ወንጌል ተኮር ስብከት | ወንጌል ደምቆ የሚያበራበት ስብከት  

ዘ ፕሪንሰስ ብራይድ የሚለው ፊልም ከምንጊዜውም ምርጥ ፊልሞች ጎራ ይመደባል ብላቹ ታስባላችሁ? ፊልሙ ላይ ያሉት ታዋቂዎቹ ንግግሮችን ካሰብን ከምርጥ ሥራዎች ጎራ ሊመደብ ይችላል። አንዱ ታዋቂ ንግግር ከፊልሙ ኢንዲጎ ሞንታያ በቪዚኒ “ሊታሰብ የማይችል!” በሚለው ንግግር ግራ ተጋብታ የተናገረችው ነው። ፊልሙ ላይ ቪዚኒ ይህን ቃል ሲደጋግምው፣ “ይህን ቃል በተደጋጋሚ ስትጠቀመው እሰማለሁ፤ ነገር ግን ቃላቶቹ አንተ ያሰብከው ትርጉም የላቸውም” ብላ ትመልስለታለች።

“ወንጌል-ተኮር” ወይም “ወንጌልን ያማከለ” የሚሉትን ተደጋጋሚ ስብከትን የሚገልጡ ዐረፍተ ነገሮችን ስሰማ ኢንዲጎ ሞንታና ያለችው ነገር አዕምሮዬ ላይ ይመጣብኛል። በተደጋጋሚ ቃላቶቹን ብንጠቀምም ቃላቶቹ ግን ያሰብነውን ትርጉም የያዙ አይመስለኝም። ስለዚህ እስቲ ይሄን ሐሳብ አብረን ለመረዳት እንሞክር።

ወንጌል ተኮር ስብከት ምን አይደለም

የተወሰኑ ወንጌል ተኮር ስብከት ያልሆኑ ነገሮችን ማንሣት ወንጌል ተኮር ስብከት ምን እንደሆነና እንዳልሆነ ለመረዳት መስመሩን ያሰምርልናል፦

  • አንድ ስብከት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ብቻ ወንጌል ተኮር ስብከት ሊባል አይችልም። አንዳንድ ስብከቶች መጽሐፍ ቅዱስን መስመር በመስመር እየተከተሉ የሚያስተምሩ ሆነው፣ ያም ብቻ ሳይሆን ስለ ኢየሱስ የሚናገር ክፍል እየሰበኩ ነገር ግን ስሑት አስተምህሮ ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ሌዋውያኑና ካህናቱ የእግዚአብሔር ቃል ልሂቃን የነበሩ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቶስ ተኮር ምስክርነትን ስለ ሳቱ ኢየሱስ ሲገሥጻቸው እንመለከታለን (ዮሐንስ 5፥39-40)።
  • አንድ ስብከት ጸጋን በማሳየት ሰዎችን ስላጽናና ብቻ ወንጌል ተኮር ስብከት ሊባል አይችልም። የወንጌሉ ጸጋ ማጽናናት ብቻ ሳይሆን ለመታዘዝም ያነቃቃል፤ ያጸድቃልም። ደግሞም ለቅድስና ያነሣሳል (ይቀድሳል)። የተደረገልን ላይ ተመሥርተን አድርጉ የተባልነውን ወደ ማድረግ ያሳድገናል፤ “ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል፤ ደግመህ ኀጢአትን አትሥራ ይለናል።”
  • አንድ ስብከት ኢየሱስ ለኀጢአተኞች የሞተውን ሞትና ትንሣኤውን እንደ ማመሳከሪያ ስለ ጠቀሰ ብቻ ወንጌል ተኮር ስብከት ሊባል አይችልም። በርግጥ ኢየሱስ ለኀጢአተኞች መሞቱ እና ትንሣኤው የወንጌል መልእክት ማዕከል ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥1-4)። ሆኖም ግን ይህን መልእክት እንደ ግዴታ ጠቅልለን የስብከታችን የሆነ ቦታ ብንሸጉረው፣ ወይም ልክ እንደ ግርጌ ማስታወሻ የስብከታችን የሆነ ቦታ ብናስቀምጠው፣ ወንጌል ተኮር ስብከት ሆነ ማለት አይደለም።

የወንጌል ተኮርነት ምስል

“ተኮር” ወይም “ማዕከላዊነት” የሚለው ቃል ለብዙ ግርታዎች ምንጭ ነው። ከኢየሱስ መልካም ዜና ስብከት ጋር “ተኮር” ወይም “ማዕከላዊነት” የሚሉት ቃላቶች ምን ግንኙነት አላቸው? እስቲ ይህን በተመለከተ የሆነ ምስል ልስጣችሁ። ፀሓይ፣ የሥርዐተ ፀሓይ ማዕከል እንደሆነች ሁሉ ወንጌልም የስብከታችን ማዕከል እንዲሆን መፈለግ አለብን። በእኛ ሥርዐተ-ፀሓይ ሁሉም ነገር በፀሓይ ዙሪያ ይዞራል፤ ደግሞም ሙቀትም ሆነ ብርሃን ከፀሓይ ያገኛል። የፀሓይ ከፍተኛ ስበት ኀያል ሁሉንም ነገር ወደ ራሱ በመሳብ በሥርዐተ-ፀሓይ ውስጥ ያሉ አካላትን አያይዞ ዑደቱ እንዲቀጥል ያደርጋል። የፀሓይ ብርሃን እና ሙቀት በምህዋሩ ውስጥ ወዳለው እያንዳንዱ ነገር ይደርሳል።

ስለዚህ ወንጌል በስብከታችን ውስጥ እንዲሁ መሆን አለበት። ክርስቶስ ፀሓያችን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሥርዐተ ፀሓያችን ነው። የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፣ የትኛውም አስተምህሮ፣ የትኛውም ሐሳብ የኢየሱስን የማዳን ሥራ ላይ መዘወር አለበት። የእግዚአብሔር ሙሉ መገለጥ፣ የሚሰሙን ሕዝቦች፣ እንዲሁም ሰባኪው የኢየሱስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ ብርሃንና ሙቀቱ ሊሰማቸው ይገባል። ስብከት እነዚህን እውነቶች ባንጸባረቀበት መጠን ነው፣ ስብከቱ ወንጌል ተኮር ነው ወይም ወንጌልን ማዕከል ያደረገ ነው ማለት የምንችለው።

በወንጌል ተኮር ስብከት ውስጥ ወንጌል ልክ እንደ ፀሓይ ሁሉንም የስብከት አካላትን ወደ ምህዋሩ እየሳበ ብርሃንና ሙቀት ይሰጣቸዋል። ወንጌል ተኮር ስብከት ወንጌል ደምቆ የሚያበራበት ስብከት ነው።

የመመዘኛ ጥያቄዎች

ስብከትን ከሥርዐተ ፀሓይ ጋር ማስተያየት በሐሳብ ደረጃ ጠቃሚ ነው፤ ነገር ግን ከላይ ያልነውን ነገር መሬት አውርደን ማየት አለብን። ስብከታችን በምን ያህል ደረጃ ወንጌል ተኮር እንደሆነ የምንመዝንበት መንገድ ይኖር ይሆን? ቀጥሎ የምናያቸው ሦስት የመመዘኛ ጥያቄዎች ስብከታችንን ለመመዘን ያግዙናል። እነዚህ ጥያቄዎች ከላይ ካነሣናቸው ጋር ካስተያየናቸው እነዚህኞቹ አዎንታዊ ናቸው። 

(1) ለስብከታችን በተጠቀምነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ወንጌሉ እንደ ፀሓይ አብርቷል ወይ?

ጥያቄው፣ የክፍሉ ዋና ሐሳብ በወንጌል ብርሃን ተነግሯል ወይ የሚል ነው። ስለ ፍጥረት፣ ጾታ፣ ኪዳን፣ ቤተ መቅደስ፣ መሥዋዕት፣ ቅድስና፣ ፍርድ፣ በረከት፣ እርግማን፣ ንጽህና፣ ጸሎት፣ ትዳር፣ ላጤነት፣ አንድነት፣ ፍትሕ፣ ተልዕኮ፣ አብ፣ መንፈስ ቅዱስ ወዘተ ስለ መሳሰሉት ጉዳዮች ምንም ብንሰብክም ዋና ጥያቄው የሚሆነው የስብከታችን ዋና ሐሳብ ግልጽ በሆነ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ፍጻሜን አግኝቷል? ቅርጽ ሰጥቶታል? እና በወንጌል ኀይል አግኝቷል ወይ ነው? በአጭር አገላለጽ የክፍሉ ዋና ሐሳብ ግልጽ በሆነ መንገድ ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ጋር ባለው ግንኙነት በደንብ መታየት አለበት። ወንጌልን ያማከለ ስብከት በምኰራብ ወይም በመስጊድ ተቀባይነት አይኖረውም።

(2) ወንጌሉ በአድማጮች ሕይወት ላይ እንደ ፀሓይ አብርቷል ወይ?

ወንጌል በክፍሉ ዋና ሐሳብ ላይ ብቻ ሳይሆን በአድማጮችም ሕይወትም ላይ ያበራል። የወንጌል ማዕከላዊነት ወይም ተኮርነት በቃሉ ትርጉም ላይ ብቻ ሳይሆን በተዛምዶአችንም ላይ ያበራል። ክርስቲያኖች ጥሪያቸው ለወንጌል ምላሽ እንዲሰጡ ነው። በክርስቶስ ባለው የእግዚአብሔር ጸጋ በክርስቶስ ያላመኑ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ፣ በክርስቶስ እንዲያምኑና እንዲድኑ አጥብቆ መነገር አለበት። በክርስቶስ ባለው የእግዚአብሔር ጸጋ አማኞች አሮጌውን ማንነት አውልቀው እንዲጥሉ፣ በአዕምሮቸው መታደስ እንዲለወጡና አዲሱን ሰው እንዲለብሱ መበረታታት አለባቸው። ሕይወት ለዋጩ ጸጋ በእውነተኛ ወንጌል ተኮር ስብከት ላይ ብርሃኑን ያበራል። በወንጌል እንድንሆናቸውና እንድናደርጋቸው የተነገሩን ነገሮች በወንጌል ከተደረጉልን ነገሮች ይነሣሉ፤ ስለዚህም ከሁለቱ አንዱን ለይተን መተው የለብንም።  

(3) የወንጌሉ ብርሃን በሰባኪው ልብ ላይ አብርቷል ወይ?

ለወንጌል ክብር ሲባል በጨረፍታ ወንጌልን በስብከት መሃል ለአመል ጣል ከማድረግ ጭራሹኑ ባይደረግ ሳይሻል አይቀርም። ሆኖም ግን በእውነተኛ ወንጌል ተኮር ስብከት፣ ሰባኪው ራሱ በመጽሐፉ ክፍለ ምንባብ ውስጥ ባለው የወንጌል እንድምታ ልቡ ይያዛል። ሰባኪው ራሱ በፀሓዩ ሙቀትና ብርሃን ስለ ተጎበኘ ሕዝቡ ፊት ሲቆም እንደ ቀዛቃዎቹ ፕላኔቶች ፕሉቶና ሜርኩሪ መሆን አይችልም። ምክንያቱም እርሱ ራሱ በክርስቶስ ውስጥ ባለው ወደር የሌለው ደስታ ውስጥ ነው። ወንጌልን ሲሰብክ እንደ መግቢያ የሚያደርገው ሳይሆን፣ ዋና ርዕሱም ዝርዝሩም ወንጌል ነው።

ሊታሰብ የማይችል!

ወንጌል ተኮር ስብከት በጥሩ ሁኔታ ሲደረግ፣ ከሚሰበከው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወንጌል እንደ ፀሓይ በሰሚዎቹ እና በሰባኪው ላይ ደምቆ ያበራል። ሊታሰብ የማይቻለው ነገር የወንጌል ማዕከላዊነት ወይም ወንጌል ተኮርነት ከዚህ ባነሰና በረከሰ ትርጉሞች መቀመጡ ነው። ስለዚህ ከላይ ያነሣሁትን ወንጌል ተኮርነት ያልሆኑ ነገሮችን አስቧቸው። ደጋግማችሁ የመመዘኛ ጥያቄዎቹን አሰላስሏቸው። መዝሙር 19፥6 ላይ “መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤ ዑደቱም እስከ ሌላኛው ዳርቻ ነው፤ ከትኵሳቱም የሚሰወር የለም።’’ እንደሚል እንደ ማለዳ ፀሓይ መስበክን መማር አለብን። ወንጌል ተኮር ስብከት ወንጌል ደምቆ የሚታይበት ስብከት ነው።

በዴቪድ ኪንግ