 ዓመት በላይ በቤቴ ውስጥ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ነበሩ። ከልጆች መታዘዝን መጠበቅ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ አቅም ይጠይቃል። ልጆች በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ መፍቀድ የበለጠ ቀላል ነው።
ውጤቱስ ምን ይሆናል? ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ልጆች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። እንዴት አድርገው ማስመሰል እንደሚችሉ ይማራሉ። እናት አቅመ ቢስ እንደ ሆነች አባት ደግሞ ልፍስፍስ እንደ ሆነ ያስባሉ። ልትቆጡ እንደ ሆነ ቀድመው ይረዳሉ። ቃላችሁን ወዳለመታዘዝ ይገባሉ። እንዲህ ያለው ነገር፣ ለሁሉም መራራ ፍሬ እንዲወጣ ያደርጋል። ነገር ግን እያንዳንዷን አለመታዘዝ ከሥር ከሥር በቋሚነት ለማረም የሚደረገው ሥራ ለወላጆችም ይሁን ለልጆች ደግሞም ለሌሎች ጣፋጭ የሆነ ፍሬን ያፈራል።
- ለዘመናት በብዙ ትውልድ ውስጥ ያለውን ይህን ብልሽት መስበር ትችላላችሁ
ወላጆች መታዘዝን ከልጆቻቸው የማይጠብቁበት አንደኛው ምክንያት፣ ሲደረግ አይተውት ስለማያውቁ ነው። ያደጉበት ቤተ ሰብ ለዘብተኝነት እና ቁጣ ብቻ የሚፈራረቅበት ነው። ስለዚህ ልጆቻቸውን በቁጣ ማሳደግ አይፈልጉም። የሚያውቁት ብቸኛው አማራጭ ለዘብተኝነት ነው። ለዚህ ዐይነት ሰዎች መልካም ዜና አለ። ይህንን መቀየር ትችላላችሁ። ወላጆች ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከጠቢብ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዝዘውን እና ጥበብ የሞላበትን ነገር መማር ይችላሉ። እንዲሁም ታጋሽ በሆነ መንፈስ፣ ጽኑ እና ፍቅር በተሞላ፣ ደግሞም በወንጌል ላይ በተመሠረተ መልኩ እንዴት አድርገው መፈጸም እንደሚችሉ መማር ይችላሉ።
- ጸጋን በተሞላ መልኩ ልጆችን ማሳደግ ከላይ ከላይ ከመታዘዝ በደስታ ወደ መታዘዝ ይመራል
መታዘዝን በእምነት መረዳት ከመቻላቸው በፊት፣ ልጆች መታዘዝ ይኖርባቸዋል። ከፍርሀት፣ ከማበረታቻና ከአክብሮት የተማሩት መታዘዝ፣ እምነትን ባገኙ ጊዜ መታዘዝ ተፈጥሮአዊው የእምነት መገለጫቸው ይሆናል። ከእምነት በፊት መታዘዝን አልጠብቅም ማለት ከንቱነት ነው። ድምር ውጤቱ ፍቅር የጎደለው ይሆናል። ከእምነት በፊት መታዘዝን አለመጠበቅ ጥልቅ የሆነ ያለመታዘዝን ልምድ ይፈጥራል። እምነት አለመታዘዝን ሊሞላው ሳይሆን ሊቋቋመው የተገባ ነገር ነው።
- ወላጆቻቸው መታዘዝን የሚጠብቁባቸው ልጆች የበለጠ ደስተኞች ናቸው
ለዘብተኛ የሆነ ልጆችን የማሳደግ መንገድ፣ ጸጋን የተሞሉ ትሑት ልጆችን አያፈራም። ይልቁንም አስቸጋሪ ልጆችን ያፈራል። እንደዚህ ያሉ ልጆች ደስ የማያሰኙ፣ ራሳቸውም ደስታ የጎደላቸው ናቸው። ነጭናጮች እና ሀፍረተ ቢስ ናቸው። “ነጻነታቸው” ለእነርሱም ይሁን ለሌሎች በረከት አይደለም። ነጻነታቸው ልክ መሪ የሌለው ጀልባ ነፃ እንደሆነው ዐይነት ነው። ይዋል ይደር እንጂ ይህ ባሕሪያቸው መከራን ማምጣቱ አይቀርም። ምናልባትም ለሞት የሚዳርግ ከፖሊስ ጋር ግብግብ ሊያመጣ ይችላል።
- መታዘዝን መጠበቅ ፍጽምናን ከመጠበቅ ጋር አንድ አይደለም
በተለይም በወንጌል በማመን እግዚአብሔርን ማወቅ እስኪችሉ ድረስ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው የእግዚአብሔር ወኪል ናቸውና ፍርድንም ምሕረትንም እናሳያቸዋለን። ሁሉም አለመታዘዝ የሚቀጣ አይደለም። አንዳንዶቹን አስተውለን እንገሥጽና እናልፋቸዋለን። ለዚህ አተገባበር መምሪያ መጽሐፍ የለውም። ልጆቻችን ከአስተዳደጋችን በመነሣት በወንጌል ውስጥ የምንመለከተው እግዚአብሔር የሚያጠፋ እሳት እንደ ሆነ (ዕብራውያን 12፥7፤ 29)፣ ደግሞም ታጋሽ እና ለመቆጣት የዘገየ እንደ ሆነ ሲማሩ ነው (1 ጢሞቴዎስ 1፥16)። ስንቀጣቸውም ሆነ በትዕግሥት ስናልፋቸው ዐላማው ፈጣን እና ደስተኛ የሆነ ፍጹም መታዘዝ እንዲኖራቸው ነው። እግዚአብሔርን በክርስቶስ ውስጥ ማወቅ የሚያፈራው ፍሬ ይህንን ነው።
ወላጆች ሆይ፤ ይህንን ማድረግ ትችላላችሁ። ወቅቱ ከባድ ነው። የሕይወቴን ስልሳ በመቶ የሚሆነውን በእዚህ ላይ አጥፍቻለሁ። ይሁን እንጂ ለዚህ የሚሆን መለኮታዊ ጸጋ አለ። ደግሞም ሽልማታችሁ የተትረፈረፈ ነው።
በጆን ፓይፐር