የዚህ ወር አራተኛው ቅዳሜ፣ ለኮሌጅ የኳስ ጨዋታ ደጋፊዎች ታሪካዊ ነበር። በአላባማና በቴኔሲ (በደቡብ ከሚገኙ በጣም ባለ ታሪክ የሆኑ ሁለቱ የእግር ኳስ ቡድኖች) መካከል የሚደረግ ግጥሚያ ነበር። የአላባማ ደጋፊዎች የአሠልጣኝ ፖል “ቤር” ብርያንትን ዝናን ያተረፈ ስም ያደንቁት ነበር። ብዙ ጊዜ “ጀነራል” ተብሎ የሚጠራው፣ ሮበርት ኔይላንድ፣ በታላቁ ብርቱካናማው ሜዳ(የቴኔሲ ቡድን) በኩል፣ ዝነኛ ሆኖ ተለይቷል። ጀነራል ኔይላንድን የማይረሳ ያደረገው፣ የተወሳሰበውን ግጥሚያ በሰባት መርሖች ማጠቃለሉ ነበር፤ እነርሱም ከውድድሩ በፊት፣ በውድድሩ ወቅትና፣ ከዚያ በኋላ አእምሮን እንዲያተኲር የሚረዱ ቊልፎች ነበሩ። አገልግሎት በርግጥ ጨዋታ ስላልሆነ፣ የቤር ወይም የጀነራል አቋም እንዲኖረኝ ማስመሰል አልፈልግም። እንደ ምክር ግን፣ በአገልግሎቴ ለመኖር የምጥርባቸውን ተለዋዋጭ የሆኑ (fluid) ሰባት መርሖችን (ያለምንም ልዩ ቅደም ተከተል) አቀርባለሁ።
የመጀመሪያው፣ አገልግሎት ከምታስቡት በላይ በጸሎት ላይ ጥገኛ ነው። እግዚአብሔር የጠላትን የጦር መሣሪያ ሁሉ እንደሚያውቅ በመገንዘብ ጸልዩ (ሮሜ 8፥35፣ 38-39)። በእናንተ ውስጥ እንዲሁም እንድትጠብቋቸው በተጠራችሁላቸው ሰዎች ውስጥ፣ እግዚአብሔር ምን መለወጥ እንደሚፈልግ በርግጠኛነት እንደሚያውቅ በመገንዘብ ጸልዩ (የርሱ ዕቅዶች ከእናንተ የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ)። እንዴት መጸለይ እንዳለባችሁ እንዲያስተምራችሁ፣ መፈለግ የሚገባችሁን ትፈልጉ ዘንድ፣ መሻት የሚገባችሁን ትሹ ዘንድ፣ እርሱ ይሠራል ብላችሁ የምታስቡትን ሳይሆን እርሱ የሚሠራውን አስተውላችሁ መለየት እንድትችሉ እግዚአብሔርን ለምኑት። በእግዚአብሔር ፈቃድ ልባችሁን ትሞሉ ዘንድ፣ በማለዳና በተደጋጋሚ፣ ያለማቋረጥና በቀጣይነት ቃሉን ጸልዩ። የኢ.ኤም. ባውንድስን ታዋቂ ቃላት አስታውሱ፣ “መንፈስ ቅዱስ የሚመጣው በዘዴ ሳይሆን በሰዎች…በተለይም በሚጸልዩ ሰዎች ላይ ነው።”
ሁለተኛው፣ ስብከታችሁን ለማሻሻል ያላችሁ ዐላማ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በተደራጀ ሁኔታ መግለጽን እንደ ልማድ አድርጋችሁ ስትጀምሩ፣ መሻሻልን ጠብቁ። ስብከት እጅግ ከባድ ሥራ ነው። በዚያ ተስፋ ከመቊረጥ ይልቅ፣ በተወሰኑ የስብከት ክፍሎች ላይ ለመሥራት ወስኑ። ምስባኩን በእነዚህ የተለያዩ ክፍሎች በዝርዝር አስቀምጡ፤ መግቢያ፣ ሐቲት፣ ማብራሪያ፣ አስተዋጽዖ፣ ድምዳሜ፣ ፍሰት (momentum)፣ ሥዕላዊ ቋንቋዎችን መጠቀም፣ ሽግግሮችና ተዛምዶ። በሁሉም ክፍሎች ላይ በየጊዜው ለማሻሻል ጣሩ፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ በዐምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በተደራጀ መንገድ ለማዳረስ ሥሩ። ምናልባት በመጀመሪያው ዓመት፣ በሐቲትና በአስተዋጽዖ ላይ አተኲሩ። በቀጣዩ ደግሞ፣ ምስባኩን በማስተዋወቅና በማብራራት ላይ አተኲሩ። በሦስተኛው ዓመት፣ ተግባራዊነትና ንቃት ላይ፣ ቋንቋውን አጥብቆ መያዝ ላይ አሻሽሉ። ከዚህ ከተደራጀ አቀራረብ ጐን ለጐን፣ ስለ ስብከት ማንበባችሁን ቀጥሉ። ልምድ ያላቸው መጋቢያን የጻፉትን አንብቡ። ክርስቲያን ፎከስ(Christian Focus)፣ ልምድ ባላቸው መጋቢያን የተጻፉ በርካታ ዐጫጭርና ተግባራዊ ጽሑፎችን አሳትሟል። ስብከት የእግዚአብሔርን ሐሳብና ባሕርይ መግለጥ መሆኑን አስታውሱ።
ሦስተኛው፣ መካሪዎችን ፈልጉ። በተፈጥሮ ሁላችንም እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያስቀመጣቸውና በእኛ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ሰዎች አሉን። ይህ በአገልግሎትም እውነት መሆን አለበት። ሲንክለር ፈርጉሰን፣ ጆን ፓይፐርና ዶናልድ ማክሎድ እግዚአብሔር ለጠራኝ አገልግሎት ዋና አካል ናቸው። በሚመጣው ሕይወት ካልተገናኘን በቀር፣ ከእነዚህ መካሪዎቼ ጋራ የመቀመጥ ዕድሉ ላይኖረኝ ይችላል። ልክ እንደ እኔ፣ እናንተም ከመካሪዎቻችሁ ጋራ መቀመጥ ካልቻላችሁ፣ ከአስተምህሮአቸው ሥር ለመቀመጥ በይነመረብን (internet) ተጠቀሙ። እነርሱ የጻፉትን አንብቡ፤ ነገር ግን ይበልጥ ግላዊ አድርጉት። ለምሳሌ፣ ሲንክለር ፈርጉሰን የጻፈውን ነገር በማነብበት ጊዜ ሁሉ፣ በአእምሮዬ ከርሱ ቃላት በፊት፣ “ውዱ ዴቭ…” የሚለውን እጨምራለሁ። ጢሞቴዎስ የጳውሎስን ደብዳቤዎች የተቀበለው በዚሁ መንገድ አይደል? (1ጢሞቴዎስ 1፥2፤ 2ጢሞቴዎስ 1፥2)። ስብከቶቻቸውና ትምህርቶቻቸው ይፈትኗችሁ። መሰናክሎችን በሚቻላችሁ መጠን ወደ ጐን ትታችሁ፣ እነዚህ ስብከቶች ነፍሳችሁን እንዲገሥጹና እንዲያበረታቱ ፍቀዱ። እነዚህን ሰዎች የምትሰሙት ሐሳብ ለማግኘት (ብቻ) ሳይሆን፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርቧችሁም ነው።
አራተኛው፣ ከሰዎቻችሁ ጋራ ጓደኛ ለመሆን ጣሩ። ከእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለን ወገን ለማወቅ ጊዜ ውሰዱ። ከማኅበር አምልኮ ውጪ ከእነርሱ ጋራ ለመሆን ፈልጉ። ከምትገናኟቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ፣ እውነተኛ ጓደኛ ኖሯቸው አያውቅም። ለእነርሱ ሊውል (ሊሰጥ) ፈቃደኛ የሆነ ሰው አግኝተው አያውቁም። ደቀ መዛሙርቱ፣ ከእነርሱ ጋራ ይሆን ዘንድ በክርስቶስ የተመረጡ በብዙ የተለያዩ ሰዎች ነበሩ (ማርቆስ 3፥14)።
ዐምስተኛው፣ በእግዚአብሔር ቃል የተሞላችሁ ሁኑ። ቃሉ፣ እግዚአብሔር ከክብር ወደ ክብር ሊለውጣችሁ (2ቆሮንቶስ 3፥18)፣ ፈጽሞ ሊያስታጥቃችሁ (2ጢሞቴዎስ 3፥16-17) እና ከጠላቶቻችሁ በላይ ጠቢባን ሊያደርጋችሁ (መዝሙር 119፥98) ተስፋ የሰጠበት ቦታ ነው። ስትረዱት፣ ልባችሁ በጋለ ስሜት እንዲቃጠል ያደርጋል (ሉቃስ 24፥32)። ከክርስቶስ ጋራ በተያያዘ እውነታን የምታገኙበት (ሉቃስ 1፥4)፣ ዐርነታችሁንም የምትረዱበት ስፍራ ነው (ዮሐንስ 8፥32)። እግዚአብሔር በሚያምኑት እንደማያፍር የምንረዳበት ስፍራ ነው (ዕብራውያን 11፥16)። ሲጠብቀን፣ ፈጽሞ አይደክምም፤ አይታክትምም (ኢሳያስ 40፥28)፤ አይተኛም፤ አያንቀላፋምም (መዝሙር 121፥3-4)። በዚህ ቃል ላለመሞላት ምን ምክንያት አለ?
ስድስተኛው፣ ነገሮችን በአዎንታዊ መልኩ ለመግለጽ ጣሩ። ብዙ ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ተወዳጅ በሆነ መንገድ መናገር እንችላለን። ሁሉንም አስተምህሮ ተወዳጅ በሆኑ መንገዶች ለመናገር እንታትራለን። ብዙዎች፣ ስለ ኀጢአትና ስለ ንስሓ ሳይሆን፣ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር እንድትነግሯቸው ይፈልጋሉ። ሁሉም የእግዚአብሔር አስተምህሮዎች ውብና የሚወደዱ መሆናቸውን ለመንጋችሁ አሳዩ። ለምሳሌ፣ ንስሓ ማለት ከክርስቶስ ጋራ በመተባበር ወደሚገኘው በረከት ደጋግሞ የመመለስ ልምምድ መሆኑን ለሕዝቡ አሳውቁ። ወይም፣ ንስሓ መግባት ማለት ክርስቶስን ለምን እንደምትፈልጉት በቀጥታ ለርሱ መናገር ነው። የእግዚአብሔርን ምሉእ ምክር በታማኝነት፣ በግልጽነትና በማራኪ ሁኔታ ለማቅረብ ትጉ።
ሰባተኛው፣ በለውጥ እመኑ። “ነገሮች እንዲሁ ናቸው…አይቀየሩም።” የሚለውን ዐረፍተ ነገር ማራመድ በጣም ቀላል ይሆናል። ለዚህ አስተሳሰብ አትገዙ። በለውጥ ማመናችሁን መቼም ቢሆን አታቁሙ። በመንፈስ ሙታን የሆኑ ሰዎች ወደ ሕይወት እንደሚመጡ ካወቃችሁ (ከቀዳሚ ተመክሮአችሁ)፣ ሌላው ሁሉ ከዚህ ጋራ ሲነጻጸር ደካማ ይሆናል። የእግዚአብሔር መገኘት ሁሉንም ነገር እንደሚቀይር አስታውሱ። ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ!