ጸሎተ ሐሙስ ጠዋት
ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት ያለው ሐሙስ ምሽት ነው። ይህ ምሽት በትምህርት የተሞላ (ዮሐንስ 13-17)፣ ታላቅ የሆነው እርሱ የታናናሾቹን እግር በማጠብ አስደንጋጭ ነገር የፈጸመበት (ዮሐንስ 13፥3-20)፣ የጌታን ራት ሥርዐት በመመሥረት አዲስ ዘመንን ያበሰረበት (ማቴዎስ 26፥20-30፤ ማርቆስ 14፥17-26፤ ሉቃስ 22፥14-20)፣ እንዲሁም ይሁዳ ከመውጣቱ የተነሣ ወሳኝ የሆነ ምሽት ነበር (ዮሐንስ 13፥30)።
አሁን ኢየሱስና ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ወደ ጌቴሴማኔ የአትክልት ስፍራ ሄደዋል (ዮሐንስ 18፥1፤ ማርቆስ 14፥32)። በዚህ ስፍራ ኢየሱስ በዓለም ላይ ከሁሉ የላቀውን ጸሎት ጸለየ። በእንጥልጥል ላይ የነበረው የእግዚአብሔር ጸጋ ክብርና የዓለም መዳን ነበር። የኢየሱስ ወደ ምድር የመምጣት ተልእኮ ስኬት የተመሠረተው በኢየሱስ ጸሎትና በተሰጠው ምላሽ ላይ ነበር። በፍርሀት ጸለየ ልመናውም ተሰማለት።
እኔ ለመመለስ የምሞክረው ጥያቄ፣ ዕብራውያን 5፥7 በጌቴሴማኔ ከነበረው ጸሎት ጋራ እንዴት ይዛመዳል? የሚለውን ጥያቄ ነው። ዕብራውያን 5፥7 እንዲህ ይላል፤ “ኢየሱስ በዚህ ምድር በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋራ አቀረበ፤ ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት።” ጩኸቱ ተሰምቷል። ልመናውንም አግኝቷል። ይህ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ምንን ያመለክታል?
በአትክልቱ ስፍራ የተሰማ ብርቱ ጩኸት
በኢየሱስ የሕይወት ተሞክሮ ውስጥ ከጌቴሴማኔ ጸሎት ይልቅ ለዚህ ገለጻ የሚቀርብ ሌላ ምንም ነገር የለም። “ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋራ አቀረበ” የሚለው ሐሳብ፣ ሉቃስ 22፥44 ላይ ካለው፣ “እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስስ ነበር” ከሚለው ጋራ በስሜት ይዛመዳል። “ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ” የሚሉት ቃላት የኢየሱስን መንፈሳዊ ጭንቀት የሚገልጽ ነው።
ዕብራውያን 5፥7 ላይ የተጠቀሰው የኢየሱስ፣ “ጸሎትና ልመና” ይዘት ምን ነበር? የጸሎቱ ይዘት፣ “ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው” (ማርቆስ 14፥36) የሚል ነበር ብለን ካሰብን፣ ታዲያ፣ “ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት” (ዕብራውያን 5፥7) የሚለው ምን ትርጕም ይኖረዋል? የዕብራውያን መልእክት የሚያስተምረው፣ ኢየሱስ “እግዚአብሔርን በመፍራቱ” ምክንያት ጸሎቱ እንደ “ተሰማለት” ይኸውም ልመናውን እንዳገኘ ነው።
ነገር ግን ጽዋው አልተወሰደም። አካላዊ ሥቃይንና መለኮታዊ ቊጣን ሙሉ በሙሉ ተቀበለ። ታዲያ ኢየሱስ፣ “ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት” የሚባለው በምን መንገድ ነው?
የመጀመሪያ ጸሎቱና የመልአኩ ርዳታ
የማቴዎስ ወንጌልም ሆነ የማርቆስ ወንጌል ኢየሱስ ሦስት የተለያዩ ጊዜያት ላይ መጸለዩንና በእያንዳንዱ ጊዜያትም ተኝተው ወደ ነበሩት ወደ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እንደ ተመለሰ ይገልጻሉ። በሌላ በኩል የሉቃስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ጸሎት አንድ አጠቃላይ ገለጻ የሚሰጥ ሲሆን፣ ለጥያቄያችን መልስ የሚጠቊመንን አንድ ዝርዝር ጕዳይ ያካትታል፤ እርሱም የመልአኩ መምጣት ነው። ሉቃስ እንዲህ ብሎ ጽፏል፣
“ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ ተንበርክኮ ጸለየ፤ እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው። እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስስ ነበር።” (ሉቃስ 22፥41-44)
መልአኩ እርሱን “ሊያበረታ” ከመምጣቱ በፊት፣ ኢየሱስ ጽዋዋ እንድትወሰድለት ጸልዮ ነበር (ሉቃስ 22፥42)። ከዚያም መልአኩ “ሊያበረታው” መጣ። ለምን ዐላማ ነው የሚያበረታው? ሊያደርገው የሚገባውን ነገር እንዲያደርግ እንደ ሆነ ግልጽ ነው። በሌላ አነጋገር፣ መልአኩ ለኢየሱስ የመጀመሪያ ጸሎት የእግዚአብሔር ምላሽ ነበር። መልአኩ የእግዚአብሔርን መልእክት ይዞ መጥቷል፤ መልእክቱም፣ ሌላ መንገድ የለም፣ ነገር ግን እረዳሃለሁ። ምንም እንኳ ከፊትህ ያለው ነገር እጅግ አስፈሪ ቢሆንም፣ ከተልእኮህ ወደ ኋላ አትመለስ። እረዳሃለሁ። አንተን ለማበርታት እነሆ መልአኬን ልኬያለሁ የሚል ነው።
ታዲያ ጥያቄው፣ ከዚያ በኋላ የተጸለዩት ጸሎቶች ይዘት ምን ነበር? የሚል ነው። ሉቃስ 22፥44፣ “እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር” ይላል። ይህ ማለት፣ “ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” የሚለውን ልመና ይበልጥ አጥብቆ ማቅረቡን ቀጠለ ማለት ነውን? ይህ ዐይነቱ ግምት ለኢየሱስ የማይመጥን ነው። ታዲያ ምን እየጸለየ ነበር? ይህ ጸሎትስ የዕብራውያን መልእክት፣ “ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት” ብሎ ከገለጸው ጸሎት የሚለይ ነውን?
ሁለተኛ ጊዜ ጸለየ
በማቴዎስ ወንጌል መሠረት፣ ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ሊጸልይ ራቅ ብሎ ሲሄድ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገራቸውን ተመሳሳይ ቃላት አልተናገረም። ለመጀመሪያ ጊዜ “አባት ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ” ብሎ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ግን፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” በማለት ጸልዮአል (ማቴዎስ 26፥42)።
ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጸልይ፣ መልአኩ መጥቶ ጽዋውን ሳይጠጣ ማለፍ እንደማይችል፣ ነገር ግን በዚህ ፈተና ውስጥ እግዚአብሔር እንደሚረዳው ለኢየሱስ ግልጽ እንዳደረገለት መገመት እንችላለን። “ጽዋው ሳይጠጣው የማያልፍ” መሆኑን ከማወቁ አንጻር፣ ኢየሱስ በሁለተኛው ጸሎቱ ላይ ጽዋው እንዲወሰድለት በመጠየቅ ፈንታ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን የጸለየው፣ ከዚህ የተነሣ ነው፤ “እኔ ሳልጠጣው ያልፍ ዘንድ የማይቻል ቢሆን (ይህም አሁን በመልአኩ መምጣት ግልጽ ሆኖልኛል)፣ ፈቃድህ ይሁን።”
የማርቆስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ሁለተኛ ጸሎት ሲናገር፣ “እንደ ገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየ” ማለቱ (ማርቆስ 14፥39)፣ ሦስቱንም ጊዜያት የተነገሩት እነዚያው ተመሳሳይ ቃላት ብቻ እንደ ሆኑ ተደርጎ ከዚህ በተቃርኖ መወሰድ የለበትም። “መጀመሪያ የጸለየውን” የሚለው ሐረግ በቀላሉ፣ “ፈቃድህ ትሁን” የሚለውን ሊያመለክት ይችላል። በርግጥም ኢየሱስ በእያንዳንዱ ጊዜ የጸለየው ይህንኑ ነው።
በዚህ ትክክለኛ ምልከታ ላይ ከሆንን፣ መልአኩ ከመጣ በኋላ የነበረው የኢየሱስ ልመና ይዘት ከበፊቱ ጋራ ተመሳሳይ አልነበረም። “ይህንን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” በማለት መጸለዩን አልቀጠለም። “እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር” ይላል (ሉቃስ 22፥44)። ጽዋው እንዲወሰድለት ይበልጥ አጥብቆ እየጸለየ ካልነበረ፣ ታዲያ ምን እየጸለየ ነበር?
ከሁሉ የላቀው የመታዘዝ ተግባሩ
ዕብራውያን 5፥7 እንዲህ ይላል፤ “ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋራ አቀረበ፤ ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት።” “ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው” ማለት “ይህን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” ማለት ካልሆነ፣ ታዲያ ምን ማለት ነው? ምክንያቱም እርሱ በርግጥ ሰምቶታል፤ ይህንም ልመና ተቀብሎታል።
ጆናታን ኤድዋርድስ (Jonathan Edwards) እንዲህ ሲል ይመልሳል፣
ይህ ክርስቶስ ሊፈጽመው የነበረው ከሁሉ የላቀው የመታዘዝ ተግባር ነበር። ድካም ያለበት ሰብአዊ ተፈጥሮው እንዲደገፍ፣ በዚህ ታላቅ ፈተና ውስጥ እንዳይወድቅ፣ እንዳይሰጥምና እንዳይዋጥ፣ እንዲሁም ኀይሉ ዝሎ መጽናት አቅቶት የተመደበለትን መታዘዝ ሳይፈጽም እንዳይቀር፣ ብርታትንና ርዳታን ይጠይቃል።
ደካማ የሆነው ኀይሉ እንዳይሸነፍ፣ በዚህ ታላቅ ፈተና ውስጥ እንዳይወድቅ፣ ሊሞተው ባለው በዚያ ሞት እንዳይዋጥ፣ በዚህም ከሞት ሳይድን እንዳይቀር ፈርቶ ነበር። ስለዚህም ሊያበረታው፣ ሊደግፈውና ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው አምላክ ብርቱ ጩኸትንና እንባን አቀረበ፤ ይህንም ያደረገው፣ ሊቀበለው ያለው ሞት ፍቅሩንና ታዛዥነቱን እንዳያሸንፈው፣ ይልቁንም እርሱ ሞትን አሸንፎ ከርሱ እንዲድን ነው።
ኢየሱስ ጽዋው እንዲያልፍለት መጸለዩን አልቀጠለም። ይልቁንም ይጠጣው ዘንድ መጸለዩን ቀጠለ።
ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ሲናገር፣ “ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው” (ፊልጵስዩስ 2፥9) ሲል፣ “ስለዚህ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው፣ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ያሳየውን የማይናወጥ ታዛዥነትን ነው፤ “ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ።…” (ፊልጵስዩስ 2፥8)። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት ያዳነው ታዛዥ ስለ ነበረ ነው። ጸሎቶቹም ተመልሰውለታል።
የአብ ምላሽ
ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ባይሆን ኖሮ፣ ለዘላለም በሞት ይዋጥ ነበር። ትንሣኤ፣ ድነት፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ጸጋ ክብርና በእግዚአብሔር ልጆች የተሞላ የወደ ፊት ዓለም አይኖርም ነበር። ኢየሱስ፣ “ከሞት ሊያድነው ወደሚችል” አምላክ የጸለየው ለዚህ ነው፤ ይኸውም፣ የማዳን ተልእኮውን ወደ ግብ ከማያደርስ ሞት እንዲያድነው ነው።
“በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት።” እግዚአብሔር በርግጥም እንዲህ ዐይነቱ ሞት በታዛዥነቱ ላይ ከሚያመጣው አደጋ ታድጎታል። ኢየሱስ ተልእኮውን አሳክቷል። ለሚያምኑ ሁሉ ድነት አለ። በእግዚአብሔር ጸጋ ክብርና በእግዚአብሔር ልጆች የተሞላ አዲስ ዓለም ይመጣል።
ይህ ሁሉ የተገኘው በዓለም ላይ ከሁሉ በላቀው ጸሎት ምክንያት ነው። እያንዳንዱ የወንጌል ተስፋ የተሳካው፣ ኢየሱስ በጸሎት ባሳየው እግዚአብሔርን የመፍራት ትጋት፣ እንዲሁም አብ በሰጠው ምላሽ ምክንያት ነው። “እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር… በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት” (ሉቃስ 22፥44፤ ዕብራውያን 5፥7)።
ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው፣ ኢየሱስ በጌቴሴማኔ ጸሎቱን ሲያጠናቅቅ፣ አብ ከመስቀሉ ውጭ ሌላ መንገድ እንደሌለ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ መንገድም ስኬታማ እንደሚሆን ግልጽ አድርጎለት ነበር። በጉ የሥቃዩን ዋጋ ያገኛል። “ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ሥቃይ በኋላ፣ የሕይወት ብርሃን ያያል፤ ደስም ይለዋል” (ኢሳይያስ 53፥10-11)።
ዕብራውያን 12፥2 “እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ” የሚለው በርግጥም ለዚህ ነው። አሁን ካለው አሠቃቂ ሥቃይ ሥር፣ የወደ ፊቱ የደስታ ጣዕም ነበረ። መልአኩ፣ “ሊያበረታው” መጥቶ ነበር፤ የሚያበረታውም ሊመጣ ያለውን ደስታ በማብራራት፣ በማረጋገጥና ከአሁን መከራው ጋራ በማገናኘት ነበር።