ምርመራ፦ በዘመናችን የስብከት ሥራ ላይ ያለው ችግር (ክፍል 1)
እኔ አባል በሆንኩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ውስጥ (የደቡብ ባፕቲስት ኮንቬንሽን)፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ስሕተት አልባ መሆናቸውን ለማሳየት የተደረገው ጦርነት ድል ተደርጎ ሊሆን ይችላል። ሆኖም፣ እኛ ሆንን ሌሎች የወንጌላውያን ቤተ እምነቶች ወይም ተመሳሳይ ጦርነቶችን ያሸነፍን አብያተ ክርስቲያናት፣ ራሳችንን ቶሎ ማመስገን የለብንም። ወግ አጥባቂ አብያተ ክርስቲያናት የቅዱሳት መጻሕፍትን ስሕተት አልባነት ሊቀበሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል በቂ መሆኑን በተግባር ይክዳሉ። ቅዱሳት መጻሕፍት የማይሳሳት የእግዚአብሔር ቃል ነው ልንል እንችላለን፤ ሆኖም ግን በቁም ነገር በመድረኮቻችን ማወጅ ተስኖናል።
ዛሬ በብዙ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የእግዚአብሔር ቃል ረሃብ አለ (ተከታታይ ስብከት እንደ ጊሊጋን ደሴት፣ ቦናንዛ እና ሜሪ ታይለር ሙር ባሉ የቴሌቭዥን ትዕይንቶች ውስጥ ቀርበዋል)። አብዛኛውን ጊዜ ስብከቶች የሚያተኩሩት፣ የተሳካ ትዳር ለመመሥረት ወይም በባሕላችን ልጆችን ማሳደግ የሚቻልበት መንገድ ላይ ነው። በርግጥ በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ስብከቶች ተስማሚ እና አስፈላጊ ናቸው። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ሁለት ችግሮች ይከሰታሉ። በመጀመሪያ፣ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ እነዚህ ጉዳዮች የሚናገሩት ነገር በአብዛኛው ችላ ይባላል። ምን ያህሎቹ ስብከቶች ጳውሎስ ስለ ወንዶች እና ሴቶች ሚና ምን እንደሚል በታማኝነት እና በአስፈላጊ ጊዜ ይናገራሉ (ኤፌሶን 5፥22-33)? ወይስ ቅዱሳት መጻሕፍት በሚናገሩት እናፍራለን?
ሁለተኛ፣ እና ምናልባትም ከዚህ በከፋ ሁኔታ እንደዚህ ዐይነት ስብከቶች የሚሰበኩት (ሁልጊዜም ማለት ይቻላል) በአግድመት ደረጃ (horizontal level) ነው። ምእመኑ በየሳምንቱ እንዲመላለስ ብቻ የሚያደርጉ ማጣበቅያ ስብከቶች ናቸው፤ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የሚንጸባረቀው እና ለሕይወት ሁሉ መሠረት የሆነው የሥነ መለኮት እይታ በቸልታ ተላልፏል። ፓስተሮቻችን ከሳምንት እስከ ሳምንት ደስተኛ ሕይወት እንዴት መኖር እንዳለብን ምክር እየሰጡ፣ የሥነ ምግባር አስተማሪዎች ሆነው ይታያሉ።
ብዙ ጉባኤዎች ምን እየተከናወነ እንዳለ በወጉ አይረዱትም። ምክንያቱም እንዲህ ያለው ስብከት የሚያስተምረው ሥነ ምግባራዊ ሕይወት፣ ቢያንስ በከፊልም ቢሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት ጋር ይስማማል። ይህም አማኞችም የማያምኑትም ያስፈልገናል ብለው ለሚያስቡት ነገር የሚቀርብ ስብከት እንዲሆን ያደርገዋል።
መጋቢዎች ስብከታቸውን በተረት እና በምሳሌዎች መሙላት እንዳለባቸው ያምናሉ፤ ስለዚህም ተረቶቹ የተገለጸውን የሞራል ነጥብ ይገልፃሉ። የትኛውም ጥሩ ሰባኪ ምሳሌዎችን ይጠቀማል። ነገር ግን ስብከቶች ምንም ዐይነት ሥነ መለኮትዊ አንድምታ በሌላቸው ታሪኮች ሊሞሉ ይችላሉ።
ወንጌላውያን አማኞች ደጋግመው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በሥነ መለኮት ትምህርት ጥሩ ሥራ እየሠሩ ነው፤ ምክንያቱም ማኅበረ ቅዱሳኑ ስለምናስተምረው ነገር ቅሬታ የላቸውም ብለው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እንዲህ ዐይነቱ አስተያየት በጣም አስፈሪ ነው። እኛ መጋቢዎች “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ” የማወጅ ኃላፊነት አለብን (ሐዋሪያት ሥራ 20፥27)። ጥሪያችንን እየፈጸምን መሆን አለመሆናችንን ለማወቅ፣ በጉባኤ ምርጫዎች ላይ መተማመን አንችልም። ቅዱሳት መጻሕፍት በሚጠይቁት ላይ መመሥረት አለብን። አንድ ጉባኤ የእግዚአብሔርን ቃል በስርዓት ተምሮ የማያውቅ ሊሆን ስለሚችል፣ እኛ እንደ መጋቢዎች የደከምንበትን ቦታ እነርሱ ላይረዱት ይችላል።
ጳውሎስ “ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ” ሲል አስጠንቅቆናል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ “ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ“ (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥3-4)። ስብከታችንን የምንገመግመው ቅዱሳን በሚፈልጉት መሠረት ከሆነ፣ ለስሕተት ትምህርት በር እያዘጋጅን ይሆናል። ምእመናችን መናፍቃን ናቸው እያልኩ አይደለም፤ ይልቁኑ ከሕዝብ አስተያየት ይልቅ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ የታማኝነት መለኪያ መሆን አለበት። የፓስተሮች ጥሪ መንጋውን በእግዚአብሔር ቃል እንዲመግቡ እንጂ፣ ሰዎችን መስማት የሚፈልጉትን በማቅረብ ደስ እንዲሰኙ መጣር አይደለም።
ብዙውን ጊዜ ጉባኤዎቻችን፣ በበሰባኪዎቻችን ጥሩ ሥልጠና አልተሰጣቸውም። የሥነ ምግባር ስብከት ጉባኤን ሁሌ ስንመገብ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡ? ደግ፣ ይቅር ባይ፣ አፍቃሪ እና ጥሩ ባል ወይም ሚስት መሆንን ይማሩ ይሆናል (በርግጥ ሁሉም መልካም ነገሮች ናቸው!)። ልባቸው ሊሞቅ አልፎ ተርፎም ሊታነጽ ይችላል። ነገር ግን የነገረ መለኮት መሠረቱን ችላ እስከተባለ ድረስ፣ የስሕተት ተኩላ ይበልጥ በቅርበት በጉባኤው ይሸሸጋል። እንዴት? ፓስተሩ ራሱ ስሑት ስለሆነ አይደለም። እርሱ በራሱ ሥነ መለኮት ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እና ታማኝ ሊሆን ይችላል። እርሱ ግን በስብከቱ ሁሉ፣ ሥነ መለኮትን በውስጥ አዋቂነት ስለሚያስበው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትርክትና ሥነ መለኮት ለሕዝቡ መስበክን ይዘነጋል።
ስለዚህ በሚቀጥሉት ወይም ሁለት ቀጣይ ትውልዶች ምእመናኑ ሳያውቁት የበለጠ ሊብራል የሆነ ፓስተር ሊሾሙ ይችላሉ። ይህ አዲስ ፓስተር ደግሞ ሰዎች ጥሩ፣ ደግ እና የፍቅር ሰው መሆን እንዳለባቸው ይሰብካል። ጥሩ ትዳር እና የተለዋዋጭ ግንኙነቶችን አስፈላጊነት ያጎላል። ነገረ መለኮቱ ከእርሱ በፊት ከነበረው ወግ አጥባቂ ፓስተር ነገረ መለኮት ስለሚመሳስል፣ በኋላው ያሉ ሰዎች ልዩነቱን እንኳ ላያውቁ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ወግ አጥባቂው ፓስተር ሥነ መለኮትን አልሰበከም። ወግ አጥባቂው ፓስተር በቅዱሳት መጻሕፍት አለመሳሳት ያምን ነበር፤ ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም፣ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩትን ሁሉ ለጉባኤው አልሰበከም።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ መለኮትን ቸል ማለት ተንሰራፍቷል። ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ በሁለት አጋጣሚዎች (አንዱ ስሙን ማስታወስ የማልችለው ግለሰብ፣ በአንድ ትልቅ ስታዲየም ውስጥ) ሰዎችን ወደ ፊት እንዲመጡ የጋበዘባቸው ገጠመኞች በአእምሮዬ ውስጥ አሉ። በስታዲየሙ የተዘጋጀው ፕሮግራም ለወንጌል ስብከት እንዲሆን ታስቦ ነበር፤ እውነት ለመናገር ግን ወንጌል አልተሰበከም ነበር። ስለተሰቀለው እና ስለተነሣው፣ ወይም ለምን እንደተሰቀለ እና እንደተነሣ ምንም አልተነገረም። እምነት ከሥራ ይልቅ ለምን እንደሚያድን ምንም አልተነገረም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ፊት መጡ፤ እና ምንም ጥርጥር የለውም የዳኑ ተብለው ተመዝግበዋል። እኔ ግን ጭንቅላቴን እየነቀነኩ ምን እየሆነ እንዳለ አሰብኩ። ቢያንስ አንዳንዶች በእውነት እንዲለወጡ ጸለይኩ፤ ማለትም ምናልባት የወንጌልን ይዘት በሌሎች አጋጣሚዎች በመስማት ቀድመው የሚያውቁ ከሆነ ብዬ። በጎበኘሁት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። ሰባኪው “ወደ ፊት ኑ” እና “ዳኑ” የሚል አበረታች ግብዣ ቢያቀርብም ስለ ወንጌል ምንም ማብራሪያ አልሰጠም!
እንዲህ ያለው ስብከት፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ባልተለወጡ ሰዎች ሊሞላ ይችላል፤ የእነርሱም አደጋ እጥፍ ድርብ ነው፤ ምክንያቱም እንደተለወጡ እና መዳናቸውን ፈጽሞ ሊያጡ እንደማይችሉ መጋቢዎች አስረግጠውላቸዋል፤ ነገር ግን ከጅምሩ አልዳኑም። ከዚያ ቀን ጀምሮ፣ እነዚሁ ሰዎች ለድኅረ ዘመናዊ ጊዜ በሚሆነው አዲሱ ወንጌል፣ ከሳምንት እስከ ሳምንት ይበረታታሉ፤ ይኸውም “መልካም ሁን” የሚል ነው!
በቶማስ ሽራይነር