አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው?

አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ማለት ክርስቲያኖች በክርስቶስ ስም በመደበኛነት ተሰባስበው፣ በወንጌል ስብከትና በወንጌል በተደነገጉ ሥርዐቶች በኢየሱስ ክርስቶስና በመንግሥቱ ያላቸውን ኅብረት በይፋ የሚያጸኑበትና እርስ በርስ የሚተያዩበት ስብስብ ነው። ይህ ትርጉም የተንዛዛ እንደ ሆነ እረዳለሁ፤ ነገር ግን ይህ ትርጉም አምስት ክፍሎች እንዳሉት ልብ በሉ፦

•        የክርስቲያኖች ስብስብ

•        መደበኛ ስብሰባ

•        በመላ ጉባኤው የሚደረግ፣ እርስ በርስ የመጽናናትና የመተያየት ተግባር

•        ክርስቶስንና የእርሱን የምድር ግዛት በይፋ የመወከል ዐላማ (በስሙ በመሰብሰብ)

•        በወንጌል ስብከትና በወንጌል በተደነገጉ ሥርዐቶች ይህን ዓላማ ማስፈጸም

የቤተ ክርሰትያን መጋቢ ሊጋቡ የመጡ ወንድና ሴትን እንደ ተጋቡ ሲያውጅ ባልና ሚስት እንደሚሆኑ ሁሉ፣ ከላይ የተዘረዘሩት የመጨረሻዎቹ አራት ነጥቦች፣ በመናፈሻ የሚደረግን ተራ የክርስትያኖች ስብስብን ወደ አጥብያ ቤተ ክርስትያንነት ይለውጣታል።

ስብስቡ በብዙ ምክንያቶች ጠቃሚ ነው። አንደኛ፣ እንደ ክርስትያን ትልቁ ውግንናችንን በአደባባይ የምናውጅበት ቦታ ነው። ቆንስላ[1] ነው፤ ማለትም የሚመጣው መንግሥት ገጽታ ነው። በንጉሣችን ፊት የምንሰግድበት ቦታም ነው፤ ይህንንም አምልኮ ብለን እንጠራዋለን። የዓለም ፈርዖኖች ቢቃወሙንም እግዚአብሔር ግን ሕዝቡን ከአሕዛብ መካከል እንዲያመልኩት ይጠራል። እግዚአብሔር ታላቅ ጉባኤውንም ይሠራል።

ንጉሣችን ሕግጋቱን በስብከት፣ በወንጌል በተደነገጉ ሥርዐቶችና ሥነ ሥርዐት ምክንያት የሚፈጽመውም በስብሰባችን ውስጥ ነው። የወንጌል ስብከቱ የመንግሥታችንን ሕግ ያብራራል። የንጉሣችንን ስም ያውጃል፤ ንጉሣችን ለመሆን የከፈለውን መሥዋዕትነትም ያብራራል። መንገዱን እያስተማረን፣ አለመታዘዛችንን ይጋፈጣል። የእርሱን በቶሎ መምጣትም ያረጋግጥልናል።

በጥምቀትና በጌታ ራት ሥነ ሥርዐት በኩል ቤተ ክርሰትያን የመንግሥታችንን ባንዲራ ታውለበልባለች፤ ሠራዊቱንም ታስታጥቃለች። መጠመቅ ማለት ራሳችንን ከአብ፣ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት እንዳለን መመስከር ነው፤ እንዲሁም ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር አንድ የምንሆንበት መንገድ ነው (ማቴዎስ 28፥19ሮሜ 6፥3-5)። የጌታን ራት በምንወስድበት ጊዜ፣ የክርስቶስን ሞትና የአካሉም አባል መሆናችንን እናውጃለን። እግዚአብሔር ሕዝቡ እንዲታወቅለትና እንዲለይለት ይፈልጋል። በቤተ ክርስቲያንና በዓለም መካከል ግልጽ መስመር እንዲኖር ይፈልጋል። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱ ወንጌል እንዲሰበክ፣ ወንጌል መስካሪዎችን ሊያጸና፣ ደቀ መዛሙርትንም ሊመለከትና አስመሳዮችን ሊያጋልጥ የፈጠራት፣ ሥልጣን የሰጣት ተቋም ነች። ይህ ማለት ታዲያ ቤተ ክርስቲያንን እንደ አንድ ተራ ቡድን አንቀላቀላትም፤ ይልቅ እንገዛላታለን።

ጆናታን ሊማን


[1] ኤምባሲ