የክሕደት ረቡዕ ማታ
ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። (ማርቆስ 14፥10)
የካህናት አለቆች እርሱን መግደል ፈልገው ነበር። ነገር ግን በአደባባይ ሊገድሉት አልቻሉም። ሕዝቡ እርሱን በጣም ይወድደው ነበር። እንዲሁም እነርሱ በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ምስል ቀድሞውኑ የተበላሸ ነበር። ቤተ መቅደሱን በማንጻቱ፣ በምሳሌዎቹ፣ እነርሱ ካዘጋጁት ከእያንዳንዱ የቃላት ወጥመድ በብልሃት በማምለጡ፣ ኢየሱስ ይህን በሚገባ አሳይቷቸዋል። ስለዚህ በድብቅ እርሱን የሚይዙበት መንገድ አስፈለጋቸው። ይህም በፍጥነት መሆን ነበረበት።
እርሱ በኢየሩሳሌም ስለ ነበር ጊዜው ደርሶ ነበር። ነገር ግን ፋሲካ ሊከበር ሁለት ቀናት ቀርተውት ነበር። ሁለት ቀናት። ምን ያደርጉ ይሆን?
በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 14፣ የካህናት አለቆችን ከደም ጥማቸውና ከነጭንቀታቸው ትተናቸው፣ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ጥቂት ማይሎች ርቃ በምትገኘው ቢታንያ ውስጥ ወዳለ አንድ ቤት ትኲረታችንን እናዞራለን። ለምጻሙ ስምዖን ግብዣ እያደረገ ነበር። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱና ሌሎችም በማእዱ ዙሪያ ተቀምጠው ነበር። ከዚያም አንዲት ሴት መጣች። ዮሐንስ 12፥3 የመጣችው ሴት የአልዓዛር እኅት ማርያም እንደ ነበረች ይነግረናል፤ ነገር ግን ማርቆስ ስሟን ሳይጠቅስ ማለፍን መርጦ፣ “አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፣ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አፈሰሰችው” ይለናል (ማርቆስ 14፥3)።
እጅግ የከበረ። እንዲያውም በገበታው ዙሪያ ለነበሩት ለአንዳንዶቹ፣ ከመጠን በላይ ውድ ነበር።
በዐሥራ ሁለቱ መካከል ያለ ከዳተኛ
የአንድ ዓመት ደመወዝ የሚያወጣ ሽቱ ከብልቃጡ ፈሰሰ። ክፍሉን የሞላው መዓዛ ለአንዳንድ እንግዶች ብክነት ሆኖ ተሰማቸው። “ሽቱው ለምን እንደዚህ በከንቱ ይባክናል?” እያሉ አጉረመረሙ። “ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፣ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር” (ማርቆስ 14፥4-5)። ይህ ከንቱ ንግግር ነበር። ለድኾች ግድ አልነበራቸውም። በርግጥ ይፈልጉ የነበረው በበጎ አድራጎት በጀታቸው ውስጥ የተሞላ የሳንቲም ከረጢት ነበር። ቢያንስ፣ ይሁዳ ይፈልግ የነበረው ይህን ነው። ሽቱን መሸጥ ሊሰርቅ የሚችልበትን ተጨማሪ ገንዘብ የማግኘት ዕድልን ይሰጠዋል (ዮሐንስ 12፥6)።
ኢየሱስ የገሊላን ባሕር እንደ ገሠጸው ሁሉ፣ ይህንም ማጉረምረም ገሠጸው። ነገር ግን ዐመፅ እየተቀነባበረ ነበር። ማርቆስ የትረካውን ትኲረት ከቢታንያ ወደ ካህናት አለቆች ይመልሰዋል። ሰላዩ ይሁዳ ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው የሁለት ማይል ፈጣን ጕዞ የሃይማኖት መሪዎቹ በስውር በሚሰበሰቡበት ስፍራ አገኛቸው። ምናልባትም በስምዖን ቤት ውስጥ በደረሰበት ኀፍረት በቊጣ እየተንገበገበ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ለገንዘብ ያለው ፍቅር አስተሳሰቡን ስላጨለመው አሁን ያየውን ብክነት ሊረሳው አልቻለም ይሆናል። ብክነት ብቻ ሳይሆን፣ ኢየሱስ ያደነቀው ብክነት ነው። ኢየሱስ፣ “መልካም ነገር አድርጋልኛለች” አለ። “ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች” (ማርቆስ 14፥6፣ 8)።
ምናልባት ይሁዳ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ሲያዘግም እነዚህን ቃላት እያብሰለሰለ ሊሆን ይችላል። “እሺ ኢየሱስ። ለመቀበር ተዘጋጅተሃል? እንግዲያውስ፣ መቃብርህን እንደምታገኝ አረጋግጣለሁ። ከሁሉም በላይ፣ ያ ሁሉ ሽቱ ሲባክን ማየት አልወድድም።”
ሠላሳ የብር ሳንቲሞች
ስለዚህ፣ ይሁዳ የካህናት አለቆች ሲጠብቁት የነበረውን መፍትሔ አቀረበላቸው፤ እርሱም ጌታውን አሳልፎ ሊሰጥ ተስማማ። ነገር ግን ያለምንም ክፍያ አልነበረም። ማርቆስ የካህናት አለቆች ለይሁዳ ገንዘብ ሊሰጡት “ቃል እንደ ገቡለት” ዘግቧል (ማርቆስ 14፥11)። “ቃል እንደ ገቡለት” የሚለው ሐረግ ይሁዳ በክፍያው እንዳልተገረመ ይጠቊማል። በምላሹ ካህናቱን ገንዘብ እንዲሰጡት የተደራደራቸው ይመስላል። የማቴዎስ ወንጌልም ይህንኑ ይነግረናል፦ “ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት” (ማቴዎስ 26፥14-15)።
የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ድራማ በሁለት ገጸ ባሕርያት ዙሪያ ያጠነጥናል፤ እነርሱም ኢየሱስን ሽቱ የቀባችው ሴትና ይሁዳ ሲሆኑ፣ ለኢየሱስ የሰጡትን የሚቃረኑ ምላሾችን ያሳያል። ነገር ግን ሦስተኛ ገጸ ባሕርይ አለ፤ እርሱም ክፉና ስውር የሆነ ተቃዋሚ ነው።
ገንዘብ።
ይሁዳና ዐብረውት የሚያጉረመርሙት ሰዎች በስምዖን ቤት የነበረውን የሽቱ ዋጋ ምን ያህል በፍጥነት መገመት እንደ ቻሉ አስተውሉ። ልምድ እንዳላቸው ሸማቾች፣ የአንድን ነገር ዋጋ በአንድ እይታ ማወቅ ይችሉ ነበር። ናርዶሱ ገና ከብልቃጡ ሳይወጣ፣ “ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ሊሸጥ ይችል ነበር” እያሉ ያሰሉ ነበር (ማርቆስ 14፥5)።
ለክርስቶስ ዋጋ ያለ ዕውርነት
ሆኖም፣ በማርቆስ ወንጌል 14 ላይ ያለው አስገራሚ ምጸት፣ ይሁዳ በኢየሱስ ራስ ላይ የሚፈስሰውን የሽቱ ዋጋ ማየት ችሎ፣ የኢየሱስን ዋጋ ግን ማየት አለመቻሉ ነው። ዐይኑ የታወረ የነገሮችን ትክክለኛ ዋጋ ማየት የማይችል ሰው ነው። በሴትዮዋ ላይ ያን ያህል የተበሳጨውም ለዚህ ነው። በሌላ በኩል ሴትየዋ፣ የሽቱውን ዋጋ የኢየሱስንም ዋጋ ማየት ችላለች። ብልቃጡንም የሰበረችው ለዚህ ነው።
የክሕደት ረቡዕ፣ 1 ጢሞቴዎስ 6፥10ን የሚያስታውስ አሳዛኝ ቀን ነው፤ “ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው። አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጕጕት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”
ነገር ግን የክሕደት ረቡዕ በተስፋም የተሞላ ነው፤ ምክንያቱም፣ የኢየሱስ ውበት ገንዘብን የመውደድ ፍላጎትን ሊያሸንፍ እንደሚችል ያሳየናል። ይህ፣ ሴትየዋ ለእኛ የምታስተላልፈው መልእክት ነው፤ ኢየሱስም ደጋግመን እንድንሰማው የፈለገው መልእክት ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል” (ማርቆስ 14፥9)።