አንድ መጋቢ ጓደኛዬ “ቤተ ክርስቲያናችሁ ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምን እየሠራች ነው?” በማለት ጠየቀ።
ወጣቶችን በተመለከተ ልዩ ዕውቀት የለኝም፤ የተወሰነ የፕሮግራም ተለዋዋጭነት ሊኖር እንደሚችል አስባለሁ። ሳምንታዊ ዝግጅት ታዘጋጃላችሁ? ለማን? ምን ታደርጋላችሁ? ልዩ ፕሮጀክቶች ወይም ጉዞዎችስ? ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በጥልቀት ማየቱን ለእናንተ እተወዋለሁ።
ነገር ግን ምንም ቢሆን ምን ልንይዛቸው የሚገቡ ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሖች አሉ። በእኔ እይታ ብዙዎቹ የወጣት ቡድኖች እነዚህን መርሖች አይከተሉም።
1) በምታደርጉት ነገር ሁሉ በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ግልጽ የሆነ መስመር አስምሩ
ኢየሱስ፣ ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ እና ሌሎችም አንድ ሰው ወጣትም ይሁን አዛውንት በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ግልጽ የሆነ መስመር ማስመር እንዳለበት አበክረው አስቀምጠዋል (ለምሳሌ፦ ማቴዎስ 18፥15-20፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፥14-7፥1፣ 1ኛ ጴጥሮስ 2፥9-12)። በጣም ኋላ ቀር ቢመስልም፣ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ስሙ በተጠራበት ሁሉ ላይ ልዩ የሆነ አትኩሮት ሲያደርግ እንመለከታለን። እንዲሁም በአዲስ ኪዳን፣ ኢየሱስ ስሙ ለተጠራባቸው ሁሉ ትኩረት ሰጥቷል (ለምሳሌ፦ ሕዝቅኤል 36፥20-27፣ 36፣ ማቴዎስ 18፥20፣ 28፥19፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 5፥4)።
የወጣቶች አገልግሎት ትልቁ ፈተና በአጭሩ ባስቀምጠው፣ በዓለም እና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን መስመር ማደብዘዝ ነው። ልጆችህ የቤተ ክርስቲያን እና በቤተ ክርስቲያን ያልተማሩ ልጆች ድብልቅ መሆናቸውን ታውቃለህ? አንዳንዶች ክርስቲያን ነን ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ አይደለንም። በእውነቱ ግን ማን ትክክለኛውን ሊናገር ይችላል?
እንግዲህ እውነታው ይህ ነው፤ ለዚህም ነው አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ላለማጥመቅ የሚመርጡት። ይህ እንደ ጥሩ እርምጃ ሊታሰብ ይችላል። በዚህ አቋም ተስማማችሁም አልተስማማችሁም በቃላቶቻችሁ፣ በፕሮግራሞቻችሁ እና በተለያዩ ዘዴዎቻችሁ ለወጣቶች “ቤተ ክርስቲያን እና ዓለም” የተለያዩ እንደሆኑ ማስገንዘብ ይኖርባችኋል። በዐሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆቻችሁን በተሻለ መንገድ መውደዳችሁን ልታሳዩአቸው የምትችሉት ወሳኙ የሕይወታቸው ውሳኔ በመስመሩ በየትኛው በኩል መቆም እንዳለባቸው የሚወስኑት ውሳኔ እንደሆነ እንዲረዱ በማገዝ ነው።
እንዲሁም የወጣቶች አገልግሎትን የቤተ ክርስቲያን አባላት መደበኛ ኀላፊነቶችና መርሖች የማይተገበሩበት እንደ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ክንፍ አድርጋችሁ አትመልከቱ። እንደዚህ ከማየት ይልቅ…
2) ታዳጊዎችን የምታጠምቁ ከሆነ እንደ አዋቂ ተመልከቷቸው
አሁንም ታዳጊዎችን አጥምቁ እያልኩ አይደለም። ማጥመቅ ይኑርባችሁ አይኑርባችሁ እርግጠኛ አይደለሁም። ነገር ግን ካደረጋችሁት (ብዙዎቻችሁ እንደምታደርጉ አውቃለሁ) እንደ አዋቂ ክርስቲያኖች ልታዩዋቸው ይገባል። በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀዋል (ማቴዎስ 28፥19)። ስለዚህ ከመላው ቤተ ክርስቲያን ጋር ለዚህ ስም ኀላፊነት አለባቸው (ማቴዎስ 18፥20፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 5፥4-5)። የቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍሎች ናቸው፤ ስለዚህም አካሉን ወደ መንከባከብ መሳብ አለባቸው (1ኛ ቆሮንቶስ 12፥21-26፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 2፥6)።
በአባላት ስብሰባም ላይ ድምጽ ሊኖራቸው ይገባል። በንስሓ ለመመለስ ፈቃደኛ ባልሆኑበት ኀጢአት ውስጥ ከተገኙ፣ ለቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ (እገዳ) ተገዢ መሆን አለባቸው። በቤተ ክርስቲያኑ ዋና ስብሰባ ላይ እንዲገኙ እና ለቤተ ክርስቲያን እንዲጸልዩ ሊጠየቁም ይገባል። የጌታን እራት ከመውሰዳቸው በፊት ቅራኔዎችን እንዲቀርፉ ሊጠየቁ ይገባል። በሽማግሌዎች እይታ ሥር መሆንን እና የመሳሰሉት ነገሮች ማድረግ አለባችው።
በርግጥ እንደ አዋቂ የቤተ ክርስቲያን አባላት ኀላፊነትን እንዲወጡ መጠየቅ የክርስትና መሠረታዊ ኀላፊነቶችን እንዲወጡ እንደ መጠየቅ ነው። ኢየሱስም በጎቹ ሁሉ በቤተሰብ ውስጥ ሁሉንም እንዲንከባከቡ፣ እርስ በርስ እንዲተያዩ፣ እርስ በርሳቸው በፍቅር እንዲተናነጹ፣ ሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ይፈልጋል። ሌሎች ልምዶችን በመለማመድ ወጣቱን ሌላ ነገር ማስተማር አያስፈልግም።
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅን ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ማጥመቅ ማለት የወጣቶች እምነት ላይ ወላጆች የሌላቸውን ሥልጣን ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ማለት ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወጣቶችን ሲያገለግሉ ሁልጊዜ ወላጆችን ማሳተፍ እንዳለባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ወላጆች የተጠመቀ ልጃቸው የቤተ ክርስቲያን አባል ይሁን አይሁን የሚለውን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔውን ለቤተ ክርስቲያን መተው አለባቸው። የመንግሥተ ሰማይ መክፈቻ የተሰጠው ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለወላጅ አይደለም (ማቴዎስ 16፥18-19)።
ይህ ሁሉ ነገር ታዲያ ከማጥመቃችሁ በፊት ቆም ብላችሁ እንድታስቡ ሊያደርጋችሁ አይገባምን? አዎ!
3) ተጠመቁም አልተጠመቁም በእድሜ ደረጃ ከተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ጋር አዋህዷቸው
የምዕራቡ ዓለም ቢዝነስ እና ሚዲያ ለወጣቶች ገበያ ለማቅረብ እና ሸማች እንዲሆኑ ለማሰልጠን ቁጥር ስፍር የሌለውን ዶላሮችን ያወጣል፦ “ሄይ ልጆች! የምትፈልጉትን ነገር በምትፈልጉት መጠን አሁኑኑ ማግኘት ትችላላችሁ!” ለምሳሌ የዛሬዎቹ ወጣቶች ከ100 ዓመታት በፊት እንደሚያደርጉት በአዋቂዎች ዓለም ውስጥ ለመኖር ሲጥሩ በቤተ ክርስቲያን አይታዩም፤ ይልቁንም እኩዮቻቸው ከሆኑ ከብዙ ወጣቶች ጋር አብረው ጊዜ ማሳለፍን ይመርጣሉ።
አግበስባሽነት ለሌሎች ከመቆረስ ጋር ስለሚጋጭ በወጣት ፕሮግራሞቻችሁ ውስጥ የአግበስባሽነትን ሐሳብ ላለማንሸራሸር በጣም ጠንቃቃ እንድትሆኑ አበረታታችኋለሁ። ነገር ግን የምታደርጉትን ሁሉ ወጣቶችን እውነተኛ ደቀ መዛሙርት በማድረግ ረገድ በእድሜ ደረጃ በተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የተሻለ እንደሚሠራ ተገንዘቡ። በድጋሚም ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን አካላት በሥራ ላይ በማየት እውነተኛው ክርስትና ምንን እንደሚወክል ይረዳሉ። ሽማግሌው ታናሹን ደቀ መዝሙር ሲያደርግ፣ ታናሹ ደግሞ ከታላቅ ሲማር ማየት ያስፈልጋቸዋል (ለምሳሌ፦ 1ኛ ጢሞቴዎስ 5፥1፤ ቲቶ 2፥2-6፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፥5)።
የክርስትና መንገድ፣ በአካል ውስጥ በአረጋውያንና በወጣት ቅዱሳን መካከል ያለ የአንድነት መንገድ ነው፤ እናም ወጣቶቻችን በዚህ መንገድ እንዲሄዱ ከፈለጋችሁ መንገዱን አሳዩአቸው።
4) ወላጆች ወጣት ልጆቻቸውን እንዲያገለግሉ አስተምሩአቸው
መጽሐፍ ቅዱስ መጋቢዎችን ሳይሆን ወላጆችን ልጆቻቸውን በሚሄዱበት መንገድ እንዲመሩአቸው ያዛል (ለምሳሌ ኤፌሶን 4፥11፣ 6፥4)። የወጣት መጋቢዎችን እናስወግድ እያልኩ አይደለም። እኔ የምለው የወጣት መጋቢዎች የእናንተ ሥራ እና ፕሮግራም ክርስቲያን ወላጆች መጽሐፍ ቅዱስን ላለመታዘዝ ማመካኛ የሚያደርጉት እንዳይሆን ርግጠኛ ሁኑ፤ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲታዘዙ የወላጆችን ሥራ አመቻቹላቸው።
5) በዚህ ወቅት ያለውን ወንጌልን የመስበክ ዕድል ተጠቀሙ
እንደ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ እያንዳንዱን የአባልነት ማመልከቻ እና ቤተ ክርስቲያናችንን የሚቀላቀሉ ሰዎች የሚናገሩትን እያንዳንዱን ምስክርነት አነባለሁ። (ይህ ለነፍሴ እንዴት ያለ ደስታ እንደሚሰጣት! )በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ አማኝ ከሆነም ካልሆነም ቤተሰብ ይምጡ ብዙዎች ወደ ጌታ የመጡት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ነው። ይህ ወቅት ለሰዎች ወንጌልን ለማካፈል አመቺ ወቅት ነው።
ይህ በፕሮግራማችሁ ውስጥ ምን ይመስላል? አላውቅም፤ ግን አንድ ነገር አድርጉ!
6) ከ1 እስከ 5 ባሉት ነጥቦች ላይ በፕሮግራም የምታደርጉትን ሁሉ፣ ሰው ሰራሽ ዕቅዶቻችሁን በእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዓላማዎች ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ አትፍቀዱላቸው ይልቁንም አመቻቹላቸው
ያሏችሁ መዋቅሮች ወይም ቡድኖች የወጣቶቻችሁን በጉባኤ ሕይወት ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎ የሚጻረር ወይም በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ያለውን መስመር እንደማያደበዝዙ አረጋግጡ። እኩዮቻቸው ብቻ ሳይሆኑ በዕድሜ የገፉ አባላትም እንዲከታተሏቸው አድርጉ።
ይህ ሁሉ በመርሃ ግብር ደረጃ እንዴት እንደሚሠራ እርግጠኛ አይደለሁም (እስካሁን ይህን ተናግሬ ይሆን?) የእኔ ሐሳብ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ በደንብ ሐሳብ ማመንጨት እንዳለብን ነው። ብዙ ወላጆች “ክርስቲያን” ወጣት ልጆቻቸው ኮሌጅ ገብተው እምነታቸውን ሲተው የሚያዩት ለምን ይመስላችኋል? የእኔ ግምት ብዙ ጊዜ በሁለት ውድቀቶች ምክንያት ነው። የደቀ መዝሙርነት ውድቀት ደግሞም በጥምቀት በአባልነት እና በተግሣጽ መዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ ጥበብን አለመጠቀም ነው።
ታዲያ ሁለታችሁም (መጋቢዎችና ወላጆች) እንዴት በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ያለውን መስመር በጥንቃቄ ታሰምራላችሁ? እንዴትስ ወንጌልን እንዲሰብኩ መርዳት ትችላላችሁ? እስኪ አንዳንድ ሐሳቦችን እንስማ!
በጆናታን ሊማን