የጾም ምስጢራዊ ጥቅሞች

አብዛኛውን ጊዜ ጾምን በአሉታዊ መልኩ የማሰብ ዝንባሌ አለን። ይህም ከምን የመነጨ እንደ ሆነ ለመረዳት አያዳግትም። ጾም መታቀብ ነው። ያለ ምግብ እና ያለ መጠጥ አልያም ሌሎች እግዚአብሔር ከሰጠን መልካም ነገሮች ተቆጥቦ መቆየት ነው። ምናልባትም ብዙዎቻችን ደጋግመን የማንጾምበት ምክንያት ጾምን የምናያይዘው ከምናገኛቸው ነገሮች አንጻር ሳይሆን፣ ከተቆጠብናቸው ነገሮች አንጻር ስለሆነ ነው።

ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ጾም መታቀብ ወይም የተወሰኑ ነገሮችን ትቶ መቆየት ብቻ አይደለም። እንዲያውም የክርስቲያናዊ ጾም ግብ ነገሮችን ትቶ መቆየት ሳይሆን አንዳች ነገርን ማግኘት ነው። መታቀባችን ሁልጊዜም የላቀ ግብ እና መዳረሻ አለው፤ እርሱም መጨረሻው ጥቅም እንጂ ጉዳት አይደለም። ክርስቲያናዊ ጾም አንድን ክርስቲያናዊ ግብ ለመምታት ሲባል የሚደረግ መታቀብ ነው። እንዲያ ካልሆነ ግን ፍጹም ክርስቲያናዊ አይሆንም።

ኢየሱስ የእርሱ ስለ ሆነችው ቤተ ክርስቲያን ሲናገር ትጾም እንደሆነ በማለት በመጠራጠር አልተናገረም። “ስትጾሙ” አለ እንጂ “ከጾማችሁ” አላለም (ማቴዎስ 6፥16-17)። በማቴዎስ ወንጌል 9፥15 ላይ “በዚያን ጊዜ ይጾማሉ” ሲል ኢየሱስ ቃል ገብቷል። በዚህም ቃሉ መሠረት የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ትጾም ነበር (የሐዋርያት ሥራ 9፥913፥214፥23)። እንዲሁም ላለፉት ሁለት ሺሕ ዓመታት ክርስቲያኖች ሲጾሙ ቆይተዋል። ስለዚህም ፍጹም ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ ስናደርገው ውጤቱ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አይሆንም። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ጾም መንፈሳዊ ድግስ እንዲሆንልን ዐላማውን እና ጥቅሙን ደጋግመን ልናስታውስ ያስፈልገናል።

የክርስቲያናዊ ጾም ዐላማ

ዛሬ ላይ ጾም በብዙ ስፍራዎች ፋሽን ወደ መሆን እየመጣ ነው። ስለዚህም ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ ከዓለም ሳይሆን ከኢየሱስ መመሪያ ለመውሰድ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ከአንድ ትውልድ በፊት፣ ጾም ለጤና ጥሩ እንዳልሆነ ብዙ ድምጾች ያስተጋቡ ነበር። ዛሬ ላይ ደግሞ የተገላቢጦሽ ነው። በርካታ የሥነ አመጋገብ ባለሙያዎች፣ “በትክክል ከተተገበረ፣ ጾም አካላዊ ጥቅሞች ሊኖሩት ይችላሉ” እያሉ እየሰበኩ ነው (Celebration of Discipline፣ 48)። ታዲያ ፋሽን በሆነው ጾም እና በክርስቲያናዊ ጾም መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

ቁልፍ ልዩነቱ ክርስቲያናዊ ዐላማው ነው። መንፈሳዊ ዐላማም ልንለው እንችላለን። ያም የቁስ ተጻራሪ በሚለው ሳይሆን ከተፈጥሮአዊው በተለየ ለማለት ነው። ታዲያ መንፈስ ስንል መንፈስ ቅዱስን ታሳቢ በማድረግ ነው። ለክርስቲያኖች ወሳኝና ሊቃለል የማይችል አንድ የክርስቲያናዊ ጾም ገጽታ ክርስቲያናዊ ዐላማው ነው። ያም ደግሞ ከልብ የሆነ ጸሎትን ለማጎልበት ወይም (ዕዝራ 8፥23ኢዩኤል 2፥12የሐዋርያት ሥራ 13፥3)፣ የእግዚአብሔርን ምሪት ለመሻት ሊሆን ይችላል (መሳፍንት 20፥26የሐዋርያት ሥራ 14፥23)። አልያም ማዳኑን እና ጥበቃውን ለመፈለግ (2ኛ ዜና 20፥3-4ዕዝራ 8፥21-23)ወይም በእርሱ ዘንድ ራሳችንን ለማዋረድ ሊሆን ይችላል (1ኛ ነገሥት 21፥27-29መዝሙር 35፥13)። ንሰሓን (1ኛ ሳሙኤል 7፥6ዮናስ 3፥5-8) ወይም ሐዘንን (1ኛ ሳሙኤል 31፥132ኛ ሳሙኤል 1፥11-12)፣ አልያም ስለ እርሱ ሥራ ያለንን ጭንቀት ለመግለጽ ሊሆን ይችላል (ነህምያ 1፥3-4ዳንኤል 9፥3)። እንዲሁም ፈተናን ለመቋቋምና ራሳችንን ለእርሱ ለማስገዛት ሊሆን ይችላል(ማቴዎስ 4፥1-11)። አልያም ደግሞ ከሁሉም በተሻለ መልኩ ፍቅራችንን እና መሰጠታችንን ለመግለጽና (ሉቃስ 2፥37) በጾማችን ውስጥ፣ “እግዚአብሔር ሆይ! አንተን የበለጠ እፈልግሃለሁ” ለማለት ሊሆን ይችላል።

ያለ መንፈሳዊ ዐላማ ክርስቲያናዊ ጾም የለም። እንዲያ ከሆነ ዝም ብሎ መራብ ብቻ ይሆናል።

የ(ክርስቲያናዊ) ጾም ጥቅሞች

ክርስቲያኖች ከምግብ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች፣ አልያም የሥነ አመጋገብ ባለሙያዎች አሁን ላይ እንደሚናገሩት፣ በጾም ሊገኙ ስለሚችሉ አካላዊ ጥቅሞች ሲሉ ሊጾሙ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ጾምን ክርስቲያናዊ የሚያደርጉት እነዚህ ግቦች አይደሉም። ይልቁንስ ዐላማ ላለው ክርስቲያናዊ ጾማችን ምን ዐይነት መንፈሳዊ ፍሬዎችን ከእግዚአብሔር ልንቀበል እንችላለን? በእምነት የተሞላ ጾምን እግዚአብሔር ምን ዐይነት ዋጋ ይሰጠዋል?

ክርስቲያናዊ ጾም ዋጋ እንዳለው ወሳኝ በሆነ ስፍራ ላይ ከክርስቶስ አንደበት በግልጽ እንረዳለን። በተራራው ስብከት ላይ ለታይታ ሳይሆን በስውር እንድንጾም ኢየሱስ ያበረታታናል። ተስፋውም ምን እንደ ሆነ ሲናገር፣ “በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል” ይላል (ማቴዎስ 6፥18)። እግዚአብሔር ለመጾማችን ዋጋ ይከፍለናል። ያ ግን የሚሆነው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ግልጽ ልናደርገው የሚገባን ወሳኝ ነገር አለ። እግዚአብሔር ዋጋ የሚሰጠው ጾም፣ የፈቃዳችንን ጥንካሬ የምናሳይበትን ሳይሆን ባዶነታችንን የምንገልጽበትንና በእርሱ ለመሞላት የተጠማንበትን ጾም ነው። ክርስቲያናዊ ጾም ከራሳችን ኀይልና አቅም የሚመጣ አይደለም። ይልቁንም የሚመነጨው፣ እግዚአብሔር ራሱ በእኛ ውስጥ ከሚሠራበት ልብ እና እግዚአብሔር ራሱ ከሚሰጠን አቅም ነው (ፊልጵስዩስ 2፥12-131 ጴጥሮስ 4፥11)።

ይህ ስለ እኛ ጥንካሬ እና ራስ የመግዛት አቅማችን እንዳልሆነ ከተረዳን፣ ለሌሎች ታይታ ሳይሆን በእርሱ ዐይኖች ፊት ስንጾም፣ እግዚአብሔር ነፃ በሆነውና ባልተገደበው ጸጋው አማካይነት ምን ዐይነት ዋጋን ይከፍላል ብለን እንጠይቅ።

  1.  ከልብ ለሆነ ጸሎት መልስ ይሰጣል

አንደኛውና ቀዳሚው መልስ ለምንጾምበት ዐላማ ዋጋ መስጠቱ ነው። ከላይ እንደተመለከትነው የጾም ልዩ ዐላማ ምን ነበር? ጾም ለጸሎት ረዳት በመሆን ያገለግላል። ወደ እግዚአብሔር ከምናቀርባቸው ጥያቄዎች ጋር ከጎን በመሆን፣ በክርስቶስ ባገኘነው ዕድል አማካይነት (ሮሜ 5፥2ኤፌሶን 2፥183፥12) ያልተለመደ ትጋትን ያሳያል። ጾም የጸሎት ሞግዚት በመሆን ከተለመደው የዕለት ተዕለት የጸሎት ኀይል በላቀ መልኩ ለእግዚአብሔር የተለየ ልመናን ያቀርባል።

በእምነት ሕይወት ውስጥ ጾም ልዩ የሆነ ርምጃ ነው። ተራ የሆነ ሕይወት ጾም አያውቀውም፤ ቋሚና ወጥ የሆነ የጸሎት ሕይወትን ይዞ ሰጪውን ስለ ምግብ እና መጠጥ ስጦታው እያመሠገኑ መኖር ነው። ጾም ግን ያልተለመደ ጸሎትን የምንጸልይበት እና ሰጪውን ከስጦታው በላይ እንደምንወደው የምናሳይበት ልዩ መንገድ ነው።

  1.  ራሱን እግዚአብሔርን የበለጠ ማግኘት

ይህ ከሁሉም ወደ ላቀው የክርስቲያናዊ ጾም ዋጋ ይመራናል። ያም ከላይ ከጠቀስናቸው “ዐላማዎች ሁሉ የሚልቅ” ነው። እርሱም ራሱ እግዚአብሔር ነው። ከእግዚአብሔር ምድራዊ ምሪት እና ጥበቃ እንዲሁም ትድግና እና መግቦት በላይ ወሳኙ ነገር ለዘላለም በእርሱ ደስ መሰኘታችን ነው።

እግዚአብሔር በመብላት እና በመጠጣት ውስጥ ስለ ራሱ ያስተምረናል። ዓለማችን በሚበላ እና በሚጠጣ ነገር የተሞላ እንዲሆን ያደረገው፣ አፋችን ሙሉ በሆነ ጊዜ መልካምነቱን እንድንቀምስ፣ ሆዳችን ባዶ ሲሆን ደግሞ ከምግብ እና ከመጠጥ ይልቅ እርሱ የላቀ እንደ ሆነ እንድንለማመድ ነው። ዋናው ድግስ እግዚአብሔር ራሱ እንደ ሆነ እንድናስታውስ ጾም ይረዳናል። “እናንት የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንት ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም፤ ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣ የወይን ጠጅና ወተት ግዙ” (ኢሳይያስ 55፥1)።

እግዚአብሔር ራሱ በክርስቶስ በኩል ምርጥ ከሚባለው ምግብ ይልቅ ያረካናል፤ ከጠለለው ውሃ ይልቅ፣ ከበለጸገው ወተት እና ከምርጡ ወይን ይልቅ ጥማችንን ያረካል። በእርሱ ውስጥ ነፍሳችን “መልካም የሆነውን ትበላለች”፤ “በጥሩ ምግብም ትደሰታለች” (ኢሳይያስ 55፥2)። “ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ዋጋ እሰጣለሁ” የሚለን እርሱ ነው (ራእይ 21፥6)። ቸርነቱን ቀምሰን ያየን (መዝሙር 34፥8) ሁላችን ከመንፈሱ ጋር በማበር፣ “የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነፃ ይውሰድ” እንላለን (ራእይ 22፥17)።

ሕመማችሁን በኢየሱስ ላይ ጣሉት

በምንጾምበት ጊዜ እውነተኛው ምግብ እና መጠጥ የዕለት እንጀራችን ሳይሆን፣ ኢየሱስ እንደ ሆነ ሆዳችን ውስጥ የሚሰማን ሕመም ማስታወሻ ነው። ኢየሱስ ቃል እንደገባው ክርስቲያኖች ይጾማሉ። ምክንያቱም እንደ እምነት ሰዎች በእርሱ ማመን ማለት የነፍሳችንን ራብ እንዲያስታግሥልን እና የነፍሳችንን ጥማት እንዲያረካልን ወደ እርሱ መምጣት ማለት እንደ ሆነ እናውቃለን (ዮሐንስ 6፥35)። ይህንንም አስረግጦ ሊያስታውሰን የሚችለው ዋነኛ ነገር ለተወሰነ ጊዜ ከምግብ እና መጠጥ መቆጠብ ነው።

ታላቁ፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ በግልጽ የማይታየው የጾም ዋጋ ራሱ እግዚአብሔር ነው። ሆዳችንን ባዶ በማድረግ፣ “አፍህን በሰፊው ክፈተው፤ እኔም እሞላዋለሁ” ይለናል (መዝሙር 81፥10)። እግዚአብሔር ለክርስቲያናዊ ጾም ዋጋ የሚሰጠው በአጽናፈ ዓለማችን ካለው ዐላማው ጋር ስለሚያቀናጀን ነው። ይህም ዐላማው እርሱን በመፈለጋችን፣ በእርሱ ደስ በመሰኘታችን እና በእርሱ እርካታን በማግኘታችን መክበሩ ነው። ለጾማችንም ዋጋ የሚሰጠን በጾማችን ውስጥ የጠየቅነውን ነገር ምላሽ በመስጠት ብቻ አይደለም። ይልቁንም በዋነኛነት ራሱን ለመሻታችን፣ ለደስታችን እንዲሁም ለእርካታችን መልስ አድርጎ ይሰጠናል።

ክርስቲያናዊ ጾም ነገሮችን ትቶ ስለ መቆየት ሳይሆን የበለጠ የምንሻው ነገር ላይ ያተኮረ ነው።