ወንጌልን ለማሠራጨት ምን ያስፈልግሃል? ይዘቶቹ ብዙ አይደሉም። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የምሥራችን የሚሰብክ ወንጌላዊ ያስፈልግሃል። ሌላ አንድ ተጨማሪ የሚያስፈልግህ ነገር አለ፤ ይኸውም ቢያንስ አንድ በወንጌሉ ያላመነ ታዳሚ ያስፈልግሃል።
ለብዙ መጋቢያን ይህ የመጨረሻው ይዘት ፈታኝ ክፍል ነው። መጋቢው በአንድ ሳምንት ውስጥ ለስብከት ዝግጅት፣ በስብሰባ፣ በምክር አገልግሎት፣ በአስተዳደር፣ በሆስፒታል ጉብኝት እያደረገ፣ በተጨማሪም ለራሱ መንፈሳዊ ሕይወትና ለቤተ ሰቡ እየተጠነቀቀ፣ እንዴት ነው የምሥራቹን ለማያምኑ ሰዎች ለመስበክ ጊዜ የሚያገኘው?
በአንድ በኩል፣ ይህ ጥሩ እና አስፈላጊ ውጥረት ነው። አንድ አገልጋይ ወደ መጋቢነት ጥሪ ሲመጣ፣ ከስብከተ ወንጌል ግንባር ወጥቶ ወደ ማዘዣ ካምፕ ይገባል። ከእንግዲህ እጅ ለእጅ የሚዋጋ ወታደር ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው እንደ ጄኔራል መሆን ነው። ሥራው ንድፍ ማውጣትን፣ ማስታጠቅን እና ውክልና መስጠትን ያካትታል (ኤፌሶን 4፥12 ይመልከቱ)። ወንጌላውያንን በማሰልጠን፣ ወንጌልን በማስተማር እና በየሳምንቱ ለተሰበሰቡ አማኞች ወንጌልን በመስበክ፣ መጋቢው የወንጌል አገልግሎቱን እየጎዳ ሳይሆን ይልቁንም እያሰፋው ነው። ይህ መልካም እና ትክክል ነው። መጋቢያኑ መንጋውን ለመንከባከብ እና በአገልግሎት ለማሠልጠን፣ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ልዩ የሆነውን ኀላፊነት በማስቀደማቸው የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማቸው አይገባም። መጋቢው የወንጌል አገልግሎት ብቸኛ ባለቤት ሳይሆን የወንጌል አገልግሎት አሳላጭም ነው።
ይህ ማለት ግን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መቆም አለበት ማለት አይደለም። ጳውሎስ ወጣቱ መጋቢ ጢሞቴዎስን “የወንጌላዊነትን ሥራ እንዲሠራ” አዝዞታል (2 ጢሞቴዎስ 4-5)። ታላቁ ጄኔራል እንኳ በልቡ ወታደር ነው። አንድ መጋቢ ሌሎች እንዴት ወንጌልን ማሠራጨት እንዳለባቸው ማስተማሩ በጣም ተመችቶት መኖር የለበትም፤ ይህ ከሆነ ወንጌልን በግሉ ለማካፈል ያለው ቅንዓት እየጠፋ ይሄዳል። ለወንጌል አገልግሎት የሚቀኑ መጋብያን፣ ቀናተኛ የሆኑ ጉባኤዎች ይኖራቸዋል። አልፎ አልፎ ወንጌልን የሚሰብኩ መጋብያን ግን ጉባኤዎቻቸው በተመሳሳይ መልኩ ለወንጌል ምስክርነት ይቀዛቀዛሉ።
መጋቢ ወንጌል ሥርጭትን ሊያዳብር የሚችልባቸው አምስት መንገዶች
ታዲያ አንድ መጋቢ የወንጌል ስብከት ዕድሎችን እንዴት መፍጠር ይችላል? በዚህ ረገድ እኔም እንደ ማንኛውም አገልጋይ ዕድገት ስለሚያስፈልገኝ፣ በተጣበበ ጊዜያቸው ውስጥ ለወንጌል አገልግሎት እንዴት ቅድሚያ እንደሚሰጡ መጋቢያን ጓደኞቼን አነጋግሬያቸው ነበር። በመልሶቻቸው መሠረት፣ አምስት ምክሮች እነሆ፦
1. ፈጠራን አክልበት
በመጀመሪያ፣ የፈጠራ ሰው ሁን። ብዙ ጊዜ የማያምኑትን ሰዎች ለመገናኘት ቀልጣፋ መሆን አለብህ። በአንድ ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚያገለግል አንድ መጋቢ፣ እርሱ እና የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ብዙውን ጊዜ የሚሰበሰቡት ከቢሮ ውጭ እንደ ሆነ ነግሮኛል። እንዲህ የሚያደርጉትም በአጋጣሚ የሚመጡ ሰዎችን ካገኙ በዛው ወንጌል ሊመሰክሩላቸው ስለ ፈለጉ ነው።
ሌሎች ደግሞ በመዝናኛ ቦታ የወንጌል ዕድሎችን መፍጠርን አንድ መንገድ ጠቅሰዋል። ከክርስቲያን ጓደኞች ጋር ከመዝናናት፣ ሕዝብ የሚያዘወትራቸውን ቦታዎች ማግኘት ትችል ይሆናል። ይህም ለአዲስ ወዳጅነት በር ይከፍታል። በአረብ ባህረ ሰላጤ የሚኖር አንድ ሰባኪ፣ በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት አንዱ ጥሩ መንገድ የቤተ ሰብ መዋኛ ቦታ እንደ ሆነ ተናግሯል።
ንቁ እና ቀልጣፋ መሆን ከጎረቤት ወይም ከካፌ አስተናጋጅ ጋር የሚደረግ ተራ ውይይትን ወደ መንፈሳዊ ጉዳዮች ለመቀየር መሞከርን ያካትታል። አንድ ሰው ስለ ዜና፣ ስፖርት፣ ወይም የአየር ሁኔታ እንኳ ሳይቀር፣ ወደ ጥልቅ ውይይት ሊመራ በሚችል መልኩ ስለ እግዚአብሔር ወይም ስለ ወደቀው ዓለም ጠቃሚ የሆነ እውነት ለማቅረብ ብዙውን ጊዜ ክፍት ይሆናል። ለዚህ ደግሞ፣ የፈጠራ ክህሎት እና አስተሳሳብ ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ የሰውን ፍርሀት አሸንፈን ክርስቶስን ለማካፈል በመንፈስ የሆነ ድፍረት እና ፍቅር ያስፈልገናል።
2. ወጥነት ያለህ ሁን
ሁለተኛ፣ ወጥነት ያለው መጋቢ ሁን። ሠራተኞቹን ለማወቅ ደጋግመህ በተመሳሳይ ምግብ ቤት ለመብላት ፈቃደኛ ነህ? ይህንን ወጥነት ለዓመታት የእኔ መጋቢ ለወንጌል ሲል አድርጎታል። በዚህ ምክንያት፣ ሁሉም አስተናጋጆች በእራት ጊዜ መንፈሳዊ ጥያቄ የሚያቀርቡለት ቄስ ሆኗል እያልን እንቀልድበት ነበር።
ሌላው ጓደኛዬ ደግሞ በየሳምንቱ ተመሳሳይ ላዎንደሪ ቤት በማዘውተር ደግሞም ከሠራተኞች ጋር ለመነጋገር ዕድሎችን በመፍጠር ስላገኘው ፍሬ አጫውቶኛል። በመጨረሻም አንዷ ሠራተኛ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት ክርስቶስን በማመን በዚያ ካሉ ሴቶች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምራለች።
3. ንቁ ሁን
ሦስተኛ፣ ንቁ ሁን። በዙሪያችን ላሉት የጠፉ ሰዎች ግንዛቤ እንዲኖረን መጸለይ አለብን። በእንግሊዝ የሚኖር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ተማሪ በባቡር ውስጥ የማያምኑ ብዙ ሰዎች ከእርሱ አጠገብ እንደሚቀመጡ ሲያስተውል መጽሐፍ ቅዱሱን ከፍቶ በግልጽ እንደሚያነብ ተናግሯል። ከዚያም ብዙ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ውይይቶች ይጀመራሉ።
እንደ ማስታወሻ፣ መጋቢ ተብሎ የመታወቅ ጠቃሚነትን ማወቅ ተገቢ ነው። ብዙ ንግግሮች የሚጀምሩት “ምንድን ነው የምትሠራው?” ለሚለው ጥያቄ “እኔ መጋቢ ነኝ” የሚል መልስ በመስጠት ነው። ይህ ተጠያቂነት እንደሚያመጣብን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ግን እንደ ዕድል እንጠቀምበት። ለምሳሌ፣ እኔ እንደዚህ ዐይነት ዐረፍተ ነገር ለማካተት እሞክራለሁ፣ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጋቢ ነኝ። እናም ስዎች ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ መንፈሳዊነት እና ስለ ኢየሱስ ያላቸውን ሐሳብ መስማት እወዳለሁ።”
እናም አንተ እንደ መጋቢ በማኅበረ ሰብህ ውስጥ ያሉትን በወንጌል የማያምኑትን ሰዎች እንዴት ማገልገል እንደምትችል አትዘንጋ። የመጋቢነት አገልግሎት የወንጌል ዕድሎችን ይዞ ይመጣል።
4. ተባባሪ ሁን
አራተኛ፣ ተባባሪ ሁን። ምዕመኖችህ በሥራ ቦታ እና በማኀበረ ሰቡ ውስጥ እያከናወኑት ባለው የወንጌል ሥርጭት ለመሳተፍ መንገዶችን ፈልግ። አንድ መጋቢ በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነጋዴዎች፣ በምሳ ሰዓት በመደበኛነት በመሰባሰብ “ስለ እግዚአብሔር የሚመራመር ቡድን” እንዴት እንዳቋቋሙ ጠቅሶ አልፎ አልፎ እንዲገኝ መጋበዛቸውን አጫውቶናል። ከእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር የእንግዳ ተቀባይነት አገልግሎትን ለወንጌል አገልግሎት ማቀድ ታላቅ መንገድ ነው። ልደት ወይም የተለያዩ ድግሶች ሲዘጋጁ፣ የጋበዟቸው የቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያን ያልሆኑ ጓደኞችን ይዘው እንዲመጡ ንገሯቸው።
5. ቁርጠኛ ሁን
አምስተኛ፣ ቁርጠኝነት ይኑርህ። አንድ መጋቢ ከላይ የተጠቀሱትን ምሳሌዎች በሙሉ መቀበል የለበትም። ነጥቡ እዚያ ላይ አይደለም። ጉዳዩ የእረኝነት አገልግሎት፣ “የጠፉትን ሊፈልግና ሊያድን” የመጣውን ታላቁን እረኛ መምሰል አለበት (ሉቃስ 19፥10)የሚለው ነው። የመጋቢነት ልዩ ጥሪ እና የጊዜ ሰሌዳ በርግጠኝነት ይህንን ፈታኝ ያደርገዋል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ የራሳችን ስንፍና እና ራስ ወዳድነት፣ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች በላይ ከወንጌል አገልግሎት እንደሚያግደን ማመን አለብን።
ወንጌልን አጥና፤ ሐሴትም አድርግበት
ስለዚህ፣ መጋቢ ሆይ! ለስብከተ ወንጌል ያለህ ቁርጠኝነት በየሳምንቱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ ውስጥ ምን ይመስላል? ለመጀመር ያህል፣ ለወንጌል በሮች አዘውትረህ እንድትጸልይ ላበረታታህ እወድዳለሁ።
ከሁሉም በላይ ግን ወንጌልን አጥና፤ ሐሴትም አድርግበት። “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፣ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ ርግጠኛ ሆነናል…” (2 ቆሮንቶስ 5፥14)። ውድ የሆነውን የክርስቶስን መልእክት በመመልከትና ይህ እውነት በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ታላቅ ኀይል መገንዘባችን፣ በዘመናችን ላለው ለወንጌል ምስክርነት መዳከም ከሁሉ የተሻለው መድኀኒት ነው።
በ ማት መርከር