ጥሪ ወደ ክርስቲያናዊ አደጋ

ክርስቶስ የዘላለማዊ ሥጋትና አደጋን በማስወገድ ሕዝቡን ወደ ማያቋርጥ ነገር ግን ጊዜያዊ ወደሆነ አደጋ ጠርቶታል።

ለኢየሱስ ተከታዮች የመጨረሻው አደጋ ተወግዶላቸዋል፤ “እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም”(ሮሜ 8፥1)። “ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን… በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ” (ሮሜ 8፥38-39)። “ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም” (ሉቃስ 21፥1618)። “ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” (ዮሐንስ 11፥25)።

የሞት ዛቻ ለገነት በር ሲሆን፣ ጊዜያዊ አደጋን ለመቀበል የያዘን የመጨረሻ ሰንሰለት ይበጠሳል። ክርስቲያን ከልቡ፣ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና” ሲል የፈለገውን የመውደድ ነፃነት ይጎናጸፋል። አንዳንድ ጽንፈኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ በመግደል ሰማዕት ለመሆን የተዘጋጁትን በተመሳሳይ ሕልም ለማታለል ይሞክራሉ። ነገር ግን የክርስትና ተስፋ የመውደድ ኀይል እንጂ የመግደል አይደለም። የክርስቲያን ተስፋ ሕይወት ሰጪ እንጂ ነጣቂ አይደለም። የተሰቀለው ክርስቶስ እርሱ እንዳደረገው፣ ሕዝቡን ለጠላቶቻቸው እንዲኖሩና እንዲሞቱ ጠርቷቸዋል። ከክርስቶስ የተፈቀደው ብቸኛ የአደጋ ምንጭ ፍቅር ብቻ ነው። “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ” (ሉቃስ 6፥27-28)።

እጅግ በሚያስደንቅ የዘላለማዊ ደስታ ተስፋ፣ ኢየሱስ የቆራጥ አደጋ ወዳዶችን እንቅስቃሴ አስጀምሯል። “ወላጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንኳ ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ከእናንተም አንዳንዶቹን ይገድላሉ” (ሉቃስ 21፥16)። አንዳንዱን ይገድላሉ ይላል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ አንተ ልትሆን ትችላለህ፤ ላትሆንም ትችላለህ፤ አደጋ ማለት ይሄ ነው። ራስ ላይ መተኮስ አደገኛ አይደለም፤ ምክንያቱም ውጤቱ ግልጽ ነው። ክርስቶስን በጦርነት ቀጠና መሃል ማገልገል ግን አደገኛ ነው። በጥይት ልትመታ ትችላለህ፤ ላትመታም ትችላለህ።

ክርስቶስ ለመንግሥቱ ጥቅም ስንል አደጋን እንድንጋፈጥ ጠርቶናል። ሁሉም የአሜሪካ ኮንስዩመሪዝም መልእክት ግን በተቃራኒው፣ “ምቾትህንና ደኅንነህትን በሰማይ ሳይሆን አሁን አሳድግ” ይላል። ክርስቶስ ግን እንደዚህ አይልም። የአደጋ ጥላ ባጠላበት ቦታ፣ በፍርሃት ውስጥ ተደፍቆ ላለ ለእያንዳንዱ ቅዱሳን እንዲህ ይላል፦ “አትፍሩ ልትገደሉ ብቻ ነው የምትችሉት”(ሉቃስ 12፥4)። አዎ ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ይበልጥ ደስተኛ ሁኑ! እንዴት? ስለ ፍቅር ስትሉ የውርደትን፣ የስቃይን፣ በውሸት የመወንጀልን ሸክም ተሸከሙ፤ “ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና”(ማቴዎስ 5፥11-12)።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በበርካታ ስፍራዎች አደጋን የማይፈሩ ሰዎችን እንመለከታለን። ኢዮአብ ሶርያውያንን በአንድ በኩል የአሞን ልጆችን ደግሞ በሌላ በኩል በገጠመ ጊዜ፣ ለወንድሙ ለአቢሳ እንዲህ ሲለው እንመለከታለን፤ “አይዞህ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ”(2ኛ ሳሙኤል 10፥12)። አስቴር ሕዝቧን ለማዳን የንጉሡን አዋጅ ስትጥስ እንዲህ ብላለች፤ “ብጠፋም እጠፋለሁ” (አስቴር 4፥16)። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፣ ንጉሡ ላቆመው ምስል አንሰግድም በማለት እንዲህ ብለዋል፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጕዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም። 17ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። 18ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” (ዳንኤል 3፥16-18)። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ እሥራትና መከራ እንደሚጠብቀው ቢመሰክርለትም እርሱ ግን፣ “ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።” (የሐዋርያት ሥራ 20፥24)።

ስቴፈን ኔል ስለ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ ቢፈጥንም ደግሞ ቢዘገይ፣ በሕይወቱ ተደራድሮ ስለ እምነቱ መመስከር ያለበት ቀን እንደሚመጣ ያውቃል።”[1] ይህ የተለመደ ነበር፤ ክርስቲያን መሆን ማለት ሕይወትን አደጋ ላይ መጣል ማለት ነበር። በዐሥር ሺህ የሚቆጠሩም ይህንን አድረገዋል። ለምን? ምክንያቱም ይህንን ማድረግ ክርስቶስን ማትረፍ እንጂ ነፍስን ማጣት ስላልሆነ፤ “ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል”(ማቴዎስ 16፥25)።

በአሜሪካ እንዲሁም በተቀረው የዓለም ክፍል እውነተኛ ክርስቲያን የመሆን ዋጋ እየጨመረ ነው። ”በአሁኑ ክፉ ዘመን” ነገሮች ተለምዶአዊ እየሆኑ ነው። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥12 ይበልጥ ትርጉም ይሰጣል፤ “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” በወንጌል ምክንያት የሚመጣን አደጋ ለመጋፈጥ የሚያስችል የአኗኗር ዘይቤን ገንዘብ ያደረጉ ሰዎች፣ አማራጭ በሌለበት ሰዓት የተዘጋጁ ይሆናሉ። ስለዚህ በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ቃላት እንዲህ ስል አጥብቄ እጠይቃችኋልሁ፦ “ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ። ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን” (ዕብራውያን 13፥13-14)።

እግዚአብሔር በሰማይ ያለውን ሁሉንም አደጋ ሲያስወግድ፣ ሺህ የፍቅር አደጋዎችን ፈቅዶ ለቋል።

በጆን ፓይፐር


[1] A History of Christian Missions, Penguin, 1964, p. 43