ጸሎተ ሐሙስ ማታ
“አባ፣ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” (ማርቆስ 14፥36)
ኢየሩሳሌምን ጨለማ ውጧት ነበር። ነዋሪዎቿ የፋሲካ ራታቸውን በልተው ጨርሰዋል። ጠቦቱና ያልቦካው ቂጣ ተበልቷል፤ ጫማዎች፣ በትርና መቀነቶች ወደ ጐን ተቀምጠዋል (ዘፀአት 12፥1-11)።
በቀያፋ ቤት ውስጥ ከአንዳንድ የሸንጎ አባላት፣ ከቤተ መቅደስ ዘብ መኮንኖችና ከኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች መካከል አንዱ ከሆነው ጋራ ስብሰባ እየተካሄደ ነበር። ከከተማዋ ምሥራቃዊ ቅጥር ውጭ በቤተ መቅደሱ ትይዩ ባለችው በተገለለችው የጌቴሴማኔ የወይራ አትክልት ስፍራ ውስጥ፣ ኢየሱስ ከሌሎቹ ዐሥራ አንድ የቅርብ ወዳጆቹ ጋራ ተቀምጦ ነበር። ዐሥራ አንዱ ወዳጆቹ ነቅተው መጠበቅ አቃታቸው፤ ኢየሱስ ግን መተኛት አልቻለም።
ታላቁ ፋሲካ ተገለጠ
ቀደም ብሎ በዚያ ምሽት፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ በዘመናት ሁሉ እጅግ አስደናቂ የሆነውን የፋሲካ ራት ተካፍሎ ነበር። በርግጥ ደቀ መዛሙርቱ ይህን የተገነዘቡት ቈይተው ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያስቡት ነበር። ኢየሱስ ይህን ፋሲካ ከእነርሱ ጋራ ሊበላ “በጣም ይመኝ” ነበር (ሉቃስ 22፥15)። ምክንያቱም፣ በግብፅ የነበረው ፋሲካ ምሳሌና ጥላ ሆኖ የሚጠቊምለት ታላቁ ፋሲካ ሊፈጸም ተቃርቦ ነበርና።
የሞት መልአክ የበኩር ልጁን ሊወስድ እየመጣ ነበር (ቈላስይስ 1፥15)። እጅግ የከፋው የእግዚአብሔር የፍርድ መቅሠፍት ሊወርድ ነው። ነገር ግን ሁሉ በሁሉ የሆነው ይህ የበኩር ልጅ (ቈላስይስ 3፥11)፣ የዓለምን ኀጢአት ለማስወገድ የሚታረደው የፋሲካ በግም ጭምር ነበር (ዮሐንስ 1፥29፤ ራእይ 5፥6)። ዘላለማዊ ታዛዥ የሆነው የበኩር ልጅ፣ ነውር የሌለበት የእግዚአብሔር በግ፣ የዐመፅ ልጆችን ኀጢአት ሁሉ በራሱ ላይ ይወስዳል (ኤፌሶን 5፥6)፤ ደሙ ይሸፍናቸዋል፤ የርሱንም ጽድቅ ይቀበላሉ (2 ቆሮንቶስ 5፥21) እንዲሁም ከሞት መልአክ ጥፋትም ለዘላለም ይከለላሉ (ዮሐንስ 11፥26)።
ስለዚህ በብዙ ወንድሞች መካከል በኲር የሆነው (ሮሜ 8፥29) ታላቁ የፋሲካ በግ፣ እንጀራንና ወይንን አንሥቶ ለመጀመሪያዎቹ ዐሥራ አንድ ወንድሞች፣ “ይህ ሥጋዬ ነው… ይህ ደሜ ነው” አላቸው (ማርቆስ 14፥22-25)። ይህን በማድረጉም አሮጌው ፋሲካ በአዲሱ ፋሲካ ውስጥ ተካተተ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ አዲሱ የፋሲካ ራት የሚበላው ኢየሱስን (1 ቆሮንቶስ 11፥23-26) በማሰብ ነው። ደግሞም ወንድሞቹንና እኅቶቹን ሁሉ ከኀጢአትና ከሞት ባርነት እንዴት ነጻ እንዳወጣቸው፣ እንዲሁም ተስፋ ተደርጎ ወደ ተሰጠው ዘላለማዊ ወደ ሆነው ወደሚወድደው ልጁ መንግሥት እንዴት እንደ መራቸው በማሰብ ነው (ቈላስይስ 1፥13)።
ስምንት የማይመረመሩ ቃላት
አሁን ግን በወይራ ዛፎች መካከል፣ ኢየሱስ እየጸለየ ነበር። ብዙ ጊዜ “ወደ ገለልተኛ ስፍራ” ወጥቶ ይጸልይ ነበር (ሉቃስ 5፥16)። ነገር ግን እንዲህ ያለ የብቸኛነት ሥቃይ አይቶ አያውቅም ነበር።
በዚህ በለመደው የጸሎት አትክልት ስፍራ፣ ኢየሱስ ሊጠጣው ያለውን የአባቱን ጽዋ በጥልቀት ተመልክቶ እጅግ ተሸበረ። ሰውነቱ ሊመጣ ካለው ከስቅለት አካላዊ ሥቃይ ለመሸሽ ፈልጎ ነበር። ቅዱስ መንፈሱም በአባቱ መተው ከሚያስከትለው እጅግ የከፋ መንፈሳዊ ሥቃይ የተነሣ በማይነገር ፍርሀት ሆኖ ቃተተ።
ወደ ዓለም የመጣው ይህንኑ ሊፈጽም ቢሆንም (ዮሐንስ 12፥27)፣ በዚህ “ጥምቀት” ላይ የነበረው ጭንቀት እጅግ ታላቅ ስለ ነበር (ሉቃስ 12፥50)፣ ኢየሱስ፣ “አባ፣ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” በማለት ጮኸ (ማርቆስ 14፥36)።
ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን። ስምንት ቃላት። ስምንት የማይመረመሩ ቃላት።
እግዚአብሔር፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ነጻ ለመውጣት ፈልጎና ተማጽኖም እንኳ፣ በእነዚህ ስምንት ዐጫጭር ቃላት ውስጥ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ያለውን ትሑት እምነትና መታዘዝ ገለጸ። ይህም ከተፈጠሩት ሰማያትና ምድር ክብር ሁሉ የላቀ ውበት ነበረው። ይህ ጥልቅ ሥላሴያዊ ምስጢር ነው፤ እግዚአብሔር ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፤ በሮማውያን መስቀል በአሰቃቂ ሁኔታ የእግዚአብሔርን መሞት የሚያስከትል ቢሆንም እንኳ፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ግን ታዛዥ ሆነ (ፊልጵስዩስ 2፥6፣ 8)። በዚያ በጨለማው ሰዓት፣ እግዚአብሔር በነፍስና በሥጋ የእግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ መንገድ እንዲፈጸም ቢመኝም፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር እንድትሆን እግዚአብሔር ፈልጓል።
በመከራ ውስጥ ያለ መታዘዝ
በዚያች ቅጽበት ሌላ ምሥጢር ተገለጠ። ከዘላለም ለእግዚአብሔር አብ ፍጹም ታዛዥ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ፣ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ” (ዕብራውያን 5፥8)። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ለማምለጥ እንደዚህ ያለ ኀይለኛ ፍላጎት የተሰማው ሌላ የሰው ልጅ ታይቶ አያውቅም። እንዲሁም በአብ ፈቃድ ላይ እንደዚህ ያለ ትሑትና ታዛዥ እምነት የተገበረ ሌላ የሰው ልጅ ኖሮ አያውቅም። “በዚህም ፍጹም ሆኖ ከተገኘ በኋላ” ማለትም፣ በአባቱ ላይ ፍጹም የሆነ የታዛዥነት መታመንን በሁሉም አቅጣጫዎች ተግባራዊ በማድረግ፣ “እርሱን ለሚታዘዙ ሁሉ የዘላለም ድነት ምክንያት ሆነላቸው” (ዕብራውያን 5፥9)።
ወልድ ለአባቱ ፈቃድ ራሱን አሳልፎ በመስጠት ይህን ፍጹምና ከምንም በላይ የሆነ ትሑት መታዘዝን ሲማር፣ ላቡ እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስስ ነበር (ሉቃስ 22፥44)።
አንድ ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ላይ፣ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ፣ ከዳተኛው ደቀ መዝሙር ችቦ የያዙ አነስተኛ የወታደሮችና የአገልጋዮች ቡድንን ይዞ ወደዚያ ለምዶት ወደ ነበረው የጸሎት አትክልት ስፍራ ለመምራት እየተዘጋጀ ነበር።
ፈቃድህ ትሁን
ለሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መቀበል ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ከእግዚአብሔር በተሻለ የሚረዳ ማንም የለም። የእግዚአብሔር አብን ፈቃድ በመቀበልም ከእግዚአብሔር ወልድ በላይ መከራን የተቀበለ የሰው ልጅ የለም። ኢየሱስ ዋጋው ምንም ይሁን ምን እርሱን እንድንከተል ሲጠራን፣ እርሱ ራሱ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነውን ወይም አድርጎት የማያውቀውን ነገር እንድናደርግ እየጠራን አይደለም።
“የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን” ኢየሱስን የምንመለከተው ለዚህ ነው (ዕብራውያን 12፥2)። ከፊታችን ለተቀመጠው ዘላለማዊ ደስታ ስንል፣ አንዳንድ ጊዜ እጅግ የሚያሠቃየውንና ለጊዜው የሚያሳምመውን የእግዚአብሔር ፈቃድ በፈቃደኝነትና በታማኝነት መታገሥ ምን ማለት እንደ ሆነ ከእኛ በተሻለ የሚረዳ ታላቅ ሊቀ ካህናታችን ነው (ዕብራውያን 4፥15፤ 12፥2)። አሁንም በሥቃዩ ውስጥ ዐልፈን ወደ ዘላለማዊው ደስታ እንድንደርስ፣ ስለ እኛ ሊማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል (ዕብራውያን 7፥25)።
ስለዚህ በዚህ የጸሎተ ሐሙስ ዕለት፣ ከእግዚአብሔር ወልድ ጋራ በመተባበር ወደ እግዚአብሔር አብ “ፈቃድህ ትሁን” ብለን እንጸልያለን (ማቴዎስ 6፥10)። በሥጋችንም ሆነ በነፍሳችን፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፈቃድ አሁን ከሚመስለው በተለየ መንገድ ቢፈጸም ብለን የምንመኝ ከሆነ፣ ከኢየሱስ ጋራ በመሆን “አባ፣ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው” ብለን በሙሉ ልብ ልንጸልይ እንችላለን። ነገር ግን ይህን ማድረግ የምንችለው፣ “ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” የሚሉትን እነዚህን ስምንት በክብር የተሞሉ ትሑት ቃላትን ከኢየሱስ ጋራ ዐብረን የምንጸልይ ከሆነ ብቻ ነው።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፈቃድ፣ አሁን ምንም ያህል የሚያሳምም ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሴት፣ እንዲሁም በነፍሳችን መዳን ይጠናቀቃል (1 የጴጥሮስ 1፥8-9)።