ወንጌል ስብከትን ከቤተ ክርስቲያን ማቆራኘት

ወንጌል ስብከት በግለሰብ ወይንስ በቡድን የሚሠራ እንቅስቃሴ ነው? ሁለቱም ነው!

እስቲ ዓሳ ማጥመድን አስብ። የመርከብ ማቆሚያ ስፍራ ላይ ዳር ሆነህ እግርህን እያወዛወዝክ፣ ማጥመጃህንም እያሰናዳህ ብቻህን የምትንሸራሸርበት ጊዜ አለ። ሆኖም በሚናወጠው ማዕበል ውስጥ የዓሳን ክምር ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግህ በሌላ ጀልባ ያሉ አጥማጆችን ጠይቅ። ምክንያቱም አንዱ ለሌላው ያስፈልገዋል።

የዓሳ ማጥመዱ ምሳሌ በወንጌል ስብከትና በአጥቢያ ቤተክርስቲያን መሃከል ስላለው ግንኙነት ልንናገር የፈለግነውን ያክል ላይናገር ይችላል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲከተሉትና ሰዎችን ለንስሓ ያበቁ ዘንድ አጥማጅ እንደሚያደርጋቸው እየነገረ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። ልክ ጀልባ ላይ እንዳሉ ዓሳ አጥማጆች ቤተ ክርስቲያንም የወንጌል ስብከትን ሥራ እንድትሠራ እንፈልጋለን።

ሆኖም የወንጌል ስብከትንና ቤተክርስቲያንን የሚያገናኝ ትልቅ ምስል አለ። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የመጀመሪያ ምዕራፎች ያስተዋለን ከሆነ፣ ሐዋሪያቱ ትንሣኤውን ሲሰብኩ ከጀርባ ደግሞ በጋራ የሚኖሩ፣ ያላቸውን በአንድነት ያደረጉና እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በሰዎች መሃከል በሞገስ የሚመላለሱ ሰዎች ያሉባት ቤተክርስቲያን ነበረች (2፥47፤ 5፥13)። በሆነ ደረጃ የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ከወንጌል ስብከት ጀርባ እንደ ምስክር ሆኖ ያገለግላል። በኢየሩሳሌም የነበሩ ሰዎች ቅዱሳንን በሞገስ እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል፤ ብዙዎችንም ወደ ድነት የመራ ይመስላል።

ምናልባት ጴጥሮስ ቀድሞ በኢየሩሳሌም የነበረውን ሁኔታ እያሰበ ይሆን ቤተ ክርስቲያንን ሲገልጽ፣ እንደ ካህናትና “የእርሱን በጎነት ለመናገር” ከጨለማ እንደተጠሩ ሕዝቦች፣ የማያምኑት መልካም ኑሯቸውን ተመልክተው “እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ”  ይገባል እያለ ይሆን? (1ኛ ጴጥሮስ 2፥9፣ 12)

በሁለቱም ማለትም በሐዋሪያት ሥራና በ1ኛ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን፣ የሚጣፍጥ ማር የሚያስገኙ በሥራ የተጠመዱ ትጉ ንቦች የሞሏት የንብ ቀፎ ተመስላ እናገኛታለን። ቀፎው ለእያንዳንዱ ንብ ተግባር መሠረት ነው፤ የሥራውም ክፍል ነው። ይህ ታዲያ በወንጌል ስብከትና በቤተ ክርስቲያን መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ሊነግረን ይችላል?

የትኛውም ምሳሌ ሁሉንም ነገር ተሸክሞ አያቀርብልንም። እስቲ ስለ ቤተ ክርስቲያንና የወንጌል ስብከት ግንኙነት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ አራት ነጥቦችን ለማቅረብ እንሞክር፤ አስከትለንም ለቤተ ክርስቲያን የሚሆኑ ተግባራዊ ትምህርቶችን እንቅሰም።

1. ወንጌል ስብከት ወደ እግዚአብሔር እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይጠቁምም፤

አንድ ሰው የስፖርት ቡድናችሁን እንዲቀላቀል ስትጋብዙ፣ ከቡድኑ የሚያገኘውን ጥቅማ ጥቅሞች ትጠቁሙታላችሁ። በጋራ ስለሚኖረው ግንኙነት፣ በየዓመቱ ስለሚኖረው ውድድርና እንደዚህ የመሳሰሉ ጥቅማ ጥቅሞችን ታቀርቡለታላችሁ። ይሄ ዐይነት አካሄድ ለወንጌል ስብከትና ለቤተክርስቲያን አይሠራም።

ወንጌል ስብከት ወደ እግዚአብሄር እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይጠቁምም። ይሄ ቀዳሚ ነጥብ ነው።

ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች ክርስቶስ ለእርሱ (እና ለእነርሱ) “የማስታረቅ አገልግሎት” እና “የማስታረቅ መልእክት” እንደሰጣቸው ነግሯቸዋል። እርሱ (እና እነርሱ) “እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን።” የማስታረቅ መልዕክቱም ግልፅና ቀላል ነው፤ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” የሚል ነው (2ኛ ቆሮንጦስ 5፥18-21)።

መልካሙ የምሥራች ወደ እርቅ የሚመራ ቢሆንም የወንጌላዊው መልካም ዜና “ከሌሎች ጋር ታረቁ” የሚል አይደለም። ይልቁን የወንጌላዊው መልካም ዜና አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት እንደሚታረቅ የሚያስረዳ ነው። ሌላው ሁሉ ከዚ ቀጥሎ የሚመጣ ነው።

2. ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ስብከት አንዱ ውጤት ናት፤

በተመሳሳይ አገላለጽ ከወንጌል ስብከት የሚጠበቀው ቀዳሚ ውጤት፣ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው። በመከተል ግን የሚጠበቅ ሌላ ውጤት አለ፤ እርሱም ከእግዚአብሔር ሕዝብ ወይም ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚሆን እርቅ ነው።

የመለወጥ አስተምህሮህ ውስጥ ሕብረት የተባለው መሠረታዊ ነገር ከሌለ፣ ከመላ አካሉ ዋነኛው ክፍል እንደ ጎደለ ያህል ነው። የኪዳኑ ራስ ከኪዳኑ ሕዝብ ጋር አብሮ የሚመጣ ነው። በክርስቶስ ያለን የሕብረት አንድነት የመለወጥ ምልክት ብቻ ሳይሆን ዋናው ክፍል ጭምር ነው። ከእግዚአብሔር ሕዝብ መታረቅና ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ ማግኘት የሚለያዩ ነገሮች ቢሆኑም ሊነጣጠሉ  ግን አይችልም።

ይሄ ሁሉ በኤፌሶን 2 ላይ በሚገባ ተገልጧል። ከቁጥር 1 እስከ 10 ስለ ይቅርታና ከእግዚአብሔር ጋር ወደላይ ስላገኘነው እርቅ ሲያብራራ “በጸጋ ድናችኋልና” ይላል። ከቁጥር 11 እስከ 20 ደግሞ ወደ ጎን ስለሆነው ሲናገር፦ “ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና፤ (ቁ.14)” ሲል ይናገራል። የቁጥር 14 ክንውን በአላፊ ጊዜ ሰዋሰው የተቀመጠ መሆኑን ያስተውሏል። ክርስቶስ አስቀድሞ አይሁድና አህዛብን አንድ አድርጓቸዋል። የሆኑትን የሆኑት እግዚአብሔር ከፈፀመው ሥራ የተነሳ ነው፤ ደግሞም ይሄን ሥራም የፈፀመው ወደላይ የሆነውን እርቅ በፈፀመበት በክርስቶስ መስቀል ነው (“አመላካች” (indicative) እና “ትዕዛዝ” (imperative) በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በኤፌሶን 4፥1-6 ይመልከቱ)።

በአጭሩ የዳንነው ወደ ሕዝብም ነው።

ይሄ በተግባር ምን እንደሚመስል የሐዋሪያት ሥራ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች በሚገባ ያሳዩናል። “ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤” (ሐዋሪያት 2፥41፤ ይመልከቱ 2፥47፤ 4፥4፤ 6፥7)። ሰዎች በክርስቶስ አመኑ ደግሞም በኢየሩሳሌም ወደምትገኘው ቤተክርስቲያን ወደ “ቁጥራቸው” ተጨመሩ። ተቆጥረዋል፤ ስማቸው ተመዝግቧል። በዚያን ጊዜ ካሜራ ቢኖራቸው ኖሮ ፎቷቸው የቤተክርስቲያኒቷ መዝገብ ውስጥ መካተቱ አይቀሬ ነበር።

የተለወጠ ሕይወት በሕብረት የተቃኘ ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖች አድራሻ ናት፤ ስለዚህ ወንጌላዊው ሰዎችን ወደዚሁ ስፍራ ይልካል።

3. ወንጌል ስብከት የቤተ ክርስቲያን ሥራ ነው፤

በሦስተኝነት፣ ወንጌል ስብከት የቤተ ክርስቲያን ሥራ ነው። ሰው አንዴ ከእግዚአብሔርና (በመቀጠል) ከሕዝቡ ጋር ከታረቀ፣ እርሱ/ሷ አዲስ ኅላፊነት ተቀብለዋል፤ ይህም ወንጌልን ለሌሎች ማጋራት ነው። “ኢየሱስም፦ በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው” (ማርቆስ 1፥17፤ ማቴዎስ 28፥19)። በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል ወንጌልን የማጋራት ኅላፊነት አለበት።

የሐዋሪያት ሥራ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች፣ የሐዋሪያቱ ስብከት ላይ ያጠነጥናሉ፤ በኢየሩሳሌም ስደት በተነሣ ጊዜ ግን ቤተ ክርስቲያን ተበተነች፤ “የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ” (ሐዋሪያት 8፥4)።

አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ እግዚአብሔርን ለማምለክና የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም የምሥራች እንዲያጋሩ ተቀምጠዋል። ለዚህ ነው አስተማሪዎች የሚያስተምሩት፣ ምዕመናንም የሚማሩት። እንዲያውም ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን ለአገልግሎት (ወንጌል ስብከትን ያካተተ) ያስታጥቁ ዘንድ እረኞችን፣ አስተማሪዎችን፣ ወንጌል ሰባኪዎችን ሰጥቷል (ኤፌሶን 4፥11)።

ዓሣ ማጥመድን በጋራ እንሠራለን።

4. ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ስብከት የኑሮ ምስክር ናት፤

በጉባኤ በጋራ የተሰባሰቡ አማኞች (የተለወጡ ሰዎች)፣ ያዳናቸውን ወንጌል በሚገባ የማድረስ ኅላፊነት አለባቸው። “የወንጌል አስተምህሮ” ሬይ ኦርትሉንድ እንደጻፈው፣ “የወንጌል ባህልን ይፈጥራል።” በቤተ ክርስቲያኖቻችን የሚገኘው ይህ ባህል፣ በውጭ ላሉት የሚማርክ መሆን አለበት (2ኛ ቆሮንጦስ 2፥15-16 ይመልከቱ)።

ይህም ማር ወደ ሞላው የንብ ቀፎ፣ ማለትም ወደ ቀደመው የቤተ ክርስቲያን ምስል ይመልሰናል። ይህንም በሐዋሪያት ሥራና በ1ኛ ጴጥሮስ የምንመለከተው ነው። በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ላይም ክርስቶስ ጨውና ብርሃን አድርጎ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲናገር እንመለከታለን (ቁ. 13-16)። በዮሐንስ 13 ላይ ደግሞ በሚገርም መንገድ ኢየሱስ ስሎልናል፤ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ (ቁ. 34-35)።”

በውጭ ላሉት የምናደርገው መልካም ሥራ እና በቤተ ክርስቲያን ላሉት የምናሳየው ፍቅር ባልንጀሮቻችንና አጠገባችን ያሉትን ወደ ክርስቶስ ይመራቸዋል።

ይሄ ሁሉ የሚባለው አጥቢያ ቤተክርስቲያን ለወንጌል ስብከት ድጋፍ ናት ለማለት ነው። የቤተ ክርስቲያን ምልልስ (ሕይወት) ለወንጌሉ ይሟገታል። አንዱ ከሌላው ጋር በሚኖረው ግንኙነት ለድነት የሆነውን የእግዘብሔርን ኅይል ይመሰክራል። በየሳምንቱ የእግዘብሔርን ቃል ስብከት ለመስማት ስንሰበሰብ፣ ደግሞም መንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቶስ መልክ በሂደት ሲያሳድገን፣ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበር ወንጌል በእኛ ሕይወት ምን ማድረግ እንደሚችል እየጠቆምን ነው።

ቀስ በቀስ የአዲስ ፍጥረት በኩር የሆነውን በመከተል፣ አዲሱን ሰው እየሆንን ነው (ቆላ 1:15) ። ይህም አዲስ ሰው ለወንጌል ሥራ እንደ ጥሩ የማስታወቂያ ሰሌዳ ወይም ድጋፍ ሆኖ ያገለግላል። በዚህም በዓለም ላሉ ሌሎች ባህሎች፣ መለኪያ (ማንጠሪያ) ባህል ሆኖ ያገለግላል።

ተግባራዊ እርምጃዎች

ከእነዚህ አራት መርሆዎች ምን ዐይነት ተግባራዊ ትምህርት መውሰድ እንችላለን? አብዛኛውን ጊዜ መጋቢዎች፣ ሰዎች ወንጌልን እንዲሰብኩ በማበረታታት በቤተ ክርስቲያን ያለውን የወንጌል አገልግሎት ለማጠናከር ይሞክራሉ። አዎን! ይሄ አንድ ነጥብ ነው። ቢሆንም ግን ቤተክርስቲያን የባህል ማንጠሪያ (መለኪያ) እየሆነች ማደጓም ወሳኝ ነው፤ ይህም ለወንጌል አገልግሎት የጀርባ አጥንት ነው።

1) የወንጌል ሥርጭት አገልግሎት ወደ ጥምቀትና ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ሊመራ ይገባል፤ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ሰብካ፣ አዲስ አማኞችን አፍርታ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ልትተዋቸው አይገባም። ወንጌል ሰብካ፣ አጥምቃ፣ ምናልባትም ሰዎችን ወደ አባልነት አሳድጋ ብቻ ልትተው አይገባም። አንዳንድ ልዩ ሁኔታዎች ካልተፈጥሩ በቀር (ለምሳሌ፣ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ)። ቤተ ክርስቲያኖቻችን የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን እንዳደረገችው ሊያደርጉ ይገባል (የሐዋሪያት ሥራ 2፥41)። ጥምቀት አንድ ግለሰብ አማኝ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን እንደ ማኅበር የምታረጋግጥበት ጽኑ ምልክት ነው። ይህም ማረጋገጫ አባል በማድረግና የጌታን እራት በመቁረስ ክትትል ባለው ሂደት ሊኮተኮትና ሊጠበቅ ይገባል። አዲስ የተፈለፈሉትን ከወፍ ጎጆ ውጭ አናደርጋቸውም፤ ይልቁን ወደ ውስጥ እናስገባቸዋለን።

2) እርስ በእርስ የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖር ለአባላት ማስተማር፤ ቤተ ክርስቲያን የአቃቢነት ጉልበቷ እንዲጠነክር፣ አባላት የቃሉን ትምህርትና የጌታን እራት በመካፈል አንድ አካል መሆናቸውን እንዲያውጁ በተከታታይነት ማሳሰብ ያስፈልጋታል (ለምሳሌ፣ 1ኛ ቆሮንጦስ 10፥16-17፣ 1ኛ ቆሮንጦስ 12)። አባላት እርስ በእርስ በመበረታታት፣ በመደጋገፍ፣ እውነትን በመነጋገር፣ በመገሳሰጽና እርስ በእርስ በመዋድድ ግንኙነታቸው እንዲዳብር ካላሳሰብን፣ ሰንበቶች እንዲያው ያልፋሉ (ለምሳሌ፣ ሮሜ 12፥9-13፤ ኤፌሶን 4፥11-32)። እንግዳ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሊበረታቱ ይገባል (ሮሜ 12፥13፣ 1ኛ ጴጥሮስ 4፥9)። ይሄ ሁሉ ለወንጌል ማራኪ የሆነ ምስክር ሆኖ ያገለግላል።  

3) አንዱ ለሌላው ዋጋ እንዲከፍል ማስተማር፤ እንዲያውም ጠንካራ በሆነ አገላለጽ፣ ክርስቲያኖች (በገንዘብ ሊሆን ይችላል ወይም በሌላ) አንዱ ለሌላው የተሻለ መስዋዕትነትን ለመክፈል ማሰብ ይገባቸዋል (ለምሳሌ፣ ሐዋሪያት ሥራ 2፥42-46፤ 2ኛ ቆሮንጦስ 8-9፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፥10)። ለራሴ ብቻ በሚል ማኅበረሰብ ውስጥ የአማኞች አብሮ መካፈል፣ ኅይልኛ የባህል ተጽዕኖ ያመጣል። አስታውሱ! ኢየሱስ የመሥዋዕትነት ፍቅር ጥጉን በማሳየት እርሱ እንደወደደን፣ ክርስቲያኖች እርስ በእርሳቸው እንዲዋደዱ ተናግሯል (ዮሐንስ 13፥34)።

4) በቤተ ክርስቲያን ጠንከር ያሉ ተግሳጾችን መለማመድ፤ ሐሳውያንና ግብዝ ክርስቲያኖች፣ ቤተ ክርስቲያን ሕያው ምስክር መሆኗን ያመቻምቻሉ። በማኅበረሰቡ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አባላት በውሸተኝነት፣ በሀሜተኝነትና በዝሙት አድራጊነት ከታወቁ የወንጌል ስብከት አገልገሎቷ ይስተጓጎላል። ይሄ ማለት ቤተ ክርስቲያን ከኅጤአት ጋር የሚታገለውን እያንዳንዱን አማኝ መቅጣት አለባት እየተባለ አይደለም። እንዲያ ከሆነ አንድም ሰው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አይቀርም። ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ለንስሓ ያልበቃን ኅጤአት በግልጽ ልትቃወምና ልትቀጣ ይገባል። ይህም ለንስሓ ላልበቃው አባል (1ኛ ቆሮንጦስ 5፥4 ይመልከቱ) በሰፊው ደግሞ ለመላው ቤተክርስቲያን ወንጌልን ለመመስከር ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል (1ኛ ቆሮንጦስ 5፥1-2)።

5) ወንጌል እንዲሰብኩ አባላትን ማስታጠቅ፤ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ እያንዳንዱ አማኝ መሠረታዊ የሆነውን የክርስትና አስተምህሮ ማብራራት መቻሉን በተለያየ መንገድ ሊያጣሩ ይገባል። ይህም በምስባክ፣ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በአባልነት ቃለ መጠይቅ ወይም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሊተገበር ይችላል (ኬቨን ማክኬይ፣ “የወንጌል ስብከት እንቅፋቶችን ማሸነፍ” ይመልከቱ)።

6) በውጭ ያሉትን የሚባርክ ኑሮ እንዲኖሩ አባላትን ማበረታታት፤ የቤተ ክርስቲያን አባላት ከሞላ ጎደል በደግነት፣ በወዳጅነትና ለእርዳታ በሚፈጥኑ እጆች ይታወቁ። ጎረቤት ደጅ ያለን ቆሻሻ ለማጽዳት በሚተጉ እጆች፣ የቢሮ ወዳጅን ለመርዳት በመፍጠን፣ ለተጠቁት ፈጥኖ በመቆም፣ ከባባድ በሆኑ ጊዜያት የጠንካራ ሠራተኞችን ሥራ በመሸፈን፣ በሁሉም መንገድ ሌሎችን ለመጥቀም የምንቸኩል መሆን አለብን። መልካም ሥራችን የወንጌል መልዕክታችንን ሊያስውብ ይገባል።

7) መደበኛ በሆነ ወይም ባልሆነ የቅዱሳን ስብስብ ላይ ሌሎችን መጋበዝ፤ የማያምኑ ወንጌልን ሰምተው ደግሞም በእንቅስቃሴ ያለችን ቤተ ክርስቲያን ተመልክተው፣ የቤተ ክርስቲያን አኗኗር አሸንፏቸው ወደ ክርስትና የመጡ እልፍ ምስክርነቶችን መጥቀስ ይቻላል። በቤተሰባቸው፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ አይተው ወደ ማያውቁት ነገር ይጠቁማቸዋል። በሌላ አነጋገር ሌሎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን መጋበዝ በርግጥ የወንጌል ስብከት አንድ አካል ነው።

8) በወንጌል ሰባኪነት ምሳሌነትን ማስቀመጥ፤ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በወንጌል ስብከት በታወቁበት ሁሉ ወንጌል የምትሰብክ ቤተ ክርስቲያንን እናገኛለን። ሽማግሌዎች የማያደርጉትን ከምዕመኑ ማግኘት አይቻልም።

9) የወንጌል ስብከትና የድነት ልምምድ ታሪኮችን ማቅረብ፤ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ትምህርቶቻቸውንና ስብከቶቻቸውን በወንጌል ስብከት የገጠማቸውን ገጠመኝ በመጥቀስ መቀመም ይገባቸዋል። የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላትም ለወንጌል ስብከት ዕድል እንዲፈጥር የጸሎት ርዕሶቻቸውን ያቅርቡ። ለጥምቀት የተሰናዱት አባላትም የተለወጡበትን ገጠመኝ እንዲያካፍሉ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል። እንደዚህ ያሉ ሌሎች ነገሮችም፣ የወንጌል ስብከት ለክርስትና ሕይወትና የቤተ ክርስቲያን ልምምድ “መደበኛ” ክፍል መሆኑን አጽንኦት ይሰጣል።

10) ስለ ቤተ ክርስቲያንህ በኩራት መናገር፤ አንዳንድ ጊዜ ሐዋሪያው ጳውሎስ በክርስቶስ እንደሚመካ ስለ ቤተክርስቲያኖቹም ይመካል (2ኛ ቆሮንጦስ 9፥2፣ 2ኛ ተሰሎንቄ 1፥4፣ ፊልጵስዮስ 2፥16 ይመልከቱ)። በተመሳሳይ ሁኔታ ክርስቲያኖች ለማያምኑ ጓደኞቻቸው ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው አዎንታዊ ወይም ንጹሕ በሆነ ኩራት እንጂ በትዕቢት መናገር የለባቸውም። ወዳጅህ ስለ ዕረፍት ቀናትህ ሲጠይቅህ፣ ቤተክርስቲያን ያሉ ወንድሞች ባለቤትህን እንዴት እንደተንከባከቧት ተናገር። በሰንበት ሰባኪው ከተናገረው የሚያበረታታ ነገር ጥቀስ። አጥቢያህ፣ ቤት የሌላቸውን ለመረዳት እንዴት መጠለያ እንደሠሩላቸው ጠቁም። ይህን በማድረግ፣ ያለ ምንም ጥያቄ ተግባራዊ ይሆናል።

መደምደሚያ

ቤተ ክርስቲያንና የወንጌል ስብከት ሥራን በምናባችን በትክክል ካገናኘን፣ በመቀጠል ደግሞ ሰዎች ወንጌል በመስበክ ተግባራዊ እርምጃ እንዲከውኑ ማበረታቱ ይበልጥ ያስፈልጋል። አስተዳደራዊ በሆኑ ነገሮች፣ በአባልነትና ሥርዓትን በመለማመድ መሣተፍ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር የሰጣትን ተልዕኮ የምትፈጽም ደግሞም በእግዚአብሄር ቃል ስብከት ሥር የምትቀመጥ ጤናማ ቤተክርስቲያንን መገንባት ያስፈልጋል።

ለዚህም አስተማሪ የሆኑና ምሳሌ መሆን የሚችሉ መንፈሳዊ መሪዎች ያስፈልጋሉ። ከሞት ወደ ሕይወት ያመጣቸውን ኢየሱስን የሚወዱና ለእርሱ በዝማሬ ምስጋና ከማቅረብ ውጭ ሌላ ማድረግ የማይችሉ አባላት ያስፈልጋሉ።

ጆናታን ሊማን