ነገረ መለኮትን ለወጣቶች እንዴት እናስተምራቸው?

ነገረ መለኮትን ለወጣቶች የማስተማሪያ ሦስት መንገዶች

በወጣቶች ወይም በኮሌጅ አገልግሎት እያገለገላችሁ ከሆነ፣ “ራት እና አስተምህሮ” ወይም “ነገረ መለኮት ዛሬ ምሽት” የተሠኙ ምሽቶችን ማስተዋወቅ፣ ብዙ ሰዎችን ለመሳብ የሚያስችል አስተማማኝ መንገድ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። በዐሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆችንና ጐልማሶችን፣ በነገረ መለኮታዊ ጥናት ውስጥ ማሳተፍ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ብዙውን ጊዜ በተለይም፣ አዝናኝ የሆኑ ነገሮች፣ እንዲሁም የሁለት ደቂቃ የቪዲዮ ክሊፖችና የድምፅ ቍርጥራጮችን የመሳሰሉ የማኅበራዊው ድረ ገጽ ባህል ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሮባቸዋል፡፡ ስለዚህም ዘላቂነት ላለውና ለተጠናከረ ነገረ መለኮታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ፍላጎት፣ በእጅጉ ሊደናቀፍ ይችላል። ቢሆንም፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ታማኝ አማኞች፣ ወጣቶቻችን ነገረ መለኮታዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸውና በእግዚአብሔር ቃል እየተመሩ በነገረ መለኮት ግንዛቤአቸው እንዲያድጉ የመፈተን ኀላፊነት አለባቸው።

በእኛ ቤተ ክርስቲያን ዐውድ፣ የወጣቶችና የኮሌጅ መጋቢያችን፣ ተማሪዎቻችንን የነጠረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ስለሚያሳውቃቸውና ወደ ጥልቅ ነገረ መለኮታዊ ግንዛቤ ስለሚገፋቸው አመስጋኝ ነኝ። የኮሌጅ ተማሪዎቻችን በታላላቅ የፒውሪታን መጻሕፍት ሥራዎች ላይ ለመወያየት ይገናኛሉ፤ እንዲሁም በእሑድ ምሽቶች፣ በታጨቁ ነገረ መለኮታዊ ርእሰ ጒዳዮች ላይ ለማብላላት ይሰበሰባሉ። የሁለተኛና የመካከለኛ ደረጃ ተማሪዎቻችን፣ ዐጭሩን የዌስት ሚኒስተር ካቴኪዝም አንድ በአንድ አጥንተዋል፤ ይህንም ያደረጉት፣ የካቴኪዝሙን ጥያቄዎች በቃላቸው በማጥናት፣ እንዲሁም የነገረ መለኮቱን ትርጓሜንና አተገባበርን በመማር ነው።

ከዚህ በታች፣ ቤተ ክርስቲያናችን በራሷ ዐውድ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በምትሻው፣ ልጆችንና ጐልማሶችን በነገረ መለኮታዊ አስተሳሰብ መቅረጽን በተመለከተ፣ ሦስት ማበረታቻዎችን በትሕትና ላቅርብ፦

1. ነገረ መለኮት አስደሳች እንደ ሆነ አሳዩአቸው

ወጣቶች ለነገረ መለኮታዊ ጥናትና ግንዛቤ ራሳቸውን እንዲሰጡ በማሳመን ረገድ፣ የመጀመሪያው “ምካቴ” የሚሆነው ነገረ መለኮት የማይተገበር ነው የሚለውን የተለመደ ምልከታ መቃወም ነው፡፡ ይህም፣ ነገረ መለኮት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መተላለፊያ ላይ ሳይሆን፣ በተጨናነቁ የሴሚናሪ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ብቻ መገኘት አለበት የሚል አስተሳሰብ ነው። ነገረ መለኮት፣ የሕይወታቸውን እያንዳንዱን ገጽታ ማለትም የአስተሳሰብ መንገዳቸውን (patterns)፣ የውሳኔ አሰጣጣቸውን፣ እምነታቸውን፣ ባህላዊ ተሳትፏቸውን፣ ተነሣሽነታቸውንና ግንኙነቶቻቸውን እንደሚቀርጽ ለወጣቶች ማሳሰቡ ጥሩ ነው። ስለ እግዚአብሔር የምናምነው ነገር፣ ስለ ራሳችን የበረታው ተግባራዊ ነገር ነው።

ምናልባትም ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በጣም አስገራሚው (አሉታዊ) የነገረ መለኮታዊ እምነት ተግባራዊ ገጽታ ምሳሌ በሮሜ 1፥18-32 ውስጥ ተዘርዝሯል። ከእምነትና ከአምልኮ ጋራ በተያያዘ የተጀመረው ኀጢአታዊ ውሳኔ (ፈጣሪን በጣዖት አምልኮ ለተመሰሉ ፍጥረቶች “መለወጥ”)፣ በሁሉም ዐይነት ኀጢአታዊ ባሕርዮችና ድርጊቶች ፍሬን አፍርቷል። በእውነት  የምናምነው ነገር በአኗኗራችን ፍሬን ያፈራል። እዚህ ነጥብ ላይ፣ ወጣቶች ቀድሞውኑም በነገረ መለኮታዊ አስተሳሰብ ሁልጊዜ ተሳታፊዎች መሆናቸውን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። በመዝሙር ግጥሞች፣ በትዊቶች፣ በቲክቶክ ቪዲዮችና በማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጽእኖ ፈጣሪዎች አማካይነት ለነገረ መለኮታዊ አስተሳሰብ “ደቀ መዝሙር” እየተደረጉ ይገኛሉ። በክርስቲያናዊ ነገረ መለኮታዊ ጥናት ላይ ባለመሳተፋቸው ገለልተኛ አይሆኑም፤ ነገር ግን ለሌሎች ልካቸውን ላልጠበቁ ነገረ መለኮታዊ ደቀ መዝሙርነት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

2. ነገረ መለኮት አስደሳች እንደ ሆነ አሳዩአቸው

ሴሚናሪ በነበርኩባቸው ዓመታቶቼ፣ ዶክተር ዲ.ኤ. ካርሰን፣ ተማሪዎቹ ያስተማራቸውን ነገሮች ሁሉ ባያስታውሱም፣ እርሱ በጣም ደስ የተሰኘባቸውን ነገሮች ሁልጊዜ የሚያስታውሱ መሆናቸውን ተናግሯል። በወጣቶች ላይ ለሚሠሩ መጋቢያንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን ሐሳብ ማቅረብ እፈልጋለሁ፤ ተማሪዎቻችሁ የነገረ መለኮት ፍቅር እንዲያዳብሩ ከምታደርጉባቸው ምናልባትም ከመጀመሪያ ርምጃዎች መኻል አንዱ፣ ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ቃሉ እንዲሁም ስለ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ውበት ያላችሁን የሚጋባ የደስታ ስሜት እንዲይዙ ማድረግ ነው።

የኮሌጅና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስለ ነገረ መለኮት ጥልቀት፣ ስለ ወንጌል ውበትና ስለ ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍት ብልጽግና ያለንን ፍቅር ሊገነዘቡ ይገባል፤ ምናልባትም ስለ ሀብቶቹ በራሳቸው መረዳት ማደግ ከመጀመራቸው በፊት ልናስገነዝባቸው ይገባል። ስለ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ለወጣቶቻችን የምንናገረው፣ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ በጣም የከበዱና የከበሩ ጒዳዮችን እንደምናካፍላቸው በሚያሳውቅ ዐይነት መንገድ ነውን?

3. ነገረ መለኮት በአምልኮ የተሞላ መሆን እንዳለበት አስታውሷቸው

ጳውሎስ፣ በኤፌሶን 1፥15-21 ጠቅለል አድርጎ ያስቀመጠው፣ ለኤፌሶን አማኞች ያቀረበው ውብ ጸሎት፣ “ነገረ መለኮታዊ ዕውቀት” ብለን በምንጠራው ጉዳይ ዕድገታቸው ርግጥ እንዲሆን የተደረገ ጸሎት ነው። ይሁን እንጂ እነርሱ በዕውቀት እንዲያድጉ ያቀረበው ጸሎት፣ ለአምልኮ ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ መሆኑ አያጠራጥርም። ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች በአምልኮ ሆነው፣ በከበረው አዳኛቸው የበለጠ ይደሰቱ ዘንድ፣ በጠለቀ ነገረ መለኮታዊ ግንዛቤ እንዲያድጉ ይፈልጋል። ይህን እንዲያውቁ ይፈልጋል፤ “በእርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ” (ኤፌሶን 1፥18-19)። ጳውሎስ ነገረ መለኮታዊ ዕውቀትን የሚፈልገው ለዕውቀቱ ብቻ ብሎ አይደለም። ለእርሱ፣ በነገረ መለኮታዊ ግንዛቤ የማደግ ዐላማና ግብ፣ ልባችንን ይበልጥ እግዚአብሔርን ወደማምለክ እንድናሳድግ፣ እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ስላለው ክቡር የማዳን ሥራው እንድናወድሰው ማድረግ ነው።

ነገረ መለኮታዊ አስተምህሮና ጥናት፣ ራሱን በቃሉ ከገለጠልን ከከበረው አምላክ ጋራ ካለው ግንኙነት ፈጽሞ መፋታት የለበትም። ስለ እርሱ ይበልጥ እየተረዳን ስንሄድ፣ እርሱን ማምለክና በእርሱ ይበልጥ መደሰት አለብን።