አሁን የራሳችሁን የግል የጸሎት ሕይወት በአዲስ መልክ ለመመልከት እና በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ልታደርጉት ስለምትችሉት አንድ ወይም ሁለት ማስተካከያዎች የምታስቡበት ጊዜ ነው። ወደ ፊት ለመራመድ እና ለማደግ የተሻለው መንገድ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ መቀየር ሳይሆን፣ በጊዜ ሂደት ውስጥ ለውጥ የሚያመጡ ትንንሽ እርምጃዎችን መለየት ነው።
ምናልባት ትንሽ ወይም ምንም የግል የጸሎት ሕይወት ላይኖራችሁ ይችላል (ይህም ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች መካከል እንደ ምንጊዜውም የተለመደ ነው)። በርግጥ ከባዶ መጀመር ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል። “ለዚህ ትውልድ ያለኝ ትልቁ ፍርሃት፣ ትኩረት ማድረግ አለመቻል ነው፤ በተለይም በጸሎት ላይ። ” የሚለው የፍራንሲስ ቻን የማንቂያ ንግግር በልብዎ ሊከብድ ይችላል። ምናልባትም ይህ ንግግር አንተን/አንቺን የሚመለከት ይሆናል። እናም ለመለወጥ ተዘጋጁ።
ራሳችሁን መመርመር የሚያስፈልግ ከሆነ እና እንደ ጀማሪ ለመማር ከፈለጉ ስለ ግል የጸሎት ሕይወት የተወሰኑ ተግባራዊ ምክሮችን ላቅርብላችሁ። በመጀመሪያ ለምን የግል የጸሎት ጊዜ ወይም “የጓዳ ጸሎት” እንዳስፈለገ በማብራራት እንጀምር።
“በጓዳ ውስጥ” መጸለይ
“የጓዳ ጸሎት” የሚለውን ስያሜ በማቴዎስ 5-7 ላይ ከሚገኘው ከታዋቂው የኢየሱስ “የተራራ ስብከት” የተወሰደ ነው። በዐውዱ መሠረት የኢየሱስ መመሪያ ይህ ነው፦ “ሰዎች እንዲያዩላችሁ፣ መልካም ሥራችሁን በፊታቸው ከማድረግ ተጠንቀቁ” (ማቴዎስ 6፥1)።
“ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኩራቡና በየመንገዱ ማእዘን ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ፤ ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል” (ማቴዎስ 6፥5-6)።
ድምጽን ከፍ አድርጎ መጸለይ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በአይሁዶች ዘንድ ሽልማት እንደሚያስገኝ ሁሉ፣ በእኛም በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በቤተ ክርስቲያን፣ በትንንሽ ኅብረቶች፣ በጓደኞች እንዲሁም በቤተሰብ ፊት ሽልማት አለው። ሌሎች ሰዎችን ማስደነቅ፣ ጸሎት ለመጸለያችን አነሣሽ ምክንያት ሊሆን ይችላል። የጸሎታችን ርዝመት፣ የድምጻችን ከፍታ፣ የቃላት እና የርዕስ አመራረጣችን በሰዎች ልብ ውስጥ ተጽዕኖ ለማሳደር ተጠቅመነው ሊሆን ይችላል።
በዚህ ቀጭን መንገድ ለመራመድ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያናችን፣ በቤታችን እንዲሁም በሌሎች ስፍራዎች በይፋ መጸለይ አለብን። እነዚህ ጸሎቶች ደግሞ ሌሎች ሰዎች እየሰሙን መሆን አለበት። እንዲሁም ጸሎቱም አብረውን ያሉትን ሰዎች ያካተተ መሆን አለበት። ነገር ግን አደጋው የሚጀምረው እግዚአብሔርን ወደ ጎን በመተው ትኩረታችን ራሳችንን ከፍ አድርጎ በማሳየት ላይ ሲሆን ነው።
የእውነተኝነት ፈተና
ነገር ግን “የጓዳ ጸሎት” በአደባባይ ለምናቀርበው ጸሎት እውነተኝነት ፈተና ነው። ቲም ኬለር በማቴዎስ 6፥5-6 ላይ እንዳብራራው፦
“ለመንፈሳዊ ታማኝነት ትክክለኛው ፈተና፣ ኢየሱስ እንዳለው የግል የጸሎት ሕይወት ነው። ብዙ ሰዎች ባህላዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው እንዲሁም በሕይወታቸው አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ ይጸልያሉ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር እንደ አባት የሆነ እውነተኛ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች፣ ከውጪ እንዲጸልዩ የሚገፋቸው ምንም ነገር ሳይኖር በራሳቸው ተነሳሽነት መጸለይ ይፈልጋሉ። በመንፈሳዊ ውድቀት ውስጥ ሆነው መጸለይ ይፈልጋሉ። የሰዎች ሽልማት በሌለበትም ስፍራ መጸለይ ይፈልጋሉ።” (Prayer, 23)
የግል ጸሎት እውነተኛ መሆናችንን ለማረጋገጥ ወሳኝ ፈተና ነው።
ለአቅም ማነስ መፍትሔ
ነገር ግን የግል ጸሎት የእውነተኛነታችን ፈተና ብቻ ሳይሆን፣ ለድክመቶቻችን ደግሞም እግዚአብሔርን ለመፈለግ ያለንን የአቅምና የፍላጎት ማነስ ችግርም መፍትሔ ነው። ጆን ፓይፐር ስለ ጸሎት እንዲህ ብሏል፦ ”ጸሎት ልባችን ምን እንደሚመኝ የሚገለጥበት መለኪያ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን በሚገባው መንገድ የማይፈልገው ልባችን መድኀኒት ጭምር ነው” (When I Don’t Desire God, 153)።
የግል ጸሎት ምን ያህል መንፈሳዊ እንደሆንን ያሳያል። የተሰበርን፣ ጎዶሎ እና ዐመፀኞች ሆነን ራሳችንን ለምናገኛቸው ቦታዎች ደግሞ መድኀኒት ነው።
የግንኙነት ስፍራ
በተጨማሪም ኬለር እንደገለጸው፣ “ከአምላክ ጋር እንደ አባት እውነተኛ ዝምድናን ለመመሥረት” ጸሎት እጅግ አስፈላጊ ነው። የጸሎት ዓላማ፣ ነገሮችን ከእግዚአብሔር ማግኘት ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱን ማግኘት ነው። ጸሎት ለእግዚአብሔር መልሰን የምንናገርበት፣ ለቃሉ ምላሽ የምንሰጥበት ቦታ ነው። እንዲሁም ጸሎት የምንፈልገው ነገር የምንጠይቅበት ብቻ ሳይሆን በራሱ በእግዚአብሔር ብቻ ሐሴት ማድረግን የምንለማመድበት ስፍራ ነው። በጸሎት፣ የእግዚአብሔርን ጆሮ የማግኘት ስጦታን እናገኛለን። በዚህም አገልጋዮች ብቻ ሳንሆን ወዳጆች መሆናችንን እንገነዘባለን (ዮሐንስ 15፥15)። እኛ ቃሉን ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን የእግዚአብሔር ልብ ያላቸው ልጆቹ ነን (ሮሜ 8፥15-16፤ ገላትያ 4፥6-7)። እግዚአብሔር ከእኛ መስማት ይፈልጋል። የጸሎት ኀይል እና ልዩ ጥቅም ይህ ነው።
ኢየሱስ “በጓዳ” ስለ መጸለይ የሰበከውን በሕይወቱ ሲተገብረው በዚህ ክፍል ላይ እናገኛለን። ኢየሱስ ምንም ድክመት አልነበረውም፤ እውነተኛ ስለ መሆኑም ምንም ጥርጣሬ አልነበረውም። ነገር ግን ከአባቱ ጋር ኅብረትን አጥብቆ ይፈልግ ነበር። ስለዚህም ደጋግሞ ብቻውን ይጸልይ ነበር። “ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላም ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፤ በጨለመም ጊዜ ብቻውን ነበረ” (ማቴዎስ 14፥23፤ ማርቆስ 6፥46)። ክርስቶስ ይህንን አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ የሚያደርገው ልማዱ ነበር። “ኢየሱስ ግን ብዙ ጊዜ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ወጥቶ ይጸልይ ነበር” (ሉቃስ 5፥16)። “ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድ ተነሥቶ ከቤት ወጣ፤ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራም ሄዶ ይጸልይ ጀመር”(ማርቆስ 1፥35)።
ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ከመምረጡ በፊት “ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ” (ሉቃስ 6፥12)። በጌቴሴማኒም ሦስት ጊዜ “ሄዶ ጸለየ” (ማቴዎስ 26፥36፣ 42፣ 44፤ ማርቆስ 14፥32-42)። አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ተሰቀለበት አርብ ዋዜማ ድረስ ከአብ ጋር ባለው ግንኙነት የግል ጸሎት ትልቅ ስፍራ ነበረው። የግል ጸሎት ያለውን ጥቅም ማጋነን አይቻልም። የግል የጸሎት ሕይወት በብዙ መልኩ የመንፈሳዊ ማንነታችን መለኪያ ነው። ጄ.አይ.ፓከር እንዴት መጸለይ እንዳለብን ሲናገር፣ “ልንመልሰው ከሚገባቸው እጅግ አስፈላጊ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ነው” በማለት አስፈላጊነቱን ገልጿል።
ለ”ጓዳ ጸሎት” የሚጠቅሙ አምስት ምክሮች
የግል ጸሎት ለክርስቲያን ያለው አስፈላጊነት ግልጽ ነው። ነገር ግን በተለያዩ የሕይወት ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ጸሎትን የምንጸልይባቸው መንገዶች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። የራሳችንን የግል ጸሎት ልምምዶቻችንን መፈተሽ ይገባናል። ለዚህም የሚሆኑ አምስት ምክሮችን ላቅርብ ።
1. ጓዳችሁን አዘጋጁ
ለግል ጸሎት የሚሆናችሁን መደበኛ ቦታ ፈልጉ። የተዘጋጀ ቦታ ካጣችሁም በራሳችሁ አዘጋጁ። በቀላሉ፣ ጠረጴዛ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ለመንበርከክ የሚመች የትኛውም ስፍራ መሆን ይችላል። ብዙ ሰዎች እንዳረጋገጡት በመኝታ ላይ ሆኖ ከመጸለይ ይልቅ ከመኝታ አጠገብ መጸለይ ይበልጥ ፍሬያማ ነው። ምናልባት ለመቀመጥ፣ ለመንበርከክ እንዲሁም ለመጻፍ እና ለማንበብ የሚሆን በቂ ብርሃን ያለው ክፍል ሊያገኙ ይችላሉ። ለጸሎት የሚሄዱበት ስፍራ መኖሩ የግል የጸሎት ሕይወትዎ ቀጣይነት እንዲኖረው ይረዳዎታል።
2. ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምሩ
ምክንያቱም ጸሎትን የጀመርነው እኛ ሳንሆን እግዚአብሔር ራሱ ነው። ስለዚህ ጸሎት እግዚአብሔር በቃሉ አማካኝነት ለሚናገረን ምላሽ መስጠት ነው። ከጆርጅ ሙለር የምንማረው ከቅዱሳት መጻሕፍት መጀመር እንዳለብን ነው። ሙለር በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ለዐሥርት ዓመታት በረጅም ጸሎት እና ለእግዚአብሔር ልብን በማፍሰስ እያንዳንዱን ቀን ጀምሬአለሁ። በእነዚህ ዓመታት የጸለይኳቸው ጸሎቶች ለእግዚአብሔር ቃል ምላሸ ሆነው ሲመጡ ብቻ እጅግ የበለጸጉና ትኩረት ያላቸው መሆናቸውን ተምሬያለሁ።”
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሙለር ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚያነብበት ጊዜ እግዚአብሔር እንዲረዳው ይጸልይ ነበር። ከዚያም የእግዚአብሔርን ቃል በማሰላሰል ከእግዚአብሔር ለመስማት ልቡን ይከፍት ነበር። ይህም በየቀኑ የእግዚአብሔርን ቃል በማሰላሰል የግል የጸሎት ጊዜውን አዳብሯል።
3. አወድሱ፣ ተናዘዙ፣ አመስግኑ፣ ጠይቁ።
መጽሐፍ ቅዱስን ካነበብንና ካሰላሰልን በኋላ ወደ “ነፃ ጸሎት” ወይም በልባችን ውስጥ ያለውን በጸሎት ከማቅረባችን በፊት ዊልያም ሎ እንዲህ ይላል፤ “ቋሚ እና በነፃነት የምትጸልዩት ነገር ይኑራችሁ።” ይህ የጠዋት የጥሞና ጊዜዎቻችን የተስተካከለ ቅርጽ እንዲኖረው ይረዳናል።
ማርቲን ሉተር ጸሎቶቻችን ጌታችን እንድንጸልይ ባስተማረን መልክ እንዲሆን ይመክራል። ይህንን ጸሎት እንዲህ ብለን ልንከፋፍለው እንችላለን፦ ውዳሴ፣ ኑዛዜ፣ ምስጋና፣ ልመና። በመጀመሪያ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና በማሰላሰል ስለ ተገለጠው እውነት እግዚአብሔርን አመስግኑት በመቀጠልም ኀጢአታችሁን ተናዘዙ፤ ከዚያም ስለ ጸጋው እና ስለ ምሕረቱ አመስግኑ፤ በመጨረሻም በቤተሰባችሁ፣ በቤተ ክርስቲያናችሁ፣ በግል ሕይወታችሁ እንዲሁም በሌሎች ነገሮች ለሚያስፈልጋችሁ ነገሮች ጠይቁ።
4. ፍላጎታችሁን ግለጹ፤ ቀጥሎም ፍላጎታችሁን በቅዱሳት መጻሕፍት ቃኙ።
በመጀመሪያ ቋሚ ጸሎት ቀጥሎም “ነፃ ጸሎት” ይኑራችሁ። ይህ “ነፃ ጸሎት” ልባችንን ለእግዚአብሔር የምናፈስበት እና በተለየዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙንን ሸክሞች እና ጭንቀቶች ለእግዚአብሔር የምንነግርበት ነው። በግል ጸሎቶቻችን ለእግዚአብሔር እና ለራሳችን ግልጽ መሆን አለብን። ለአባታችሁ የልባችሁን ንገሩት። እርሱ አስቀድሞ የልባችሁን ያውቀዋል። ነገር ግን ከእናንተ መስማት ይፈልጋል። ይህ የማይነገር ስጦታ ነው።
ነገር ግን ጸሎት የልቦቻችንን ፍላጎት የምንናገርበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን ፍላጎቶቻችንም ጭምር የሚቀረጹበት ነው። በጸሎት ውስጥ ኀይል አለ። ጸሎት ከምንም ነገር በላይ ልቦቻችንን መቀየር ይችላል። በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመዝሙረ ዳዊት እና የሐዋሪያትን ጸሎት (በኤፌሶን 1፥17-21፤ 3፥16-19፤ ፊልጵስዩስ 1፥9-11፤ ቆላስይስ 1፥9-12) የምንከተል ከሆነ ፍላጎቶቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይበልጥ እየተቃኘ ይመጣል።
5. ጸሎቶቻችሁን ሁሌም አዲስ አድርጉት
ለአዲስ ዓመት፣ ለአዲስ ወር፣ ወይም በአዲስ የሕይወት ወቅት የተለያየ የጸሎት ልምምድ ይኑራችሁ። ጸሎቶችን በትኩረት እና በጥንቃቄ ጻፉ። ለእግዚአብሔር ያላችሁን ፍቅር በጾም ጸሎት አሳድጉ፤ ከሕይወት ትርምስ ዕረፍት ወስዳችሁ በጸጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኙ።
በግል ጸሎት ውስጥ ያለውን ልዩ ጥቅምና ኀይል ለማግኘት ትኩረት ልናደርግ ያስፈልጋል። በሕይወታችን ውስጥ ይህን ያህል ቦታ የሚገባቸው ነገሮች እጅግ ትንሽ ናቸው።
በዴቪድ ማቲስ