መለወጥ[1] ከኀጢአት መራቅ እና ወደ እግዚአብሔር መመለስ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ምናልባት ይህን ፍቺ የሚይዘው ጥንታዊው ጥቅስ 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥9 ነው፤ “በእንዴት ያለ አቀባበል እንደ ተቀበላችሁንና ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖታት ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለሳችሁ እነርሱ ራሳቸው ይናገራሉ፤” እዚህ ላይ ወደ እግዚአብሔር መመለስ እና ከጣዖት መራቅን ሁለቱ የመለወጥ ነጥቦችን በግልጽ እናያለን።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ መለወጥ፦ ከተስፋ ቃልነት እውን ወደ መሆን
በብሉይ ኪዳን ተስፋ የተሰጠው ታሪክ፣ ማለትም በእባቡ ላይ የሚፈጸመው የእግዚአብሔር ድል ነሺነት ታሪክ በአዲስ ኪዳን እውን ሆኗል(ዘፍጥረት 3፥15)። ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳንን፣ አዲስ ፍጥረትን፣ አዲስ ዘፀአትን፣ እና አዲስ ልብን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ተስፋ ሰጥቶ ነበር። እናም አዲስ ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ሞት እና ትንሣኤ እነዚህ ተስፋዎች ሁሉ ፍጻሜ እንዳገኙ አውጇል።
መለወጥ በተመሳሳዮቹ ወንጌላት ውስጥ
በሲኖፕቲክ(በተመሳሳዮቹ)[2] ወንጌላት ማለትም በማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ ውስጥ በብሉይ ኪዳን የተነገረው የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ፣ “የእግዚአብሔር መንግሥት” በሚለው ቃል ተገልጿል። በእነዚህ ወንጌላት ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ማዕከላዊ ሚና ቢኖረውም፣ ነገር ግን መንግሥቱ መለወጥን የሚጠይቅ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። መለወጥም ንስሓ እና እምነትን በማካተት ሊገለጽ ይችላል። ማርቆስ 1፥14-15 እንዲህ ይላል፤ “ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፦ ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።” በኢሳይያስ የተሰበከው ከግዞት የመመለስ የምሥራችን (የእግዚአብሔር የማዳኑ ተስፋዎች ፍጻሜ የምሥራችን) ማጣጣም የሚችሉት ከኀጢአታቸው ንስሓ የገቡ እና በወንጌል የሚያምኑ ብቻ ናቸው።
በተመሳሳዮቹ ወንጌላት ውስጥ ያለው ወንጌል፣ በኢየሱስ ሞት እና ትንሣኤ ላይ ያተኮረ ነው፤ ምክንያቱም በሦስቱም መጻሕፍት ውስጥ የኢየሱስ መሰቃየት እና ከሞት መነሣት ታሪኩን ገዝቶት እናያለን። የታሪኩ ቁንጮ ነው! ያለ መስቀሉ መንግሥት የለም። ኢየሱስ የመጣው “ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ለማዳን” ሲሆን (ማቴዎስ 1፥21) ይህም መዳን እውን የሚሆነው ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ በማድረግ ለእነርሱ ሲሞት ነው( ማቴዎስ 20፥28፤ ማርቆስ 10፥45)። ስለ መንግሥቱ የሚናገሩ አንዳንዶች ስለ መለወጥ ብዙም አይናገሩም፤ ነገር ግን በተመሳሳዮቹ ወንጌላት ውስጥ መለወጥ ፍንትው ብሎ ይታየናል።
መለወጥ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ
የመለወጥ ማዕከላዊነት በዮሐንስ ወንጌልም ውስጥ ይታያል። በርግጥም ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው ሰዎች “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ” ነው ( ዮሐንስ 20፥31)። ዮሐንስ በወንጌሉ ውስጥ “ማመን” የሚለውን ግስ 98 ጊዜ ተጠቅሞታል። ይህም እምነት በወንጌሉ ውስጥ ያለውን አስፈላጊነት አጉልቶ አሳይቷል። ዮሐንስ የእምነትን ጥልቀትና ተግባር ለማሳየት ብዙ ቃላትን ይጠቀማል። ማመንን እንደ መብላት፣ መጠጣት፣ ማየት፣ መስማት፣ መኖር፣ መምጣት፣ መግባት፣ መቀበል እና መታዘዝ አድርጎ ያቀርበዋል። ዮሐንስ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማመንን ለመግለጽ የተጠቀማቸው ግሶች የመለወጥን ታላቅነት ያሳዩናል። እንግዲህ መለወጥ የዮሐንስ ወንጌል ዋና ማዕከል ነው። ኢየሱስ “የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ነው ብለው የሚያምኑ ብቻ የዘላለም ሕይወት አላቸው (ዮሐንስ 1፥29)። በሌላ አነጋገር፣ የተለወጡ ብቻ የዘላለም ሕይወትን ያገኛሉ(የሚመጣውን ዓለም ሕይወት ይካፈላሉ)።
መለወጥ እና የእግዚአብሔር መንግሥት በሐዋርያት ሥራ ውስጥ
መለወጥ በወንጌል ውስጥ ማዕከላዊ ሚና እንዳለው አስቀድመን ካነሣነው መረዳት ይቻላል፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም ተመሳሳይ የሆነ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ወንጌል ለአድማጮች የተብራራባቸው በርካታ ስብከቶችን እናገኛለን (ለምሳሌ፦ የሐዋርያት ሥራ 2፥14-41፤ 3፥11-26፤ 13፥16-41)። ሰሚዎቹም ብዙውን ጊዜ ንስሓ እንዲገቡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል (የሐዋርያት ሥራ 2፥38፤ 3፥19፤ 8፥22፤ 17፥30፤ 26፥20)። ይህም ንስሓ፣ “ወደ እግዚአብሔር መመለስ” ተብሎም ተገልጿል (የሐዋርያት ሥራ 3፥19፤ 9፥35፣ 40፤ 11፥21፤ 14፥15፤ 15፥19፤ 26፥18፣ 20፤ 28፥27)። የወንጌል መልእክት ከኀጢአት እና ከአሮጌው ሕይወታችን እንድንርቅ አስቸኳይ ጥሪን ያቀርባል። በተመሳሳይም ምሥራቹን የሚሰሙት፣ እንዲያምኑና የሚያምኑትን እንዲኖሩ ተጠርተዋል (የሐዋርያት ሥራ 16፥31 ፤ 26፥18)። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ “ማመን” የሚለው ቃል ክርስቲያኖችን ለመግለጽ 30 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፤ ይህም “እምነት” የክርስቶስ የሆኑትን ሰዎች ያመለክታል።
ወንጌል ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም መስፋፋቱን መጽሐፉ ስለሚዘግብ፣ መለወጥ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወቱ እምብዛም አያስገርምም (የሐዋርያት ሥራ 1፥8፤ 1፥6፤ 14፥22)። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ዋና ጭብጥ እንደሆነም ልብ ሊባል ይገባል። የመጽሐፉ መጀመሪያ እና መጨረሻ ይህን ያሳየናል (የሐዋርያት ሥራ 1፥3፤ የሐዋርያት ሥራ 28፥31)። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን መንግሥት በሮም ሰብኳል (የሐዋርያት ሥራ 20፥35፤ 28፥23፣ 31)። ፊልጶስ ደግሞ “የእግዚአብሔርን መንግሥትና የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ምሥራች ሰበከ” (የሐዋርያት ሥራ 8፥12)። ይህም መንግሥቱ ወንጌልን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ያሳያል። ከላይ እንዳየነው የተሰበከው ወንጌል፣ ሰሚዎቹ ንስሓ ገብተው እንዲያምኑ ጥሪ ያቀርባል። ስለዚህም መለወጥ ለመንግሥቱ አዋጅ መሠረት እንደሆነ እናያለን። አንዱ የአማኞች አስደናቂ ተስፋ፣ ዓለምን ወደ እግዚአብሔር አገዛዝ መመለስ ነው። ነገር ግን የሚመጣውን አዲስ ዓለም የሚያጣጥሙት፣ ንስሓ የገቡ እና ያመኑት ብቻ ናቸው። የሐዋርያት ሥራ ደጋግሞ አጽንኦት እንደሚሰጠው፣ ለማመን ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ይፈረድባቸዋል።
መለወጥ በጳውሎስ ዕይታ
ጳውሎስ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ አይጠቀምም። ነገር ግን የነገረ ፍጻሜ አተያዩ በደንብ የታወቀ እና ከመንግሥቱ የፍጻሜ ባሕርይ ጋር የተስማማ ነው። እንደ ወንጌላት ጽሑፎች፣ እርሱም “በመካከላችን ያለ ነገር ግን በሙላት ያልተገለጠ” የነገረ ፍጻሜ ታሪክን ያውጃል። ጳውሎስ ብዙ ጊዜ መጽደቅ እና መዳን የሚገኘው በእምነት ብቻ እንደሆነ ያስተምራል (ሮሜ 3፥21-4፥25፤ 9፥30-10፥17፤ 1 ቆሮንቶስ 15፥1-4፤ ገላትያ 2፥16–4፥7፤ ኤፌሶን 2፥8-9፤ ፊልጵስዩስ 3፥2-11)። ንስሓ የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ አይጠቀምም፤ ሆኖም ግን ጥቂት ቦታዎች ላይ እናያለን(ለምሳሌ፦ ሮሜ 2፥4፤ 2 ቆሮንቶስ 3፥16፤ 1 ተሰሎንቄ 1፥9፤ 2 ጢሞቴዎስ 2፥25)።
ጳውሎስ በክርስቶስ በኩል የተገኘውን የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ለመግለጽ ብዙ ቃላትን ይጠቀማል። እነርሱም መዳን፣ መጽደቅ፣ ቤዛነት፣ ማስታረቅ፣ ልጅነት፣ ማስተሰረያ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ናቸው። በጳውሎስ ነገረ መለኮት ውስጥ በክርስቶስ በኩል ያለው የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ትልቅ ሚና መጫወቱ የማያከራክር ቢሆንም፣ እንዲህ ያለው መዳን የሚሰጠው ግን ለሚያምኑት ወይም ለተለወጡት ብቻ ነው።
እንደ ጳውሎስ ገለጻ፣ አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣትና የፍጥረትን መታደስ በጉጉት ይጠባበቃሉ (ሮሜ 8፥18-25፤ 1 ተሰሎንቄ 4፥13-5፥11፤ 2 ተሰሎንቄ 1፥10)። ነገር ግን እየመጣ ላለው አዲስ ዓለም የታጩት፣ የተለወጡት ሰዎች ናቸው። ስለዚህም ከሚድኑት ወገን እንዲሆኑ ጳውሎስ ለአሕዛብ ወንጌልን ለማዳረስ ተግቶ ይሠራል (ቈላስይስ 1፥24-2፥5)፤ ወንጌልን ላልሰሙት ለማድረስ ይተጋል (ሮሜ 15፥22-29)።
መለወጥ በሌሎቹ መልእክቶች ውስጥ
የተቀሩት የአዲስ ኪዳን መልእክቶች የተለያዩ ሁነታዎችን በማስመልከት የተጻፉ ናቸው። ቢሆንም የመለወጥ አስፈላጊነት በእነዚህ መልእክቶች በገሃድ ወይም በውስጥ ታዋቂነት ተገልጿል። ለምሳሌ፣ ወደ ዘላለማዊ ዕረፍት የሚገቡት ያመኑ እና የሚታዘዙት ብቻ እንደሆኑ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ እናገኛለን (ዕብራውያን 3፥18፣ 19፤ 4፥3፤ 11፥1-40)። ያዕቆብን ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ተረድተነዋል። የተናገረው በትክክል ሲተረጎም፣ የንስሐ እምነት ለመጽደቅ አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምራል (ያዕቆብ 2፥14-26)። እንዲሁም ጴጥሮስ መዳን በእምነት እንደሆነ ያስተምራል (1 ጴጥሮስ 1፥5፤ 2 ጴጥሮስ 1፥1)። ደግሞም የመጀመሪያው የዮሐንስ መልእክት የተጻፈው ለሚያምኑት የዘላለም ሕይወት እንዳላቸው ለማረጋገጥ ነው (1 ዮሐንስ 5፥13)።
መለወጥ በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ
የራእይ መጽሐፍ ታሪኩን ያጠናቅቃል፤ ይህም አስቀድሞ በኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚፈጸም ለአማኞች ያረጋግጣል። ክፉን የሚያደርጉና ከአውሬው ጋር የሚስማሙ ለዘላለም ይፈረድባቸዋል፤ እስከ መጨረሻ የሚጸኑ ግን ወደ ሰማያዊቷ ከተማ ይገባሉ፤ እርስዋም አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት። የራእይ መጽሐፍ፣ ንስሓ የገቡት ብቻ ሕይወትን እንደሚያገኙ ያስረዳል (ራእይ 2፥5፣ 16፣ 21፣ 22፤ 3፥3፣ 19፤ 9፥20፣ 21፤ 16፥9፣ 11)።
ዋናው ጭብጥ ባይሆንም ለአጠቃላይ ታሪኩ መሠረታዊ ነው
ለማጠቃለል ያህል መለወጥ በርግጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ዋና ጭብጥ አይደለም። አማኞች እግዚአብሔርን እንዲያከብሩና ለዘላለም በእርሱ እንዲደሰቱ ተደርገዋል። እኛም በእርሱ እየተደሰትን በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም እናከብረዋለን።
ነገር ግን በአዲስ ፍጥረት የሚደሰቱት የተለወጡ ሰዎች ብቻ ስለሆኑ፣ መለወጥ ለታሪኩ መሠረታዊ ነው። የሰው ልጅ ለመዳን ከኀጢአት ፊቱን መልሶ ወደ እግዚአብሔር መዞር አለበት። ከኀጢአታቸው ንስሓ ገብተው በተሰቀለውና በተነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ማመን አለባቸው። አንድ ሰው ለዚህ ዓለም መሻሻል በጥቂቱ ሆነ በብዙ መንገድ አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ ዳግም ካልተወለደ (ካልተለወጠ) በመጨረሻው ቀን ሥራው እርባና ቢስ ነው።
(ይህ የመለወጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ መለኮት ክፍል 2 ነው።)
በቶማስ ሽራይነር
[1] “Conversion” ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” (‘መ’ ትጠብቃለች) በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይበሉ።
[2] ሲኖፕቲክስ ወንጌላት ተብለው የሚጠሩት ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ ወንጌላት ሲሆኑ ይህን ስያሜ ያገኙት እርስ በርሳቸው ስለሚመሳሰሉ ነው።