የጌታ እራት እንዴት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ይመሠርታል?

እጮኛሞች ተጋብተዋል የምንለው መቼ ነው? “አዎን ቃል እገባለሁ” ሲሉ ነው? የሚያጋባቸው አገልጋይ፣ ባልና ሚስት ብሎ ሲጠራቸው ነው? የጋብቻ ሥነ ሥርዐቱ ሲጠናቀቅ ነው?

እነዚህ እያንዳንዱ ነገሮች፣ ለጋብቻ ምሥረታ አስፈላጊ ሚና ቢኖራቸውም እርስ በርስ ግን የተያያዙ ናቸው። የጋብቻ ሥነ ሥርዐት ካልተጠናቀቀ ሙሉ ለሙሉ ተጋብተዋል ለማለት የምንቸገረው ለዚህ ነው። ይህ ደግሞ ሕጋዊ መሠረት አለው። የዚህ ግንኙነት መቋረጥ ፍቺ ብቻ ሳይሆን የሕጋዊ ውል ማቋረጥ ነው።

እነዚህ ነገሮች ሁሉ፣ እንዴት ከጌታ እራት ጋር ይገናኛሉ? ብዙ ክርስቲያኖች፣ የጌታን እራት እንደ ግል የጥሞና ጊዜ አድርገው እንደሚቆጥሩ አስባለው። ወደ ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ፤ የእግዚአብሔርን ቃል እሰማለሁ፤ እንጀራውን እቆርሳለሁ፣ ጽዋውንም እጠጣለሁ፤ የክርስቶስ ሞትና የኀጢአቴን ስርየት አስታውሳለሁ፤ ከዚያም ወደ ቤቴ እሄዳለሁ። በርግጥ “ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ” የምንፈጽመው ሥርዐት ስለ ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ጋር እናያይዘዋለን። ለአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ግን የጌታ እራት እና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያላቸው ግንኙነት ከዚህ የዘለለ አይደለም።

ነገር ግን የጌታ እራት፣ ቤተ ክርስቲያንን አንድ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት መሟገት እፈልጋለሁ። የጌታን እራት በጋራ መውሰድ፣ ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ከሚያደርጓት አስፈላጊ ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ነው። ክርስቲያኖች የጌታን እራት በጋራ በሚወስዱበት ጊዜ አንድ አካል ይሆናሉ። የጌታ እራት ብዙዎችን አንድ ያደርጋል።

በሁለት ምክንያቶች በዚህ ሐሳብ ላይ አተኩራለሁ። በመጀመሪያ፣ ይህ ሐሳብ በወንጌላውያን ክርስቲያኖች ዘንድ፣ በስፋት ችላ የተባለ ጉዳይ ነው። በመቀጠል እንደምናየው፣ ጳውሎስ የጌታ እራት ብዙዎችን አንድ እንደሚያደርግ በግልጽ አስተምሯል። ነገር ግን ይህ የጳውሎስ ንግግር፣ ስለ ጌታ እራት እና ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን አስተሳሰብ እንዲቀርጽ የፈቀዱ በቁጥር እጅግ ያነሱ መጋቢዎች እና አብያተ ክርስቲያናት ናቸው ያሉት። ሁለተኛው ደግሞ፣ መጋቢዎች እና ቤተ ክርስቲያን የሚገጥሟቸውን በርካታ ተግባራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የጌታ እራት እንዴት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚመሠርት ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ በጌታ እራት ላይ ማን ሊሳተፍ ይችላል? ማንስ ሊመራው ይገባል? ይህንን የጌታ እራት ለመውሰድ የትኞቹ የቤተ ክርስቲያን ስብሰባዎች ተፈቅዶላቸዋል?

የጌታን እራት እንዴት መውሰድ እንዳለብን ጥበብ በተሞላበት መንገድ ለማወቅ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መነጽር አተኩረን ልናይ ይገባል።

እንዴት የጌታ እራት ብዙዎችን አንድ ያደርጋል?

ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፥16-17 የተናገረውን አስታውሱ፦ “የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።” ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች፣ የሚቆርሱት እንጀራ እና የሚጠጡት ጽዋ፣ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ለማድረግ እና በሞቱ ያገኙትን በረከት ለማሰላሰል እንደሆነ ያሳስባቸዋል። ጳውሎስ በቁጥር 17 ላይ በክርስቶስ እና በአማኞች መካከል ባለው “ቀጥተኛ” ግንኙነት ላይ በመመርኮዝ  የ“ጎንዮሽ” ግንኙነትን ይመሠርታል። “እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።” ጳውሎስ በዚህ ክፍል ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ ብዙዎች ሆነን ሳለን አንድ አካል መሆናችንን ነው። በጌታ እራት ላይ የምናደርገው የጋራ ተሳትፎን በመጥቀስ ጳውሎስ ይህን ሐሳብ ደግፎ ሁለት ጊዜ ጽፎታል። “እንጀራው አንድ እንደ ሆነ… ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።” ጳውሎስ ይህንን ሐሳብ ሁለት ጊዜ አጽንዖት ሰጥቶ መድገሙ፣ እንጀራው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት በላይ ትርጉም እንዳለው ያመለክታል። በምትኩ፣ የጌታን እራት በጋራ በማክበር ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደ ተመሠረተ ጳውሎስ ይነግረናል። አንድ እንጀራ ስላለ፣ አንድ አካል አለ።

ጳውሎስ፣ የጌታ እራት ብዙዎችን አንድ እንደሚያደርጋቸው ይናገራል። የጌታ እራት “እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ” አንድ አካል ያደርገናል። በሌላ አነጋገር፣ የጌታ እራት ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው። እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ፣ ስለ እንጀራ እና እንዴት እርሱን መብላት እንዳለብን አይደለም። ከአንድ በላይ የሚቆረስ እንጀራ የሚያስፈልጋት፣ ብዙ የአባላት ቁጥር ያለባት ቤተ ክርስቲያን አንድ አይደለችም ማለትም አይደለም። በምትኩ፣ ጳውሎስ “አንዱን እንጀራ” ሲል ቤተ ክርስቲያን እንደ ማኅበር በጋራ የምታከብረውን የጌታን እራት ለመወከል ነው። የጳውሎስ ሐሳብ፣ የጌታን እራት በምንወስድበት ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እናደርጋለን። በክርስቶስ ያለን አንድነት ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አንድነትን ይፈጥራል።

በሌላ አነጋገር፣ የጌታ እራት የአዲስ ኪዳን መሐላ ምልክት ነው። የጌታን እራት በምንወስድበት ጊዜ ከክርስቶስ ጋር እና እርስ በርስ ያለንን ግንኙነት እናድሳለን። ይህ በሁለት መልክ የተቀመጠው ግንኙነት ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ያደርጋታል።

የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ደረጃዎች

እግዚአብሔር፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን በሁለት ደረጃዎች ፈጥሯል። የመጀመሪያው ደረጃ፣ ክርስቲያኖችን ፈጥሯል። እንዴት? እግዚአብሔር ስለ ወንጌል የሚሰብኩ ሰባክያንን ይልካል (ሮሜ 10፥14-17)። ለሚሰሙትም ወንጌሉን ተቀብለው እንዲመሰክሩ መንፈሱን ይልክላቸዋል (1 ቆሮንቶስ 12፥3)። የእርሱ ቃል በሕይወታቸው እንዲሰራ፣ በክርስቶስ አዲስ ሕይወትን ይሰጣቸዋል (ያዕቆብ 1፥18)። እግዚአብሔር፣ ቃሉ እና መንፈሱን በመላክ ቤተ ክርስቲያንን ፈጥሯል። እግዚአብሔር የወንጌል ሕዝቦችን ፈጥሯል። እነዚህም ሕዝቦች ክርስቶስን በማመን የዳኑ ናቸው። ይህ የመጀመሪያው ደረጃ ነው።

ሰዎች ወደ ክርስቶስ ሲመጡ፣ ዓለም አቀፋዊ ለሆነው የክርስቶስ አካል ብልቶች ይሆናሉ። በመንፈስ አንድ ናቸው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ለመፍጠር፣ ሰዎች ወደ ክርስቶስ መምጣት ብቻ ሳይሆን ወደ ሰዎችም መምጣት አለባቸው። በአንድነት መምጣት አለባቸው፤ ይህ ደግሞ ትጋትን ይፈልጋል። ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ በአንድ ከተማ ወይም በአንድ ክፍል ስለተገኙ ብቻ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አትፈጠርም። አለበለዚያ፣ ሌላ ክርስቲያንን ሱቅ ውስጥ ስታገኙት ቤተ ክርስቲያን በተፈጠረ ነበር። ስትለያዩ በፈረሰም ነበር። ቤተ ክርስቲያን የ”ክርስቲያን” ስብስብ ብቻ አይደለም። የእያንዳንዱ ሰው ድምር ውጤት ብቻ አይደለም። ሰዎችን አንድ የሚያደርግ የላቀ ነገር አለ።

የወንጌል ሕዝብ እና ወንጌላዊ ሥርዐት

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን ለመፍጠር የወንጌል ሰዎች ወንጌላዊ ሥርዐትን ሊፈጥሩ ይገባል። ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ እና ያስገዙ ሲሆኑ ቤተ ክርስቲያን ትወለዳለች። ይህ ሁለተኛው ደረጃ ነው። ወደ ኋላ ተመልሳችሁ የትዳሩን ምሳሌ አስቡ። ትዳር ሊፈጠር የሚችለው፣ ወንድ እና ሴት ባል እና ሚስት ለመሆን ራሳቸውን ሲሰጡ ነው። ቃል ኪዳኑ ትዳርን ይመሠረታል። በተመሳሳይ፣ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላኛቸው ራሳቸውን ሲሰጡ እና ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንድታደርግ ያዘዛትን፣ ይኸውም ለአምልኮ፣ እርስ በእርስ በፍቅር ለመተናነጽ፣ ሸክምን ለመጋራት፣ ለመጠመቅ እንዲሁም የጌታን እራት በጋራ ለመውሰድ ሲሰበሰቡ ቤተ ክርስቲያን ትወለዳለች።  

ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ለወንጌል ትክክለኛ ምላሽ እንድንሰጥ ያስቻለን የማዳኑ ሥራ፣ አንዳችን ለአንዳችን የተሰጠን እንድንሆን ያስችለናል። የእግዚአብሔር ሥራ እና የእኛ ሥራ በውድድር ውስጥ አይደሉም። እንደ ክርስቲያን መሰብሰብ የቻልነው እግዚአብሔር መጀመሪያ ክርስቲያን ስላደረገን ብቻ ነው። እግዚአብሔር፣ ክርስቲያኖችን በመፍጠርና አንዳቸው ለሌላቸው የተሰጡ እንዲሆኑ በማስቻል ቤተ ክርስቲያንን ፈጥሯል።

ጥምቀት እና የጌታ እራት

ክርስቲያኖች እነዚህን ሥርዐቶች የሚፈጽሙት እንዴት ነው? የጥምቀት እና የጌታ እራት ሥርዐቶች እጅግ ወሳኝ ሚና አላቸው። በጥምቀት፣ ለክርስቶስ እና ለሕዝቡ በይፋ ቃል ትገባለህ/ሽ። ጥምቀት፣ እምነታችን ይፋ የሚሆንበት ነው። አዲስ አማኝ እምነቱን ለዓለም የሚያሳይበት እና ቤተ ክርስቲያንም እንደ አማኝ የምትቀበልበት ሥርዐት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ጥምቀት አማኝን ከዓለም የሚለየው ነው። በጥምቀት፣ ቤተ ክርስቲያን “ይህ የኢየሱስ ነው” ብላ ለዓለም ትናገራለች።

በጌታ እራት፣ ለክርስቶስ እና ለሕዝቡ ያለንን መሰጠት እናድሳለን። ከጥምቀት በተለየ ሁኔታ፣ የጌታ እራት ሁላችንም በጋራ የምንፈጽመው ሥርዐት ነው። የጌታ እራት፣ ክርስቲያኖችን ከከበባቸው ዓለም ለይቶ አንድ አካል መሆናቸውን የሚያሳይ ሥርዐት ነው። በውስጡ የሚደረጉት ሥርዐቶችን አይተን “ክርስቲያኖች” እንድንል ሳይሆን “ቤተ ክርስቲያን” እንድንል ያደርገናል።

እስቲ አስቡት፣ አንድ ክርስቲያን ወደ አዲስ ከተማ በመሄድ ወንጌልን ሰብኮ በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ ክርስቶስ መጡ። የመጡትን ሁሉንም አጠመቃቸው። እነዚህ የተጠመቁ ክርስቲያኖች እንዴት እና መቼ ቤተ ክርስቲያን ይሆናሉ? ለዚህ ጥያቄ እጅግ መሠረታዊ እና አስፈላጊ መልስ አቀርባለሁ። ይህም፣ ቤተ ክርስቲያን የሚሆኑት የጌታን እራት አንድ ላይ ሲወስዱ ነው። የጌታን እራት መውሰድ፣ ለክርስቶስ እና ለወንድሞቻችንን ያለንን መሰጠት እንደሚገልጽ አስታውሱ። በጌታ እራት ውስጥ የሚገኘውን የክርስቶስን ትሩፋቶች ማግኘት ማለት የክርስቶስን ሕዝቦች እንደ ወንድም እና እኅት መቀበል ማለት ነው። የጌታ እራት ራሱ ከ“ክርስቲያኖች ስብስብ” ወደ “አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን” እንድንሸጋገር እና አንዳችን ለሌላኛችን የተሰጠን እንድንሆን ያደርገናል። በጌታ እራት ምክንያት እንደ አንድ አካል ተሰብስበናል። ጳውሎስ እንደሚለው “እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና” (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥17)።

አብያተ ክርስቲያናት መጀመሪያ እንደ ቤተ ክርስቲያን ሲመሠረቱ፣ አባላት እርስ በርሳቸው የገቡት ቃል ኪዳን ምን እንደሆነ እና ምን እያደረጉ እንዳሉ ማብራራት ብልኅነት ይመስለኛል። በኮንግሪጌሽናሊስት (Congregationalist) እና ባፕቲስ (Baptist) ወግ ይህ “የቤተ ክርስቲያን ቃል ኪዳን” ተብሎ ይጠራል። ይህም የጌታን እራት በሚወስዱበት ጊዜ ይነበባል። ይህ ጥሩ ልምምድ ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ የቃል ንግግር ግን፣ የጌታን እራት ከመውሰዳችን ተነጥሎ ብቻውን ቤተ ክርስቲያንን ሊፈጥር አይችልም። ነገር ግን ይህ ቃል ኪዳን፣ የጌታ እራት ከጀርባው ያነገበውን ትርጉም ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ የቃል ኪዳን ንባቦች መረዳታችንን ያሳድጉታል። እንዲሁም እንጀራውንና ጽዋውን ስንወስድ ምን እያደረግን እንደሆነ ያስታውሱናል።

የቤተ ክርስቲያን አጀማመር፣ እንደ ትዳር አጀማመር ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ ምሳሌ እንደ ሌሎች ምሳሌዎች ፍጹም አይደለም። ነገር ግን የተሻለ መረዳት እንዲኖረን ያግዘናል። ትዳር የሚፈጠረው፣ ወንድ እና ሴት ቃል ኪዳን ሲፈጽሙ እና አገልጋይ ወይም ሕጋዊ ሰው ትዳራቸውን ሲያረጋግጥ ነው። “አዎ ቃል እገባለሁ” የሚለው መሐላ አዲስ ግንኙነትን ያስጀምራል። ነገር ግን ይህ ግንኙነት የሚጸናው ባል እና ሚስት በአካል ግንኙነት ሲያደርጉ ነው።

እንዲሁም በተመሳሳይ፣ የአማኞች ስብስብ  ያላቸውን አንድነት የጌታን እራት በጋራ በመውሰድ ካላጸኑ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሊሆኑ አይችሉም። ቤተ ክርስቲያን ለመሆን የሚፈልጉ አማኞች፣ የጌታን እራት አንድ ላይ ካልወሰዱ፣ የክርስቶስን ትእዛዝ መተላለፍ ብቻ ሳይሆን መጀመሪያውኑ ቤተ ክርስቲያን አይደሉም። የጌታ እራት፣ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ሥርዐት ነው።

የጌታ እራት የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ይሠራል? የጌታ እራት እና ጥምቀት፣ የወንጌል ሕዝብ ወንጌላዊ ሥርዐትን የሚፈጥሩባቸው መንገዶች ናቸው። የጌታ እራት ክርስቲያኖች በጋራ መጥተው፣ አንዳቸው ለሌላኛቸው ራሳቸውን የሚሰጡበት እና ከ”ብዙ” ወደ “አንድ” የሚሻገሩበት ሥርዐት ነው። በጌታ እራት፣ ከክርስቶስ ጋር ያለን ኅብረት የእርስ በርስ ግንኙነትን ይፈጥራል። የጌታ እራት ብዙዎችን አንድ ያደርጋል።

በውበት የተሞላ ግልጽነት

እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ያለው ዕቅድ ግልጽ እና ውበትን የተሞላ ነው። ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት ምን ያስፈልጋል? በወንጌሉ ሥርዐት የሚመራ፣ በስብከተ ወንጌል የተገኘ የወንጌል ሕዝብ። ቤተ ክርስቲያን፣ ወንጌል እና ሥርዐቶቹ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚመሠርቱበት ቦታ ነው። ጥምቀት፣ አንዱን ከብዙ ጋር ያገናኛል፤ የጌታ እራት ደግሞ ብዙዎችን አንድ ያደርጋል።

ጥምቀት እና የጌታ እራት፣ ወንጌሉን በቤተ ክርስቲያን ቅርፅ እና መዋቅር ውስጥ ያስገባሉ። ብዙዎችን አንድ ማድረግ፣ የወንጌል ምልክት ነው። ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረት በአንድነት ሲመጡ ከወንጌል የሚርቁ ሳይሆን ወንጌሉን በጥልቀት የሚረዱ ይሆናሉ።

ቦቢ ጀሚሰን

***

የአርታዒ ማስታወሻ፥ ይህ መጣጥፍ ከ ተሻሻለው “Understanding the Lord’s Supper, in the Church Basics series (B&H, 2016).” የተወሰደ ነው። በB&H ፈቃድ እንደገና ታትሟል።