በአንድ የክረምት ማለዳ፣ መጽሐፍ ቅዱሴን እያነበብኩና ማስታወሻ እየያዝኩ በምወደው ካፌ ውስጥ ተቀምጬ ነበር። አንድ ሰው በተቀመጥኩበት ሲያልፍ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበብኩ እንደሆነ አስተዋለና ከእኔ ጋር ማውራት ጀመረ። በአካባቢያችን ያለ የአንድ ትልቅ የብልጽግና ወንጌል የሚሰብክበት ቤተ ክርስቲያን አባል መሆኑን ነገረኝ። መጽሐፍ ቅዱስ በዋነኝነት እግዚአብሔር እኛን ሊባርከን ስላለው ሐሳብ የሚገልጽ መጽሐፍ እንደሆነ ያምን ነበር። እኔም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ማንነት እንዲሁም ስለ እኛ ማንነት እና እግዚአብሔር እኛን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ያደረገውን ነገር የሚናገር መጽሐፍ ነው ስል መለስኩለት።
ወንጌልን እያካፈልኩት ክርስቲያኖች ኢየሱስን በመከተል መከራን እንደሚቀበሉ ቃል እንደተገባላቸውም ነገርኩት። እርሱም እምነት እስካለን ድረስ እግዚአብሔር ይባርከናል፤ ከመከራም ይጠብቀናል በማለት መለሰልኝ። እግዚአብሔር አማኞች ዕለት ተዕለት ፈተና እንዲሁም የተለየ ስደት እንደሚደርስባቸው ቃል የገባባቸውን በርካታ ክፍሎችን ጠቅሼ ስነግረው፣ እጆቹን በማጣመር፣ “ይህን ለሕይወቴ አልቀበልም” አለ። እኔና ባለቤቴ በቅርቡ የፅንስ መጨንገፍ ደርሶብናል፤ እናም ይህንን ለእርሱ ለማካፈል ተገደድኩ። እንደነዚህ ዓይነት ፈተናዎች ሲያጋጥሙን “ይህን ለሕይወቴ አልቀበልም” በማለት እንዲሁ ልንርቃቸው እንደማንችል ገለጽኩለት። በተጨማሪም ኢየሱስ ዓለምን እንዳሸነፈ እና በመከራዎቻችን ውስጥ እኛን እንደማይተወን ቃል የመግባቱን የምሥራች ነገርኩት።
ግልጽነቴ እና የፈተናዬ ክብደት ከጠበቀው ውጪ የሆነበት መሰለኝ፣ በፍጥነት ሐዘኑን ገልፆ ከነበረው ንግግር ራሱን አገለለ። ግን የገጠመኝ ነገር “በብልጽግና ወንጌል” የሚያምኑትን ሰዎች ወንጌል ለመስበክ ራሳችንን እንዴት በተሻለ ሁኔታ ማዘጋጀት እንችላለን ስል ማሰብ ጀመርኩኝ።
ይህ በጣም ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ እኛን ጤናማ፣ ሀብታም እና ስኬታማ ለማድረግ ሞቷል የሚለውን ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክት ለተቀበሉ ሰዎች ወንጌልን ማካፈል በብዙ ምክንያቶች ፈታኝ ቢሆንም፣ ሁለቱ ግን ዋነኞች እንደሆኑ አምናለሁ፦
1. የብልጽግና መልእክት የሥጋን ምኞት ይማርካል
በመጀመሪያ የብልጽግና መልእክት የሥጋን ምኞት ይማርካል። “ብልጽግና ወንጌል” በተፈጥሮ ያለንን በጤናና በሀብት የመባረክ ፍላጐታችን ላይ በማተኮር፣ ኀጢአተኛ ልባችን የሚሻውን ነገር ለመስጠት ቃል ይገባል። ስለ ኀጢአትና ንስሓ ስለ መግባት ምንም ጥሪ የለውም። ራስህን ስለ መካድ፣ መስቀልህን ተሸክመህ ኢየሱስን ስለ መከተል ምንም ጥሪ የለውም። ለሞትም ጥሪ የለውም (ማርቆስ 10፥34-35)።
በዚህም ምክንያት የብልጽግና “ወንጌል” ለተቀበለ ሰው ወንጌልን ስናካፍል፣ የሥጋን አምሮት በሚማርክ መልእክት ማመኑን ትቶ በምትኩም በእውነተኛው የወንጌል መልእክት እንዲታመን እንጠራዋለን።
2. እኛ የምንጠቀማቸውን ተመሳሳይ ቃላት በተለየ ትርጉም ይጠቀማሉ
ሁለተኛ፣ የብልጽግና “ወንጌል” ተከታዮች እኛ የምንጠቀመውን ተመሳሳይ ቃላት ይጠቀማሉ፤ ነገር ግን የተለያየ ትርጉም ይሰጧቸዋል። ለምሳሌ እኔ እምነት የሚለውን ቃል ስጠቀም ቃሉ እውነት እንደሆነ እና ልጁም ክርስቶስ እንደሆነ ለማመን እግዚአብሔር የሰጠኝን ስጦታ ማለቴ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 2፥14፤ ዮሐንስ 6፥44፣ 65)። ብዙ የብልጽግና “ወንጌል” ተከታዮች እምነት የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ እግዚአብሔርን እንደ ጉዳይ አስፈጻሚ የምንጠቀምበት መሣሪያ ማለታቸው ነው። እምነት በቀላሉ ከእግዚአብሔር የምንፈልገውን ለማግኘት የምንጠቀምበት መገበያያ ነገር ነው።
ሌላ ምሳሌ ደግሞ፣ ወንጌል የሚለውን ቃል ስጠቀም የኢየሱስን ሕይወት፣ ሞት እና ትንሣኤ የምስራች ማለቴ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥1-4፤ ገላቲያ 2፥10-14)። ብዙ የብልጽግና “ወንጌል” ተከታዮች ወንጌል የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ፣ ወንጌል ማለት እግዚአብሔር ጤናማ እና ባለጠጋ እንድንሆን ያመቻቸውን “የምሥራች” ማለታቸው ነው።
የብልጽግና ወንጌል ተከታዮችን በወንጌል ለመድረስ የሚያግዙ አምስት ምክሮች
ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች በተለይም መጋቢዎች የስብከተ ወንጌልን ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባ እና “በጊዜውም ሆነ ያለጊዜው ዝግጁ መሆን” እንዳለባቸው ግልጽ አድርጓል (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥1-5)። ታዲያ በብልጽግና “ወንጌል” የሚያምኑትን እንዴት ወንጌልን እንሰብካላቸዋለን?
1. የእግዚአብሔር ጸጋ ባይረዳን እኛም ብንሆን የስሕተት ወንጌልን እንደምናምን በትሕትና እንቁጠር
ከእግዚአብሔር ጸጋ ውጭ እኛም ብንሆን የውሸት ወንጌልን እንደምናምን በትሕትና እንወቅ። የብልጽግና ወንጌል ለሥጋ አምሮት የሚስማማ መልእክት መሆኑ እውነት ከሆነ በኃጢአት ምክንያት ሙት ለነበርን ለእኛ፣ እንግዲህ የብልጽግናን ወንጌል እንደ ሐሰት ወንጌል የምንገነዘብበት ብቸኛው ምክንያት በእግዚአብሔር ጸጋ አብርሆት ነው (ኤፌሶን 2፥1)። ይህ እውነት የብልጽግናን “ወንጌል” ውሸት ከሚያምኑት ጋር በትህትና ወደ መነጋገር ሊመራን ይገባል።
2. በብልጽግና “ወንጌል” ውስጥ እውነት የሆነውን ሐሳብ በመለየት አረጋግጥ
ግልጽ ላድርግ፥ ብልጽግና “ወንጌል” የስሕተት ወንጌል ነው። ነገር ግን ስሑት አስተምህሮዎች ተቀባይነትን ለማግኘት ከእውነተኛው ነገር ጋር መቀራርብ ይኖርባቸዋል። ስለዚህ በብልጽግና ወንጌል ውስጥ እውነት የሆነውን ነገር አረጋግጥ።
የብልጽግና “ወንጌል” የተመሰረተው የእግዚአብሔርን መኖር በሚያምን ንጽረተ ዓለም ላይ ነው። ኢየሱስን በመከተል በዚህ የሕይወት ዘመን ጭምር በረከቶች እንዳሉ በትክክል ያስረግጣል (ማርቆስ 10፥29-30)። እግዚአብሔር ጸሎትን እንደሚሰማ እና እንደሚመልስ በጽኑ ያምናል (ያዕቆብ 5፥16)። እግዚአብሔር የእምነትን ዋጋ እንደሚከፍል ያረጋግጣል (ማቴዎስ 9፥29)። የብልጽግና “ወንጌል” ሙሉ በሙሉ ከእውነት የራቀ አይደለም። ይህን አለመቀበል ትክክል አይሆንም፤ ደግሞም ለምስክርነት እንቅፋት ይሆንብናል።
3. የብልጽግናን “ወንጌል” ውሸቶችን እና ጉድለቶችን አጋልጥ
የብልጽግና “ወንጌልን” ውሸቶችን እና ጉድለቶችን አጋልጥ። የብልጽግና ወንጌል አንዱ አደገኛ ውሸት ከእግዚአብሔር የምትቀበሉትን ነገር የሚወስነው በእምነታችሁ ብዛት ነው የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዋናው ነገር የእምነታችን መሰረት እንጂ ባለን የእምነት መጠን ልክ እንዳልሆነ ግልጽ ያደርጋል። በጣዖት ላይ ትልቅ እምነት ቢኖረንም አያድነንም ፣ በኢየሱስ ላይ የተደረገ ትንሽም እምነት ያድነናል (ዮሐንስ 14፥1-14)።
የብልጽግና “ወንጌል” ገዳይ ጉድለት መከራ በሚመጣበት ጊዜ ምንም ዓይነት እርዳታ አለመስጠቱ ነው (ዮሐንስ 16፥33)። በአምላክ ላይ ያለን እምነት ከመከራ ነፃ እንደሚያደርገን ካመንን፣ አምላክ ዋሽቶናል፣ አምላክ የለም፣ ወይም በቂ እምነት የለንም ብለን ለመደምደም እንገደዳለን። ነገር ግን ከእነዚህ አንዱም እውነት አይደለም።
4. የመጽሐፍ ቅዱስን ወንጌል ተስፋ ያዝ
የመጽሐፍ ቅዱስን ወንጌል ተስፋ ያዝ። ከአግዚአብሔር ምንም መልካም ነገር የማይገባን መሆኑን ወንጌል ይነግረናል። ለኀጢአታችን የዘላለም ቅጣት ይገባናል። ነገር ግን በምሕረቱ ባለ ጠጋ የሆነው እግዚአብሔር፣ በኢየሱስ ማንነት እና ሥራ ባለው የእምነት ድነት በኩል ያጸድቀናል። በዚህ ሕይወት ውስጥ መልካም የሚመስሉ በረከቶችን ብናገኝም ባናገኝም፣ መልካሙ ዜና በክርስቶስ በማመን ኀጢአታችን ይቅር ተብለን የእግዚአብሔር ቤተሰብ መሆናችን ነው። ይህ ዕውቀት ነገሮችን እንደ ጣዖት እንዳናይ ወይም በዚህ ሕይወት ውስጥ ጥሩ ነገሮችን ሳናገኝ ስንቀር ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል።
5. ትልቁ ደስታችን እግዚአብሔር እንጂ እግዚአብሔር በባረከን ቁስ አለመሆኑን የሚያሳይ ለጋስ የሆነ ሕይወት ኑር
በመጨረሻም፣ ትልቁ ደስታችን እግዚአብሔር እንጂ እግዚአብሔር በባረከን ቁስ አለመሆኑን የሚያሳይ ለጋስ የሆነ ሕይወት ኑር። በብልጽግና ወንጌል ላይ አሳማኝ በሆነ መንገድ ከተከራከርን በኋላ ነገር ግን ገንዘብንና ንብረትን ለማግኘት እና ለማጠራቀም የምንኖር ከሆነ በከንፈሮቻችን የተገነቡትን ሁሉ በሕይወታችን እናፈርሰዋለን።
እግዚአብሔር ከሰጠን ሀብት ላይ ለጋስ ሕይወትን ስንኖር፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ወንጌል ለማካፈል እድሎች እንፈጥራለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ ”የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ” (2ኛ ቆሮንቶስ 8፥9)።
በልግስና መስጠት ክርስቶስ ከሁሉ የላቀ ሀብታችን እንደሆነ እና እግዚአብሔር ከሚሰጠን ከማንኛውም ነገር በላይ እርሱንና እርሱ ለእኛ የሠራልን ሥራ ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ለሌሎች በግልጽ ያሳያል።