ፊሊፕ ብሩክስ በታዋቂው የስብከት ትርጉሙ፣ “ስብከት ማለት እውነትን በማንነታችን ማስተላለፍ” ነው ሲል ተናግሯል፤ እንዲህ ብሎ ሲናገር ስለ አንድ ሰው የራሱ ማንነት እንጂ ስለ ሌላ ሰው ማንነት እያወራ እንዳልሆነ አምናለሁ።
ብዙ ጊዜ ቢወስድብኝም አሁን ላይ በመድረክ ላይ ራሴን መሆን ተምሬያለሁ። ይህን በማድረጌ ስብከቴ መሻሻሉን ወይም ወደ ኋላ መመለሱን እኔ ራሴ ምንም ማለት አልችልም። ነገር ግን ራስን መሆን ማለት፣ ስብከት እውነተኛ ሲሆን፣ የማይቆረቁርና ወጥ በሆነ መንገድ ቀጣይነት ያለው ሲሆን ነው። አውቃለሁ እንደ ሰባኪ ገና ብዙ የምማረው ነገር አለ፤ እንደማስበው የዛሬ 10 ዓመትም ቢሆንም “ስብከትህ በእነዚህ ዓመታት በጣም ተሻሻሽሏል” የሚለውን አስተያየት ከሰዎች መቀበሌ አይቀሬ ነው። ነገር ግን አሁን የሚሰማኝ በራሴ ማንነት እየሰበኩ እንደሆነ ነው።
እንደ ብዙዎቹ ወጣት ሰባክያን እና እንደ አንዳንድ የድሮ ሰባኪዎች የራሴን የስብከት “ድምጽ” ለማግኘት ብዙ ለፍቻለሁ። የሪፎርመሮችን (ተሐድሶአውያን) እና የፒውሪታኖችን መጻሕፍት በብዙ ማንበብ የጀመርኩት ኮሌጅ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነበር። የማነበው መጻሕፍት በሙሉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፉ ነበሩ፤ ወይም ደግም ከመቶ ዓመት በፊት የተተረጎሙ ነበሩ።
በዚህም ምክንያት የምጽፋቸው ነገሮች “ከላቲን መጽሐፍ የተተረጎመ” ተብሎ ለሚሰጥ ሽልማት የምጽፍ ነበር የሚመስለው (ያኔ ብዙ ስብከት አልሰብክም ነበር)። ብዙ ጊዜ የምጠቀማቸው ዐረፍተ ነገሮች ከባባድ፣ ረዣዥምና ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነበሩ። የምጠቀመው ሰዋሰው የድሮና በጣም ብዙ ቃላት እጠቀም ነበር። አንድ በብዙ የሚያበረታታኝ አስተማሪ፣ ለማደንቃቸው የድሮ ሰዎች ሳይሆን በዘመኔ ላሉ ሰዎች እንድጽፍ በብዙ ሞግቶኛል።
በጊዜው ትንሽ ከበድ ያለ ምክር ነበር። ምክሩን ራሱ እንደ ተቀበልኩት እርግጠኛ አልነበርኩም። ያው እነዚህን ጥንታዊ ቃላቶችን ራሱ መጠቀሜ ለእምነት ያለኝን መሰጠትም አይደል የሚያሳየው? መልሱ! አያሳይም ነው። ራሴን መሆን እንጂ እንደ ፒውሪታኖች መናገር ወይም መስበክ አያስፈልገኝም።
ሴሚናሪ ሳለሁ አብሬአቸው የምማራቸው ተማሪዎች የአብዛኞቹ አሰባበክ ልክ እንደ ስብከት ዘዴ መምህራኖቻቸው ነው። አሁንም ድረስ አብዛኞዎቹ እንደዛው ነው የሚሰብኩት። የትም ቦታ ብትሄዱ ሁሌ የሚያጋጥማችሁ የስብከት አስተማሪዎች ቁርጥ ራሳቸውን የሚመስሉ ሰባኪዎች ማፍራታቸው ነው። አንዳንዱን ስሕተት አስተማሪዎቹ ነው መውሰድ ያለባቸው፤ ምክንያቱም ለእነርሱ የሠራላቸው፣ ለሁሉም ተማሪዎቻቸው ግን የማይሠራ የስብከት ዘዴ ላይ ያልተገባ አትኩሮት ይሰጣሉ። ይህ ማለት ግን ተማሪዎቻቸው ንጹሕ ናቸው ማለት አይደለም፤ እንዲያውም እነርሱም ጋር ስሕተቶች አሉ። በጣም የምንወደውን ሰው መሆን ስለምንፈልግ ያንን ሰው ስናገኝ እንደ ወረደ እርሱን እንደግመዋለን ወይም እንኮርጀዋለን፤ በተለይ ደግም የስብከት ዘዴ የሚያስተምሩንን ሰዎችን። ጎርደን ኮንዌል በነበርኩ ጊዜ ብዙ ትንንሽ ሆዶን ሮቢንሰኖችን አይ ነበር። ይሄ ማለት እነዚህ ተማሪዎች መጥፎ ሰባኪ ይወጣቸዋል ማለት ሳይሆን፣ ማወቅ ያለባቸው እውነታ ግን አንድ ሆዶን ሮቢንሰን ብቻ መኖሩን ነው። ወደፊት ሊኖር የሚችለውም አንድ እርሱ ብቻ ነው። እነርሱ ደግሞ እርሱን መሆን አይችሉም።
በሮቢንሰን ስብከቶች የተባረኩትን ያክል ብዙ ሰባኪዎችንም ለማስመሰል ተፈትኛለሁ። በርግጠኝነት መናገር የምችለው በአገልግሎቴ የመጀመሪያዎቹ ዐመታት የጆን ፓይፐር ቅጂ ነበርኩ። ፓይፐርን በብዛት ከመስማቴ የተነሣ በርግጠኝነት ጸሎቶቼ ፤ የማነሳቸው ጭብጦች እና ስለ ‘ሐሤት!” ሳወራ ራሱ ፓይፕራዊ ነበርኩ።
እንዳትሳሳቱ ከፓይፐር መማርን ወይም በጎ ተጽዕኖ መኖሩን አቃቂር እያወጣሁ አይደለም። የእርሱ ስብከት በብዙ ከእኔ እንደሚሻል አውቃለሁ። ነገር ግን እርሱ ራሱ፣ “እኔ የምሰብከውን ወንጌል ስበክ። ነገር ግን እንደ እኔ ግዴታ መስበክ የለብህም።” እንደሚለኝ አውቃለሁ። ብዙ ዓመታት ቢወስድብኝም አሁን ላይ በስተመጨረሻ ፓይፐርን አለመሆን ችግር እንደሌለው ተረድቻለሁ። አይደለም የስብከት ስጦታችን ቀርቶ አንድ ዐይነት ስብዕና (ማንነት) እንኳ እንዳለን አላስብም።
ከላይ ካነሣኋቸው ሰዎች ሌላ እነርሱን መምሰል የምፈልጋቸው ታዋቂ ሰዎች ነበሩ። የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል ሳስተምር እንደ አሊስተር ቤግ ደስ የሚል ዘና የሚያደርጉ ጨዋታዎችን ብችል ከነአነጋገሩ ብመስለው ብዬ አስባለሁ። እንደ ቲም ኬለር በአስተሳሰቤ አዳዳስ መንገዶችና ካለሁበት ባህል ጋር የተስማማ አሰባበክ ቢኖረኝ ብዬ እመኛለሁ። እንደ ሲ.ጄ መኽንይ አዝናኝና ትሑት መሆንን እፈልጋለሁ። አንዳንዴ እንደ ማርክ ዲስኮል ፊት ለፊት ለመናገር ይዳዳኛል። እንደ ካርሰንም ብሩህ ጭንቅላት ቢኖረኝ እፈልጋለሁ (እንድ እርሱ “አይ-ዛያሃ” ማለትም ሞክሬ አውቃለሁ። ያው ግን ሰዉ እያረኩ እንደሆነ ገብቶታል)። ከዚያም በላይ እንደ ሮብ ቤል ዘና ባለ መንገድ መስበክም ፈልጌ አውቃለሁ።
በእነዚህ ዓመታት ብዙ ዐይነት የስብከት ዘዴዎችን ሞክሬአለሁ። የምወዳቸው ሰባኪዎችን እየተከተልኩ ማስታወሻ ሳልይዝ ሰብኬአለሁ፤ በግማሽ ገጽ ወረቀት ማስታወሻ ሰብኬ አውቃለሁ፤ ሙሉ ጽሑፍ ስብከትም ሰብኬአለሁ። አሁን ባለሁበት አገልግሎትና አሰባበክ ዘዬ የምጠቀመው ሙሉ የተጻፈ ማስታወሻ ወይንም ግጥግጥ ብሎ ብዙ ሐሳቦች ከተሞነጫጨሩበት ማስታወሻ ነው። የስብከት ዘዴ መምህራኖች ባይመቻቸውም የምለው እናንተ ራሳችሁ የሚመቻችሁንና የሚሠራለችሁን ዐይነት የአሰባበክ ዘዴ መምረጥ ይኖርባችኋል። ብዙ የጥሩ ስብከት መመዘኛ ቢኖሩንም ከዚያ ውጪ ደግሞ ብዙ “ለምን እንደሆነ ባላውቅም ይኼኛው ይስማማኛል፤ ይሠራልኛል” ምንላቸው ነገሮች አሉ።
በፈረንጆች 2002 ከተሾምኩበት ጀምሮ በግምት ለ500 ያህል ጊዜ ሰብኬአለሁ (የማታ ፈረቃም አለን)። እንደምገምተው የራሴን የስብከት ድምጽ ከማግኘቴ በፊት ወደ 450 ስብከት ሰብኬአለሁ። ይህ ማለት እነዚያ ስብከቶች ሁሉ መጥፎ ናቸው ወይም ለራሴ ታማኝ አልነበርኩም ማለት አይደለም። የሌለኝን የስኮትላድ አወራር ዘዬ ወይም ደግሞ ያልኖርኩበትን ያላደኩበትን ቦታዎች ታሪክ እንደ ራሴ አወራለሁ ማለትም አይደለም። ነገር ግን “በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ” የሚለውን የጳውሎስን ንግግርና ጥበብ ለመረዳት ይህን ያክል ጊዜ ወስዶብኛል ማለቴ ነው።
ሰባኪያን ለመማር ከሚከብዳቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው በተለይም ወጣት ሰባኪያን ራስን መሆን ነው። የሌላን ሰው ስሜት፣ ትምህርትና ቀልዶች አንውረስ፤ የራስን ማንነትም አናውልቅ። ምክንያቱም የምናደንቃቸውና የምንከተላቸው ሰዎች የአንተን ማንነት በትክክል ስለማይጋሩት። ከእነዚህ ሰዎች መማር ጥሩ ነው፤ ነገር ግን እሁድ የምታገለግላቸው የቤተ ክርስቲያንህ ሰዎች አንተን መስማት ነው ያለባቸው እንጂ የምታስመስለውን ወይም የምታደንቀውን ሰባኪ አይደለም። ማንነታችን ያለማቋረጥ በመንፈስ ቅዱስ ነጥሮ ይውጣ፤ እናም እግዚአብሔር የእውነት ቃል በማንነትህ ውስጥ አልፎ ያብራ። እንደሚሞት ሰው ለሚሞቱ ሰዎች ስበክ፤ ይህን ስታደርግም ማንነትህን አትርሳ።
በኬቨን ዲያንግ